መንግስትና የኢትዮጵያ አርብቶ አደር

 

የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች መኖሪያ 61 በመቶ የሆነውን የአገሪቱን መሬት ይሸፍናል። በአርብቶ አደርነት የሚኖረው ህዝብ ደግሞ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እስከ 15 በመቶ ይደርሳል። የኢትዮጵያ አርብቶ አደር በዚህችው አገር ወሰን ውስጥ የሚኖር ቢሆንም የማይደረሰበት፣ የማይታይ፣ የማይሰማ የሩቅ ሰው ሆኖ ነው የኖረው፤ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ መንግስታት አያውቁትም ነበር። እሱም እንዲሁ ሳያውቃቸው ኖሯል። የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ለቀደሞዎቹ መንግስታት የማይጨበጥ፤ እዚህ ሲሉት እዚያ፣ እዚያ ሲሉት እዚህ የሚገኝ ነበር።

የቀደሙት የኢትዮጵያ መንግስታት አርብቶ አደሩን አያስተዳድሩትም ነበር ማለት ይቻላል። የመንግስት መዋቅር ወደአርብቶ አደሩ መኖሪያ መንደሮች አልዘለቀም ነበርና፤ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት አልነበረም። በዚያን ጊዜ አርብቶ አደሩ ሀኪም ቤትና ትምህርት ቤት ለተሰኙት ተቋማት ባእድ ነበር። ተፈጥሮ ከምትሰጠው ውሃ፣ የጸሃይና የጨረቃ ብርሃን የዘለለ የንጹህ ውሃ አቅርቦትና የመብራት አገልግሎት፤ ወዘተ. አያውቅም ነበር።

በዚህም የኢትዮጵያ አርሶ አደር ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው የኖረው ማለት ይቻላል። በየጎሳው በባህላዊ የአስተዳደር ስርአት፤ ታዲያ፤ ግጭት ለአርብቶ አደሩ የአጋጣሚ ሳይሆን የዘወትር ህይወቱ አካል ነበር። ከአጎራባች ጎሳና አልፎ አልፎም ከአገር ድንበር ተሻገረው ከሚኖሩ አርብቶ አደሮች ጋር በውሃና በግጦሽ ሳር ይጋጫል። አርብቶ አደሮች ግጭት የሚፈቱበት ባህላዊ ስርአት ያላቸው መሆኑ ባይካድም ህይወታቸው ግን ሁል ጊዜ ስጋት ላይ ነች። ታዲያ አርብቶ አደሩ ደህንነቱን የሚጠብቅለት የመንግስት ሃይል ሰለሌለ ጦርና ጠመንጃ አብሮት እንደተፈጠረ የአካሉ ክፍል ያህል አይለየውም።

የአርብቶ አደሩ ኑሮ በእንስሳት ላይ የተመሰረተ ነው፤ በቀንድ ከብት፣ ግመል፣ ፍየልና በግ እርባታ፤ እንሰሳቱ ህይወቱ ናቸው። ወተታቸው፣ ቂቤያቸው፣ ደማቸው ቀለቡ ነው። እህል ብዙ አይፈልግም፤ ትንሽ ማሽላ ወይም በቆሎ በቂው ነው። እርሱንም ቢሆን አርሶ አያመርትም፤ ከአጎራባች አርሶ አደሮች በከብት ይለውጣል እንጂ፤ ከብቶቹ ለአርብቶ አደሩ የቀለቡ ምንጭ  ብቻ አይደሉም። ይልቁንም ማዕረጉም ጭምር እንጂ፤ ብዙ ከብት ያረባ አርብቶ አደር ባለማእረግ ነው። እናም እንስሳት ከሚሰጡት ቁሳዊ ፋይዳ በላይ ይወዳቸዋል። ያረባቸዋል፣ ይንከባከባቸዋል። ቀለቡም ማዕረጉም ስለሆኑ፤

