የትምክህትና የጥበት ጎራው ያልሰመረ ጋብቻ

ኢትዮጵያን ሁከት ውስጥ ከትቶ ያልተረጋጋችና በሠላም መታጣት የምትናጥ አገር እንድትሆን በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። ለዚህም ስኬታማነት ሲባል የትምክህትና የጥበት ኃይሎች ግንባር ፈጥረውና ጋብቻ መሥርተው መክረዋል። ከዚያም እልፍ ሲል እርስ…በርስ ተሞካክሸዋል፤ ተደጋግፈዋል።

 

በግልጽ እንደሚታወቀውና ብዙዎችም እንደሚስማሙበት ግን የጥበት ኃይሉ በየትኛውም መሥፈርት ከትምክህተኛው ጋር የጋራ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም። በእርግጥ ሁለቱን ኃይሎች የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ቢኖር በወጣቱ ተጠቅመው የሥልጣን ኮርቻው ላይ ለመፈናጠጥ ያላቸው  ምኞት ብቻ ነው። 

 

ሁለቱ ኃይሎች እርስ በርስ የሚጠፋፉ ሆነው ሳሉ አገራችንን ወደ ሁከት ለማምራት ግን ግንባር ፈጥረው በጋራ ሲቆሙ ታይተዋል። የእነዚህን የጥፋት ኃይሎች ቁርኝትን አሊያም ትስስርን ኅብረተሰቡ ጠንቅቆ ያውቀዋል።

 

በመሆኑም በቃችሁ፣ ከእንግዲህ ልጆቻችንን መጠቀሚያችሁ አታደርጉም፣ ንብረታችንን አታወድሙም ብሎ የጥፋት ድርጊቶቻቸውን አስቁሟቸዋል። ይሁንና እነዚህ ኃይሎች ነገም መልካቸውን ቀይረው እንዳይመጡ ኅብረተሰቡ ከወዲሁ ሊጠነቀቅ ይገባዋል።

 

ጠባቡና ትምክህተኛው ኃይል በሥልጣን ሱስ ናውዘዋል። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ስለመናድ የሚዶልቱትን የአመፅ ሴራቸውን ሲያውጠነጥኑ፤ እንቅልፍ አጥተው በማደር የሚታወቁት የውጭና የውስጥ ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ስለመሆናቸው ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

እንዲሁም ደግሞ እንደነ ጁሐር መሐመድ እና በኦሮሞነት ሽፋን የሚነዛ አፍራሽ ፕሮፖጋዳቸውን ለማዛመት ያለመ የዲያስፖራ ፖለቲካን እንደ አትራፊ የእንጀራ ገመድ የቆጠሩት መሰሎቹን ጭምር ከጠባብ ብሔርተኞቹ የኦነግ መሪዎች ተለይተው በማይታይ ፈጣጣ ጎጠኝነት የተጫረውን የአመፅ እሣት ይበልጥ ለማቀጣጠል ሲሞክሩ የመስተዋላቸው ጉዳይ አደባባይ የወጣ ግልጽ ጉዳይ ነው።

 

የጥበት ጎራው አቀንቃኞች በኦሮሞ ብሔርተኝነት ዙሪያ የሚያነሱትን ጎጠኛ የመከራከሪያ ሃሳብ ከኦነግ የመገንጠል አጀንዳ በውል የሚለየው ምክንያታዊ ትንታኔ ምን እንደሆነ ግልፅ ያደረጉበት አጋጣሚም የለም። የጥበት ኃይሎቹ አመራሮች  በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ሳይቀር እየተጋበዙ የሚሰጡት አስተያየት፤ የኦሮሚያ ክልል ለጋ ወጣቶችን ለጠባብ ብሔርተኝነት አደጋ የሚያጋልጥና ንፁህ ልባቸውን ለአመፃ ተግባር እንዲሸፍት ጭምር አያደርግም ብሎ መውሰድ ከቶ አይቻልም።

 

በዚያ ላይ ደግሞ እዚህ አገር ውስጥ “ሠላማዊ ትግል” እናካሂዳለን የሚሉትና ግን ደግሞ እነኦነግ ከሚያራምዱት አቋም የሚለያቸው ተጨባጭ መሥፈርት ምን እንደሆነ ለመረዳት በሚያስቸግር መልኩ ነውጠኝነትን እንደ በጎ ተግባር ሲወስዱት የምናያቸው አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኦሮሞ ህዝብ ስም በትረ ሥልጣን የሚጨብጡበትን ቀን ከመናፈቃቸው የተነሳ ሥርዓቱ ላይ የማይጎነጉኑት ሴራና የማይፈፅሙት ደባ ይኖራል ተብሎ አይታመንም፡፡

