በሕዝብ የተመረጡትን የግብፅ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲን ከመንበረ ስልጣናቸው አስወግደው በሲቪል ልብስ የግብፅን ቤተ-መንግስት የተቆጣጠሩት የግብፅ ጦር ሰራዊት መሪዎች ለዚህ ያበቃቸው ወታደር መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በሙርሲ ኢህገ-መንግስታዊነት ላይ የተደመረው የሳኡዲ መጠን የለሽ ገንዘብ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።
አሁን ደግሞ የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ቤተ መንግስት ካስገቧቸው የግብፅ ባለስልጣናት እሳት እና ጭድ መሆናቸው ገሃድ ወጥቷል። ሁለቱም በየፊናቸው አንዱ ሌላው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚያስችሏቸውን ወይም የሚመስሉ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ገብተዋል። የመቀመሪያ መድረካቸውንም በዋናነት በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ ሀገሮች ውስጣዊ ፖለቲካ ላይ ያደረጉ ስለመሆናቸው ብዙዎች እየመሰከሩ ነው።
የሁለቱ ሃገራት ፖለቲካዊ ቁርሾ መነሻዎቹ፣ ሁለቱ ሀገሮች በዓረቡ ዓለም በሚገኙ የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት ፓርቲዎች ወይም ተዋጊዎች ላይ ያላቸው ፖለቲካዊ አረዳድ፤ በየመን እና በሶሪያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ አፈታት ዙሪያ፤ ኢራን በመካከለኛ ምስራቅ ፖለቲካዊ ውስጥ ያላትን ሚና እያደገ መምጣቱን የሚረዱበት መንገድ ለመሰረታዊ ልዩነታቸው በምክንያትነት ይቀመጣሉ። ዝርዝሩ ብዙና ጉዳያችን ስላልሆነ ትተነዋል። የዛሬው ጉዳያችን በመድረክነት በመረጡት የአፍሪካ ቀንድ አውራ መሆናችን እና የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ነው።
የግብፅ ፕሬዝደነት ጀነራል አል-ሲሲ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ከፕሬዝደነት ሳልቫኪር ጋር በካይሮ ከተማ መወያየታቸው የቁመራው መጀመሪያ መሆኑን ቀጠናውን እና አባይን የሚከታተሉ ጠበብቶች ይመሰክራሉ። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የዲፕሎማሲያዊ ውጤት መሆኑ ቢነገርና ይህም ለእውነት ያደላ ቢመስልም የሳዑዲ ዓረቢያ የልዑካን ቡድን የታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን መጎብኘቱን ከላይ ለተመለከተው የግብጽን ቁማር ለማክሸፍ ይልቁንም ግብጻውያን ለአባይ ካላቸው ምልከታ አኳያ ግብጽን ለማናወዝ የተደረገ ነው ሲሉ ልሂቃኑ ያሰምሩበታል።
የልሂቃኑን መደምደሚያ ትክክል የሚያስመስለው ደግሞ የሳኡዲ ልኡካንን ጉብኝት ተከትሎ አል-ሲሲ የተፋሰሱ አባል ሃገር ከሆነችው የዑጋንዳ ፕሬዚደነት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እና የቀንዱ አሸባሪ ከሆነው የሻቢያ አገዛዝ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታው ነው።
በእርግጥ የደቡብ ሱዳን እና የአስመራ መንግስታት አሁን ባለቸው መንግስታዊ ቁመና የጥፋት ተልኮን መሸከም በሚችሉበት ትከሻ የላቸውም። ግን ደግሞ በተፋሰሱ ሃገራት መካከል በሂደት ላይ ከሚገኙት የስምምነት ሰነዶች አኳያ ነገሩ ሲሰላ ችላ ሊሉት የማይገባ ቁማር መሆኑን ያመላክታል። ደቡብ ሱዳን ኔሽን ሆነ የመንግስት ግንባታ ሒደቱን ያልጨረሰ በጎሳ ፖለቲካ ተቸንክሮ የቀረ ነው።
