የአክራሪው ኃይል ባዶ ተስፋ…

አክራሪው ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግሥቱ ካስቀመጠው አኳኋን ውጭ በድርድርም ይሁን ህገ መንግሥቱን በመጣስ መንግሥታዊ ሥልጣን መያዝ እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቃል። ኃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም የጎዳና ላይ ነውጥ እና ትርምስ መፍጠር በህጋዊ መንገድ ያጡትን ሥልጣን በአቋራጭ በግርግር ለመቆናጠጥ የመቧዘኑ ምስጢር  ኃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንደሆነ በግልፅ ይታወቃል።

 

የአክራሪው ኃይል አማኞችም ሆነ ቅዠት የተለያዩ የማደናገሪያ የፈጠራ ወሬዎችን በማዘጋጀት የምዕመኑን አስተሳሰብ በመስለብና በማታለል  የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያስችለው አፍራሽ ድርጊት ውስጥ ከተዘፈቀም ሰነባብቷል።  

 

ይህ አክራሪው ኃይል በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎችን የሚፃረር በመሆኑ ዛሬ ላይ በግልጽ በሚታይ መልኩ ተቀባይነት አጥቷል። ማንኛውን ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚተላለፍ ድርጊት ነው፡፡

 

ምን ይህ ብቻ! አክራሪው ኃል ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ኃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም በግል ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተግበር ወይም የመግለፅ መብትንም የማያከብር በመሆኑ በሕዝቦች ዘንድም ተቀባይነት ሊኖረው አልቻለም።  

 

የአክራሪነትና የፅንፈኝነት ጫፍ የንፁኃን ዜጎችን አስተሳሰብና አመለካከት በጫና የመቀየር አካሄዱ ካልተሳካ ወደ ጅምላ ግድያ የሚሸጋገር ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በመሆኑ በማንኛውም መሥፈርት ኃይማኖታዊ ተልዕኮ የሌለው እንደሆነ  አያጠያይቅም፡፡

 

ዜጎችን በመረጡትና በያዙት ኃይማኖት ምክንያት ለማሸማቀቅ መሞከር በኃይል ኃይማኖታቸውንና እምነታቸውን ለማስቀየር መንቀሳቀስ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ተቀባይነት የሌለው ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ ነው። እዚህ ላይ እንዲህ ዓይነቱን ፀረ ሠላም እንቅስቃሴ የሚሸከም ኅብረተሰብ በአገሪቱ እንደሌለ መገንዘብ የግድ ይሆናል። የእኔን ኃይማኖት ካልተከተልክ በስተቀር አማኝ አይደለህም አሊያም ከሃዲ ነህ በማለት ማሸበርም ሆነ አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ መፈፀም የእምነት ተቋማትን ማፍረስና መካነ መቃብሮችን ማውደም በእውነት በፀረ ሠላም ኃይሎች የሚጠነሰስ ሴራ ብሎም የሌሎችን ነጻነት በማፈን ድብቅ ዓላማን ለማሳካት የተያዘ እንቅስቃሴ መሆኑ ከማንም የተሸሸገ ጉዳይ አይደለም።  

 

እነዚህ ድርጊቶች የአክራሪነትና ፅንፈኝነት መገለጫዎች ናቸው። በአገራችን እየተፈፀመ ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ሽብርተኝነት ፀረ ልማት በመሆኑ ይህንን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንጂ ለመንግሥት ወይም ለሌላ ወገን ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ የኃይማኖት አክራሪነት በጥቅሉ የዜጎችን የኃይማኖትና እምነት ነፃነት በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ እንደሆነ ለማየት ይቻላል። የኃይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስም ሌላው ተግባራቸው ነው። ይህም ሁኔታ መንግሥታዊ ኃይማኖትን ለመመሥረት የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ ከመሆኑ ሌላ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሥርዓቱን ለመቀልበስና ሕገ መንግሥቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የሚጠነጠን ድርጊት እንደሆነ ለሁሉም እሙን ነው፡፡

 

አክራሪው ኃይል እኩይ ተልዕኮውን ለማከናወን ወጣቶችን የዓላማው ማስፈፀሚያ አድርጎ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ችግሩ ምን ያህል ፈታኝና አስከፊ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ፅንፈኛው ኃይል የተለያዩ በሬ ወለደ ዓይነት የማደናገሪያ አጀንዳዎችንና አማላይ ዘዴዎችን በመጠቀም ወጣቶችን በዓላማ ማስፈፀሚያነት ለመጠቀም ያለ የሌለ አቅሙን በመጠቀም እየተፍጨረጨረ ነው።

 

አገራችን በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ጎዳና ላይ በፍጥነት እየገሰገሰች ትገኛለች፡፡ የአክራሪዎች ዓላማ አልፋና ኦሜጋም ይህ በፍጥነት እየገሰገሰ ያለው ዕድገታችን በእንጭጩ በመግታት አገሪቱ ለዓላማቸው የተመቸች ሆና እንድትኖር የማድረግ ትንቅንቅ ነው። በሌላ አገላለፅ የአገራችን የህዳሴ ጉዞ በማሰናከል በድህነትና በኋላ ቀርነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን በከፍተኛ መስዋዕትነት ትናንት ወዳለፍነው ድቅድቅ ጨለማ የመመለስ ተግባር ነው።

