የዳያስፖራ ፖለቲከኞች  ከእንግዲህ  የጥፋት እጃችሁ አጥሯል!

 

ጽንፈኛው ዳያስፖራ አገራችንን ወደሁከት እንድታመራ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች የህዝቦችን የአብሮ መኖር እሴት እንዲሸረሸር ብሄርን ከብሄር፣ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት  ተሯሩጠዋል፣ የንጹሃን ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነዋል፣ የህዝብና የግለሰቦች ንብረት እንዲወድም  አድርገዋል፣ ዜጎች ተወልደው ካደጉበትና ለረጅም ጊዜ ከኖሩበት አካባቢዎች እንደባዕድ ተቆጥረው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፣ ወዘተ ተካሂደዋል።  እነዚህ ሃይሎች ከዚህ ተከፋም  እኩይ ተግባረትን  በእናት አገራቸው  ላይ ፈጽመዋል። አስፈጽመዋል። በቅርቡ በአገራችን በተከሰተው ሁከትና ረብሻ ተዋናይ የሆኑት ትምክህትና ጥበት ግንባር ፈጥረው  ታይተዋል። 

 

እነዚህ ሁለት ጽንፎች የማይገናኙና  ሆነው ሳለ ለጥፋት  ሲሆን  እርስ በርስ ሲሞከሻሹና  ሲደጋገፉ ታይተዋል። የጥበት ሃይሉ በየትኛውም መስፈርት ከትምክህተኛው ጋር የጋራ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም። በእርግጥ ሁለቱን ሃይሎች የሚያመሳስላቸው በወጣቱ ተጠቅመው የስልጣን ኮርቻው ላይ ለመፈናጠጥ ያላቸው  ምኞት ብቻ ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የስልጣን ምንጭ የህዝብ ድምጽ ብቻ ነው።  

 

ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ሁለቱ ሃይሎች እርስ በርስ የሚጠፋፉ ሆነው ሳሉ አገራችንን ወደ ሁከት ለማምራት ግን ግንባር ፈጥረው ህዝቡን ሲያውኩ ነበር።  የእነዚህን  የጥፋት ሃይሎች ቁርኝት ህብረተሰቡ አውቆታል። በመሆኑም በቃችሁ ከእንግዲህ ልጆቻችንን መጠቀሚያ አታደርጉም፣ ንብረታችንን አታወድሙም  ብሎ ድርጊታቸውን አስቁሟቸዋል። ይሁንና እነዚህ ሃይሎች ነገም መልካቸውን ቀይረው እንዳይመጡ ህብረተሰቡ ከወዲሁ ሊጠነቀቅ ይገባል።

 

ዳያስፖራ ፖለቲከኞች ያሰቡት አልተሳካላቸውም እንጂ ባለፈው ጊዜ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በቀሰቀሷቸው አመጾች ሰዎች ለሞት እና ለእንግልት እንዲሁም ለንብረት ውድመት ተዳርገዋል፡፡ ይሁንና ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት በመቻላቸው አገራችን ወደ ቀድሞዋ መረጋጋት ተመልሳለች፣ ልማቱም ቀጥሏል፣ ህዝቦችም የቀድሞው አብሮነታቸው ተመልሷል፤ የቱሪስት ፍሰቱም ወደነበረበት ተመልሷል።  ጽንፈኛው ሃይል ቆሜለታለሁ የሚለውን  ህዝብ መሃበራዊ መገልገያዎች ሲያወድም፣ የራሱን ህዝቦች ሲገድልና ሲያሰቃይ ነበር።

 

በአንድ ወቅት ኦብነግ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በራሱ ጎሳዎች ላይ ይፈጽመው የነበረውን ድርጊት ማስታወስ ይቻላል። ኦነግም በኦሮሞ ህዝብ ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ሲፈጽም ነበር።  እነዚህን የጥፋት ሃይሎች ከህዝብ የነጠላቸው የመጀመሪያው ነገር ይህ ሰይጣናዊ ድርጊታቸው ነበር። አሁንም ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች አንዱ የጥፋት በር ሲዘጋባቸው ሌላውን ያማትራሉ። ትላንት የተጠቀሙበትን መንገድ ነገ ላይ ላይጠቀሙ ይችላሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ የእነዚህን የጥፋት ሃይሎች መሰሪ አካሄድ ሊያውቅ ይገባል።

 

ኦነግና ግንቦት ሰባት  መበታተኗን፣ ውድቀቷን፣ ድህነቷን ብቻ ሁሉን መጥፎ ነገር ለአገራችን ከሚመኙ ሃይሎች ጋር በማበር ለጥፋት ተላልከዋል።  ኦነግና  ግንቦት ሰባት ከያዛችሁት እኩይ ተግባር የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነው። የበደላችሁትን ህዝብ የመካሻው ወቅት አሁን ነው።  ከእንግዲህ እጃችሁን ከመሰብሰቡ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖራችሁም፡፡ አማራጩ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ የያዛችሁትን የጥፋት መንገድ ትታችሁ ሰላማዊውን የትግል መስመር ብትከተሉ የተሻለ ነው።