ይህም በመሆኑ የግብፅን የጥፋት ተልዕኮ ፈፃሚ ለመሆን ቀርቶ፣ እንደሀገር ለመቀጠል ያላቸው ጊዜ በጣት የሚቆጠር መሆኑን አስታከው በጫወታው ስራ እንዳንፈታ የሚመክሩ ብዙ ናቸው። በተመሳሳይም የኢሳያስ አገዛዝም የግብፅን የጥፋት ተልዕኮ ለመሸከም ቢሞክርም፣ ውጤቱ ግን ከአገዛዙ ሕልውና ጋር የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስም የግብጽ አስተሳሰብ የት ጋር እንዳለና ተልእኮውን የሚሸከም አካል እስከተገኘ ድረስ ፍላጎቷ ምን እንደሚሆን ፍንጭ የሚሰጥ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ጨዋታ እንደሚያስፈልግ አለመጠራጠር ተገቢ ነው።
የዑጋንዳው ፕሬዚደነት ዮዌሪ ሙሴቬኒ በኢንቴቤ የተፈረመውን የናይል ውሃን በፍትሃዊነት የመጠቀም መርህን የሚዘሉ አይደለም። እንደውም ኢትዮጵያ በናይል ውሃ የመጠቀም መብቷ ሊጠበቅላት ይገባል ብለው በአደባባይ የሚናገሩ ናቸው። ዑጋንዳም ብትሆን 200 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ከቻይና መንግስት ጋር እየሰራች ነው የምትገኘው።
እነዚህ ባሉበት ሁኔታ የአል-ሲሲ ከላይ የተመለከቱ ሃገራት ጉብኝት ዓላማው ምንድን ነው? የሚለውን እና ከሁለትዮሹም ሆነ የሶስትዮሽ፤ እንዲሁም በጠቅላላው የተፋሰስ ሃገራት ዘንድ የመጨረሻ ሊሆን የሚችለውን የህግ ተቀባይነት ስለታላቁ ግድባችን መልስ መስጠት ያስፈልጋል። ግብጽንና አልሲሲንም ለይቶ ጉዳዩን በማስላት የዲፕሎማሲያዊ መርሃችንን አቅጣጫ ማጠየቅ የዚህ ተረክ መነሻ ነው።
መጀመሪያ ከአል ሲሲ እንነሳ እና ግብጽን እና ግብጻውያኑን ከታሪክና ህግ አኳያ እንመለከታለን። አል ሲሲ የመሐመድ ሙሪስን መንግስት በሃይል በማስወገድ በተወሰኑ የግብፅ ማሕበረሰብ ቅቡልነታቸውን ማረጋገጥ ችለው የነበሩ ቢሆንም፣ ግብፅ ባጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ማሕራዊ መሰረታቸው እየተሸረሸረ መጥቷል። በተለይ ከፍተኛ መጠን ያለው የግብፅ ሕዝብ በመንግስት ድጎማ የሚኖር በመሆኑ የኢኮኖሚ ቀውሱን ተከትሎ ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተጋልጧል።
አል ሲሲ የግብፅ ማክሮ ኢኮኖሚን ለማሻሻል ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም ከአይ.ኤም.ኤፍ. ጋር ድርድር አድርገው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፤ በተደረሰው የድርድር ስምምነት ግብፅ በሶስት ዓመታት ውስጥ 12 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአይ.ኤም.ኤፍ ታገኛለች። ዶላሩ ግን በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ደግሞ የአል ሲሲን ማሕበራዊ መሰረቶች መሸርሸር መጀመራቸው ነው አል-ሲሲ አስቀድሞ ወደተሸነፉበት ቁማር ውስጥ የገቡት ይላሉ ልሂቃኑ ።
የአይ.ኤም.ኤፍ. ቦርድ መግለጫ እንደሚያሳየው፣ ግብፅ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማስተካከያ ፕሮግራሞች ቀርጻ የምትቀርብ ይሆናል። በተለይ መስተካከል ያለባቸው የግብፅ ገንዘብ ከሚገባው በላይ የምንዛሪ መጠኑ መጨመር፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መከሰቱን፤ የበጀት ጉድለት፤ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር፤ የኢንቨሰትሮች በግብፅ ኢኮኖሚ አለመተማመን እና ሌሎችንም በሚቀርበው ማስተካከያ ላይ ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተለይም የውጭ ምንዛሪውን ሊብራል ማድረግ፤ የውጭ ምንዛሪውን መቀነስ፤ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን መጨመር፤ ጠንካራ ሞኒተሪ ፖሊሲ በማበጀት የዋጋ መናርን መቆጣጠር፤ ዓመታዊ የበጀት ጉድለትን መቀነስ፤ ቫትን ወደ ሥራ ማስገባት፤ የሃይል አቅርቦት ድጎማን መቀነስ፤ የደመወዝ አከፋፋል ስርዓቱን ማመጣጠን፤ ቁጠባን በመጨመር ድሃውን ሕዝብ ማገዝ፤ አስር በመቶ የመንግስት እዳን ለመቀነስ አቅዶ መስራትና የመሳሰሉት የሚታለፉ እንደማይሆኑ ይጠበቃል።
