ባለፉት የዴሞክራሲና የልማት አመታት የሃገራችን ህዝቦች የምርጫ ተሳትፎ በየምርጫ ዘመኑ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመምጣት ላይ ነው፤ ይሁን እንጂ፣ በምርጫ ያልተሳካላቸው ሃይሎች የምርጫ ሂደትን ጨምሮ የማንነትና መሰል ጥያቄዎች በተነሱ ጊዜ አጀንዳውን በመጠምዘዝ ወደቀለም አብዮት የመለወጥ ሙከራ ሲያደርጉ የቆዩ መሆኑ ይታወቃል። በተመሳሳይ መልኩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ከነችግራቸውም ቢሆን በየወቅቱ እያደገ የመጣ መሆኑና በዚህም የመድበለ ፓርቲ ስርአቱ በመጠናከር ላይ የሚገኝ መሆኑም እንደዛው። በሌላ በኩል ግን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመስራት የቆረጡ ፓርቲዎች መኖራቸው ለተጀመረው የመድበለ ፓርቲ ስርአት መጠናከር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም ማስታወስና እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።
ሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ስትነሳ የግጭትና የብጥብጥ ምንጭ የነበረውን ድህነትና ኋላቀርነት ደረጃ በደረጃ ለማስወገድ የሚያስችሉ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ፕሮግራሞች በመንደፍ ነው። የዴሞክራሲ ጥያቄ በአገራችን ቁልፍ ከሆኑት የትግል አጀንዳዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ማሳያው ለቀለም አብዮት ማመቻቺያ የሚሆኑት አጀንዳዎች እዚሁ ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸው ነው።
በዚህች ሃገር ዜጎች ለዘመናት ተነፍጓቸው የቆዩትን የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና ከቦታ ቦታ በነጻነት የመዘዋወር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የህግ ጥበቃና እውቅና የተሰጣቸው ከመሆናቸውም በላይ የዴሞክራሲ ባህልና እሴት ግንባታ በዝቅተኛ ደረጃ ይገኝ ስለነበር ይህንኑ ክፍተት ለመሙላትና አስተሳሰቡ ስር እንዲሰድ የተለያዩ የዴሞክራሲ ተቋማት ተደራጅተው ስራቸውን በመስራት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
በብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ የፖለቲካ ስርዓት ኢትዮጵያን የሚያጠፋና እያጠፋ ያለ ነው ብለው የሚያምኑት ፅንፍ የወጣ የትምክህት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በአንድ በኩል፤ አገሪቱን ለመበታተንና በየብሄራቸው የጠባብ ቡድናቸውን ለማረጋገጥ ከተቻለ በሀገር አቀፍ ደረጃም አምባገነንነታቸውን ለመጫን የሚያልሙ ጠባቦች በሌላ በኩል ለመጨረሻው ፍልሚያ የተሰለፉበት የምርጫ 97 ሃይሎች አሁንም ያረፉ አይመስልም ፡፡
ልክ እንደ 97ቱ በሰብአዊ መብት ጥላ ስር የሚቆምረውን ሂዩማን ራይትስ ዎችና መሰል ግብረ አበሮችን ይዘው ዛሬም በአስቸኳይ አዋጁ ላይ ለመንጠልጠል እየሞከሩ ነው።
ባለፈው ዓመት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ በዜጎች ላይ እየተደረገ የቆየው የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች እመቃ ቀጥሏል ሲል የተለመደውን መግለጫ ያወጣው የቱርኩ መፈንቅለ መንግስት፤ የሊቢያው የቀለም አብዮት፤ የዩክሬኑ ብርቱካናማ አብዮት አቀነባባሪው እና ስፖንሰሩ ሂዩማን ራይትስ ዎች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለፈውን የፈረንጆች ዓመት በከባድ መከራና የመብት ክልከላዎች ማሳለፏን የጠቆመው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የጅምላ እስርና የማህበራዊ ሚዲያዎች ክልከላ አድርጓል ሲል የሚተቸው ይህ ተቋም የአደባባይ ሰልፎችን በማይፈቅዱትና ለአመታት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር በሚገኙ ሃገራት ውስጥ ተቀምጦ ነው። በሃገሪቱ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉንና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ለእስር መዳረጋቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በእስር ላይ ቆይተው የተፈቱ አብዛኞቹ ዜጎች ግርፋት እንደደረሰባቸው መናገራቸውን፤ የእስረኞች ኢ-ሠብአዊ አያያዝን በተመለከተ መንግስት ትርጉም ባለው መልኩ ምርመራ አካሂዶ የእርምት እርምጃ አለመውሰዱንና የውጭ መርማሪዎች ወደ ሃገሪቱ ገብተው ምርመራ እንዳያካሂዱ መከልከሉን በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
