አገራችን የዴሞክራሲ ስርዓቷ ለማጎልበት አጠናክራ በመስራት ላይ ትገኛለች። ባለፉት 22 ህገ-መንግስታዊ ዓመታት አገራችን የህዝቦቿን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስጠበቅ ችላለች፤ በየአምስት አመቱ የሚካሄድ ምርጫ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመረጡት አካል መተዳደር የሚችሉበትን ሁኔታ አካሂደዋል፤ በፌዴራል ስርዓቱ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ችለዋል። ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት አጎልብተዋል። አዎ በእነዚህ ዓመታት አንዳንድ አፍራሽ ሃይሎች የፈጠራ ወሬቸውን ቢነዙም እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአገራችንን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማጎልበት ስራ ላይ ነን።
ኢትዮጵያ በአለማችን እጅግ ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የቻለች በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ለውጦችን ማሳየት የቻለች አገር ሆናለች። ከቅርብ ጊዜ በፊት በምግብ ሰብል ራሷን መቻል የተሳናት አገር በተከታታይ አመታት እንዲህ ያለ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ መቿሏ ጠንካራ አመራር እንዳላት የሚያሳይ ጉዳይ ነው። በአካባቢው ካሉ አገሮች በአጠቃላይ ግብርና ምርት ከፍተኛውን ቁጥር ከመያያዟም ባሻገር በዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን በዋና ዋና ምርቶች ብቻ ከ320 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል በመሰብሰብ ላይ ነው። የግብርናው ዘርፍ የአገራችን ዋንኛ ሞተር ነው። አዎ ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የግብርና ምርታችንን በማዘመን አገራችን የጀመረችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል ስራ ላይ ነን።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታዳሽ የሃይል ምንጭ ለመሆን በርካታ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነች። ከእነዚህ መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ነው። ይህ ፕሮጀክት 6 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል ያመነጫል። ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ የምትገነባው ይሁን እንጂ የአካባቢውን አገሮች በኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስተሳስር በመሆኑ ለቀጠናው ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው። ብዙውን ጊዜ ታዳጊ አገሮች እንዲህ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚገነቡት በብድርና እርዳታ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ይህን የባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀውን ፕሮጀክት እየገነባች ያለችው በውስጥ ገቢዋ በቻ መሆኑ በራሱ ፕሮጀክቱን ልዩ ያደርገዋል። በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በተፋሰሱ አገራት መካከል መተማመንን ያጎለብታል፣ የወንዙም ዘላቂ ህይወትም ይረጋገጣል። ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የይቻላል መንፈስን እንዲጎለብት ያደረገ፣ ህዝቦች በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደሚቻል የለውጥን መንገድ ያመላከተ በመሆኑ ለታዳጊ አገራት ትልቅ ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ፕሮጀክት ነው። አዎ ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ አገሮች ጭምር የሚተርፉ እንደህዳሴው ግድብ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነን።
የአገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትና የአገሮችን የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ ነው። ኢትዮጵያ በምትከተለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አገራችን ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ በአለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነት እንድታገኝ አድርጓታል። በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን በተባበሩት መንግስታት ያላት ተሰሚነት በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረከኮች ያላት ተሰሚነት አድጓል። አዎ ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገራችን በአለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እንዲጎለብት በመስራት ላይ ነን።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ዳርፉር፣ አብዬ፣ በደቡብ ሱዳን፣ የሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ነች። የኢትዮጵያ ህዝባዊ፣ በዲሲፒሊን የታነጸና እጅግ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት መገንባት ችላለች። ኢትዮጵያዊያን ሰላም አስከባሪ ኃይሎችም በተሰማሩበት አገር ሁሉ በህዝብ የተወደዱና ምስጋና የተቸራቸው ናቸው። አዎ ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ የኢትዮጵያዊያን በጠነካራና በዲሲፒሊን በታነጸው ሰራዊታችን የአህጉሪቱን ሰላም በማስከበር ስራ ላይ ነን።
