የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፉ ሲዳሰስ

ሚዲያ ታላቅ ሀይል ነው፡፡ ብዙዎች ሊገምቱትም ሆነ ሊያስቡት ከሚችሉት በላይ የገዘፈ አቅም አለው፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ፋይዳም የላቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፉ የሚዲያ ባለቤትና በርካታ ጋዜጠኞችን ቀጥሮ የሚያሰራው መንግስት ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ ያለው ሚዲያ ጅምሩ ቢኖርም በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር ሌሎቹ የፋይናንስ አቅማቸው የሚያወላዳ አይደለም፡፡ የሚዲያን ነጻነት በተመለከተም በመገናኛ ብዙሀንና በመረጃ ነጻነት ሕጉ ላይ በግልጽ ሰፍረው የሚገኙት ሕጎች በራሱ በመንግስት ውስጥ በሚገኙ ኃላፊዎችም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደማይደረጉ ራሳቸው ጋዜጠኞቹ በስፋት ይናገራሉ፡፡

ሳንሱር በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ጋዜጠኞች የሕዝብ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን አውጥተው እንዳይሰሩ የኃላፊዎች ቀጭን ትእዛዝ፣ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ጣልቃ ገብነት ጭምር በገሀድ የሚታይ ክስተት መሆኑን ሰሞኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ባዘጋጀው መድረክ  በየቡድኑ በነበሩ ውይይቶች በስፋት ተነስቶአል፡፡ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን በማጋለጥና በመዋጋት ረገድ ሰፊ ድርሻውን የሚወጣው ሚዲያ በዚህ መልኩ ተተብትቦ ከተያዘ በነጻነትና እንዲሰራ ካልተደረገ ከችግሩ ውስጥ መውጣት ከቶውንም አይታሰብም፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት (ኢንቬስቲጌቲቭ ጀርናሊዝም) በስፋት በስራ ላይ እንዲውል መንግስት ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ደጋግሞ የገለጸ ቢሆንም በጋዜጠኛው በኩል ከፍተኛ ስጋቶች መጋረጣቸው አንዱና አከራካሪው ጉዳይ ነው፡፡ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች እጀ-ረጅም ስለሆኑ ጋዜጠኛው ተንቀሳቅሶ ለመስራት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተለያየ መልኩ ሊያስተጓጉሉት እንደሚችሉም በውይይቱ ተገልጾአል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽቤት ሚኒስትር ዲኤታ ዛዲግ አብርሀም በዚህ ሀሳብ አይስማሙም፤ ስራው ሳይጀመር ፍርሀት ውስጥ የመግባት ያህል መሆኑን ነው የሚገልፁት። የምርመራ ጋዜጠኝነት ቁርጠኛ ውሳኔ አደጋን ወስኖ ለመቀበል ዝግጁ የመሆን ከባድ ሀላፊነትን ይጠይቃልና አስተያየታቸው ትክክልም ነው፡፡

ደፍሮ ወደስራው መግባት፣ ሰፊ መረጃዎች የሚገኙበትን መረብ መዘርጋት፣ በራስ አቅም ራስን ከጥቃት ለመከላከል የተለያዩ የሽፋን ዘዴዎችን መጠቀም፣ አስፈላጊ ሲሆንም ከአካባቢው ጋር የመመሳሰል፣ ማንነትን ለግዜው መቀየርና የመሳሰሉትን ሁሉ በስፋት የሚጠይቅ ጥብቅ ስራ ነው የምርመራ ጋዜጠኝነት፡፡ ነጮቹ የምርመራ ጋዜጠኝነትን በሽፋን ስር የሚካሄድ ዘመቻ (under cover operation) ይሉታል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ለማካሄድ እጅግ ሰፊና ሊሰራባቸው የሚገቡ አንኩዋር ጉዳዮች አሉ፡፡ ማነው ጥበቃና ዋስትና ለጋዜጠኛው የሚሰጠው ለሚለው ጥያቄ ሚኒስትር ዴኤታ ዛዲግ አብርሀም በሕገመንግስቱ በሰፈረው ሕግ መሰረት መንግስት በሕዝብና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚሰሩ ስራዎች ሁሉ ጋዜጠኞችን የመጠበቅና ዋስትና የመስጠት፣ የመከላከል ግዴታውን ይወጣል ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ሁኖ ስራውን በቁርጠኝነት መጀመሩ ለሀገርም ለሕዝብም ጠቃሚ በመሆኑ ከፍርሀት ባሻገር ዛሬ ነገ ሳይባል ስራው ውስጥ መግባት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ስራውን የሚጀምረው ጋዜጠኛ ስለጉዳዩ ለመንግስት አሳውቆ ቢገባ እያንዳንዱን የደረሰበትን ደረጃ በተለይ ለዚህ ተብሎ ለተቋቋመው ክፍል እያሳወቀ ቢንቀሳቀስ የት እንደሄደ፤ የት ቦታ እንደሚገኝ ከታወቀ ተፈላጊው ድጋፍና ክትትል በመንግስት በኩል ስለሚደረግ የጋዜጠኛውን ለአደጋ ተጋላጭነት ይቀንሳል፡፡ ችግር የለብኝም ካለም በግሉ ሊያካሂደው ይችላል፡፡ ውሳኔው የራሱ የጋዜጠኛው ነው፡፡

