“. . .ስራ ለባሪያ ነው” የሚለውን አመለካከት እንሻር

በያዝነው አመት የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህ ትኩረት የተሰጠው ወጣት ትውልድ የሃገሪቱን የመሪነት ሃላፊነት ለመረከብ አፋፍ ላይ ይገኛል። ወጣቱ ሃገሩን የሚወድ፣ በሃገሩ ተስፋ ያለው፣ ሃገሩን በትውልድ ቅብብሎሽ ማዝለቅና መምራት የሚችል እንዲሆን በፍጥነት በማደግ ላይ በሚገኘው የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ማደረግ ያስፈልጋል። አቋምና አመለካካቱን የሚያስተናግድለት ፖለቲካዊ ሁኔታም ይሻል። በያዝነው ዓመት ወጣቱ በስራ ፈጠራ የኢኮኖሚ ተሳታፊ እንዲሆን የማድረግ እንዲሁም ፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆን የማደረግ ዕቅድ መነሻ የሆነው ቀዳሚ ምክንያት ይህ ነው።

እርግጥ ወጣቱን በስራ ፈጠራ የኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲኖረውና ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ተግባር አዲስ አይደለም። በ1998 ዓ/ም በተቀረጸው የወጣቶቸ ልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች በስራ ፈጠራ የስራ እድል አግኘተዋል። ከአነስተኛና ጥቃቅን ስራ ተነስተው ወደኢንቨስተር ባለሃብትነት ለመሸጋጋር የበቁም አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ፓኬጅ አሁን በሚፈለገው መጠን ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ አላስቻለም። ይህን በተመለከተ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በያዝነው አመት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይስራ ዘመን መክፈቻ ያጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የአመቱን የመንግስት የክንውን እቅድ ባሳወቁበት ንግግር፤

መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደተንቀሳቀሰ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ከ3ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ይታመናል። ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚሀ ላይ በመመስረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር ፈፅሞ የሚመጣጠን እንዳልሆነ ታይቷል።

ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም፤

የአገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ፣ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት እድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል። ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን የግድ ይላል። በዚህ መሰረት፣ መንግስት በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል። ለዚህም ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ አሥር ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።

ብለዋል።

በዚህ መሰረት ሰሞኑን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶች የዕድገትና ልማት ፓኬጅ የፈንድ አስተዳደር ማዕቀፍ መዘጋጀቱን አስታውቋል። ፓኬጁ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የተመደበውን 10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ጥቅም ላይ የማዋል ዓላማ ያለው መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። የወጣቶች የዕድገትና ልማት ፓኬጅ የፈንድ አስተዳደር ማዕቀፍ በአለም አቀፍ ደረጃና በሃገር ውስጥ ተግባራዊ ተደርገው ውጤታማ መሆናቸው ከተረጋገጠ ተቋማት ልምድ በመውሰድ የተዘጋጀ ነው። ልምድ የተወሰደባቸው ተቋማት የብድር አሰጣጣቸውም ሆነ በብድር አመላለስ 98 በመቶ ስኬታማ መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን  ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከፈንዱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች እድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ያሉ ስራ አጥ ወጣቶች ብቻ ናቸው፣ ወደ ተግባራ ለመግባት በየአካባቢው ትክክለኛ ስራ አጥ ወጣቶችን የመለየት ስራም እየተከናወነ ነው። በየአካባቢያቸው አዋጭ የስራ መስኮችን የመለየትና ወጣቶችን አጠቃላይ በፓኬጁና በተዛማጅ ጉዳዮች የማሰልጠን ስራ የተጀመረባቸው አካባቢዎችም መኖራቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርም ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ከተመደበው የተዘዋዋሪ ፈንድ 5 ቢሊየን ብሩ ወደ ባንክ ፈስስ ማድረጉን አስታውቋል። ይህ ገንዘብም እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ወጣቶቹ የቅድመ ዝግጅት ስራዎቻቸውን ጨርሰው እንዲጠቀሙበትም ተገልጿል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ለፌደራል መንግስት የ18 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ሲያጸድቅ፣ ከዚህ ውስጥ 5 ቢሊየን ብሩ ለወጣቶች የስራ አድል ፈጠራ ተንቀሳቃሽ ፈንድ የሚውል መሆኑን መገለጹም ይታወሳል።

እስካሁን ወጣቱን የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የተከናወኑት ተግባራት ተስፋ ሰጪዎች ናቸው ማለት ይቻላል። አሁን ቀሪው ስራ በተለይ ለወጣቶች የስራ ፈጠራ የተመደበውን ከፍተኛ ባጀት ከኪራይ ሰብሳቢነት በጸዳ ሁኔታ ለታለመለት ወጣቱን አምራችና ተጠቃሚ እንዲሆን የማስቻል ዓላማ ብቻ መዋል ይኖርበታል። በ1998 ዓ/ም ተቀርጾ ወደስራ የገባው የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አፈጻጸም ከፍተኛ ችግር እንደነበረበት ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ሙላቱ በምክር ቤት የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህን በተመለከተ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና ተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአፈፃፀም ብቃት መጓደልና በስነ ምግባር ጉድለቶች ሲደነቃቀፉ  ነበር ማለታቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው እንደገለጹት ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ ፈጠራ ብቻ መዋል የነበረበት ሃብት ከዚህ ተጠቃሚ መሆን ለማይገባቸው ሰዎች እንዲሰጥ የተደረገበት ሁኔታ ነበር። ሰዎች የማይገባቸውን ብድር ወስደው ለሌላ ዓላማ ያዋሉበት ሁኔታ ነበር። ለስራ ፈጣሪ ወጣቶች የተዘጋጁ የመስሪያ የምርት ማሳያ/መሸጫ ቦታዎች ከተገቢው ውጪ አገልግሎት ላይ የዋሉበት እንዲሁም ተዘግተው ለዓመታት ያለአገልግሎት የተቀመጡበት ሁኔታ በስፋት ታይቷል።

