የጥልቅ ተሀድሶው ንቅናቄ በሕዝቡና በመንግስት ሰራተኛው ውስጥ በስፋት ቀጥሎአል፡፡ ዋነኛ ግቡ የተፈጠሩትን መሰረታዊ ችግሮች በመፍታት፤ ሰፊ ግንዛቤ እንዲፈጠር በማስቻል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ በመንግስት ሰራተኛው በኩል በተለይ ከሕዝብ ጋር በሚያገናኙት የአገልግሎት ዘርፎች የታየው መጠነ ሰፊ ችግር ሙስናን ኪራይ ሰብሳቢነትን የመልካምአስተዳደር እጦትን፣ የፍትህ መረገጥን በመንግስት ንብረት ያለአግባብ መጠቀም ተገቢ ላልሆኑና በሕገወጥ መንገድ ለሚሰሩ ስራዎች ተባባሪ በመሆን በኩል ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡
አብዛኛው የሕዝብ ቅሬታ መሰረቱ በየደረጃው ያሉ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሕዝቡን በቅንነት ከማገልገል ይልቅ ጉቦ የመቀበል፣ ሕዝቡን የማመላለስ፣ የተለየ ጥቅም በመፈለግ ማጉላላት፣ ከመንግስት ቢሮዎች ሕጋዊ ሰነዶችን ውጭ ላሉ ሙሰኞች አሳልፎ መስጠት፣ እንዲጠፉ ማድረግ፣ በሕገወጥነት የማይገባቸውን ሰዎች የሀሰት ሰነዶች ከፋይል ጋር ማያያዝ ሌሎችንም ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ይህ ሁሉ ሕገወጥ የአሰራር መናጋት የነገሰው ብልሹ ባለስልጣናትና ከስራቸው ያሉ ተባባሪዎች ከሙሰኞች ጋር በመመሳጠር በሚፈጽሙት ድርጊት ነው፡፡ እነዚህ ክፍሎች በየቦታው በሕዝቡ ውስጥ የሚፈጽሙት ወንጀል ነው በአጠቃላይ የሕዝብን ቁጣ ያስነሳው፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘው የመንግስት ሰራተኛው ከውጭ ካሉ ደላሎችና ሙሰኞች ጋር በመተባበር የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በሚከተሉት ሕገወጥ አሰራር ሕዝቡ እንዲመረር፤ ዜግነቱን እንዲጠላ አድርገውታል፡፡
ችግሩን ከስሩ ነቅሎ ለማስወገድ የግድ ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ በተሀድሶው ውስጥ እንዲያልፍ ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ የጉዳዩ አሳሳቢነት በተለይ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር በሚያገናኙ አገልግሎት ሰጪ ስራዎች ተሰማርተው የሚገኙትን ክፍሎች ይመለከታል፡፡ በሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተሀድሶ ንቅናቄው በሰራተኛው ውስጥ መካሄዱ ተሀድሶውን ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ ትርጉም ያለው የአሰራር ለውጥ ለማምጣትም ያስችላል፡፡
በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በሰራተኛው ውስጥ በተካሄደው ግልጽ ውይይት እያንዳንዱ ራሱን እንዲፈትሽ፣ ስህተቱን እንዲያርም፣ ዳግም ሕዝብን የሚያስከፉ ብልሹ አሰራሮች ውስጥ እንዳይገኝ በተመሳሳይ ሁኔታም በየደረጃው ያሉ ሀላፊዎች በቀጥታ ሰራተኛው ፊት ቀርበው ደካማና ጠንካራ ጎናቸው ተለይቶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ሰራተኛውም ሆነ ኃላፊዎች ስህተታቸውን ለማረም ቃል ገብተዋል፡፡
ሰራተኛው በየስራ ክፍሉ በተናጠል በጋራ ደግሞ ሁሉም በተገኙበት ከየመስሪያ ቤቶቹ ልዩ ባሕርይ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ፣ ግልጽና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ውይይቶች መደረጋቸው ሀገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ መስናው፣ ኪራይ ሰብሳቢነቱ፣ የፍትህ ጥሰቱ የሚካሄደው በአየር ላይ አይደለም፡፡ በተለይ በመንግስታዊ ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ መስሪያ ቤቶችና የራሱን የመንግስትን ማሕተም በመጠቀም ወንጀሉ ሲፈፀምበት ይታያል፡፡
ችግሩ እየሰፋ ድንበር ጥሶ ያለፈበት ምክንያት በራሱ በመንግስት ሕዝብን እንዲያገለግሉ የተመደቡት በተለያየ ደረጃ የነበሩና ያሉ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ከቀበሌ፣ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ፣ ክልል ድረስ እንዲሁም በፍርድ ቤቶችና በተለያየ ተቋማት ውስጥ ሙስና በሰፊው እንዲንሰራፋ በማድረጉ በኩል የላቀው አስተዋጽኦ የእነሱው እጅና ድጋፍ ያለበት በመሆኑ ነው፡፡
የመንግስትንና የሕዝብን ሀብት ሕግና ስርአቱን መጠበቅና ማስጠበቅ የሚገባቸው መንግስታዊ አካላት ለሙሰኞች አጋርና ተባባሪ ሰነድ አውጪና ቀያሪ የሀሰት ሰነዶችን ሕጋዊ አድርገው ሰጪና አቀባባይ ባይሆኑ ኖሮ የሕዝብ ብሶትና መከፋት ድንበሩን ጥሶ ጣሪያ ባልነካ ነበር፡፡እነሱ ሕጉንና ስርአቱን ተከትለው ቢሰሩ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሕገወጥነት ባልተንሰራፋ ነበር፡፡ለብልሽቱ ከታች ያለው ሰራተኛም በሰፊው እጁ አለበት፡፡
መንግስታዊ ተቋማት ሲባል ሁሉንም የሚመለከት መሆኑ እንዳለ ሆኖ በተለይ ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ስራዎች የሚሰሩት መሬት፣ የቤት ካርታ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፍርድቤት፣ ፖሊስና የመሳሰሉትን ይመለከታል፡፡ ለዚህ ነው ጥልቀታዊው ተሀድሶ በሁሉም የመንግስት መስሪያቤቶች ውስጥ በስፋት እየተካሄደ ያለው፡፡
የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነትን ሕገወጥ ተግባር ማደሪያቸው አድርገው በጉቦ አቀባይነትና ተቀባይነት፣ በተላላኪነት፣ በጉዳይ አስፈጻሚነት የግል ጥቅማቸውን በማሳደድ የተጠመዱትን፣ በዚህም ሕገወጥ ድርጊት የከበሩትን በሙሉ አጋልጦ ማውጣት ጤነኛ መንግስታዊ አሰራርና አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ አስፈላጊና ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡
የተሀድሶው መንግስታዊና ሕዝባዊ ንቅናቄ ሕገወጦችን እየመነጠረ ሲያወጣ ድርጊታቸው እየተመዘነ በየደረጃው ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ ሲቻል ብቻ ነው የተሻለ አሰራር ማስፈን የሚቻለው፡፡ ከዚህ አንጻር በሁሉም መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ባሉ አመራሮችም ሆነ ሰራተኞች ውስጥ የሚካሄደው የተሀድሶ ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይታመናል፡፡ መንግስታዊ ስራዎችና የፖለቲካ ስራዎች በቅጡ ተለይተው መቀመጥም አለባቸው፡፡ ተሀድሶው ከጅምሩ ይህንን ለይቶ ያስቀመጠ ቢሆንም ዛሬም ሰፊ የጎራ መደበላለቅ መኖሩ ሲነገር ይሰማል
ጠንካራ ሀገራዊና ሕዝባዊ ተልእኮውን በውል ለይቶ የሚያውቅ ሕዝቡን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግል ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ሲቪል ሰርቪስ ብቻ ነው ለመንግስትም ለሕዝብም የሚጠቅመው፡፡ በሕብረተሰቡ ውስጥ ነግሶ የኖረው ሙስናና ጉቦን የሚያወድስ ኋላቀር አስተሳሰብ መልሶ ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዳ በመሆኑ ከስሩ ተነቅሎ እንዲመክን ለማድረግ ሰፊ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ በመንግስትም ሆነ በገዢው ፓርቲ በኩል ጠንካራ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የተሀድሶ ስልጠናው በመንግሥት ሰራተኞች የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማረም እንደሚያስችል የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ለመገናኛ ብዙሀን የገለጹትም ከዚህ መሰረታዊ እውነታ የመነጨ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁሉም የመንግስት ሰራተኛ ስልጠና እንዲሰጥ የተደረገው በሰራተኛው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና የሕዝብ አገልጋይነት ስሜትን የተላበሰ ሰራተኛ ለመፍጠር መሆኑንም አስምረውበታል፡፡
በርግጥ የመንግሥት ሰራተኛው ሀገሪቱ በየዘርፉ ላስመዘገበችው እድገት ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ሰራተኛው የሚጠበቅበትን ያህል የሕዝብ አገልጋይነትን መንፈስ ተላብሶ ለሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት፣ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስን አለመላበስ ኃላፊነትን ለግል ጥቅም ማዋል በመንግሥት ሰራተኛው ላይ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮች መሆናቸውን፤ በሀገሪቱ በሁሉም የአስተዳደር እርከን ያለው የመንግሥት መዋቅር በአገልጋይነት መንፈስ ማገልገል ቢችል 70 ከመቶ የሚሆነው ችግር ሊፈታና ሊቃለል እንደሚችል ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የገዘፈ እውነት ነው፡፡ ለመንግስት ሰራተኞች የሚሰጠው ስልጠና የሀገሪቱ መንግሥት የሚከተለውን የልማትና የዲሞክራሲ አማራጮች ግልጽ የሚያደርግ ሲሆን በፐብሊክ ሰርቪሱ አካባቢ የሚታዩ ብዥታዎችን በማጥራትም ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ሊመልስ የሚችል፤ የለውጥ መሳሪያዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ አደራጅቶና አቀናጅቶ ጥቅም ላይ በማዋል ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚበቃ በአመለካከቱና በክሂሎቱ የላቀ የመንግሥት ሰራተኛ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ሰራተኛውን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ባበረከተው አስተዋጽኦ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርገው በተለያየ ጊዜ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ያገናዘበ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን በቀጣይም የሀገሪቱን የኑሮ ሁኔታ በማጥናት የመንግሥትን የመክፈል አቅም በማገናዘብ ኑሮውን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