እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲ አራማጅ ሀገር በርካታ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። እንኳንስ ባለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ በመጡ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ባሉበትና እሳቤዎቹ ሙሉ ለሙሉ ባልተወገዱበት እንደ እኛ ያሉ ሀገራት ቀርቶ፤ በዳበሩ ሀገራት ውስጥም ቢሆን ዴሞክራሲን ትክክለኛና ተገቢ በሆነ መንገድ ያለ ህፀፅ መገንባት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን እንደ ሀገር ከዴሞክራሲ አኳያ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መፍታት ይኖርብናል፤ ይገባናልም። ለዚህ ደግሞ የዛሬ 22 ዓመት ገደማ በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሙሉ ፈቃድ ዕውን የሆነው ህገ መንግስት ዋስትና ነው።
እርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ችግር ዴሞክራሲ ብቻ አይደለም። ከሰላምና ከልማት አኳያ የተገኙት ውጤቶች አበረታች ቢሆኑም፣ ችግሮች መኖራቸው ግን አይታበይም። በአጭሩ ኢትዮጵያ ከሰላም፣ ከልማትና ሀዴሞክራሰ ስርዓት ግንባታ አኳያ ያስመዘገበቻቸው ሁሉን አቀፍ ድሎች ተምሳሌታዊና ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ዕውን የሆኑ ቢሆኑም፤ በተለያዩ ወቅቶች ችግሮች መከሰታቸው ነባራዊ ነው። ያም ሆኖ በሁሉም መስኮች የሚከሰቱ ችግሮችን ህገ መንግስቱን ምርኩዝ አድርገን መፍታት እንችላለን— ህገ መንግስቱ የሁሉም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነውና።
በመሰረቱ የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን እንደ ችግር ጊዜ መውጫ አድርጎ መመልከት ከማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር የሚጠበቅ ነው። ለዚህም ሩቅ ሳንሄድ የዛሬ ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንደ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውንና ሁከት ለመለወጥና ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ በማድረግ ላይ የሚገኘውንና በህገ መንግሰቱ መሰረት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መጥቀስ ይቻላል። ይህም ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ችግሩን በህገ መንግስቱንና በህገ መንግስቱ አግባብ ብቻ የሚፈታ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ታዲያ ይህን መሰሉ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ዕውን እንዲሆን በሙሉ ድምፁ ካፀደቀው ህዝብ በስተቀር ማንም ከመሬት ተነስቶ ሊጥሰው አሊያም እንዲቀር ሊያደርገው አይችልም። የራሱ የሆነ ህግና ስርዓት ያለው በመሆኑም በገዥው ፓርቲም ይሁን በተቃዋሚዎች ወደ ጎን ሊባል አይችልም። ከዚህ ይልቅ ህገ መንግስቱን ለሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮች እንደ መፍትሔ ማፈለቂያ መጠቀም ይገባል። በተለይም በአጎራባች ክልሎች ውስጥ ሰነከባለሉ በመጡ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና በግጦሽ ሳቢያ የሚፈጠቱ ችግሮችን በህገ መንግስቱ አግባብ መፍታት ይገባል።
እርግጥ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ አይችልም። ሆኖም እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በሥልጣኔ በበለፀጉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ አይቀርም። ነባራዊ ክስተት ነው። ለነገሩ የሰው ልጅ ሰው ከራሱ፣ በአቅራቢያው ካለው ማህበረሰብና ከተፈጥሮ ጋር መጋጨቱም አይቀሬ ነው። ይህ በየትኛውም ዓለም ሊኖር የሚችል ግጭት ደግሞ በህግና በስርዓት መመራት ይኖርበታል። በተለይም ዜጎች በሙሉ ፈቃዳቸው ዕውን ባደረጓቸው መሰረታዊ የህገ መንገስት ድንጋጌዎች መፈታት ይኖርባቸዋል።
እርግጥ ለአብዛኛዎቹ ግጭቶች መነሻ ምክንያት በዓለማችን ላይ ያለው የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ነው። ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች አይደለችም— እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት አለባት። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ ነው። ዋናው ነገር የተከሰተውን ግጭት በችግርነት መዝግቦ መፍትሔውን ከህገ መንግስት መሻት ተገቢ ነው።
እርግጥ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ህብረ ብሔራዊ ሆኖ መዋቀሩ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተመቸ ከመሆኑም በላይ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ማንነቶችንና የጋራ እሴቶችን እያጎለበቱ መምጣታቸውን ያሳያል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አዲሱ ሥርዓት ከተመሠረተ ወዲህ በተወሰኑ አካባቢዎች በጎሣዎች መካከልና በአንዳንድ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ፌዴራል አወቃቀሩ የፈጠራቸው አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም፡፡
