የሀገራችንን የዲሞክራሲ ምሕዳር ማስፋት የጥልቁ ተሀድሶ አንዱ መሰረታዊ ትኩረት ነው፡፡ ዲሞክራሲ የሕዝብ መሰረታዊ መብት መገለጫ አይነተኛ መልክ ነው፡፡ ሕዝቡ የተገኙትን ዲሞክራሲዊ መብቶቹን በላቀ ደረጃ በማሳደግ እንዲጠቀም ለማድረግ ሰፊ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ለዚህም፣ ጅምር ዲሞክራሲውን በማጎልበት ረገድ የበለጠ ርቀት መራመድ ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡
የዲሞክራሲ መብቶች መከበር በመርህና በተግባር የሕዝብን የላቁ መብቶች ስራ ላይ ማዋልን ይጠይቃል፡፡ እነዚህም መብቶች በሕገመንግስቱ ውስጥ በስፋት ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡ ያለምንም ገደብ ሕዝቡ በነጻነት የሚሳተፍባቸው ዲሞክራሲዊ ምርጫዎች፤ ሀሳብን በነጻነት በንግግርም ሆነ በጽሁፍ የመግለጽ፤ እምነትን በጻነት የማራመድ፤ የመደራጀት፤ የፈለጉትን የፖለቲካና የሀይማኖት እምነት የመከተል፤ የመሰብሰብ፤ በነጻነት ተንቀሳቅሶ የመስራት ወዘተ መብቶች ሁሉ በኢትዮጵያ ሕገመንግስትም ሆነ በአለምአቀፍ ደረጃ የተከበሩ፤ የማይጣሱ ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብቶች ናቸው፡፡
የዲሞክራሲ መሰረታዊ መብቶች የበለጠ እንዲጎለብቱ ለማድረግ እሰከዛሬ ከተሰሩት ስራዎችም በላይ ሰፊ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ የሕዝብ ተወካዮችን ለመምረጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝብን ለማገልገል የተሻለ ለመስራት እንችላለን፤ አማራጭ ፖሊሲ አለን የሚሉና በሕጋዊነት የተመዘገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደቱ ውስጥ በነጻነት የመሳተፍ መብታቸው በሕግ የተከበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ –
እኛ አብዛኛው የዓለም ሀገሮች የሚከተሉትን የአብላጫ ድምጽ ስርኣት የምርጫው ሥርኣት አድርገን ስንጠቀምበት ቆይተናል፤ እስከአሁን የሠራንበትም ዲሞክራሲያዊ አሰራር ነው፡፡ እውነታው ሲታይ ግን ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ምክር ቤታችን ከኢሕአዴግ ውጪ ድምጽ የሰጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ድምጽ ለማሰማት በሚያስችል ደረጃ ላይ አልነበረም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የኢሕአዴግ ወይም የሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥፋት ስለሆነ አይደለም።
ሲሉ በዘንድሮው የፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ መግለጻቸው በኢህአዴግ በኩል ዲሞክራሲያዊ አሳታፊነትን ለመተግበርና ምህዳሩን ለማስፋት ያለውን ዝግጁነት ያረጋግጣል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሕዝብ መርጦን መቀመጫ ወስደን አሁንም እያለገልን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን በዚህ የምርጫ ሥርዓት አንድ ምርጫ ክልል ላይ ለምርጫ የተወዳደሩ በርካታ ተወዳዳሪዎች ኖረው የኢሕአዴግ እጩ 51 በመቶ ቢያገኝ፤ ሌላው ተወዳዳሪ 49 በመቶ ቢያገኝ አንኳን መቀመጫ አያገኝም፡፡ ሆኖም 49 በመቶ ያህሉን የመረጡ ሕዝቦች አሉ፡፡ የእነዚህ ሕዝቦች ድምፅ የሚሰማበት ሁኔታ ባለመመቻቸቱም ኢሕአዴግ እጅግ አብላጫውን ድምጽ ይዞ ወደ ምክር ቤት መግባቱን አስምረውበታል፡፡