 

ጠባቡና ትምክህተኛው ሃይል በስልጣን ሱስ ናውዟል። የዲያስፖራ ፖለቲካን እንደ አትራፊ ቢዝነስ በመቁጠር አንዳንድ  ግለሰቦች  የዳያስፖራ ፖለቲከኝነትን የሙሉ ጊዜ ስራ አድርገውታል።  እነዚህ ሃይሎች የተሳሳተ መረጃ  ለዳያስፖራው አባላት በማቀበል ሁከትና ብጥብጥ መፍጠርን እንደገቢ ማስገኛ መንገድ ተጠቅመዋል። ይህ ተግገባር ህዝብን መክዳት ነው፤ አገርን መሸጥ ነው። አሁን አሁን ኦነግንና ግንቦት ሰባትን ይህ እኩይ ተግባራቸው ከህብረተሰቡ እንዲነጠሉ አድርጓቸዋል። ይሁንና አሁንም ከጥፋት ድርጊታቸው ይሰበሰባሉ ማለት አይቻልም።  

 

አንዳንድ በአገር ውስጥ “ሰላማዊ ትግል” እናካሂዳለን የሚሉ ፓርቲዎች ከነኦነግ የሚለያቸው ተጨባጭ መስፈርት ምን እንደሆነ ለመረዳት በሚያስቸግር ሁኔታ ነውጠኝነትን እንደ አማራጭ  የትግል  መስመር እንደሆነ ማማተር ሁኔታ ይታይባቸው ነበር። ኦነግንና ግንቦት ሰባትን አይነት ሽብርተኛ ድርጅቶችን ያለማውገዝ በራሱ  ነውጠኝኘነት ነው። 

 

አሁን ላይ ኢህአዴግ  ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር ለመነጋገር እንዲቻል መድረኮች በመካሄድ ላይ ነው። በመሆኑም  ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀውን ነገር አጀንዳዎች ማራመድ ይኖርባችኋል። አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲህ ያለ መድረኮች ሲዘጋጁላቸው ተከራክረው የሃሳብ ብልጫውን ከመውሰድ ይልቅ በትናንሽ ጉዳዮች ላይ ሲጨቃጨቁ አገራዊ ጉዳዮችን ይዘነጓቸዋል።

 

ከዚህ በፊት በነበሩ የድርድር መድረኮች ላይ እንደተመለከትነው ለአንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አጀንዳ የሚያቀብሉት  ጽንፈኛው ዳያስፖራ  ፖለቲከኞች ሆነው ይታያሉ። ጽንፈኛው ዳያስፖራ ፖለቲከኞች አገራችን ከተረጋጋች ህልውናቸው እንዳበቃለት ስለሚረዱ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ነውጦችንና ሁከቶችን  ወደኋላ አይሉም።  እነዚህ የጥፋት ሃይሎች በተቻላቸው መጠን ሁሉ ጭር ሲል አይወዱም። እነታማኝና ጃዋር የዳያስፖራ ፖለቲከኝነት የትርፍ ጊዜ ስራ ሳይሆን ዋንኛ የገቢ ምንጭ ነው። በመሆኑም አገር ቤት ሰላም ውሎ ካደረ እነዚህ ሃይሎች የገቢ ምንጫቸው አደጋ ላይ የወደቀ ስለሚመስላቸው በተቻለ አቅም ሁከትና ብጥብጥን በሚዲያዎቻቸው  ሲሰብኩ  ውለው ያድራሉ።

 

ጃዋርና አጋሮቹ ሁከትና ብጥብጥን ሲፈበርኩ ውለው ሲፈበርኩ ያድራሉ።  የፈበረኳቸውን የሃሰት መረጃዎች ሳይታክቱ  በመርዘኛ ሚዲያዎቻቸው ወደ አገር ቤት ለማሸጋገገር የማያደርጉት ጥረት የለም። የዳያስፖራ ፖለቲከኞች በአገራችን የታዩት መልካም ነገሮችን ሁሉ በዜሮ የማጣፋት ነገር ክፉኛ ተጠናውቷቸዋል። የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ትኩረት  የፌዴራል ስርዓቱን በተቻለ አቅም ሁሉ ማጣጣል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ  ስራ ላይ ነው። እባካችሁ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች  በሪሞት ኮንትሮል የሚካሄድ  ፖለቲካ የለምና ከጥፋት ድርጊታችሁ ተመለሱ።  የበደላችሁትን ህዝብ ይቅርታ ጠይቁና ወደአገር ቤት ተመልሳችሁ ሰላማዊውን ትግል ተቃላቀሉ። ከእንግዲህ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች  የጥፋት እጃችሁ አጥሯል።