መዋቅራዊ ለውጥ የሚያስፈልገው እድገቱን ተከትሎ አዳዲስ ሥራዎችን እና ለግል ባለሃቶች አመቺ የሥራ ከባባዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፤ የንግድ ሥራ ፈቃድ አሰጣጥና ለማስተካከል፣ የሕዝብ ሃብቶች በመንግስት የተያዙ ድርጅቶችን በተገቢው ሁኔታ ለማስተዳደር፣ የሃይል አቅርቦት ዘርፍና ድጎማን ለማስተካከል ስለሆነ እነዘህ ዘርፎች መዋቅራዊ ለውጥ እንዲሰራባቸው የሚጠበቁ ናቸው።
እነዚህ ከላይ በቅድመ ሁኔታ የተቀመጡት ደግሞ ውስጡ ወታደር የሆነውን የአል-ሲሲ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ የሚከቱ ቅድመ ሁኔታዎች ስለመሆናቸው መገመት የማይከብድና በልሂቃኑ ምልከታ ለመስማማት የሚያስችሉ ምክንያቶች ናቸው። እንደ ልሂቃኑ ከላይ የተመለከቱት የአል-ሲሲ ጉምኝቶችም እነዚህን የግብፅ ሕዝብ ፍላጎት ማሟላት ያልቻለው እንደቀድሞዎቹ የግብፅ መሪዎች፣ ሕዝቡን በናይል ውሃ የብሔርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥ ለማጦዝ እየሰሩ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው።
በነገራችን ላይ እስካሁን ከነበሩት የግብፅ መንግስታት ጀነራል አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ በናይል ውሃ አጠቃቀም በጠረጴዛ ዙሪያ እንወያይ ያሉ እና ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የተወያዩና በመወያየት ላይ የሚገኙ ብቸኛ መሪ በመሆናቸው ልናደንቃቸው ይገባናል። ምንም እንኳን፣ ተስፋውም ያልተሟጠጠ ለመሆኑ በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የአል-ሲሲ አስተሳሰብ ለውስጥ የፖለቲካ መታገያ ያደረጉ በርካታ የግብፅ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን እና ስራችን አኳያ ልንዘነጋ አይገባም።
ቀጥለን የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የውሃ መፍትሄ ከአለም አቀፍ ህግጋትና ተሞክሮዎች አኳያ እንመልከት። ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰሶችን በማጥናት ለዘርፉ ዕድገት የሚበጅ ሐሳብ እንዲያቀርብና የሕግ ረቂቅ እንዲያዘጋጅ ከ46 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በታኅሳስ ወር 1970 የተደረገው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የጉባዔው የሕግ ክንፍ ለሆነው ዓለም አቀፍ የሕግ ኮሚሽን (አይኤልሲ) ስልጣኑን በውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 2669 በሙሉ ድምፅ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ የጉባዔው አባላት ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ባደረጉት ውይይት ከተነሱት ጉዳዮች እና ከላይ ለተመለከተው ውሳኔ ካበቋቸው ምክንያቶች መካከል የተወሰኑትን፣ ይልቁንም ድንበር ተሻጋሪ ከሆነው አባያችን ጋር የሚያያዙትን ነጥቦች እዚህ ጋር ማስታወስ ተገቢ ነው።
