የዘንድሮው የሀገራችን የመኽር ምርት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ውጤት እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡ በመኸር ምርቱ የ12 በመቶ እድገት እንደሚገኝ አስቀድሞ በተደረገ የቅድመ ምርት ግምገማ ውጤት ለማወቅ ተችሎአል፡፡ ውጤቱን በተሳካ ሁኔታ ለማስገኘት የተቻለው መንግስት ድርቅን በመከላከል ድንገተኛውንና ግዜውን ጠብቆ የሚመጣውን የዝናብ ውሀ ጉዳት ሳያስከትል እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሚቻል በሁሉም ክልሎች ለአርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት ሰፊ ስልጠና በመስጠቱ ነው፡፡
አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና እውቀቶችን ዝናብ በሌለበትም ወቅት መስኖን በመጠቀም እንዴት ማምረት እንደሚችል ሰፊ እውቀት በማግኘቱ ይሄንንም በስራ ላይ በማዋሉ የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ለወደፊቱም በዚሁ አቅጣጫ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ድርቁ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚመጣ ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው፡፡ መነሻው ያደጉና የበለጸጉ ሀገራት በከባድ ኢንዱስሪዎቻቸው አማካኝነት የሚለቁት የተበከለ ጋዝ ልቀት ሲሆን ይህም የተፈጥሮ አየርንብረት እንዲዛባ፤ ለድርቅ፤ ላልተጠበቀ ዝናብ መከሰት፣ ለጎርፍ መጥለቅለቅ፤ ለውቅያኖሶችና ለባህሮች ከአቅም በላይ ሞልተው መገንፈልና መሬትን ማጥለቅለቅ፤ ለድድር የበረዶ ክምሮች መቅለጥ፤ ለመሬት ናዳ፤ በረሀማነት በከፋባቸው አካባቢዎችም ለተፈጥሮ ደኖች በእሳት መንደድና መቃጠል ዋነኛ ምክንያት እየሆነ መጥቶአል፡፡
በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ ባለፉት የሀምሳ አመታት ታሪክ ውስጥ አልታየም፡፡ አልተሰማም፡፡ መንግስት ያለውን አቅም በመጠቀም ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሕዝቡ ተደራሽ የሚሆን ርብርብ በማድረጉ አደጋውን ለመቀነስ ተችሎአል፡፡ ዘንድሮ ድርቁ ቀድሞ ባልተከሰተባቸው አንዳንድ ቦታዎች በተለይም በምስራቁ የሀገራችን ክፍል አየል ብሎ ታይቶአል፡፡ የፌደራሉ መንግስትና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ የምግብና ውሀ እደላ በተከታታይና በማይስተጎጎል ሁኔታ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ድርቁ በእንሰሳት ላይ ከበድ ያለ ጉዳት አድርሶአል፡፡ በውሀ እጥረት እንሰሳት አልቀዋል፡፡ ቢሆንም ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በሌላው የሀገራችን ክፍል የተገኘው ከበቂ በላይ የሆነው ተረፈ ምርት በድርቅ ለተጎዱት አካባቢዎች በግዢ ተገዝቶ እንዲደርስ ለማድረግ መንግስት የርብርብ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ዘንድሮ ከአጠቃላይ ግብርና ምርት የመኸሩ ብቻ 12 በመቶ እንደሚመዘገብ ሲጠበቅ የበልግና የመስኖ ምርት ሲጨመር ከተጠበቀው በላይ ይሄዳል፡፡ ይህ የአሁኑ ከፍተኛ ውጤት የተገኘው በሀገራችን የግብርና እድገት መመዝገብ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ የመጀመሪያው ትልቁ እድገት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩ የነበረውን ምቹ የዝናብ ስርጭት ተጠቅሞ ያፈራውን ሰብል ለመሰብሰብ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ዘመናዊ የአጨዳ ማሽነሪዎችንና ኮምባይነሮችን ተጠቅሞአል፡፡ የሀገራችንን ግብርና ወደ ሜካናይዜሽን ለመለወጥ የግል ባለሀብቶች፣ መንግስት፣የሕብረት ስራማህበራት ማሽኖቹን ገዝተው በስፋት አሰማርተዋል፡፡
በአንዳንድ የገጠሩ አከባቢዎች በነበረው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት የተነሳ ሰብሉ በወቅቱ ሳይዘራ ወይንም ሳይታረስ ቀርቶ አርሶ አደሩ ወደማምረት ተግባር ላይገባ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበር፡፡በአብዛኛው ቦታ የመኸር ምርት አርሶ አደሩ በንቃት ተሳታፉ በመሆኑ ውጤቱ መመዝገቡን፤ከኢንዱስትሪ ልማት ፍጥነት አኳያም በማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት መሰረት እያንዳንዱ ፋብሪካ የምርታማነት መጠኑ አለመቀነሱን እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መጨመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሀን ገልጠዋል፡፡
በዘንድሮው 2008 አ.ም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች በብዛት በስፋት ወደስራ ገብተዋል፡፡ በሁከቱ ሳቢያ በደረሰባቸው ቃጠሎ ስራ ላይጀምሩ ይችላሉ ተብለው የተገመቱ 26 ኢንዱስትሪዎችና የአበባ እርሻ ልማቶች መንግስት 450 ሚሊየን ብር ካሳ በመስጠቱ በሁለት ወር ስራቸውን በመደበኛ ሁኔታ ጀምረዋል፡፡ ትልቅ ስኬትና ድል ነው፡፡
የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማሰናከል ታቅዶና ተወጥኖ የመንግስትና የባለሀብቶችን እንዲሁም የህዝብ ሀብት የሆኑትን ድርጅቶች ፋብሪካዎች ንብረቶች በእሳት በማጋየት በማውደም ከስራ ውጭ እንዲሆኑ ለማድረግ የተፈጸመው የጥፋት ድርጊት በመንግስትና በሕዝቡ ርብርብ እንዲገታ ተደርጎአል፡፡ በተፈጠረው ሁከት ከደረሰው ጉዳት አንጻር ሲፈተሸ በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ሴክተሩ የከፋ ችግር አልገጠመውም፡፡ስራዎቹን በተቀላጠፈ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡
ጸረ ሰላም ሀይሎች አንዱና ዋነኛ ኢላማቸው አድርገው ለመንቀሳቀስ የሞከሩት በተለያየ አቅጣጫ ያለውን የሀገሪቱን የቱሪስት ገበያ ለማምከን ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡ የመጀመሪያው አለም አቀፍ ቱሪስቶች ከውጭ ወደ ሀገራችን እንዳይመጡ ለማድረግ ሰላምና መረጋጋት የለም፤ በየቦታው ሁከትና ትርምስ አለ፤ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጆአል፤ በሰላም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይቻልም የሚሉ ሰፊ ቅስቀሳዎችን የራሳቸውን ሚዲያና ሶሻል ሚዲያውን በመጠቀም መልእክቶችን ለውጭ ሀገራት አሰራጭተዋል፡፡ ይህም የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት የተደረገ እኩይ ዘመቻ ቢሆንም አልተሳካላቸውም፡፡
ይህ በጥናትና በእቅድ የተደረገ ሴራ ዋነኛው ግቡ አለም አቀፍ ቱሪስቶች ከአመት አመት ቁጥራቸው እያደገ ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪስቶች መዳረሸ እያደረጉ ከቱሪዝም የምታገኘው ገቢ እየጨመረ ስለመጣ ይሄንን የሀገሪቱን ገቢ ለማስቆም ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ ጥረታቸው አይናቸው እያየ መክኖአል፡፡
ሁከቱና ትርምሱ በአጭር ግዜ አብቅቶ የነበረው ሰላምና መረጋጋት ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሶአል፡፡ የነበረው መደናገጥ በሰላምና በመረጋጋቱ ተተክቶአል፡፡ የሀገሪቱና የሰላሙ ባለቤት ዋነኛው ሀይል ህዝቡ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላሙንና ጸጥታውን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ተችሎአል፡፡ በዚህ የተነሳ የቱሪዝም ገበያው እያደገ በመሄዱ ባለፈው ሩብ በጀት ዓመት ብቻ 250ሺህ ቱሪስቶች አገራችንን ጎብኝተዋል፡፡ በዘንድሮው አመት ከ800ሺህ እስከ 900ሺህ ቱሪስቶች ሊጎበኙ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከቻይናው ማዕከላዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ዓመታዊ እድገቱን በሁለት አሀዝ በማስቀጠል በተያዘው ዓመት ኢኮኖሚውን በአማካይ በ11 በመቶ ለማሳደግ መታሰቡን ተናግረዋል፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ አዎንታዊ እድገት መመዝገቡንና በተለይም በኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ረገድ የገዘፈ አቅም እየተፈጠረ በመምጣት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አሁን በትክክለኛው መንገድ ላይ እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት የአገሪቷን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ሰሞኑን በተመረቀው የጊቤ 3 ኃይል ማመንጫና በሌሎችም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን፤አገሪቷ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር አባል በመሆኗ ማመንጫዎቹ የቀጣናውን ፍላጎት ለማሟላት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለቻይናው ቴሌቪዥን ጣቢያ ገልጸዋል፡፡
አገሪቷ ቢያንስ የ11 በመቶ አማካይ ዓመታዊ እድገት ለማስመዝገብ አቅዳ ኢኮኖሚው በየዓመቱ በ10 ነጥብ 1 በመቶ አድጓል፡፡ የተመዘገበው ፈጣን እድገት በተመሳሳይ በአቻነት ከሚገኙት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ጋር በንጽጽር ሲታይ የእኛ በእጥፍ የአደገ ለመሆኑ በተደጋጋሚ ምስክርነት ተሰጥቶበታል፡፡
አገሪቷ ባለፈው ዓመት ከባድ የድርቅ አደጋ አጋጥሟት እንደነበረ አስታውሰው፤የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ያጋጠመውን የድርቅ አደጋ ተቋቁሞ 8 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን፤ በዚህ ሳቢያም ከ8-10 የነበረው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ አማካይ ዓመታዊ እድገት ወደ 2 ነጥብ 9 ዝቅ ለማለት መገደዱን፤ ይህንንም መሰረት በማድረግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በመፍጠር የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲገነባ ለማስቻል በትጋትና ጥንካሬ እንደሚሰራ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሰነድ ላይ የሰፈረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ነው ርእሰ-ጉዳያችንን “አዎ፤ ትክክለኛው መንገድ ላይ ነን” ስንል የጀመርነውና እሱንም ይዘን ለመዝለቅ የቻልነው፡፡