በተለይ በቅርቡ በሀገራችን የተቋቋመውና ኤፍቢአይን ይመስላል የተባለው ልዩ የምርመራ ቢሮ አዲስ ቢሆንም ልክ እንደሌሎቹ፤ አሜሪካና የመሳሰሉት ሀገሮች ሁሉ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ለሚሰራው ጋዜጠኛ ድጋፍና ትብብር በማድረግ የሙያ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ማደረግ ይችላል፡፡ በሌሎች ሀገራት ጋዜጠኛው አሳውቆ በሚንቀሳቀስበት ስፍራ ሁሉ አደጋ እንዳይደርስበት በስውር ልዩ ክትትልና ጥበቃ ይደረግለታል፤ መረጃዎቹ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ በመሆኑ የተለየ ጥበቃ አለው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ሀገር ላይ ለስራው ወዲያና ወዲህ የሚባዝን ጋዜጠኛ በሚንከራተትበት ቦታ ሁሉ ከአደጋም ጋር ሊጋፈጥ ስለሚችል፤ ይህንን ሊመክትና ሊከላከል የሚችልበት ብቸኛው ሀይልም መንግስት ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ አንጻር የጋዜጠኛውም ስጋት ተገቢና ትክክለኛ ነው፡፡

ቦብ ሂችኮክ፣ የእንግሊዙ አለም አቀፍ የቶምሰን ፋወንዴሽን ጋዜጠኝነት ትምህርት ተቋም መምህርና እድሜ ዘመኑን በጋዜጠኝነት የሰራ፣ በአፍሪካ ውስጥ በበርካታ ሀገራት ጋዜጠኞችን ያሰለጠነ  እውቅ ሰው ነው፡፡ ቦብ ሂችኮክ፣ በተለይ በምርመራ ጋዜጠኝነት የተለየ እውቀት፣ ችሎታ፣ ስልትና ዘዴን የሚጠይቅ ሙያ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡

ቦብ ሂችኮክ ራሱ በምርመራ ጋዜጠኝነት ብዙ ግዜ ተሰማርቶ ሰርቶአል፡፡ ቀድሞ የእንግሊዝ አየር ወለድ አባል የነበረና ከሰራዊቱ ከለቀቀ በኃላም ወደጋዜጠኝት ሙያ ገብቶ እድሜ ዘመኑን አገልግሎ ያለፈ ሰው ነው፡፡ ቦብ የምርመራ ጋዜጠኝነት ድፍረት፣ ልበሙሉነት፣ ቆራጥነት፣ የመጣውን ችግር ለመሸከም ወስኖ መንቀሳቀስ፣ የሚፈለገውን መረጃ ለማግኘት ማንነትን አስመስሎ እስከመቀየር ድረስ የሚያስኬድ መሆኑን እንደ ኢላማውና ክትትል እንደሚደረግበት ጉዳይ ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ራስን ከአካባቢው ጋር የማዋሀድ ከባድ ስራን የሚጠይቅ መሆኑን ይናገራል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው ግንዛቤም ይሄው ነው።

ቦብ በ1984 አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች የስራ አጋሮቹ ጋር መጥቶ ቀደምት ለነበሩት አንጋፋ ጋዜጠኞች በጋዜጠኝነትና በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ሰፊና እጅግ በጣም ብቁ የሚያደርጉ ስልጠናዎችን  ሰጥቶ መመለሱ ይታወቃለ፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣  በሀገር ደረጃ በመንግስት ተቋማት በየግል ድርጅቶች ኮርፖሬሽኖች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሰሩ የውጭ ኢንቨስተሮች ዙሪያ ስላለው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ብክነትና ዘረፋ በሁሉም መስክ የሚሰራ፣  በእውቀት የጎለበተ፣ የሰለጠነ ተገቢው የቴክኒዮሎጂ አጠቃቀም እውቀት ያለው፣   የምርመራ ጋዜጠኛን በሚገባ አሰልጥኖ ወደስራው ማስገባት እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡

ቀደም ሲል እንዳልነው፣ መስኩ በደመነፍስ የሚሰራ ሳይሆን በቂ እውቀትና ዝግጅትን የሚጠይቅ እንጂ አንድ ጋዜጠኛ ጋዜጠኛ ስለሆነ ብቻ የሚሰራው አይደለም፡፡ በጥቅም አለመደለል፣ አለመገዛት፤ ምስጢርን የመጠበቅ፤ በመጠጥ፣  በምግብ አለመሸነፍ፤ ለማታለያ፣ ለማባበል ተልከው በሚቀርቡ ውብና አማላይ ሴቶች አለመጠመድ፤ በብዙ መሰናክሎች ውስጥ የማለፍ ብቃትና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል የምርመራ ጋዜጠኝነት፡፡ ከኢንተለጀንስ ስራ ጋርም ይመሳሰላል፡፡

ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ሀይል በአለም ላይ እንደታየው ሁሉ መንግስትን እስከመገዳደር የሚደርስ የፋይናንስ አቅም እንዳለው በብዙ ሀገራት የሚታወቅ እውነት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ መደለያ የማቅረብ፣ የመሸለም፣ ብዙ ሚሊዮን ብሮችን  የማፍሰስና  ክትትሉን የማሰናከል አቅም አለው፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ይህንን ሁሉ ተጋፍጦ፣  ሀገሬና ሕዝቤ ይበልጥብኛል ብሎ በቁርጥ ውሳኔ የሚጸና፣  ሙያውን አክባሪ  ፈተናዎችን ለመጋፈጥ የቆረጠ ጋዜጠኛን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ መጀመሪያ መቅደም ያለበት አሁን በስራ ላይ ላሉት ጋዜጠኞች ተደጋጋሚ የሰልጠናዎችን መስጠትና ማብቃት የገቢ ነው፡፡

የሰሞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽቤት ለጋዜጠኞች፣ ለሕዝብ ግንኙነትና  ለሶሻል ሚዲያ ባለሙያዎች ያዘጋጀው ስልጠና ሙሉ ግልጽነት የተሞላበት፣ በሀገሪቱ ሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ስራዎች ዙሪያ የነበረውንና ያለውን መሰረታዊ ችግር አበጥሮና አንጠርጥሮ ያወጣና ለመክላት የሚያስችለውንም መፍትሄ ማስቀመጥ ያስቻለ ነው፡፡

የመንግስት ሚዲያውም ሆነ በየመስሪያቤቶቹ ያሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ሰራተኞች በሕግ የተቀመጠውን በመስራትም ሆነ በመፈጸም በማስፈጸም ረገድ ያለባቸውን የገዘፈ ጉድለት ስህተት መረጃን በተገቢው መንገድ ለሕዝብ ያለማድረስ የመደበቅ ችግሮች  ለጋዜጠኞች ያለመስጠት የመከልከል ችግርና ዳተኝነት ምንያህል መንግስትንም ሆነ ሕዝቡን እንደጎዱት በግልጽ የቀረበበት ነው፡፡ሰሚና ከስህተቱ የሚማር ከተገኘ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡

ይህ የመንግስት ፍላጎትና አላማ እንዳልሆነ፣ ከመሰረታዊ ስህተታቸው ታርመው ጋዜጠኞች ጠንካራ የሚዲያ፣  የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችም ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ስራዎቻቸውን እንዲሰሩ ቁርጠኛ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር አስችሎአል ማለት ይቻላል፡፡ በመንግስት በኩልም ቢሆን በሕዝብ ግንኙነቱም ሆነ በሚዲያው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ከፍርሀትና ከአድርባይነት ተላቅቀው በትክክል የሕዝቡን ችግር ነቅሶ በማውጣት እንዲሰሩ ውይይትና ክርክር እንዲደረግባቸው፣  ለችግሮቹም ቢሆን የጋራ መፍትሄ እንዲገኝ የማድረግ ጠንካራ ፍላጎት ያለው መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጾአል፡፡