ከ300 በላይ ወንዞች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሐይቆችና የጉድጓድ ውኃዎች በሁለትና ከዚያ በላይ አገሮች የጋራ ባለቤትነት ሥር ናቸው፡፡ እነዚህ ተፋሰሶች ከመሬት ክፍል ውስጥ 45 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ፡፡ ከ40 በመቶ በላይ ከሚሆነው የዓለም ሕዝብ ሕይወት ጋርም በቀጥታ የተቆራኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ የማውጣት ተግባር ዘግይቷል ከሚባል በስተቀር አስፈላጊነቱ አጠራጣሪ አልነበረም፡፡ ስለሆነም በስቶኮልም፣ ማር ዴል ፕላታ፣ ደብሊን፣ ሪዮና ማራኬሽ ኮንፈረንሶች አማካይነት የተደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ተከትሎ እ.ኤ.አ. ግንቦት 21 ቀን 1997 የተመድ ዓለም አቀፍ የውኃ ኮንቬንሽን ፀድቋል፡፡
ይህ ውሳኔ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመጨረሻ ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰሶችን በአግባቡ ለመጠቀም፣ ለማልማት፣ ለመጠበቅ፣ ለማስተዳደርና ለመጠበቅ እንዲሁም ለአሁኑና ለቀጣዩ ትውልድ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ለማስቻል በአስቸኳይ የጋራ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ያገናዘበና እኛም በአባይ ወንዝ ላይ የምንከተለው መርሆ ቅጂ ወይም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሃገራችን ሁሌም እንደምትለው እና የማያወላውል አቋም አድርጋ ከያዘችው አንጻር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለ ትብብር ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰሶችን በአግባቡ ለመምራት፣ ለመጠበቅና በጋራ ለመጠቀም እንደማይችል ያረጋገጠ መሆኑን የሚያሳይ ስምምነት ነው፡፡
የግብጽን የተለያዩና የሚዋዥቁ አቋሞችን ጨምሮ ከላይ የተመለከቱ የአል-ሲሲ የፖለቲካ መቆመሪያ መድረኮች አዋጭነት ለማስላት በዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ የፍልስፍና ማዕቀፍ ውስጥ የትኞቹ መርሆዎች፤ የአብዛኛውን አገሮች ይሁንታ ካገኙት መርሆዎች አንጻር የሃገራችንን አቋም መመዘን ተገቢ ይሆናል።
አንድ ወንዝ በርካታ አገሮችን አቋርጦ ሊያልፍና የጋራ ንብረታቸው ሊሆን ይችላል፤ እያንዳንዱ አገርም በወንዙ ላይ ያለው ጥገኝነት፣ አስተዋጽኦና ጥቅም ይኖራል፡፡ ይሁንና እነዚህን ፍላጎቶችና ጥቅሞች ማስታረቅ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን ከላይ በተመለከተው አገባብ ዓለም አቀፍ ስምምነት አለ፡፡ አይኤልሲ በተሰጠው ስልጣንና በስልጣኑ አግባብ ያስቀመጣቸው ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን ለማስተዳደር፣ በጋራ ለመጠቀምና ለመከላከል የሚያስችሉት ድንጋጌዎች በስፋት ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡
ይህ ስምምነት የማዕቀፍ ስምምነት ነው፡፡ ምክንያቱም አገሮቹ በመደራደር፣ በመወያየትና በመስማማት ዝርዝር ጉዳዮችን በሌላ ስምምነት በመወሰን ከኮንቬንሽኑ ጋር አጣጥመው እንዲሄዱ ዕድሉን ይሰጣቸዋል፡፡ ስምምነቱ አምስቱን መሠረታዊ መርሆዎች ያስቀምጣል፡፡ በስምምነቱ ውስጥ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሀ አጠቃቀም ቅድሚያ የሚሰጠው መርህ ሲሆን የተቀሩት መሠረታዊ ጉዳት ያለማስከተል ግዴታ፣ የታቀዱ ዕርምጃዎችንና ፕሮጀክቶችን ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ማስታወቅ፣ አካባቢን መጠበቅና የግጭት አፈታት መርሆዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆዎች ደግሞ የኢትዮጵያም መርሆዎች በመሆናቸው በየትኛውም አይነት ፖለቲካዊም ይሁን ሌላ ውሳኔ አባያችንን ስጋት ውስጥ አይከተውም።