ታዲያ አርብቶ አደሩ ከብቶቹ እንዲቀልቡት፤ ረብተው፤ በዝተው ማዕረጉን ከፍ እንዲያደርጉለት ሳርና ውሃ ያስፈልጋቸዋል። ሳርና ውሃ ደግሞ ወቅት ጠብቆ በዝናብ መባቻና ማግስት የሚገኝ እንጂ ዓመቱን ሙሉ የለም። ውሃም ቢሆን በክረምት እንጂ በጋ ላይ እንደልብ አይገኝም። ከዚህ በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ለመኖር አመቺ  ባልሆኑ ዝናብ አጠር ቆላማ አካባቢዎች የሚኖር በመሆኑ ለከብቶቹ ሳርና ውሃ የማግኘቱን ነገር ፈታኝ አድርጎበታል። ይህ ብቻ አይደለም፤ እያሰለሰ አገሪቱን የሚመታት ድርቅ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለከፋ አደጋ ያጋልጠዋል/አጋልጦታል።

እርግጥ፤ ድርቅ አርሶ አደሩንም ምሮት አያውቅም። ጥቃቱ ግን በአርብቶ አደሩ ላይ ይበረታል። የሚበረታበትም አርብቶ አደሩ ምን ሃብታም ቢሆን ለከርሞ ብሎ በጎተራ የሚያከማቸው ቀለብ የሌለው በመሆኑ ነው። ሰማይ ደመና ርቆት ውሃ አላግት ብሎ  ምድር ስትደርቅ፣ የየእለት ቀለቡን  የሚለግሱት ላሞቹ፣ ፍየሎቹና ግመሎቹ ጡታቸው አላግት ይላል። ጠውልገው ደም መስጠት አይችሉም። የምድር መድረቅና የአርብቶ አደሩ ምግብ ማጣት የሚከሰቱት አንድ ላይ ነው ። ከከባድ ድርቅ በኋላ የማገገሙም ነገር ቀላል አይደለም። ከብቶቹ በድርቅ ያልቃሉና።

ይህ ብቻ አይደለም። ለአርብቶ አደሩ የእለት ደራሽ እርዳታ የማቅረብ ስራ ከአርሶ አደሩ ጋር ሲነጻጻር እጅግ አስቸጋሪ ነው። አስቸጋሪ የሚያደርገውም አርብቶ አደሩ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ የሌለው መሆኑ ነው። የተንከራታቹ አርብቶ አደር አድራሻ አይታወቅም። መሰረተ ልማትም ሰለሌለው ለእርዳታ አቅርቦት ያስቸግራል።

ይህ ማለት ግን፤ አርብቶ አደሩ ተሰፋ ቢስ ደሃ ነው ማለት አይደለም። በገንዘብ ሲሰላ በከፍተኛ ዋጋ የሚገመቱ ከብቶች አሉት። አገሪቱን በእንስሳት ቁጥር ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደረጋት በአርብቶ አደሩ እጅ ያሉ ከብቶች ናቸው። እነዚህ ከብቶች በእንክብካቤ ቢያዙና ህጋዊ የገበያ ስርአት ውስጥ ቢገቡ ለአርብቶ አደሩም ለአገርም ትልቅ ፋይዳ እንደሚነ ኖራቸው አያከራክርም።

ይህ ከላይ በአጭሩ ያሰፈረኩት እውነታ የአርብቶ አደሩን አናኗር በጨረፍታም ቢሆን የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህን ከመንግስት ተነጥሎ፣ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ ሆኖ በስጋት የተሞላውን አርቶ አደር የኑሮ ሁኔታ መቀየር ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም። በመሆኑም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የመንግስት መዋቅር ወደአርብቶ አደሩ መዝለቅ ጀምሯል። መንግስት የአርብቶ አደሩን አካባቢ መሰረት አድርጎ፤ የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህን በማድረግ ረገድም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ አርብቶ አደሩን ጭምር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናጸፈው ፌደራላዊ ህገመንግስታዊ ስርአት ቀዳሚ ድርሻ አለው።

