የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከ25 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እንጂ በዕድሜ ያን ያህል እንደ ሌሎቹ ሀገራት የረጅም ዕድሜ ባለቤት አይደለም። ዴሞክራሲ አሁን ላለው የዕድገት ደረጃ የበቃው በአንዴ አይደለም—በጊዜ ሂደት ውስጥ እንጂ። ይህ ዕውነታም እንኳንስ ገና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታን በማከናወን ሂደት ላይ ላለን ህዝቦች ቀርቶ፤ ዴሞክራሲን ከ200 ዓመታት በላይ ያስኬዱት አሜሪካ እና የምዕራቡ ሀገራትም ቢሆኑ የገነቡት ዴሞክራሲ የበርካታ ዓመታት ውጤት መሆኑን ያስረዳናል።
ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሚመጣ የሂደት ውጤት ነው። የመራጩ ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው። ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው። ለዚህም ነው— ዴሞክራሲ በአንዴ የሚገነባ ሳይሆን በጊዜ ዑደት ውስጥ ከህዝቡ አስተሳሰብ ደረጃ ጋር እያደር አብሮ የሚራመድ ሂደት ነው የሚባለው።
ከዚህ አኳያ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 25 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ጅምር በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም። አሁን የምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም። እናም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል።
ከመሰንበቻው በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ 21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ክርክርና ድርድር ለማካሄድ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ለመወያየት መስማማታቸው ተዘግቧል። ዴሞክራሲን ከማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ ይህ በገዥው ፓርቲ አማካኝነት የተጠራው የውይይት መድረክ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው። እንዲህ ዓይነት መድረኮች በበዙና በተበራከቱ ቁጥር የሀገራችን ዴሞክራሲ ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። እናም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የሚካሄደው ክርክርና ድርድር ከዚህ ዴሞክራሲያዊ አውድ ብቻ መታየት ያለበት ይመስለኛል።
በመሆኑም በአንዳንድ ፅንፈኛ ወገኖች እንደሚነገረው የሚካሄደው ድርድርና ውይይት ለታይታ አሊያም ከፍራቻ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ይገባል። እንደሚታወቀው ገዥው ፓርቲ ከአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጋር ያደረገው መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል የነበረው አንዱ ጉዳይ የዴሞክራሲ እጦት ነው። ደርግን አስወግዶ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቢሆን፣ ይህን የህዝቦችን ጥያቄ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ጥረት አድርጓል። ገዥው ፓርቲ ገና ከስልጣን መባቻው ወቅት ጀምሮ የታጠቁና ወደ 17 የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማወያየትና በማከራከር ባህሉ የሚታወቅ ነው። ይህም ዴሞክራሲን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማስቻል ክርክርና ድርድር ማድረግ ለገዥው ፓርቲ አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። እናም ሰሞነኛው ለድርድርና ለክርክር የሚሆን ስምምነት በኢህአዴግና በሀገራችን ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማካኝነት ለመካሄድ የተያዘው ውጥን ከታይታ አሊያም ‘ገዥው ፓርቲ ስለ ፈራ ነው’ ከሚለው የፅንፈኞች የተዛባ ምልከታ ጋር ምንም የሚያገናኘው አንዳችም ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።
እርግጥ አንዳንድ ፅንፈኞችና የሀገራችን ሰላምና ልማት እንዲሁም ዴሞክራሲያችን በሚፈለገው መጠን እንዳይሰፋና ጥልቀት እንዳይኖረው የሚሹ የውጭ ሃይሎችና ተላላኪዎቻቸው እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑ ማናቸውንም ነገር ማጥላላትና ለጉዳዩ ያልተገባ ስም መለጠፍ የተለመደ ተግባራቸው በመሆኑ ተግባራቸው እምብዛም የሚያስደንቅ አይደለም።
ሆኖም ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ማናቸውም ዴሞክራሲን የሚያጎለብቱ ተግባራት የህዝቡን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ እንጂ ፅንፈኞችና የውጭ ሃይሎች ተላላኪዎች እንደሚያስወሩት የተዛባ አስተሳሰብ አይደለም። በመሆኑም እዚህ ሀገር ውስጥ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የሚካናወኑ ማናቸውም ሁነቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የታገሉላቸውን መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆመ ታስቦ የሚከናወን ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። ስለሆነም በገዥው ፓርቲም ይሁን በመንግስት በኩል የሚከናወኑ ጉዳዩች ሁሉ ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ሲባል እንጂ፣ ለታይታ አሊያም ለሌላ ጉዳይ የሚከናወኑ አይደሉም፤ ሊሆኑም የማይቸሉ መሆናቸውን በሰከነ አዕምሮ ግንዛቤ መያዝ ይገባል ባይ ነኝ።