በሚዲያው በኩል የሚታዩ የለውጥ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም አሁንም ሙሉ በሙሉ በሚፈለገው መንገድ ላይ አልገባም፡፡ የሚዲያውና የኮሙኒኬሽኑ ስራ ሰፊና መሰረታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው መስክ ነው፡፡ ባለሙያው የሕዝብ አገልጋይነትን ማስቀደም ለሕዝብ እውነት በመቆም መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህች ሀገር ማንም ሰው ከሕግ በላይ የለም፡፡ ብዙ የተለፋላትን መስዋእትነት የተከፈለላትን ሀገር ለግለሰቦች ሲባል አሳልፎ የሚሰጥ፣  ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር የሚፈቅድ ማንም ጅል የለም ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታ ዛዲግ አብርሀም፡፡

ሚዲያውም ሆነ የሕዝብ ግንኙነቱ መስክ መሰረታዊ ከሆ ኑት ችግሮቹ ማለትምከአድርባይነትና ከፍርሀት ቆፈን ወጥቶ በትክክል የሕዝብ አገልጋይ ሁኖ መስራት ያለበት ግዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፡፡ መንግስት የትኛውንም ሕግ ቢያወጣ፣ ቢናገር ስለግልጽነትና ተጠያቂነት መረጃንም በአግባቡ ለሕዝብ ስለማድረስ ትክክለኛነት ቢያሳውቅ ዋናውና ቁልፉ ሀይል በስራው ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛም ሆነ የሕዝብ ግንኑነት ሰራተኛው ኃላፊው በተግባር ሊያውለው ካልቻለ ፋይዳ የለውም፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በመገናኛ ብዙሀንና በመረጃ ነጻነት ሕጉ መሰረት በሕግ የተከለከሉና የሚታወቁ የብሔራዊ ደህንነትና የሀገሪቱ መከላከያ ብሔራዊ ምስጢሮችን ካልሆነ  በስተቀር ሌሎች መረጃዎችን የመከልከል ሕጋዊ ስልጣን የላቸውም፡፡ እንዲያውም ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ መረጃዎችን ባለመስጠትና ምስጢር ነው በሚል ሽፋን በመከልከል በሕግ፣  በፍርድቤት ሊከሰሱና ሊጠየቁም ይችላሉ፡፡

ሕዝብ ማወቅ ያለበትን መረጃ እንደግል ንብረታቸው የሚቆጥሩ፣ ሕጉን በትክክል የማያውቁ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ሁሉም ነገር የማይሰጥ ምስጢር ነው ብለው ቆልፈው መቀመጥን የመረጡ መረጃ የሕዝብ ንብረት እንጂ የእነሱ የግል ጉዳይ እንዳልሆነ በቅጡ ስለማወቃቸውም ለመረዳት አስቸጋሪ ሁኖ ቆይቶአል፡፡ ይሁን እንጂ፣ አሁን በዘርፉ ከፍተኛ ችግር እየጋረጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡

መንግስት ያወጣውን ሕግና ደንብ በማስፈጸም ረገድ መሰናከል የመሆን ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ብዙ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ ፈጥኖ መታረም ከሚገባውም ችግር አንዱ ይሀው ነው፡፡

ማነቆውን የፈጠሩት በስራው ላይ ጫና እንዲኖር ያደረጉት በየቦታው የነበሩና ያሉ ግለሰብ  ኃላፊዎች እንጂ የመንግሰት አቋም እንዳልሆነ እንዲያውም ከመንግስት ፍላጎት ውጪ  ሲኬድበት የነበረ አካሄድ መሆኑን ስብሰባው አጉልቶ አሳይቶአል፡፡ ከዚህ አንጻር አሁንም ረዥም ርቀት በመሄድ ሊሰራ የሚገባው ሰፊ የቤት ስራ ከፊታችን አለ፡፡ ከሚዲያውና ከሕዝብ ግንኙነቱ ስራ አንጻር ጎልተው የወጡት ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ዝርዝሩን ወደፊት እንመለስበታለን፡፡