ዲሞክራሲውን በማስፋቱ ረገድ ሲናገሩ የቀደመውን ሁኔታ መነሻ አድርገን ሕገመንግሥቱ ሲቀረጽ ከነበረበት የምርጫ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አኳያ ተቀምጦ የነበረው ትክክልም ቢሆን ዛሬ በሒደት ያጋጠመንን ሁኔታ ስንፈትሽ ሌላው የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥርአት ተብሎ የሚወሰደውን የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትን በተወሰነ ደረጃ ብናዳቅል፤ ከእነዚህ ድምጾች ውስጥ ተወክለው መጥተው የሚሳተፉ ቢኖሩ ድምጻቸውን ለማሰማት ይችላሉ የሚል እምነት ነው ያለን።
ሲሉም ገልጸውታል ከላይ የጠቀስነውን ንግግራቸውን አጠናክረውታል፡፡ ይህ የገዥው ፓርቲ ውሳኔ የዲሞክራሲውን ምህዳር በማስፋትና ሁሉንም ወገን አሳታፊ በማድረግ ረገድ ተገቢና ትክክለኛ አካሄድ በመሆኑ በበዙዎች ይሁንታን አግኝቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በጉዳዩ ያገባናል የሚሉ ኃይሎችን በማሰባሰብ ከሚመለከታቸውና በሕጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ በመሆን ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ብንከተል ታዳጊ ዲሞክራሲያችንን በተሻለ ደረጃ ፈቀቅ ለማድረግ ይጠቅመናል? በሚለወ ሀሳብ ዙሪያ የድርድር መድረክ እንደሚኖር የጠቆሙ ሲሆን፤ ይህም የዲሞክራሲ ምሕዳሩን የበለጠ በማስፋት ረገድ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድርድር ላይ ተመሥርተን ማስተካከያ ማድረግ ካለብን የተለያዩ ሕጎችን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘና የድርድሩን ውጤት መነሻ በማድረግ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልም ካስፈለገ ይህንን እርምጃ ያለማቅማማት በመውስድ የዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ሕዝባዊ ውክልናውም የበለጠ መዳበር ያለበት መሆኑን መግለፃቸውን ተከትሎ ይህንን ማድረግ መቻልም በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አንድ ትልቅ ፖለቲካዊ እርምጃ መሆኑን የወቅቱን ያገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
መንግሥት ሕገመንግሥቱን እስከ ማሻሻል ድረስ እየሄደበት ያለው ቁርጠኛ አቋም የዲሞክራሲውን ምሕዳር የማስፋቱ ተግባር የጥልቅ ተሐድሶው አንዱና መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡
የዲሞክራሲውን ምሕዳር በማስፋት ረገድ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የብዙሀን ማሕበራት፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሲቪክ ማሕበራት፣ በተለያየ አደረጃጀት ውስጥ ያሉና በሕጋዊነት የተመዘገቡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ዲሞክራሲ የሕዝብ መሰረታዊ መብት ስለሆነ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የሚመለከትና ሁሉንም የሚያሳትፍ ሂደት ነው፡፡
ዲሞክራሲ ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ቡድኖች፣ ድርጅቶች ተብሎ የሚሰጥ ወይም የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሀገሪቱ የሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንደመሆንዋ መጠን አሳታፊነቱም ሁሉንም የሚያቅፍ፣ ማንንም የማያገል መሆን እንዳለበት ይታወቃል፡፡ የዲሞክራሲ መብት መከበር ለሀገራዊ ልማትና እድገት የጎላ ፋይዳ አለው፡፡