እርግጥም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካካል ይደረጋል ተብሎ የታሰበው ዛሬ አይደለም። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ትናንት የነበረና ነገም የሚኖር ነው። በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዩችንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት “…የሀገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ አንዱ ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ ይሆናል። ሀገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ አገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል።…” ማለታቸው ይህንኑ የክርክርና የድርድር መንፈስ ለማመላከት ይመስለኛል። ይህ ሁኔታም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ሁሉንም ነገር አስበውበትና በመርህ ደረጃ አምነውበት እንጂ ተግባራቸው ከታይታ አሊያም ከፍራቻ ጋር የተያያዘ ስለሆነ አይደለም።
ዴሞክራሲን ለማስፋትና ለማጠለቅ ተብሎ ገና በጅምር ላይ የሚገኝ፣ ክርክርና ድርድር መሆኑ እየታወቀ፤ በአንዳንድ ፅንፈኛና ህገ ወጥ ቡድኖች “ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንቢያው ቂጢጥ” እንደሚባለው ሂደቱን ለማጣጣል አስቀድመው የሚያነሷቸው ነጥቦችም ትርጉም አልባ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። በተለይም ‘ከክርክሩና ከድርድሩ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ፣ የታሰሩ ወገኖች ይፈቱ፣ ሁሉም ተቃዋሚዎች (በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ጭምር ማለታቸው ነው) ይሳተፉ…ወዘተ. የሚሉ አጀንዳዎችን በማንሳት የሚነዛው አሉባልታዊ አስተሳሰቦች መታረም መታረም የሚኖርባቸው ይመስለኛል።
እርግጥ እነዚህ አስተሳሰቦች ፅንፈኞቹና ተላላኪዎቻቸው በክርክርና በድርድር ሽፋን የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ለማወክ የሚያግዛቸውን አጀንዳ ለማራገብ የተሰነዘሩ መሆናቸውን ለማወቅ ነብይ መሆንን የሚጠይቅ አይመስለኝም። አንድን ጉዳይ ህጋዊ ለማድረግ በሚደረግ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ ህገ ወጥነትን በማቀንቀን ወንጀለኞችንና አሸባሪዎችን ዕውቅና ለመስጠት የሚደረግ አላስፈላጊ እንካ ሰላንቲያዎችም ናቸው።
ክርክሩና ድርድሩን ያዘጋጀው አካል ገና ከመነሻው ያስቀመጠው ነገር ቢኖር፤ እዚህ ሀገር ውስጥ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንጂ ህገ ወጦችንና አሸባሪዎችን አይደለም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታም ፅንፈኞቹና ተላላኪዎቻቸው ባልተጠሩበትና በማይመለከታቸው ጉዳይ በለመደ አፋቸው እጃቸውን ለመዶል መሞከራቸው ባልተጋበዙበት ቤት የመቀላወጥ ያህል የሚቆጠር ነው። እናም በእኔ እምነት ይህን እጅግ የተዛባ፣ ህገ ወጥነትን የሚያገዝፍና የህግ የበላይነትን የሚደፈጥጥ አካሄድ ገዥውም ፓርቲ ይሁን ከእርሱ ጋር ለመደራደር ቀነ-ቀጠሮ የያዙት ህጋዊና ሰላዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ሊኮንኑት የሚገባ ይመስለኛል።
እርግጥ ኢህአዴግና የሀገር ውሰጥ ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚዎች መካከል የሚደረገው ክርክርና ድርድር በመጀመሪያው ቀን ስምምነታቸው ላይ በሀገር ጉዳይ ዙሪያ ለመወያየት ተስማምተዋል። በዚህም በአራት ጉዳዩች ላይ በቅድሚያ መነጋገራቸው ተዘግቧል። እነርሱም የስብሰባ ስነ ስርዓቱ ምን መሆን አለበት?፣ የመድረክ መሪነቱ እንዴት መካሄድ ይኖርበታል?፣ የፕሬስ መግለጫ አሰጣጡ እንዴት ይሁን? እና የታዛቢዎችን ሁኔታ የተመለከቱ ናቸው። በዚህ መሰረትም ከ15 ቀናት በኋላ ሁሉም ፓርቲዎች የየራሳቸውን ሃሳብ ይዘው እንደሚመጡ ተግባብተዋል። ከዚህ ውጭ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ፅንፈኞች፣ የሀገራችንን ሁለንታናዊ እመርታ የማይሹ ሃይሎችና ተላላኪዎቻቸው በቀላዋጭነት የሚያቀነቅኑት ሃሳብ ምንም ዓይነት ከጉዳዩ ጋር ግንኙንት የሌለው ከመሆኑም በላይ፤ የራሳቸውን የሁከት አጀንዳ እያራመዱ በመሆኑ በተከራካሪዎቹና በተዳዳራሪዎቹ ወገኖች ሊወገዙ ይገባል።
እርግጥ የሀገራችንን ዴሞክራሲ ለማጎልበትና ለማጠለቅ ገዥው ፓርቲ፣ ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ውጤት ሊያሙ አይችሉም። የሀገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለፓርቲዎች ተሳትፎ የሚሰጠውን ትኩረት ባልተናነሰ ሁኔታ፤ በከፍተኛ ትምህርትና በልዩ ልዩ የስራ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምሁራን፣ የተለያዩ የሲቪክ ማህበረሰብ አደረጃጀቶችና በእነርሱ ውስጥ የታቀፉ ዜጎችን በቀጥታ በማሳተፍ ጠቃሚ ሃሳቦቻቸውንም ማካተት ይገባል። በመሆኑም በክርክሩና በድርድሩ ወቅት እነዚህ ጉዳዩችም ታሳቢ መሆን ይኖርባቸዋል። ክርክርና ድርድር ሲባል በውጤቱ የሚገኘውን ግብዓት ለሀገር ግንባታና ዕድገት ለማዋል እንጂ፣ የሀገራችን ውድቀት ለሚመኙ ኃይሎች ፍላጎት ማሳኪያ አለመሆኑን ተወያዩቹ አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል እላለሁ። የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚሰፋውና ጥልቀት የሚኖረው በሀገራችን ህዝቦች ፍላጎትና ይሁንታ ላይ ተመስርቶ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ከተከራካሪዎቹና ከተዳራዳሪዎቹ የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም።