16ኛው የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ቀን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ “የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል። የሀገራችን አርብቶ አደሮች የሆኑት የኦሮሚያ፣ የአፋር፣ የኢትዮጵያ ሶማሌና የደቡብ ክልል ተወካዮችም የየክልላቸውን ተሞክሮ አቅርበው ውይይት አድርገዋል። በዚህም ገንቢ የሆነ የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገልጿል። በልምድ ልውውጠ ላይ አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በመቀየር ህይወቱ እንዲለወጥ ያስቻለና ይህንንም ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዲገባ ተነግሯል።
እንደሚታወቀው የሀገራችን አርብቶ አደሮች በጋራ ጉዳዮቻቸው የሚመክሩበት መድረክ እንዲኖራቸውና በሀገሪቱ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ የመሆን ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄዎቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲያነሱ እንደነበር ይታወቃል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በመላው ህብረተሰብ ሆነ በፖሊሲ አውጪውና በአስፈጻሚው በኩል ስለ አርብቶ አደሩ የህይወት ዘይቤና የኑሮ መሰረት አጠቃላይ ግንዛቤ ውስን ነበር። በዚህም ሳቢያ አርብቶ አደሮች በጋራ ጉዳያቸው የሚመካከሩበት የጋራ መድረክ አልነበራቸውም። ሆኖም ይህን ችግር የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ሁለንተናዊ ለውጦችን በማድረግ አርብቶ አደሩ ችግሩን ተመካክሮ የሚፈታበትን መድረኮች እያመቻቻ የነበሩት የግንዛቤ እጥረቶች በሂደት እንዲፈታ እያደረገ ነው። በተለይም በመንግስት በኩል በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የአርብቶ አደር ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት አርብቶ አደሮች ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው መከበሩንናከሀገሪቱ ልማት እንደ ማንኛውም ዜጋ ተጠቃሚ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራዎች እንዲከናወኑ በመደረግ ላይ ናቸው።
በዓሉ ልምድ ከመለዋወጥ ባሻገር፤ የአርብቶ አደሮች ያሉባቸውን የልማት ችግሮች ለመንግስት ከፍተኛ አመራሮች የሚያቀርቡበት፣ መንግስትም በተጠያቂነት እንዲያዳምጥና እንዲመልስ፣ የዘገዩ ስራዎች ካሉም በፍጥነት እንዲፈጸሙ በማድረግ ረገድ ፋይዳው የላቀ ነው። የበዓሉ ተሳታፊዎች ራሳቸውን ከጠያቂነት ወደ ተሳታፊነት የሚያሸጋግሩበት ዕለት ነው ቢባልም ከእውነታው መራቅ አይሆንብኝም። ምክንያቱም ቀደም ሲል በመጠየቅ ብቻ ዕውን የሚያደርጓቸውን ጉዳዩች በራሳቸው ተነሳሽነትና ተሳታፊነት እንዴት እንዳከናወኗቸው የሚያስረዱበት ዕለትም ስለሆነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችንም በመከላከል የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበዓሉ መከበር የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል። እርግጥ ላለፉት 16 ጊዜያት በተከናወኑ ስራዎች ቀደም ሲል የማይታወቀው ወጋቸውና ባህላዊ ትውፊቶቻቸው እንዲታወቁ ማድረግ ተችሏል።
ምንም እንኳን የበዓላት መከበር ለአንድን የህብረተሰብ ክፍል ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ፋይዳዎችን ሊያስገኙ ቢችሉም፤ ዋናው ጉዳይ የአርብቶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ ለመለወጥ የተከናወኑ ስራዎች ያሉበት ደረጃ ነው። እናም ከአርብቶ አደሩ አኳያ የተከናወኑትን ስራዎች እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው አርብቶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት ለማቋቋም የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራትን በማቋቋም የብድር ተጠቃሚ በማድረግ በልማት ላይ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ በር ከፍቷል፡፡ በዚህም በርካታ ዜጎችንም ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ አርብቶ አደሩ እንስሳትን በማደለብና ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ መሆን ችሏል፡፡ በገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበራትም አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግም የአርብቶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት የመለወጥ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በአርብቶ አደሩ አካባቢ ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስና ለመከላከል ያልተማከለ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራ በወረዳና በክልል አማካኝነት እንዲተገበር በመደረጉ እንደ እየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ስርዓት እንዲዘረጋ ድጋፍ የማድረግ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
የተጠናከረ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በማቅረብ ሂደት ውስጥም በልማት ሰራተኛውና በህብረተሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት ወሳኝ በመሆኑ የልማት ሰራተኛውንና የተጠቃሚውን ጥምርት ለይቶ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ እርግጥ ጥመርታውን ከሚወስኑት በርካታ ሁኔታዎች መካከልም የአካባቢው የአየር ፀባይ፣ የመሬት አቀማመጥ፣ የህዝብ አሰፋፈርና የቦታ ርቀት እንዲሁም የትራንስፖርት አመቺነት፣ የአመራረነትና የአኗኗር ዘይቤና የተጠቃሚው የግንዛቤ ደረጃ ወሳኞች ናቸው፡፡
ያም ሆኖ ግን መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት ለአብርቶ አደሮች አካባቢ በአንድ ቀበሌ ሦስት የልማት ሰራተኞች ተመድበው የሚሰሩ ሲሆን፤ የልማት ሰራተኞቹ በአንድ ቀበሌ ከ300 እስከ 350 የሚደርሱ አርብቶ አደሮችን ያገለግላሉ። ይህም አርበቶ አደሩ ራሱን ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲቀይር ያስችለዋል።
በሌላ በኩልም አርብቶ አደሮችን በመንደር የማሰባሰብ ስራ ውጤታማ ለማድረግ የልማት ማዕከላትን በማቋቋም የግብርና ግብዓትን በማቅረብ አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡ በልማት ማዕከላት ውስጥም የእንስሳት ጤና ኬላዎችን በመገንባት የውስጥ ቁሳቁሶችን በማሟላት ወደ ስራ ተግብቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህ መንግስታዊ ጥረቶችም በሁሉም የአርብቶ አደር ማህበረሰቦች ውስጥ ገቢራዊ የሆኑና በመሆን ላይ የሚገኙ ናቸው።
የአርብቶ አደሩንና የከፊል አርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ የኑሮ ደረጃውን ለማሻሻል በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የተከናወኑ ስራዎችን በማየት አርብቶ አደሩ ቀደም ሲል በተበታታነ እና በልማቱ ላይ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችገሩ የአኗኗር ዘዴዎችን በመቀየር፣ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እና ህብረተሰቡን በአንድ አካባቢ በማስፈር የተጀመሩ የውጥን ስራዎች ይጠቀሳሉ።
አርብቶ አደር ማህበረሰቦች በደረቃማና የውኃ እጥረት በሚታይባቸው የሀገሪቱ ክፍል እንደመኖራቸው መጠን፤ የአኗኗር ዘይቤያቸው እና ህልውናቸው በውኃ መኖርና አለመኖር ሊገለፅ የሚችል ነው፡፡ ውኃ ለእንስሳቶቻቸው፣ ለግጦሽ መሬታቸውና ለራሳቸው በቀላሉ የማይገኝ ሀብት በመሆኑ፤ የአኗኗር ሁኔታዎችንም ይወስናል፡፡
በዚህም ምክንያት በአርብቶ አደሮች አካባቢዎች ይህን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሀብት ተንከባክቦና ቆጥቦ ማቆየት ዋነኛው ተግባር ነው፡፡ ለዚህም ነው ከፍተኛ የውሃ ችግር ባለባቸው የክልሉ አርብቶ አደር አካባቢዎች በህብረተሰቡ፣ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት የገፅና የከርሰ ምድርን ውኃ መጠቀም የሚያስችሉ የውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡
አብዛኛው የአርብቶ አደር ማህበረሰብ የሚኖርበት አካባቢ በረሃማ ከመሆኑ አንጻር ሊፈጠሩ የሚችሉ በሽታዎች ሀገሪቱ በምትከተለው በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ስራ ውጤታማ ክንውኖች ተካሄደዋል፡፡ በተለይም ማህበረሰቡ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ለመቀነስ ተችሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የአርብቶ አደሩንና የከፊል አርብቶ አደር ህብረተሰብ ኑሮው በእንስሳት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለእንስሳቶች አስፈላጊውን ህክምና የሚሰጡ የእንስሳት ጤና ኬላ ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን፣ የንጹህ መጠጥ ውኃን እና ሌሎች የማህበራዊ ግልጋሎት መስጫ ተቋማት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፈቃደኝነት መንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሙ ጋር አብረው እየተካሄዱ ናቸው። ይህም ከዚህ በፊት በተበታተነ ሁኔታ ይኖር የነበረውን አርሶ አደር በተሰባሰበ ሁኔታ ከሀገሪቱ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችለው ነው፡፡
እርግጥ መንግስት በሁሉም አካባቢዎች በአርብቶ አደርነት ብቻ የሚተዳደረውን ማህበረሰብ በተጨማሪም በአርሶ አደርነት እንዲሳተፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናውን ራሱን ችሎ እንዲያረጋግጥ እየተደረገ ያለው ጥረት እጅግ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱ የነደፈችውን የልማት ራዕይ በማሳካት ረገድ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል። ለዚህ ደግሞ በየጊዜው የሚካሄዱት የአርብቶ አደር ቀን በዓላት የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ። በዕለቱ ከቀረቡት የልምድ ልውውጦች መረዳት የሚቻለውም የአርብቶ አደሩ ህይወት እየተለወጠ መሆኑን ነው። እናም በቀጣይም የአርብቶ አደሩን ህይወት ይበልጥ ለመቀየር በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ ከበዓላቱ የሚገኙትን ግብዓቶች በተገቢው መንገድ በመጠቀም ገቢራዊ ማድረግ ይገባል እላለሁ።