አባያችን እና ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ስጋት እንደሌለባቸው ግልጽ ለማድረግ የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ከላይ የተመለከተውን አለም አቀፍ ኮንቬንሽን በማጣቀስ የወሰናቸውን ሁለት ጉዳዮች ለአብነት እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ. በ1997 በሃንጋሪና በስሎቬኒያ መካከል የነበረው ክርክር ሲሆን፣ ሁለተኛው እ.ኤ.አ. በ2010 በአርጀንቲናና በኡራጓይ መካከል የነበረው ክርክር ነው፡፡
አይሲጄ እ.ኤ.አ. በመስከረም ወር 1997 ያየው የጋብሲኮቮ ናጋይማሮስ ጉዳይ ሃንጋሪና ስሎቫኪያ በዳኑብ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የፈጠሩትን አለመግባባት የተመለከተ ነበር፡፡ አይሲጄ ይህን ጉዳይ ያየው ስምምነቱ ከፀደቀ ከአራት ወራት በኋላ ሲሆን፣ በወቅቱ አንድም አገር ስምምነቱን አላፀደቀውም ነበር፡፡ ሃንጋሪና ስሎቫኪያም ፈራሚ አገሮች አልነበሩም፡፡ አይሲጄ እ.ኤ.አ በ2010 አርጀንቲናና ኡራጓይ በኦሮጎ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የነበራቸውን አለመግባባት ለመቅረፍ ስምምነቱ ላይ ተመሥርቷል፡፡
በተመሳሳይ አርጀንቲናም ሆነ ኡራጓይ የስምምነቱ አካል አልነበሩም፡፡ ስምምነቱ ካለው የልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ባህሪ ባሻገር አገሮቹ ልዩ ተጨባጭ ሁኔታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ማሻሻያ እያደረጉ እንዲጠቀሙበት ተመቻችቶ የተቀረፀ ነው፡፡
በእርግጥ በፍትሐዊና በምክንያታዊ አጠቃቀምና መሠረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ መርሆዎች መካከል ያለው ግንኙነት ባለፉት 200 ዓመታት ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግን የገጠመው መሠረታዊ አተካሮ ነው፡፡ የትኛው ይበልጥ ይጠቅማል? ለየትኛው ቅድሚያ ይሰጣል? የሚሉ ጥያቄዎች ያለማቋረጥ ይነሳሉ፡፡ እንግዲህ የኛ ጉዳይም የሚመጣው እዚህ ጋር ነው። ግብፅ በዋነኛነት የምትጠቅሰው መሠረታዊ ጉዳት ያለማስከተል ግዴታን ነው፡፡
ግብፃዊያን እየተጠቀሙ ያለው ውኃ ታሪካዊ መብት እንደሆነና ሌላ ማንም አገር ጣልቃ ሊገባበት እንደማይችል ያስባሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ መሠረታዊ ጉዳት ያስከትላል የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ሁሉ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ታስቀድማለች፡፡ ምክንያቱም ግብፅ የምትጠቀመውን መጠን ግምት ውስጥ ሳታስገባ ውኃው ላይ ድርሻ እንዲኖራት ስለሚያደርግ ነው፡፡
ስለዚህ እና ከላይ ከተመለከቱት ከአምስቱ የኮንቬንሽኑ ቅድሚያ ትኩረቶች አኳያ የኢትዮጵያ አቋም በመጀመሪያው ረድፍ ላይ መገኘቱ እና ዋነኛ ማእቀፍ መሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የግብጽ መሟገቻ ከማእቀፍ ውጭ ተያያዥ እና ይልቁንም ለሁለቱ ሃገራት ድርድር የተተወ መሆኑ አባያችን እና ግድባችን ስጋት አልባ ይሆናሉ ማለት ነው ።