በመሰረቱ ይህ አይነቱ አካሄድ የተቋሙ መደበኛ አሰራር ነው። ምርመራ አደርጋለሁ በሚል ሰበብ ገብቶ ጉድ የሰራቸውን ግብጽና ቱኒዚያን ማስታወስ ይበቃል። ክሪሚሌን ካልገባሁ እያለ የነዳጁን መስመር ሊቆጣጠር ሽቶ በካራቴው ንጉስ ድባቅ የተመታው ይህ ተቋም በዚሁ በምርመራ አስባብ የነበረ መሆኑንም ማስታወስ ይበቃል። ለራሳችን እንበቃለን እያልን የበላችሁን ቦታ የማውቀው እኔ ነኝ ሲል ዝንተ አለም ሙጭጭ የሚል አካል ለነገር ካልሆነ ሰብአዊነት አሳስቦት ነው ለማለት ይከብዳል። ሰብአዊነት ካሳሰበው እዛው ባጠገቡ ጥቁሮችን አሽቀነጥራለሁ ሲሉ፤ ሙስሊሞችን አስወጣለሁ ሲሉ፤ ግንብ በመገንባት ሌላውን ጥርግርጉን አወጣለሁ፤ ከስራም አፈናቅላለሁ ሲሉ በአደባባይ ስለሚናገሩት ትራምፕ፤ ጥቁሮችን የማባረር ዘመቻዎች በይፋ ስለጀመሩቱ አውሮፓውያን ከነካቶሊኩ ቄሳር ጎን ተሰልፎ አይደረግም ሲል ምነው አልሰማነው?።
በየትኛውም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገራትም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጽንሠ ሃሳብ መሠረት ከምርጫ ውጪ የሚደረግ የስልጣን ዘመቻ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሃገራችን በምትከተለው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገራት እንደሚደረገው ሁሉ ሃሣብን በነፃ የመግለፅ፣ የመደራጀት፣ የመሠብሠብ እንዲሁም ሠላማዊ ሠልፎችን የማድረግ መብት የተፈቀደና ህገመንግስታዊ ዋስትናም የተሰጠው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ግን ደግሞ ሃሣብን በነፃነት በመግለጽ መብት ሽፋን፣ በመሠብሠብና በመደራጀት መብት ስም፣ በሠላማዊ ሰልፍ ጥላ በመከለል የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ህገወጥ እንቅስቃሴ የመመከትና በህግ አግባብ እርምጃ የመውሰድ መብት እንዲሁ በስልጣን ላይ ለሚገኘው መንግስት የተሠጠ ሃላፊነትና ሃላፊነቱም በህገመንግስቱ የተረጋገጠ ነው፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች በሚዘምርለት የባለፈው አመት “ተቃውሞ” የህዝቡ ሰላምና መረጋጋት፣ እንደዚሁም የሕዝብ ደኅንነት ጉዳይ አደጋ ውስጥ ወድቆ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። እነዚህን ሥጋቶችና ብጥብጦች በመደበኛው መንገድ ለማስታገስ ተደርገው የነበሩ ሙከራዎች ሁሉ ሲከሽፉ ልክ እንደፈረንሳይና እንግሊዝ አዋጅ ብናወጣ ምናለበት። ለኛ ሲሆን ሂዩማን ራይትስ ዎችን ስለምን ያንገበግበዋል? እዚህ ድረስ የነዳጅ ገፍግፎ ለምርመራ ከሚኳትን አጠገቡ ያሉትን ስለምን አይመረምር? እዚያም ያሉት ሰብአዊ መብታቸውን የሚሹ ማህበረሰቦች ናቸው እኮ።
ሂዩማን ራይትስ ዎች በሚዘምርለት ከላይ የተመለከተ “ተቃውሞ” ምክንያት በደረሰው አደጋ የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ በሥጋት ውሰጥ ገብቶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፤ ለበርካታ ዜጎች ሕልፈትም ምክንያት ሆኗል። በኢንቨስትመንትና በሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እጅግ ከፍተኛ አደጋንም ከስቶ የነበረ መሆኑ ሲታወስ ይህን በመደበኛ የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ ልትፈቱ ይገባችሁ ነበር ብሎ ወቀሳ “አልበላሽምን ምን አመጣው” እንዳለችው እንሰሳ አይነት ነገር ይሆናል።