በቀደሙት ስርአቶች የመንግስት መዋቅርና የመንግስት ስልጣን ከላይ ወደታች የሚወርድ በመሆኑ፣ መድረሻውም ህዝብን ማገልገል ሳይሆን የወሰን አንድነት ያላትን አገር መጠበቅና የስርአቱን ገዢዎች ጥቅም አስተማማኝ ማድረግ ስለነበር ወደአርብቶ አደሩ አልዘለቀም።   አሁን ግን፤ የመንግስት መዋቅርና የስልጣን ምንጭ ህዝቡ በመሆኑ አርብቶ አደሩ ወኪሉን መርጦ ራሱን በራሱ የማስተዳደር፣ በፌደራል መንግስት ውስጥም የመወከል እድል አግኝቷል። የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ስልጣን በውክልና ሰጥቶ ራሱን በራሱ ማስተዳደር መጀመሩ የመንግስት መዋቅር አጠገቡ እንዲሆን፣ ከመንግስት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሎታል። አሁን አርብቶ አደሩ ኢትዮጵያዊ እየተሰማው ነው። አርብቶ አደሩ መንግስትን ያውቀዋል፤ መንግስትም አርብቶ አደሩን ያውቀዋል። እርግጥ አርብቶ አደሩ ለዘመናት ከመንግስት መዋቅር ውጭ በራሱ ባህላዊ ስርአት ሲተዳደር ስለኖረ፣ የመንግስት መዋቅር ከዚህ ባህላዊ የአስተዳደር ስርአት ጋር በመደጋገፍ ነው የሚሰራው፤ ይህ ደግሞ የመንግስትን የአገልግሎት ተደራሽነት አሰተማማኝ አድርጎታል።

አሁን አርብቶ አደሩ ልጆቹን ማስተማር ጀምሯል። ከአስር ዓመት በፊት በአንዳንድ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶች እስከመቋቋም የተሄደበት ሁኔታ መኖሩ ይታወሳል። አርብቶ አደሩ የሰውና የእንስሳት ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። ይሁን እንጂ፤ ከአርብቶ አደሩ ተንቀሳቃሽ የኑሮ ዘይቤ በመነጨ ችግር የተነሳ የአገልግሎት አሰጣጡን የተሟላ ማድረግ አልተቻለም። ይህን ችግር ለማቃለል አርብቶ አደሩን በማወያያትና በመተማመን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በመንደር መሰባሰቡን ተግባራዊ ለማድረግ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የመንግስት አስተዳደር መዋቅሮች፤ ክልላዊ መንግስታትና የዞን መዋቅሮች የአርብቶ አደሩ ችግር ምንጭ ውሃ መሆኑን ለይተው ወንዞችን በመጥለፍና የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት ሰፊ የውሃ ልማት ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ። በተለይ ከ85 በመቶ በላይ ህዝባቸው በአርብቶ አደርነት የሚተዳደርባቸው የኢትዮጵያ ሶማሌና የአፋር ክልሎች በዚህ ረገድ ሰፊ ስራ ሰርተዋል።

የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ከቦታ ቦታ የሚንከራተተው ለመዝናናት ወይም ዘላንነት ምቾት ስላለው አይደለም። የህይወቱ መሰረት ለሆኑት ከብቶቹ ውሃና ሳር ፍለጋ እንጂ፤ አርብቶ አደሩ ውሃ እንደልብ ካገኘ ከዚያ ቦታ መሄድ አይፈልግም። የመንደር ማሰባሰቡንና የውሃ ልማቱን ስራ በማስተሳሰር፣ አርብቶ አደሩ አንድ ቦታ ረግቶ እንዲኖር፣ ከከብት ርባታው ጎን ለጎን የእርሻ ስራ እንዲለማመድ እየተደረገም ነው። አርብቶ አደሩ አንድ ቦታ ረግቶ መኖሩ ደግሞ ዘላቂ የኑሮ መሻሻል የሚያስገኝለትን፣ ልጆቹን የማስተማርና የተሟላ የጤናና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን እንዲገኝ ማድረግ ያስችላል። ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ከሌሎች መሰል ማህበረሰቦች ጋር በውሃና በግጦሽ ሽሚያ ሳቢያ ይቀሰቀስ የነበረውንም ግጭት በማስቀረት ሰላምን ማረጋጋጥ ያስችላል። ይህ ደግሞ ለአርብቶ አደሩ የበለጠ የኑሮ ዋስትና ይሰጣል።

