ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን ሀገራዊ መልክ በማስያዝ በሰፊው እየሰራ ይገኛል፡፡ ጥልቀታዊው ተሀድሶ በሁሉም ክልሎችና ተቋማት እየተከናወነ ሲሆን በየዘርፉ ያሉ ችግሮች በሀላፊዎችም ሆነ በሰራተኞች ደረጃ የሚነሱ ቅሬታዎች የአስተዳደር፣ የአመራር፣ የፍትህ፣ የመብት ጥያቄና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በስፋትና በጥልቀት እየፈተሸ በሰፊ ዲሞክራሲያዊ መድረኮች ያለአንዳች የሀሳብ ገደብና ተጽእኖ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ያለውን ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ በወፍ በረር መቃኘቱ የዚህ ፅሁፍ ተግባር ነው፡፡
የጥልቀታዊው ተሀድሶ ዋናው ቁልፍ ግብ የተጀመረውን ሀገራዊ የልማትና የእድገት ጉዞ ለማደናቀፍ በጋሬጣነት የተከሰቱትን የሙስና የኪራይ ሰብሳቢነት፤ ከዚህም ጋር በጽኑ የተቆራኙትን የጠባብነትና የትምክህት አመለካከቶችን፣ ጥገኛነትንና አድርባይነትን ከስሩ ነቅሎ ለማስወገድና የጋራ የሆነ ሀገራዊ መግባባት በሁሉም መስክ በመፍጠር የተጀመረውን ሀገራዊ ልማትና እድገት ሳይስተጓጎል ማስቀጠል ነው፡፡ ችግሮቹ አንዴ ይፈታሉ? ተብሎ ባይጠበቅም በየደረጃው የሚካሄደው ትግል ተጠናክሮ መቀጠሉ ግን የግድ ነው፡፡
የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማው ከመነሻው በአመራሩ ዘንድ ያለው የአመለካከት ክፍተት መቀረፍ እንዳለበት መግባባት ላይ ለመድረስ ያስቻለ በመሆኑ ነው በየደረጃ ወደ ሰፊው ሕብረተሰብ እንዲወርድ የተደረገው፡፡ በተደረገው ሰፊ ግምገማ አመራሩ በውጤታማነት መመዘን እንዳለበት አቅምና ብቃት ያላቸውን ሰዎች በተገቢው ቦታ መመደብ ተገቢ መሆኑ መተማመን ደረጃ ላይ ተደርሶ ነው ከላይ እስከ ታች ሽግሽግ የማድረግ ስራ የተሰራው፡፡
በአመራር ደረጃ የተደረገው ለውጥ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ታይቶበታል፡፡ ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል የተሻለ ለውጥና እድገት ሊያመጣ እንደሚችልም ይታመናል፡፡ የመንግስት አመራር አካላትን ሀብትና ንብረት በተመለከተ ካስመዘገቡት ውጭ አለ የሚሉ የሕብረተሰቡ ክፍሎች ጥቆማ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን ጠ/ሚሩ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከትና አመጽ ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት ከመቻሉም በላይ ሀገሪቱ ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት አስወግዶአል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ወደ ነበረበት የቀድሞው ሁኔታ በመመለሱ ግጭት እንዲፈጠር ይሮጡ የነበሩ ሀይሎችን ጥረት ማምከን አስችሎአል፡፡
ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ የቤቶች ልማት ስራው ግንባታ ቆሟል የሚለው አስተያየት ተገቢ አይደለም፡፡ በክረምት ወቅት እና ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ መቀዛቀዝ ተስተውሎበት የነበረ ቢሆንም የግንባታ ስራው ዛሬም በሰፊው እንደቀጠለ ነው፡፡
ቀደም ባሉት ግዜያት ቤቶችን ወደ ተጠቃሚዎች የማስተላለፉ ሂደት በጣም አሰልቺም አድካሚም የነበረ ሲሆን ይህን ለማስቀረት የአንድ መስኮት አገልግሎት ተጀምሮ እስከ 9 ወር ይፈጅ የነበረውን አሰራር ወደ ሁለት እና ሶስት ወር መቀነስ ተችሎአል፡፡ ይህም በተገልጋዮች ዘንድ የተሻለ አገልግሎትን በመስጠት እርካታን መፍጠር ችሎአል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ 131 ሺህ ቤቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ብድር መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡ በያዝነው ዓመት መጨረሻ 30 ሺህ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ እቅድ መያዙ ታውቆአል፡፡ ቤቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለተገልጋዮች እንዲተላለፉ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ግንባታዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ከግንባታዎች መዘግየት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አመለካከቶች የሚንሸራሸሩ ቢሆንም የግንባታ ዘርፉ ለሀገሪቱ ገና አዲስ መሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ በስፋት የሚስተዋለው ችግር የአመለካከት እና የአቅም ችግር መሆኑን ጥራት፣ ተወዳዳሪነት እና ዋጋ በዘርፉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ጠቅሰው በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር መቅረፍ ጊዜ ቢፈልግም ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ለማስቀረት በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ መጓተት አለ የሚለውን በተመለከተ ሁሉም ፕሮጀክቶች አልተጓተቱም፤ ሁሉም ግን ጥሩ ሄደዋል ማለት አንችልም፡፡ ሲሉ ያለውን እውነት አሳይተዋል፡፡ ትክክልም ነው፡፡
በግንባታ ዘርፉ ከፍተኛ ምዝበራና ሙስና በኪራይ ሰብሳቢዎች አማካኝነት መካሄዱ ከግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ጀርባ በሙስና መረብ የተሳሰረው ክፍል የመንግስትንና የህዝብን ሀብት ያለምህረት በማን አለብኝነት ሲዘርፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሀገሪቱ ፈርጀ ብዙ ግንባታዎች በጎላ ደረጃ በብዙ መስኮች ተካሂደዋል፤ እየተካሄዱም ይገኛሉ፡፡
ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው የመንግስትን ሕግ በመጣስ ያለጨረታ መመዘኛውን ለማያሟሉ በሕጋዊ መስፈርቱ ማለፍ ለማይችሉት ሙያዊ እውቀትና ብቃት ለሌላቸው የግንባታ ጨረታዎችን እየሰጠ ጥራትና ብቃት የሌላቸው መንገዶች ኮንዶሚኒየም ቤቶች ወዘተ ሲሰሩ ኖረዋል፡፡ ይሄን ማስተባበል አይቻልም፡፡ በአንድ ወቅት ፋና ኮርፖሬት ያወጣቸው መረጃዎችም ይህንኑ በተጨባጭ ያረጋግጣሉ፡፡
ይህ የሚያሳየው መንግስታዊና ሕዝባዊ ሀላፊነትን በታማኝነትና በቅንነት ለመወጣት ያለመቻል ስግብግብነትና ግለኝነት ያስከተለው ውጤት መሆኑን ነው፡፡ እንዳይደገም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ባለቤት የሆነ አካል፣ ይህ ራሱም በሌላ ከፍተኛ ተቆጣጣሪ አካል የቅርብ ክትትል እንዲሰራ ካልተደረገ በስተቀር በዚህ ዘርፍ ያለው ችግር መግለጽ ከሚቻለውም በላይ እየተራመደ ያለ መሆኑን ሕዝቡ ይናገራል፡፡
መንግስት ለግንባታው በከፍተኛ ወጪ የሚገዛቸው ብረቶች ሌሎችም ጭምር በመመሳጠር የሚሸጡበት የግለሰቦችን ቤትና ፎቆች በሌሎች ቦታዎች ለመገንባት የሚውሉበት ሁኔታ በሰፊው መታየቱም ይነገራል፡፡ በዚህ መንገድ በሀገር ሀብት በዘረፋ የከበሩ ተሸፍነው የሚኖሩ ዛሬም የግንባታ ጨረታ ሲኖር ተጠርተው የሚሰጣቸው ወይም ካለጨረታ ወደስራ የሚገቡ እልፎች መሆናቸው በተጨባጭ ሊደረስበት ይችላል፡፡ ትኩረት በመንግስት ሊሰጠውም ይገባል፡፡
ሕዝብን ካስመረረው አንዱ ዘርፍ ይሀው ታላቅ ሀገራዊ ምዝበራ የሚካሄድበት የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲሆን መንግስት የተለየ የቁጥጥር ስልትን ማስቀመጥ ካልቻለ በነበረበት እንደሚቀጥል ትልቅ ስጋት አለ፡፡