ግብፅ ቅድሚያ የምትሰጠው ለመሠረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ቢሆንም የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (ሲኤፍኤ) ከተመድ ኮንቬንሽን የተወሰደ ነው ። ለፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ቅድሚያ የሚሰጥ፤ ይልቁንም ማእቀፉንም እዚሁ ላይ ያደረገ መሆኑ ነው ቁማሮቹ ሁሉ አስቀድመው የተበሉ ስለመሆናቸው ማጠየቂያ የሆነን።
የግብጽና ሱዳን የ1959 ስምምነት ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችን ያገለለ መሆኑ ሌላኛው የአባያችንን ስጋት አልባ መሆን ማጠየቂያ ነው፡፡ ሲጀምር ስምምነቱ ራሱ ሌላ የተፋሰሱ አገር የሌለ ይመስል ‹‹የናይል ውሃን በሙሉ ለመጠቀም›› የሚል ገለጻን ይዟል፡፡ ግብፅና ሱዳን ከውኃው ድርሻ የሚፈልግ ሌላ አገር ለእነሱ ማመልከቻ ማስገባት እንዳለበት ሁሉ በሰነዱ አስፍረዋል፡፡ ምን ያህል ውኃ ማግኘት እንዳለባቸው የመወሰን ሥልጣንንም ለራሳቸው ሰጥተዋል፡፡ ማመልከቻውንም ውድቅ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ወስነዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርሆዎችን ሁሉ የሚጥስ ስምምነት በማለት አንድ አገር ሊፈርም የሚችለው እጅግ መጥፎው ስምምነት እንደሆነ ሊሂቃኑ ይመሰክራሉ ፡፡ ፡፡
አሁን ሱዳን ከግብፅ ተፅዕኖ ተላቃ በነፃነት ውሳኔዎችን ማሳለፍ ጀምራለች፡፡ ይኼ ጤናማ ምልክት ነው፡፡ ይኼ ሱዳንን ብቻ ሳይሆን ግብፅንም የሚጠቅም ነው፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ በመሆን የተሳሳተ ውሳኔ መወሰን ብቻ ሳይሆን እንዲፈጸም ይወተውቱ እንዳልነበር፤ አሁን ሱዳን ትክክለኛ ውሳኔ መወሰን በመጀመሯ ግብፅም አንዳንድ ውሳኔዎች ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀምራለች፡፡ ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች በሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ተቀባይነት ካገኙ ሁለቱ አገሮች የሲኤፍኤው አፅዳቂ የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡
ሱዳን በሁለቱ አገሮች አጋርነት ደካማዋ ክፍል ሆና ነው የቆየችው፡፡ በ1959 ስምምነት መሠረት የሱዳን የውኃ ድርሻ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ቢሆንም፣ ሱዳን ግን ስትጠየቀም የቆየችው 12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ ነው፡፡ 6.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ወደ ግብፅ ይሻገር ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት የተቋቋመው ኮሚሽን በሱዳን ፕሮጀክቶች ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን፣ በግብፅ ግን የመከታተል ሥልጣን ብቻ ነው የተሰጠው፡፡
የውንዝ ስለዚህ ሱዳን በርካታ ጥቅሞቿን አሳልፋ በመስጠት ግብፅን የበላይ አድርጋ ብትቆይም አሁን ለራሷ ጥቅምና ፍላጎት መቆም መጀመሯ ከላይ ግብጽንም እያለሳለሳት መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ምልከታና ግምገማ ከላይ ለተመለከቱ የአል-ሲሲ ቁማሮች አስፈላጊ መሆኑን ማጤንና አለመዘንጋት ስለአባያችን እና ታላቁ ግድባችን ስጋት አልባ መሆን ተገቢ ይሆናል ፡፡