ሰሞኑን 16ኛው የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ቀን 85 በመቶ ያህሉ ህዝብ በሚኖርበት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ተከብሯል። ይህ መንግስት የአርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል። የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት የላቀ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለህዳሴያችንበሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ በተከበረው የአርብቶ አደር ቀን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በበአሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በዓሉ አርብቶ አደሩን የተመለከቱ ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ መስመሮችን ቀጣይነት ለማረጋጋጥና የበለጠ ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ ተሞክሮ የምንለዋወጥበት ነው ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑትን ተግባራት በመዳሰስ ለቀጣይ የህዳሴ ጉዞ ልምድ የሚቀሰምበትና ለአርብቶ አደሩ የልማትና የሰላም ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት ደግሞ የሚያረጋግጥበት፣ ቃልኪዳኑን የሚያድስበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ ተግባራዊ በማድረግ፤ የአርብቶ አደሩን ገቢ በማሳደግ የኑሮ ደረጃውን ማዘመን እንደተቻለ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአርብቶ አደሩ አካባቢ በፈቃደኝነት ላይ በመመስረት የሚከናወነው የመንደር ማሰባሰብ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረታዊ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል። አርብቶ አደሩን ከእንስሳት ልማት በተጓዳኝ በሰብል ልማት በተለይም፤ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቅባት እህሎች የማምረት ተግባር ላይ በስፋት በማሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ ማድረግ መጀመሩ ወደ ዘመናዊ አርብቶ አደርነት የሚሸጋገርበት ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ በማሳያነት አንስተዋል።

እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች በአገሪቱ ድንበር አካባቢ ነው የሚኖሩት፤ ይህ ሁኔታ ከተንቀሳቃሽ የኑሮ ዘይቤያቸው ጋር ተገናኝቶ፣ በአጎራባች አገራት ተመሳሳይ የኑሩ ዘይቤ ካላቸው ማህበረሰቦች ጋር እንዲገናኙም እንዲጋጩም ምክንያት ሲሆን ኖሯል። ይህ ግጭት መንግስታትን የሚያገናኝ ጉዳይ እንዲፈጠር የሚያደርግበት አጋጣሚም የተለመደ ነው። በአርብቶ አደሮች መካከል ያለ የግብይት ስርአትም በአመዛኙ ድንበር ዘለል የሚሆንበት አጋጣሚ የሰፋ ነው። ይህን መነሻ በማድረግ በጅግጅጋ በተከበረው ኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች በአል ላይ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ባለስልጣናት፣ የጎረቤት አገራት የአርብቶ አደር ተወካዮች፤ እንዲሁም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል። የአርብቶ አደሩን ኑሮ አካባቢያዊ ቅርጽ ሰጥቶ መመልከት፣ የድንበር አካባቢ ግጭቶችን ለማስቀረትና አርብቶ አደሩንና አገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የገበያ ልውውጥ ስርአት ለመዘርጋት መሰረት ለመጣል ያስችላል።

ይህን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በጅግጅጋ በተከበረው 16ኛ የአርብቶ አደሮች በአል ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የአርብቶ አደሮችን ድንበር ተሻጋሪ የግብይትና የግንኙነት ባህሪ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች በዓል በተጨማሪ በዓሉ አህጉራዊ ገጽታ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። የአርብቶ አደሮች በዓል በኢጋድ አባል ሀገሮች ደረጃ እንዲከበር ለማድረግ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት አድማሱን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

እንግዲህ መንግስት ሳያውቃቸው፣ እነርሱም መንግስትን ሳያውቁት ተገፍተው በመንግስታዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች እጦት ውስጥ በድህነትና ዋስትናው ባልተረጋገጠ የስጋት ህይወት ውስጥ ሲኖሩ የነበሩትን የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ህይወት ወደተሻለ ሁኔታ ለማሸጋጋር ትኩረት ተሰጥቶት የልማት ስትራቴጂ መነደፉ ድንቅ ነገር ነው። የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በውሃ ልማት በመደገፍና ረገቶ እንዲኖር በመንደር በማሰባሰብ የግብርና ስራ በማለማማድ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ከሚፈለገው አንጻር ገና ቢሆኑም፤ ጅምሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። በአጠቃላይ ባዕድ የነበሩት መንግስትና አርብቶ አደሩ መተዋወቃቸው ለአርብቶ አደሩ ህይወት ሽግግር መሰረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።