በሀገሪቱ ከተነገቡት ታላላቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ የባቡር ፕሮጀክቶች (የኢትዮ-ጂቡቲ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር) በተያዘላቸው ጊዜ በመጠናቀቃቸው በጥሩ አፈጻጸም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሆን ተብሎ እንዲጓተቱ የሚደረጉት በሙሰኛውና በኪራይ ሰብሳቢው መመሳጠርና ሴራ ሲሆን ይህም ተጨማሪ ገንዘብ ከመንግስት እንዲወጣ በማቀድ የሚሰራ እጅግ የከፋ የሌብነትና የምዝበራ ስራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የትኛውም ፕሮጀክት ጸድቆ ወደስራ ሲገባ በመጀመሪያው ውል ስራውን ለመጀመር የሚያስችለው ክፍያ በውሉ መሰረት ይወስዳል፡፡ ፕሮጀክቱ ያሳየው ለውጥና የተራመደበት እድገት እየታየ ተጨማሪ ወጪ ከመጀመሪያው በውል ከተቀመጠው ገንዘብ ተቀናሽ እየተደረገ ስራው ሲያልቅ የመጨረሻው ክፍያ እንደሚከፈል ይታወቃል፡፡
የመጀመሪያውን ክፍያ በልተው የሚጠፉም ይኖራሉ፡፡ ወይንም የገበያው ዋጋ ስለጨመረ ስራውን መስራት አልቻልንም በሚል ከውሉ ውጪ ተጨማሪ ክፍያ የሚጠይቁበትም ሁኔታ ታይቶአል፡፡ ይሄ ውስብስብ ችግር የውሉን ሕግ መሰረት ባደረገ መልኩ ሊፈታ ይገባዋል፡፡
ከመንገድ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ 82 በመቶዎቹ በተያዘላቸው የግዜ ሰሌዳ እየተካሄዱ ሲሆን 18 በመቶዎቹ ተጓተዋል፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታን በተመለከተ የሀዋሳ፣ ሽሬ እና ጂንካ አውሮፕላን ማረፊያዎች ለግንባታው ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድመው መጠናቀቃቸው የሚበረታታ ነው፡፡ ግንባታውን ያከናወኑት የሀገር ወስጥ ተቋራጮች ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ውይይት ወቅት መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ከሀይል ማመንጫ ጋር ተያይዞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ጊዜ 58 በመቶ ደርሶአል፡፡ ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ እየተራመደ ይገኛል፡፡ በመስኖ ግድቦችና በከተሞች የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ላይ መጓተቶች መኖራቸውን ለፕሮጀክቶቹ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ከአፈጻጸማችን ተረድተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በዘርፉ የሚስተዋሉ የአቅም እና የልምድ ማነሶችን ለመቅረፍ የውሀ ስራዎች ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መቋቋሙን ገልጸዋል።
ስኳር ፋብሪካዎችን በተመለከተ የስኳር ፕሮጀክቶቻችን ከእቅድ ጀምሮ ችግር እንዳለባቸው መቀበል አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስሩን የስኳር ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ መጀመራችን አቅምን የሚፈታተን ነበር ብለዋል፡፡ በስኳር ፕሮጀክቶቹ ግንባታ በኩል ያጋጠሙት ፈተናዎች ከባድ ቢሆኑም ዛሬ ላይ መፈታታቸው ግንባታውን በሚያከናውኑ ድርጅቶች በኩል ችግር እንደነበር በተለይም የሕንድ ኩባንያዎች አቅም ማነስ እና ባህሪ መወሳሰብ ከችግሮቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በቻይና ኩባንያዎች ግንባታቸው በመከናወን ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ግንባታቸው በመከናወን ላይ የሚገኙት ኩራዝ አንድ እና በለስ አንድም ከነበሩበት ደረጃ ያደጉ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የመኸር ምርት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ12 በመቶ እድገት አሳይቶአል፡፡ በተያዘው የምርት ዘመን ከበልግና መስኖ እርሻው ጋር ተዳምሮ የበለጠ ምርት እንዲኖረን ያግዛል፡፡ አርሶ አደሩ በምርቱ ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፉ ለተገኘው እድገት መሰረታዊ ምክንያት መሆኑም ታውቆአል፡፡