 

መለስ ብለን ለማስታወስ ያህል ጁሐር መሐመድ የተባለውን ጎጠኛ ግለሰብ ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፈ የፖለቲካ ተንታኝ ተደርጎ የመቆጠር እድል ያስገኘለት ምክንያትም አገር ቤት ያሉት ሥልጣን ናፋቂ የኦሮሞ ተወላጅ ተቃዋሚዎች እያቀነባበሩ የሚያቀብሉት የውንጀላ ፍብረካ መሠረተ ቢስ ተግባር ነው ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም፡፡

 

የጥበት ኃይሎቹ ወጣቶችን ለአመጽ በማነሳሳት እልቂት ወደ ሥልጣን የመውጣት ህልማቸውን ለማሳካት ሲሞክሩ ከሚስተዋሉባቸው የአመፅ ናፋቂነት አዝማሚያዎች መካከል አንዳንዶቹን ለመመልከት ያህል ጥቂት ነጥቦችን መቃኘቱ ጠቃሚነት አለው፡፡

 

"የኦሮሞ ህዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚረጋገጥበት እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓተ መንግሥት በኢትዮጵያ እንዲመሠረት እንፈልጋለን፡፡ እናም ያን ለማድረግ ስንል ከማንኛውም ሀሳባችንን ከሚቀበል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ተባብረን ትግላችንን ለማስቀጠልና ኢሕአዴግ ተገዶ የኦሮሞን ጥያቄዎች እንዲመልስ ለማድረግ ተዘጋጅተናል" ሲሉም ይደመጣሉ።  

 

የዛሬዋ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የተመራችበትን ሥርዓተ መንግሥት “ውግዝ ከመአሪየስ” የማለት ያህል በሚቆጠር ፅንፈኛ አቋምም ይቃወማሉ።  

 

ኢሕአዴግ በኦሮሞ ህዝብ የዘመናት ታሪክ ልዩ ሥፍራ የሚያሰጠውን ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ መርቶ ዛሬ ላይ ወደደረሰበት አመርቂ ውጤት ለማሸጋገር የቻለ ታጋይና አታጋይ የፖለቲካ ድርጅት ስለመሆኑ አምኖ መቀበልን እንደ ውርደት ያዩታል።

 

የጥበት ኃይሎቹን የተጠና ዘረኝነት ልብ ላለ ታዛቢ አደገኛ የማነካካት ፖለቲካዊ ቁማር በመጫወት የተካኑ ስለመሆናቸው ለመረዳት ብዙ መድከም አያስፈልግም።

በኦሮሞ ሰፊ ህዝብ ጫንቃ ላይ ታዝለው እንዳሻቸው መወዛወዝን ምርጫቸው አድርገው ሲላወሱም ይስተዋላሉ – የጥበት ኃይሎቹ።

 

የጥበት ኃይሎቹ የዜጎችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዴሞክራሲያዊ መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቶ ከተረጋገጠ ሁለት አሥርት ዓመታት የመቆጠራቸውን ታሪካዊ እውነታ ክደው ሊያስክዱ ሲሞክሩም ይስተዋላሉ።

 

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይማር ባስተማራቸው ጥቂት ሥልጣን ናፋቂ የፖለቲካ ልሂቃን ፀረ ሠላም የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክንያት ለአላስፈላጊ የህይወትና የንብረት ኪሳራ እየተዳረገ የሚኖረው እስከ መቼ ድረስ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ አጥጋቢ ምላሽ ይሻል፡፡

 

በትግል ሂደታቸውና አቋማቸው ጨርሶ የማይተማመኑት፣ ለጥፋት ተግባር ሲባል ብቻ ከያሉበት ዋሻ ተጠራርተው የተሰባሰቡት፣ ከበስተጀርባቸው የሸጎጡትን ጎራዴ ትንሽ እልፍ ሲሉ የሚማዘዙት፣ ለጥፋት፣ ለሁከትና ሽብር ሲሉ በጋብቻ የተሳሰሩት የትምክህትና የጥበት ኃይሎች ተካክደው የቃል ኪዳን ቀለበቶቻቸውን ወንዝ ሳይሻገሩ የሚወራወሩ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።