አንዳንዶቹ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የጎሣ ግጭቶች ናቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ ከልምድ ጉድለት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦትና ይህንን ተንተርሰው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ግጭቶች እንደነበሩ እሙን ነው፡፡ እነዚህ ግጭቶች በሂደት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ፌዴራል ሥርዓቱ ከተመሠረተ ጀምሮ ለተከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ መንስኤዎች ካለፉት ሥርዓቶች የተወረሱ ችግሮች ነበሩ፡፡
ዛሬ በመላ አገሪቱ የተረጋገጠው ሠላም የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንዲኖር በማስቻሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት መላ አቅማቸውን አቀናጅተው በድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ መዝመታቸው የሥርዓቱ ስኬቶች አንዱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ መብቶች ስለተመለሱላቸው ሀገራቸውን ለመለወጥ እንደ አንድ ማኅበረሰብ በልማት አጀንዳዎች ላይ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ህገ መንግስቱ የሰላም ዋስትና መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡
እርግጥ እዚህ ሀገር ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት ሀገራችን የምትከተለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።
ዳሩ ግን ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ሆኖም አንዳንዶች ይህን እውነታ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ጥላሸት ለመቀባት ቢሞክሩም፤ ከእነርሱ እሳቤ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ህገ መንግስቱ ምላሽ እየሰጠ መጥቷል—ላለፉት 22 ዓመታት። በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥም ህገ መንግስቱ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል።
እንደሚታወቀው ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የተገነባ አይደለም። በሂደቱ ውስጥ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። እናም በሂደቱ ውስጥ ጥቃቅን ስንክሳሮች ሊያጋጥሙት ይችላል። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ችግሮች ህገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው።
ከዚህ አኳያ በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ 22 ዓመታትን ተሻግሯል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ችሏል።
ሆኖም ጥቂት ወገኖች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ የችግሮች መንስኤ አድርገው በመመልከት በተሳሳተ መንገድ ህገ መንግስቱን ሲቃወሙ ይታያሉ። እርግጥ ማናቸውንም ጉዳዩች መቃወም (ህገ መንግስቱን ጨምሮ) ይቻላል። ህገ መንግስታዊ መብትም ነው።
ዳሩ ግን ተቃውሞው መሰረት ያለውና በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ የተመረኮዘ መሆን ይኖርበታል። ይህን ግን ከስሜታዊነትና ከጥላቻ በፀዳ ሁኔታ ማቅረብ የሚችል ያለ አይመስለኝም። ቢኖርም አብዛኛዎቹ ውንጀላዎች በማስረጃዎችና በመረጃዎች ላይ የተመሰረቱ አይደሉም። እናም መከራከሪያቸውን “እንዲህ ነው” ብሎ ማቅረብ ማቅረብ የሚችሉ አይመስለኝም። እንዲያው በደፈናው “ህገ መንግስቱ ሊቀየር ይገባል” ይላሉ።
ሆኖም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለት፣ አካላቸውን ያጡለትና ለተግባራዊነቱም የተረባረቡለት ነው። ይህ ዕውነታም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተስማምተው ያፀደቁትና የሉዓላዊ ሥልጣናቸው ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት እነዚሁ ህዝቦች እስካሉ ድረስ ፈራሽ የሚሆንበት ምንም ዓይነት ዕድል አለመኖሩን የሚያመላክት ነው። ከዚህ ይልቅ የሀገራችን ህዝቦች በሙሉ ፈቃደኝነታቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ በሀገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን እየፈቱበት የሀገራችንን አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በመፍትሔነት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ሆኗል።
ይህ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎት ልክ እንደ መቃወም መብት ሁሉ ህገ መንግስታዊ መብት ነው። ይህ መብትም በጥቂቶች ፍላጎት የሚቀለበስ ሊሆን አይችልም። እናም ህገ መንግስቱን የማሻሻልም ይሁን የመተው አሊያም የማፅናት መብት የሀገራችን ህዘቦች እንጂ የጥቂት ፅንፈኞች ፍላጎት ሊሆን አይችልም።
ህገ መንግስቱ ላለፉት 22 ዓመታት ያጎናፀፈን ድሎች በርካታ ናቸው። የሀገራችን ህዝቦች አንደኛው የሌላኛውን መብት የማክበርና የመቻቻል ተግባሮች ተጠቃሽ ናቸው። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተጎናፀፉት ህገ መንግስታዊ መብት ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን ማሳለጥ ችለዋል። ይህ ተግባራቸውም የሀገራቸውን መፃዒ ዕድል የሚወስን በመሆኑም፤ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ የሚፈጠሩ ችግሮችን ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው በመፍታት መቀጠላቸው አይቀርም—ባለፉት ዓመታት ህገ መንግስቱ የችግሮች መውጫ ቀዳዳ መሆኑን በተግባር አስመስክሯልና።