የተሐድሶው ልዩ ትኩረት ለወጣቶች

ወጣቱ የሕብረተሰቡ ትኩስ ኃይል የነገው ትውልድ ተረካቢ፣ ሀገር ገንቢና ታላቁን ሀላፊነት ተሸካሚ ነው፡፡ በየትኛውም አለም ወጣቱን ያላቀፈና ያላሳተፈ እንቅስቃሴ በሀገር ደረጃ የተፈለገውን ግብ አይጨብጥም፡፡ ለዚህ ነው በመንግስት በኩል እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም የበለጠ ወጣቱን ሙሉ በሙሉ አሳታፊ የሚያደርግ ልዩ ትኩረት የሰጠ ጥልቅ ተሀድሶ በመካሄድ ላይ የሚገኘው፡፡

በሀገራችን ወጣት ተብሎ የሚጠራው የሕብረተሰብ ክፍል ከ15 እስከ 29 ዓመት ያለው ነው፡፡  ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ቁጥር 52 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በ25 አመታት ውስጥ 103 ሚሊዮን ደርሶአል፡፡ የ51 ሚሊዮን ጭማሪ አሳይቶአል፡፡ ከአጠቃላይ ሕዝባችን ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣቱ ነው፡፡ ይሄ ቁጥር በኢኮኖሚስቶች ስሌት በተወሰኑ አስር አመታት ውስጥ ከፍታው ያሻቅባል፡ በእጅጉ ይጨምራል፡፡

መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ እንደገለፀው ከሕዝቡ ቁጥር መጨመር ጎን ለጎን ይሄንን ሊሸከም የሚችል ብሔራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ወጣቱን በከፍተኛ ደረጃ አሳታፊና በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ማድረግ የጥልቁ ተሀድሶ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባሉት አመታት ወጣቱን በአነስተኛና ጥቃቅን ማሕበራት በማደራጀት ከመንግስት ብድርና ቁጠባ ተቋም ገንዘብ አግኝተው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እጅግ ሰፊ የሆነ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎአል፡፡

በዚህም መነሻነት ባገኙት ድጋፍና ብድር በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውን የቻሉ፤ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ በካፒታል አቅማቸውም የደረጁ መለስተኛ ፋብሪካዎችን ለመመስረት የበቁ ወጣት ኢንተርፕሬነሮችን በስፋት ማፍራት ተችሎአል፡፡ በጥልቅ ተሀድሶው ለወጣቶች በተሰጠው የተለየ ትኩረት መንግስት ይህንን የሕብረተሰብ ክፍል የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በመላው ሀገሪቱ 10 ቢሊዮን ብር መድቦ የየራሳቸውን ስራ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታዎች አመቻችቶአል፡፡

በሕብረተሰቡ ውስጥ ስራን አክብረው ማንኛውንም አይነት ስራ ሳይንቁ የሚሰሩ የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም አዳዲስ ስራዎችን የሚፈጥሩ ራሳቸውን ለውጠው ሕብረተሰቡንም በስራ ተነሳሽነትና ፈጠራ የሚለውጡ ወጣቶችን ሀገሪቱ ከመቼውም ግዜ በላይ ማየት የምትፈልግበት ግዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡

በአለማችን የአዳዲስ የስራ ፈጠራ ባለቤቶች አዲስ ሀሳብ አመንጪዎች በሀገር ግንባታና ልማት በግንባር ቀደምትነት ትልቁን ድርሻ የሚወጡት ወጣቶች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ተምረናልና  መንግስት ስራ ያስገባን የሚለው አመለካከት ሙሉ በሙሉ መለወጥ አለበት፡፡ ሀገሪቱ ከምትከተለው የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ስርአት አንጻር የሚበረታታው ዜጎች በአላቸው አቅም ወይም በማሕበር ተደራጅተው ከመንግስት ብድር በመውሰድ የራሳቸውን ስራ በመፍጠር ራሳቸውን ሕብረተሰቡንም ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉበትን መንገድ ማስላትና መከተል ነው፡፡

ለልማቱ አጋዥ ኃይልና ስራ ፈጣሪ በመሆን ለሌሎች ዜጎችም የስራ እድል የሚፈጥሩበት የፋብሪካ የኢንተርፕራይዝ ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ መንገስት ሲያመቻች ወጣቱ እድሉን አስፍቶ ለመጠቀም የበለጠ አቅሙን ማጎልበት አለበት፡፡ መንግስት ባለው የተወሰነ አቅም ለ70 ሚሊዮን ወጣቶች የሚሆን ስራ ከፍቶ ሊያስገባ አይችልም፡፡ ትልቁ ስራ ያለው መኖርም የሚገባው በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ነው፡፡