ኢትዮጵያ የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር ማስመር ዝርጋታ፣ በአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የኃይል አቅርቦት ወዘተ…በማካሄድ የአካባቢው አገራት ህዝቦችን ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረግ ላይ ነች። አገራችን የምትከተለው ፖሊሲ የአካባቢው አገሮች በምጣኔ ሀብት ጥቅም እንዲተሳሰሩ ለማድረግና የቀጠናው ሰላም ዘለቄታዊነት እንዲኖረው የምታደርገውን ጥረት ያሳያል። እነዚህ ታላላቅ መሰረተ ለማቶች የቀጠናውን አገሮች ፖለቲካል፣ ኢኮኖሚካልና ማህበራዊ መስተጋብሮች ያጠናክራሉ። አዎ ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አፍሪካዊያንን በተለይ በቀንዱ አካባቢ የሚገኙ አገሮችን በመሰረተ ልማት በማያያዝ ህዝቦች በጋራ ጥቅም እንዲተሳሰሩ በማድረግ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጠንክረን በመስራት ላይ ነን።
መንግስት የአገሪቱን ኢኮኖሚ የመዋቅር ሽግግር እንዲያደርግ እንዲሁም ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው። በአገሪቱ ወደ አስራ አንድ የኢንደስትሪ ፓርኮችን የሚገነቡበትን ስፍራዎች በመምረጥ ወደ ግንባታ ተሸጋግሯል። ለኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከተመረጡ አስራ አንድ አካባቢዎች አዲስ አባባ ሶስት ክላስተሮች ማለትም ለሚ አንድና ሁለት እንዲሁም ቂሊንጦ አካባቢ፣ ሃዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ ባህርዳርና ጅማ ደብረብረሃን ተጠቃሽ ናቸው። ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የከተሞችን የተቀናጀ እድገት ያፋጥናሉ፣ ለዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ፣ በተመሳሳይ ለኢንደስትሪ ልማት የሚያግዝ መሰረተ ልማትን በቀላሉ ለማስፋፋት ስለሚያስችሉ ወጪ ቆጣቢ ናቸው፣ በፓርኮች አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ ፋብሪካዎች በአንድ ክላስተር ማሰባሰብ ስለሚቻል የምርት ከብክነትን ያስወግዳል፤ ይህም አለም አቀፍ የምርት ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል፤ የከተማ መሬትን በአግባብ መጠቀም ያስችላል፤ በአነስተኛ ስፍራ ላይ ለበርካተ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ያስችላል። አዎ ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአገራችንን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የመዋቅር ሽግግር እንዲያደርግ ጠንክረን በመስራት ላይ ነን።
ባለፈው ዓመት አገራችን በ50 ዓመታት የአገራችን የታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ተመታለች። ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎቻችን በድርቅ ተጠቅተው ሳለ የዓለም ዓቀፉ ምላሽ እጅግ የተቀዛቀዘ ነበር። ይሁንና አገራችን በተከታታይ ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት በፈጠረችው አቅም ሳቢያ ዜጎቿን ከድርቅ መታደግ ችላለች። ድርቁ ዘንድሮም በአንዳንድ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ አጥቅቷል። መንግስት በድርቅ ለተመቱ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ምግብና ውሃ እንዲሁም ለእንሰሳት መኖ ከማቅረብ ባሻገር የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዝ ዘላቂ የልማት ስራዎችን በማካሄድ ላይ ነው። አዎ ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በድርቅ በተመቱ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እርስ በርሳችን እንረዳዳለን፤ እንዲሁም የድርቅ ተጋላጭነታችንን በዘለቄታ ሊቀርፉ የሚችሉ ስራዎችን ጠንክረን በመስራት ላይ ነን።
አገራችን በፈጣን ለውጥ ውስጥ ነች፤ ይህን ፈጣን ዕድገት የማስቀጠል ዋንኛ ኃላፊነት የሚወድቀው በወጣቱ ላይ ነው። በመሆኑም ይህ ኃይል እያንዳንዷ አካሄዱ አገርን ሊያለማ ወይም ሊያጠፋ እንደሚችል ተረድቶ እያንዳንዷን እርምጃውን በቅጡ አጢኖ ሊራመዳት ይገባል። ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኛ አሜሪካን ተቀምጦ ወጣቱን ለፖለቲካ ፍጆታው መጠቀም ይፈልጋል። ዳያስፖራው የተሳሳተ መረጃውን በፌስቡክና በመርዘኛ ሚዲያዎቹ (በኢሳትና ኦ ኤም ኤን) በመርጨት ወጣቱን ለሁከትና ረብሻ ለማነሳሳት የተለያዩ ዘዴዎችን ሲጠቀም ቆይቷል። የጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ከእንግዲህ ወጣቱን ለሁከትና ብጥብጥ ማነሳሳት የሚችሉበት መንገድ አይኖርም። የጽንፈኛውን የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ድብቅ አጀንዳ ወጣቱ ነቅቶባቸዋል። ከእንግዲህ ጽንፈኛውን የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የጥፋት እጃችሁን ሰብስቡ።