የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመገንባት ጉዳይ አገራዊ የጋራ ህልውናችንን የማስቀጠል አለማስቀጠል ጉዳይ እንጂ ምርጫ አይደለም የሚለው ፅኑ አቋም ዛሬም ድረስ ሊሰመርበት የሚገባ ነጥብ ነው።
ላለፉት 25 ዓመታት በዚህች አገር ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ስለመከፈቱ ካስመሰከርንባቸው እውነታዎች መካከል ቀዳሚ ሥፍራ ይይዛል። የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሲባል በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በኩል ያልተቆጠበ ጥረት የተደረገበት እልህ አስጨራሽ ሂደት ነበር ቢባል ተገቢ ይሆናል።
በዚህች አገር ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ልዩ ሥፍራ እንደሚሰጠው በርካታ የውጭ ታዛቢዎች ሳይቀር የመሰከሩለት የፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የደነገጋቸው ዓለም አቀፋዊ ደረጃቸውን የጠበቁ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አከባበር ድንጋጌዎች በየትኛውም መመዘኛ ቢለኩ እኛ ከምንለው ጋር የሚቃረን እውነታ መኖሩን አያመለክቱምና ነው፡፡
ይሁን እንጂ ግን ለዘመናት “ንጉስ አይከሰስ፤ ሰማይ አይታረስ” ከተሰኘው የገዥ መደቦች ኦሪታዊ ፈሊጥ በመነጨ የአፈና ሥርዓት ሥር ስትማቅቅ ለቆየችው አገራችን የ1983ቱ ታሪካዊ ድል ያመጣላትን ሥር ነቀል ለውጥና የለውጡ መገለጫዎች የሆኑትን ፈርጀ ብዙ ፋይዳዎችም ጭምር አምነው ላለመቀበል የተገዘቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ከትናንት እስከ ዛሬ የሙጥኝ ያሉት አቋም አሁንም ድረስ እያስገረመን ይገኛል፡፡
ይህን ስንል ደግሞ በተለይም አንዳንድ ፅንፈኝነት የተጠናወተውን አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከያኔው አንስተው አሁንም ድረስ ሲያነሱ የሚደመጡትን "የብሔራዊ መግባባት" ጥያቄ ጉዳይ እኛ እንደምንረዳው ከሆነ፤ ገና ድሮ ምላሽ አግኝቷልና ነው፡፡ እስቲ ይህን መከራከሪያችንን በምክንያታዊ ማብራሪያ አስደግፈን ለማስገንዘብ እንሞክርና ከዚያ ፍርዱን ለአንባቢያን እንተወዋለን፡፡
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ደጋግመው ስለሚያነሱት ጥያቄ የሚሰማንን መግለፅ እንዳለብን ያመንነው በተለይ አገራችን ኢትዮጵያ ለሁለተኛው አምስት ዓመት የትግበራ ዘመን የነደፈችውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጠቃላይ ይዘት በተመለከተ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አካላት ጭምር ገምግሞ አስተያየት እንዲሰጥበት ሲባል መንግሥት ላቀረበላቸው ግብዣ "መጀመሪያ መቅደም ያለበት "አገራዊ መግባባት የመፍጠር ጉዳይ ነው" በሚል ሰበብ ግብዣውን ሳይቀበሉት የቀሩ ጥቂት ፓርቲዎች መኖራቸው የቅርቡ ትውስታችን ነው።
እነዚሁ ኃይሎች በዚያን ወቅት ለአንዳንድ የግል ፕሬስ ሚዲያ ውጤቶች በሰጡት ምላሽ "በህዝብ ተመርጦ ሥልጣን ያልያዘ መንግሥት የነደፈውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንድንገመገም ስንጠራ ከሄድን እኮ ለኢሕአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ እውቅና መስጠት ይሆንብናል" ሲሉ መደመጣቸውን ጭምር ስንታዘብ እነሆ ዛሬ በዚህ ጽሁፍ አንዳንድ መሠረታዊ የመከራከሪያ ነጥቦችን እያነሳን እንመለከት ዘንድ ወደናል፡፡