አሁን በተዘጋጀው የወጣቶች ፓኬጅ የዚህ አይነት ከስነምግባር ውጪ የሆነ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ሊፈጸም የማይችል መሆኑን የሚያረጋገጥ የአሰራር ስርአት ሊዘረጋ ይገባል። አዲስ የቁጥጥር የአሰራር ስርአት ስለመዘርጋቱ ምንም የተሰማ ነገር የለም። እርግጥ የፓኬጁ መዘጋጀት በተበሰረበት ወቅት በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ወጣቶች ስራ ለማግኘት በሚጥሩበት ጊዜ በፖለቲካ ልዩነት አድልዎ አልያም ሌሎች የመልካም አስተዳደር እክሎች ካጋጠሟቸው ይህን ችግር የፈጠሩ አመራሮችን ወይም ሰራተኞችን በማጋለጥ ተጠያቂ ማድረግ ይገባቸዋል የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ማሳሰቢያው ብቻ በቂ አለመሆኑ ግን መታወቅ አለበት። የሚያጋልጡበት የአሰራር ስርአትም ሊዘረጋ እንደሚገባ ግን መታሰብ አለበት።

ከወጣቶች የስራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ሌላው ሊታወስ የሚገባው ጉዳይ የሃገራችን የሰራ ባህል ወይም ስራ ላይ ያለን አመለካከት ነው። ኢትዮጵያ የእደጠበብ ስራ ማለትም የማምረት ሰራ ሰዎች ተገደው የሚገቡበት ወይም በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች የተገፉ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ የሚሰሩት አለያም በባርነት ስር ያሉ ሰዎች ብቻ የሚፈጽሙት ሆኖ መኖሩ ይታወቃል። በእደጥበብ የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከሰው በታች እንደሆኑ ነበር የሚቆጠሩት። አለያም ባሪያዎቸ ናቸው። ታዲያ በዚህ ስራ ለባሪያ ነው የጨዋ ልጅ ተግባር ቤተስኪያን መሳለም ነው ሲል በኖረ ማህበረሰብ ውስጥ በተለይ በገጠርና በትናናሽ የሃገሪቱ ከተሞች ወጣቶች ያገኙት ስራ ላይ የመሰማራት ድፍረት የሚያጡበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም። ይህ ጎታች አመለካከት ላይ ባለፉ ሁለት ሶስት አስርት ዓመታት መሻሻል መታየቱ ባይካድም አሁንም ሙሉ በሙሉ ያልሻረ መሆኑ ግን እርግጥ ነው።

ባለፉ አመታት በተለይ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ዝንድ ይህ ችግር ታይቷል። በይፋ ለጄን ያስተማረኩት ክራቫት አሰሮ ቢሮ እንዲሰራ እንጂ ድንጋይ እንዲፈልጥ አይደለም ያሉ ወላጆችን ሰምተናል። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር ይህን አመለካካት ያንጸባረቁበት ሁኔታ ነበር። ከዩኒቨረሲቲ የተመረቁ ወጣቶች ድንጋይ ፈላጭ ሆኑ በማለት ታዋቂና የተማሩ የሚባሉ የተቃዋሚ አመራሮች ጭምር በይፋ የወጣቱን የስራ ተነሳሽነት የሚገድሉ አስተያየት ሲሰጡ እንደነበረ ይታወሳል።

በአጠቃላይ ወጣቱን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግስት የተያዘውና ወደተግባራዊነት ለመሸጋገር ቀናት የቀሩት ፕሮግራም ድንቅ ነው። ይሁን እንጂ ፕሮግራሙ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ኪራይ ሰብሳቢነትን በተለይ “. . . ስራ ለባሪያ ነው” የሚለው ስራ ላይ ያለን ጎታች ነባር አመለካከት ሊሻር ይገባል።

 

 

የጋምቢያው ፕረዚዳንት ወደ ጊኒ ሸሹ

ጋምቢያን ለ22 ዓመታት የመሩትና ከወራት በፊት በምርጫ የተሸነፉት ያህያ ጃሜህ ሀገር ለቀው ወጡ፡፡

ጃሜህ መዳረሻቸውን ጊኒ ያደረጉ ሲሆን በቋሚነት ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንደሚያቀኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ጃሜህ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በርካታ የሀገሪቱ ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸው ተገኝተው አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡

ደጋፊዎቻቸው በአውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው እያለቀሱ ሲሸኟቸው አብዛኛዎቹ ጋመቢያዊያን ደስታቸውን በመግለጽ ላይ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

ባለፈው ታህሳስ በተደረገ ምርጫ አዳማ ባሮ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ጃሜህ ስልጣን እለቃለሁ ካሉ በኋላ ምርጫው ችግር ነበረበት በሚል ስልጣን እንደማይለቁ መናገራቸው በአገሪቱ አለመረጋጋት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

ይህንን ተከትሎ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ባሮው በዓለ ሲመታቸውን በስደት በሚገኙበት በሴኔጋል የጋምቢያ ኤምባሲ ፈጽመዋል፡፡

ጃሜህ ከስልጣን ለመውረድ የተስማሙበት መንገድ ገልጽ ያለመሆኑን የዘገበው ቢቢሲ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ መዘጋጀት የራሱ ተጽእኖ መፍጠሩ ታውቋል፡፡