ይህ ዲሞክራሲያዊ የሕዝብ መብት እንዳይጠለፍ መስራት ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ መሰረታዊ ተግባር ነው፡፡ የዲሞክራሲ አለመኖርና መጥፋት ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋትን ከማጥፋትም አልፎ ሀገራዊ ሕልውናንም አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ላይ ጥቁር ጥላ ያጠላል፡፡ ሀገራዊ የልማትና እድገት ስራዎችንም ያሰናክላል፡፡ ሀገር እስከማፍረስና መበተንም ደረጃ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ሀይል ከአክራሪ የውጭ ሀይሎች ጋር እንዲሰለፍ፣ መሳሪያም እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ጦሱና መዘዙ ብዙ ነው፡፡
የዲሞክራሲው መስፋት በተቃራኒው የውጭ ሀይሎችን ሴራና ደባ ለማምከን መግቢያ በርና ቀዳዳ እንዳያገኙ በማድረግ ሀገሩን፣ ሰላሙን፣ ልማትና እድገቱን ህዝቡ ነቅቶ እንዲጠብቅ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ የአክራሪው ተቃዋሚ ጎራ አንዱ ጩሀትና መነገጃው የዲሞክራሲ መብት ተረግጦአል፤ ነጻነት የለም፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይገፋሉ፤ ይታሰራሉ፤ ይሳደዳሉ ወዘተ የሚል ስለሆነ የዲሞክራሲ ምሕዳሩ መስፋት በዚህ ረገድ ያሉ ጩሀቶችንም የማምከን አቅም አለው፡፡
ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች የራሳቸው ሆነ ግልጽ አላማና ፖሊሲ የላቸውም፡፡ እስካሁን ካለው ልምድ ተቃዋሚው በግልብ ስሜታዊነት መንግስትን ከመቃወምና ከማውገዝ ባለፈ ተጨባጭ አማራጮችን ይዞ የሚሞግት አይደለም፡፡ ይህም ለበርካታ አመታት ሊታረም ያልቻለ የውድቀታቸው ሁሉ መነሻ ነጥብ ሆኖ ቆየቷል፡፡ አብሮ በመስራት፣ በመደማመጥ፣ በመነጋገር፣ ልዩነትን አቻችሎ በጋራ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ይዘው የሚራመዱ አይደሉም፡፡
እርስ በእርሳቸው በመከፋፈል የሚናቆሩ፣ የሚባሉ፤ አይደለም ሀገርና ሕዝብን ለመምራት ራሳቸውም መደማመጥና ተከባብረው መስራት የማይችሉ መሆናቸውን ሕዝቡ በበርካታ አመታት ተሞክሮው ለይቶ አውቆታል፡፡ ዛሬም ከትላንት ውድቀታቸው አልተማሩም፡፡ ከበቀልና ከጥላቻ አረንቋ አልተላቀቁም፡፡
ተቃዋሚው ከጭፍን ጥላቻ ወጥቶ የተሰሩትን ታላላቅ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ስራዎችን ማስተዋል፣ መቀበል፣ በሰላምና በአብሮነት ለጋራ ሀገር በአንድ ቆሞ ለመስራት ራሱን በጥልቀት መፈተሸ ይገባዋል፡፡ ጥልቅ ተሀድሶን እነሱም ቢሞክሩት መልካም ነው። ሀገርን የማፈራረስ ሳይሆን በተጀመረው መልካም ግንባታ ላይ የመጨመር፣ የማሳደግ፣ በጥላቻ ተውጦ ለእኔ ያልሆነች ሀገር ትፈራርስ ከማለትና ለውጭ ሀይሎች መሳሪያ ከመሆን፣ በቅጥረኝነት ከመሰለፍ ተላቆ ለሀገሩ ሰላም፣ ልማትና እድገት በመቆም ገንቢ ሚና የሚጫወቱበትን መንገድ ማስላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድን ወገን ብቻ መወንጀሉ ፋይዳ የለውም፡፡ ዲሞክራሲውን የማስፋት ስራ ለመስራት ሁሉም የየራሱን ድርሻ በሕዝባዊና ሀገራዊ ፍቅር ላይ ተመርኩዞ መወጣት አለበት የሚለው የወቅቱ አገራዊ ጥሪ ነውና ምላሻችን ይፍጠን፡፡