ይልቁንም በዚህ አዋጅ በተመለከቱ ድንጋጌዎች ላይ የተጣሉት ገደቦች በሙሉ ህዝቡ ሙሉ እንቅስቃሴውን በተረጋጋ መልኩ ማከናወን የሚያስችለው ሰላም ለማግኘት ያለሙና መደበኛ ሕይወትን ለመመለስ የሚረዱ እንጂ እንደነሀገረ አሜሪካ አፋኝ ስላለመሆናቸው በንጽጽር መመልከት ነው። ሂዩማን ራይትስ ዎች በሚዘምርለት “ተቃውሞ” ሰሞን የሕዝቡ መደበኛ እንቅስቃሴ ተገድቦ የነበረ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የተደራጁ ትንንሽ ቡድኖች ግለሰቦችን ሲያጠቁ እንደነበር፣ ሱቆችን ሲያዘጉ፣ ፋብሪካዎችን ሲያወድሙ እና መንገዶችን ሲዘጉ የነበረ መሆኑና ምናልባትም የስፖንሰር ክፍያው በነግንቦት 7 በኩል ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር አይከፋም።
ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዋለው ለበጎ ዓላማና ችግሮችን መቅረፍ እንዳስቻለ ባለቤቱ እየመሰከረ ባለበት ሰአት ላይ የሂዩማን ራይትስ ዎች ጩኸት ላልተሳካው ድራማው የተቆጨ አስመስሎበታል።
በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳደሩ ጉዳዮች መካከል አለመረጋጋት አንዱ ነው፡፡ በምጣኔ ሃብታዊ ተመራማሪዎች ጥናት መሰረት አንድ ዓመትና አንድ ዓመት ከመንፈቅ የቆዩ ግጭቶች ከ10 እስከ 15 በመቶ የአገሪቱን የመነገድ አቅም ያቀጭጫሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግጭቱ ካቆመ በኋላ አገሪቱን ወደነበረችበት ለመመለስ ከ10 እስከ 15 ዓመታት እንደሚፈጅባትም ጥናቶቹ ያረጋግጣሉ፡፡ በመሆኑም ነገሮች ችላ በሚባሉበት ጊዜ፣ የሰዎች ትኩረት ከኢንቨስትመንትና ከምርት ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ያዘነብላል፡፡ መንግሥታት ሙሉ ጊዜያቸውን የፖለቲካ ትኩሳቶችን ለማርገብ በሚያውሉበት ጊዜ በልማት ጉዳዮች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመመልከት በሃገራችን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስቀድሞ የነበርንበትን ማስታወስ በቂ ነው።
ጦርነት በበዛባቸው የአፍሪካ አገሮች ከጦርነቱ በኋላ ወደነበሩበት ለመመለስ 15 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ ሶሪያን ያየን እንደሆነ አሁን ከሚታየው አኳያ፣ አገሪቱ ከ30 ወይም ከ40 ዓመታት በኋላም ልታገግም እንደማትችል ጥናቶች እያሳዩ ነው፡፡ መፍትሔ የሚሆነው መንግሥት የትኛውም አካል ላለበት ችግርና ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በመወያየትና በመነጋገር መፍታት ነው፡፡ የትኛውንም ያለመግባባትና ቅሬታ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ይኖርበታል እንጂ ከላይ በተመለከቱት አግባቦች ሲሆን ሃገር አደጋ ላይ መውደቋ አይቀሬ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2000 በፊት በነበሩ አሥር የአፍሪካ አገሮች ላይ ጥናት ያደረጉ እና እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ውስጥ በየዓመቱ ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን የሚያስታውሱት ጠበብቶች በግርድፉ ሃያ ወይም ከዚያም በላይ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን፤ በእነዚህ አገሮች የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከዜሮ በታች ወይም ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ባለው ዝቅተኛ መጠን ሲያድግ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡
ስለሆነም ከመሬት ተነስቶ ወደነበርንበት መመለስ ያስቻለንን አዋጅ ከሰብአዊ መብት ጋር አያይዞ ድራማ ለመስራት መሞከር የተለመደና የሰለቸ ተውኔት ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አላማ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠልና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር እንጂ በተገላቢጦሽ ህዝቡን መፈናፈኛ ለማሳጣት እንዳልሆነ ከላይ በተመለከቱት አስረጂዎች ተገንዝቦ በሰብአዊ መብት ስም ህልውናችንን ለማሳጣት የሚዳክሩትን ከላይ የተመለከቱ ሃይሎች እናንተን ልንሰማ የምንችልበት ጊዜም ሆነ ህሊና የለንም ልንላቸው ይገባል።