መንግስት ሊያደርግ የሚችለው ትላንት እንዳደረገውና ዛሬም በማድረግ ላይ እንደሚገኘው ሁሉ ወጣቶች እየተደራጁ የራሳቸውን ስራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ፕሮፖዛል (የስራ እቅድ ፕላን) አውጥተው በዚሁ መሰረት የገንዘብ ብድርና ድጋፍ አግኝተው ስራ እንዲከፍቱ፤ ሰርተውም ራሳቸውንና ሕብረተሰቡን እንዲጠቅሙ ማስቻል ነው፡፡

በታየው ሀገራዊ ተጨባጭ ልምድ ተደራጅተው መንግስትን ብድር ጠይቀው ተፈቅዶላቸው አግኝተው ስራ ይከፍታሉ፤ ሰርተው ይኖራሉ ሲባል ገንዘቡን ተከፋፍለው ወስደው በማጥፋት ያባከኑ ተመልሰውም ለቤተሰብና ለሕብረተሰብ ሸክም የሆኑ ወጣቶችን አይተናል፤ አንድ፣ ሁለትም ብለን ቆጥረናል፤  በሂደትም እየተጣራ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል፡፡

ይህ ሁሉ የወደቀና የወረደ አስተሳሰብ ቤተሰብን፣ ሕዝብን፣ ሀገርን በእጅጉ የጎዳና የሚጎዳ  በመሆኑ በአሁኑ ሰአት ከመንግስት ለወጣቱ በሚሰጠው ብድር ላይ ከአለፉት ልምዶች በመነሳት ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ገንዘቡ በትክክል የታቀደለት ስራ ላይ ለመዋሉ በየቀጠናው የወጣቶች ፕሮጀክቶችን እግር በእግር የሚከታተሉ ቢሮዎች ይቋቋማሉ፡፡ አንድም በትክክል በስራ ላይ መዋላቸውን ለራሳቸውም ለሕብረተሰቡም በሚጠቅም መልኩ መሰራት አለመሰራቱን ላልተፈለገ ጉዳይ መዋል አለመዋሉን የሚቆጣጠር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ገንዘቡ በብድር ከመንግስት የተገኘና የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ሰርተው ወጣቶቹ አግኝተው ተለውጠው አትርፈው ደረጃ በደረጃ በተቀመጠለት የግዜና የአከፋፈል መጠን  ላበደራቸው ተቋም የሚመልሱት ነው፡፡

ይሀው ገንዘብ ተመልሶ ለሕብረተሰቡ አገልግሎትና ልማት የሚውል በመሆኑ ወጣቶች በከፍተኛ ሀገራዊ የኃላፊነት ስሜት ጥንቃቄ ሊያደርጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች፤ ደላላዎች ጭምር ይህን የወጣቱን ሕይወት ለመለወጥ በመንግስት በኩል ለስራ የተዘጋጀውን ገንዘብ ከወጣቱ ጀርባ ሁነው በመጠቀም ለመቀራመት የተለያዩ ውጥኖችን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ መንግስትም ወጣቱም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉበት ይገባል፡፡

ወጣቱ ሕይወቱን፣ ኑሮውን አካባቢውን ብሎም ሀገርን መለወጥ በሚያስችለው በዚህ የተለየ አጋጣሚ ውስጥ እድሉ በብልጣብልጦች እንዳይነጠቅ ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ፣ መጠንቀቅ ገንዘቡን በተገቢው እቅድና ፕላን መሰረት በተጨባጭ ስራ ላይ ማዋል መቻል ይጠበቅበታል፡፡ እንደነዚህ አይነት እድሎች ተመልሰው ሊገኙ አይችሉምና፡፡

ወጣቱ መንግሥት ለጀመረው ጥልቅ ተሐድሶ  ግንባር ቀደም ተሳታፊና አጋዥ ሀይል ስለሆነ የበኩሉን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት ወጣቱ የዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም በማሰብ  የሚኖር አዳዲስ የለውጥ ሐሳቦችን የሚይዝ የትኩስ ጉልበት ባለቤት በመሆን ሀገሩን በማልማትና በማሳደግ ረገድ መሪ ተዋናይ ሁኖ መስራት እንዳለበት ያምናል፡፡

በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር እጦትና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ምክንያት ወጣቱ ትልቅ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን መንግሰት በውል ተገንዝቦ በጥልቀታዊው ተሀድሶ ልዩ ትኩረትና ቦታ የሰጠው ለወጣቱ ነው፡፡ቀደም ሲል በታየው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆን የመንግሥትን ጨምሮ በግለሰቦችና ቡድኖች ሀብት ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱት በአብዛኛው ወጣቶች የመሆናቸው እውነት ሲታይ ከስራ ማጣት የተነሳ ለተቃዋሚዎች መሳሪያ ለመሆን የመጋለጣቸውን አደጋ ለመገንዘብ ተችሎአል፡፡

ይህን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት በጥልቅ ተሐድሶው አማካኝነት ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ገንቢ ስራ ለመስራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በወጣቶች ፓኬጅ ተይዘው ተግባራዊ ሳይሆኑ የቆዩ ተግባራትን ለመፈጸም በርካታ ስራዎችን እየሰራም ሲሆን የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድን ማቋቋም እንደሚገባ አምኖበት ተግባራዊ አድርጓል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለተወካዮች ምክርቤት ባደረጉት ንግግር ያሉን ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች የበለጠ ጥልቀት ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ፤ በተለይም የሥራዎቻችን ሁሉ አስኳል የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደጉ ላይ ነው በማለት የገለጹት መንግስት ለወጣቱ የሰጠውን የተለየ ትኩረት ያሳያል፡፡

ቀደም ሲል የነበረው ችግር የፋይናንስ አቅም እጥረት ቢሆንም፤ እስከዛሬ ባንኮች የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የመሳሰሉት ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ የሚሆን ገንዘብ በመስጠት ረገድ የየበኩላቸውን አድርገዋል፡፡ ከተጨባጩ የወጣቶቻችን መሻትና ፍላጎት አንጻር በፊት የነበረው የኢኮኖሚ አቅም በቂ ሁኖ ባለመገኘቱ መንግሥት 10 ቢሊዮን ብር በመመደብ የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንዲቋቋም አድርጓል፡፡ ነገር ግን ይሄንን ፈንድ ለማቋቋም የዘገየ ቢመስልም ቀድሞም በመጠናት ላይ የነበረ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ለሀገራችን ወጣቶች ችግር አቅም በፈቀደ መጠን ችግር ፈቺ፣ አምራች፣ አትራፊና ተጠቃሚ ሰራተኛ ዜጋ እንዲሆኑም የሚያስችል ነው፡፡

ወጣቶች ሊሠሩአቸው የሚገቡ ስራዎችን በአግባቡ ሰርተው የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ስራ ወጣቱን በስፋት ባሳተፈ መልኩ እንደሚከናወን የመንግሥት ድርሻ ብቻ ሳይሆን የወጣቶችቻንንና የሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ፣ ፓኬጆቹ ውስጥ የነበረውን ውስን የወጣቶች ተሳትፎ በማስቀረት ሙሉ በሙሉ ባለቤት የሚሆኑበትና በስፋት የሚሳተፉበት እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውም ከዚሁ አንፃር መታየት አለበት፡፡

ወጣቱ የገዢውን ፓርቲና የመንግሥትን የጥልቅ ተሐድሶ እንቅስቃሴ በጥልቀት በመገንዘብ ሀገሩን ለማልማትና ለማሳደግ፤ ሰላሟንም ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡ በተለይም ሀገሪቱ በሕዳሴው ጉዞዋ በፍጥነት እየተራመደችና አዳዲስ ድሎችንም እያስመዘገበች መገኘቷ፤ ያለውም ልማትና እድገት ለወጣቶች ታላቅ ተስፋ መሆኑን ወጣቶች በውል መረዳት አለባቸው፡፡

ወጣቶችን ጨምሮ ከመላው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቀውን ያህል ከእድገቱ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ፣ የሥራ አጥነት ችግር በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተፈታ፣ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ለሥርኣቱ አደጋ ሆነው መደቀናቸውን ወጣቶች በውል ተገንዝበው ከመንግስት ጎን በመቆም የበለጠ ለሀገር ልማትና እድገት፣ ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት በንቃት መሳተፍ ያለባቸው ግዜ ቢኖረ አሁን ነው፡፡