እንግዲያውስ በእኛ እምነት እነዚህ ፅንፈኛ ፓርቲዎች የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካ ኃይሎች ዛሬ እንኳን ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ያቀረበላቸውን የአብረን እንስራ ግብዣ ተቀብለው የራሳቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ የማበርከት አዝማሚያ ከማሳየት ይልቅ የሰማነውን ኢ ምክንያታዊ መከራከሪያ የሙጥኝ ማለታቸው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ትዝብት ላይ ይጥላቸው እንደሁ እንጂ ሌላ ትርፍ አያስገኝም፡፡ በተለይም ደግሞ ኢሕአዴግን ሕዝብ ሳይመርጠው ሥልጣን የጨበጠ አምባገነናዊ አገዛዝ አድርጎ ለመፈረጅ መሞከር ትዝብት ላይ ከመጣል ያለፈ ኪሳራ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ለመገንዘብ ፖለቲከኛ መሆን አይጠይቅም፡፡
ምክንያቱም ኢሕአዴግ እልፍ አዕላፍ የትግሉ ሰማዕታት የወደቁለትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የመገንባት መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የሚታትረውን ያህል ተቃዋሚዎቹ የሚያሳዩት የነውጥ ናፋቂነት አዝማሚያ ባፈጠጠና ባገጠጠ መልኩ ገሃድ ወጥቷልና ነው፡፡
ስለዚህ እርስ በርስ ወደ መናቆር አደጋ ሊወሰድ የሚችለውን የሥልጣን ናፋቂ ኃይሎች ጭፍን ተቃውሞ መስማት የሰለቻቸው የአገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኢሕአዴግን እንደመረጡ ብቻም ሳይሆን ለምን እንደመረጡት ጭምር አሳምረው ያውቃሉ አለን፡፡
ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ከመጀመሪያው አምስት ዓመት በተሻለ መልኩ ተግብረን፤ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው የዓለማችን አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ለማድረግ ሲባል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም ጭምር ያሳተፈ የውይይት መድረክ ላይ እንዲገኙ በመንግሥት ሲጋበዙ የተለመደውን ተልካሻ ሰበብ አስባብ እንደ ቅድመ ሁኔታ በማቅረብ ግብዣውን ሳይቀበሉት ለቀሩ ቡድኖች ዛሬም ደግመው ደጋግመው ሊያውቁት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር እነርሱ ኢሕአዴግን በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ለመውቀስም፤ ለመክሰስም የሚያስችል የሞራል ብቃት እንደሌላቸው ነው፡፡
እንጂማ መላው የአገራችን ሕዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት ባስከፈላቸው የዘመናት ትግል የተቀዳጁትን የግንቦቱን ድል ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የመከፈቱን እውነታ አምኖ መቀበል "ለወያኔ ሥርዓት እውቅና እንደመስጠት የሚቆጠር ውርደት" መስሎ የሚሰማቸው ግብዝ ተቃዋሚዎች ደጋግመው ሲያመነዥጉት ከሚስተዋለው ጭፍን ተቃውሞ ወይም የጥላቻ ፖለቲካ ጋር መጋፈጥ ግድ ባልሆነ ነበር፡፡
በተለይም ደግሞ እነርሱ "ብሔራዊ እርቅ ማውረድ ያስፈልጋል" እያሉ ከትናንት እስከ ዛሬ ሥርዓቱን ለማጥላላት ሲሞክሩ የሚስተዋሉበት አግባብ ሲጤን ምን ያህል አስተዛዛቢና የማያቀባብርም ጭምር ሆኖ እንደሚገኝ መግለጹ ተገቢነት ይኖረዋል።