 

ኢትዮጵያውያን ያሳለፉትን አስከፊ ድህነትና ኋላ ቀርነት  ጠንቅቀው ያውቁታል። ያ ታሪክ ተመልሶ እንዲመጣ የሚፈቅዱበት መንገድ የለም። በአክራሪነትና ፅንፈኝነት ላይ የሚኖራቸው ትግል ለአፍታም ቢሆን አይዘነጋም። በአክራሪዎችና ፅንፈኞች ላይ የሚወሰደው ሕጋዊ ርምጃም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።

 

ፅንፈኞች በአገር ውስጥም ሆነ  በውጭ የሚገኙ ፀረ ሠላም  ኃይሎችን በማስተባበር የሞት የሽረት ትግል ያደርጋሉ። በአገር ውስጥ አንዳንድ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችን እንዲሁም አፍራሽ ሚዲያዎችን በማስተባበር በቅብብሎሽና በቅንጅት የሚሰሩበት ሁኔታም በስፋት ታይቷል።  

 

በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ የቆየው የመቻቻል እና አብሮ የመኖር እሴት እንዲቀጥል የኃይማኖት ተቋማቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ቢሰጡም እንቅስቃሴው ሌላ ተልዕኮ ያለውና ኃይማኖታዊ ባለመሆኑ ዛሬም አልተዳፈነም። ከጥንት ጀምሮ በኃይማኖቶች መካከል ያለውን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት ለማስቀጠል እያንዳንዱ የኃይማኖት ተቋማትና የእምነቱ ተከታዮች አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው። በተለይ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሠላም እምነቱን እንዲያራምድና ለፀጥታ መሰናክል የሆኑ አካላትን ቀድሞ እንዲከላከል ለማድረግ  ለእምነቱ ተከታዮች በየመስጂዱ በሠላም ዙሪያ ትምህርት የመስጠቱን ተገቢነት አጠናክሮ ማስኬድ ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም።

 

ሙስሊሙ ኅብረተሰብ አክራሪነትን ለመከላከልና የአገሪቱን ሠላም ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የፀረ ሽብር ዘመቻን እየደገፈ ይገኛል። በዚህም  በርካታ የሽብር ተግባራትን ማክሸፍ ተችሏል። በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የተገነባው ተቻችሎና ተከባብሮ በሠላም የመኖር እሴት ለማስቀጠል በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ኃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ተግባራትን ለመዋጋት የኃይማኖት ተቋማት በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ከመፍጠር አንፃር ትልቁን ድርሻ ወስደው ሊሰሩ ይገባል። መንግሥት ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ህገ መንግሥታዊ  መብቶችን የሚጥሱና የህዝብን ሠላም የሚነሱ አካላት ላይ በተለያየ ጊዜ ሕጋዊ እርምጃ ቢወስድም   በህገ መንግሥቱ የተመለሱ ጥያቄዎችን እንዳልተመለሱ በማንሳት ሽብርን ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት መከሰታቸው አልቀረም።

በኃይማኖት ስም አልፎ…አልፎ በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገራት እየተፈፀመ ያለው የአሸባሪነት ተግባር እየተስፋፋ መጥቷል ለማለት ባያስደፍርም ብቅ ጥልም እያለ በማድረስ ላይ ያለው ጉዳት ሙሉ በሙሉ መግታት እንዳልተቻለ  እሙን ነው። በናይጄሪያ፣ በግብጽ፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በግብጽ፣ በሊቢያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት የኃይማኖት አክራሪነት እንቅስቃሴ ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ቀደም ሲል በሶማሊያ ጠንካራ ይዞታ መስርቶ የነበረው አልሸባብም በኢትዮጵያ የሽብር ተግባራትን በተለያየ ጊዜ ለመፈፀም ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።  ግንቦት ሰባት፣ ኦብነግና ኦነግ የሚባሉ ቡድኖችም አልሸባብና የኤርትራ መንግሥት በሚሰጧቸው መመሪያ እና ድጋፍ መሠረት የኢትዮጵያን ሠላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱም ታይተዋል።

የሽብር ቡድኖቹ በዋናነት ኢትዮጵያ ላይ አነጣጥረው እየሰሩ እንደሆነም እሙን ነው። የእነዚህ ቡድኖች ዋና ዓላማ የአገሪቱን የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴን ማኮላሸት እንደሆነ ካለፉት 25 ዓመታት እንቅስቃሴያቸው ለመረዳት ይቻላል። በአገሪቱ እየተካሄዱ ባሉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመፈፀም ፍላጎት ቢያሳዩም በመላው ኅብረተሰብ ጥረት ምኞታቸው ሳይሳካ ቀርቷል። ሃሳብ ውጥናቸው ዳር ሳይደርስ መክኗል። ዓላማ – ተስፋቸውም ባዶ ሆኖ እንዲሁ ቀርቷል።