ምክንያቱም፤ ፅንፈኞቹ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት አመለካከትን የሚያቀነቅኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች አሁንም ድረስ በቀጠለ ኩርፊያቸው ምክንያት፤ ፈርጀ ብዙውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ፤ አሊያም ደግሞ ለማጓተት ያለመ ሴራ መዶለትን የመረጡት "አገራዊ መግባባት ሳይፈጠር ስለልማት ማሰብ አይቻልም" በሚል ሰበብ እንደሆነ ይታወቃልና ነው፡፡
ስለዚህም እነርሱ የሚጠይቁትን ዓይነት "ብሔራዊ እርቅ" አሊያም ደግሞ "አገራዊ መግባባት" ገዥው ፖርቲ ኢሕአዴግ ሳይወድ ተገዶ እንዲቀበል ለማድረግ ሲባል፤ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ መንግሥት የነደፋቸውን የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይሳኩ የማድረግ ዓላማ ይዘው ለመንቀሳቀስ እንደወሰኑ የሚያመላክት ድባብ ስለመኖሩ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
ከዚህ አኳያም ነው፤ ይበጃል የሚባለውን ቀና መንገድ ሊጠቆምና መስማት ቢፈቅዱ እውነቱን ሊነገራቸው ተፈልጎ ይህ ርዕሰ ጉዳይ መነሳቱ። ስለሆነም ዛሬም ድረስ የተለመደውን ሰንካላ ሰበብ አስባብ እንደምክንያት እያቀረቡ የኩርፊያ ፖለቲካቸውን የሙጥኝ ያሉት አንዳንድ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ቡድኖች አሁን እንኳን ወደ አዕምሯቸው ይመለሱ ዘንድ በአፅንኦት ልንገልጽላቸው እንሻለን፡፡
በተለይም እነርሱ መፈጠር አለበት እያሉ የሚናገሩለትን "አገራዊ መግባባት" ስንመለከተው ማንንም ሊያሳምን እንደማይችልና ከጥላቻ ፖለቲካቸው በሚመነጭ ግትር አቋም ለግብር ይውጣ የሚቀርብ ኢ ምክንያታዊ መከራከሪያ የመሆኑ ጉዳይ በፈጠጠና ባገጠጠ መልኩ ይገለጽልናል፡፡
ወጣም ወረደ ግን፤ የተቃውሞው ጐራ ጽንፈኛ ኃይሎችና ምዕራባውያን ኒዮ ሊበራል የእንጀራ አባቶቻቸው በተቀናጀ መልኩ የሚያቀነባብሩት ፀረ ኢሕአዴግ ሴራ ስላልተሳካ "በኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች መካከል እርቀ ሠላም ለማውረድ የሚያስችል አገራዊ መግባባት መፈጠር አለበት" የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ተራ ብልጣ ብልጥነት ስለመሆኑ ነው ልናሰምርበት የሚገባን፡፡
እንዴት ቢባልም ተሸናፊዎቹ ቡድኖች ሕገ መንግሥቱን እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንም ጭምር እንደማይቀበሉትና በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ታግለው ሊያስወግዱት እንደሚፈልጉ ደጋግመው ሲናገሩ መደመጣቸው አልበቃ ብሎ፤ የአመፅ ስትራቴጂያቸውን መሠረት አድርገው የአዲሲቷ ኢትዮጵያን ሕዝቦች እርስ በርስ ለማናቆር የማይፈነቅሉት የጥፋት ድንጋይ አለመኖሩን ልቦናቸው ሲያውቀው ጭራሽ በእነርሱ ብሶ አገራዊ የጋራ መግባባት ስለመፍጠር ጉዳይ እንድናስቀድም ሊያሳስቡን መሞከራቸው በእርግጥም የለየለት ብልጣ ብልጥነት እንጂ ሌላ ስም ሊገኝለት አይችልምና ነው።
በመጨረሻም ከትናንቱ ተሞክሯችን ተነስተን ዛሬ በኢሕአዴግ እና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውይይት በቀጣይም የሚደረገው ድርድርና ክርክር በሰለጠነና ጨዋ በሆነ መንገድ ፍጻሜ ያገኛል ብዬ አምናለሁ።