ባለፈው ሳምንት በመገናኛ ብዙሐን በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ስራዎች ላይ ያተኮረ፤ ለአምስት ቀናትም የዘለቀ ስልጠና በሁለት ተከታታይ ዙር ተካሂደዋል፡፡ በየመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አማካኝነት የተካሄደው ይሀው ስልጠና ያሉትንና የተስተዋሉትን ሰፊና መሰረታዊ ችግሮች ለመዳሰስ የሞከረ ነው፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ሚኒስትር ዲኤታ ዛዲግ አብርሀም በሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን፣ በመልካም አስተዳደርና በኒዮሊበራሊዝም ላይ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ዘነበ በየሰላም ጋዜጠኝነት እና ሌሎች ተያያዥ ርእሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው በየቡድኑ ሰፊ ወይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በስልጠና/ውይይቱ ሚዲያውም ሆነ የኮሙኒኬሽኑ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሙያዊ ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣቱ በሰፊው ተገልፇል፤ የሕዝቡን መሰረታዊ ጉዳዮችና የሚስተዋሉ ችግሮችን በአደባባይ አቅርቦ ለሕዝብና ለመንግስት በማሳወቅ ረገድ ሚዲያው ሰፊ ክፍተቶች ያሉበት ስለመሆኑም እንደዛው። የሕዝብ ግንኙነቱ ዘርፍ ሕግ ከሚፈቅደውና በአዋጅ ከተቀመጠው ውጪ ሕዝብ ማወቅ የሚገባውንና ለሕዝብ መድረስ ያለበትን መረጃ አንቆና ቆልፎ በመያዝ ለጋዜጠኛውም ሆነ በሕጋዊነት መረጃ ለሚጠይቀው ክፍል የሚከለክል መሆኑ በቡድን ውይይቶቹ ተነስቷል፡፡
እንዲያውም መስሪያ ቤቱን የሚመለከቱ መረጃዎች በጋዜጦች ታትመው ሲወጡ ደውለው ከማስፈራራትም በላይ ጋዜጠኞቹ በሕግ ይጠየቁልን እስከማለት ድረስ የሚሄዱ፤ የሕዝብ ግንኙነትን ስራና ሀላፊነት በቅጡ የማያውቁ የሹሞችና የኃላፊዎች ጋሻጃግሬ እስከመሆን ድረስ የሚራመዱ፤ መንግሰት የሰጣቸውን ኃላፊነትና አደራ በቅጡ ካለመረዳት ለሕዝብ ከመቆም ይልቅ ለኃላፊዎች የግል አገልጋይ አስኪመስሉ ድረስ ቆመው የሚሞግቱ ወዘተርፈ በሰፊው መታየታቸው የሙያውን ክብር ዘቅ ያደረገ፤ የተሰጣቸውን አደራ በአግባቡ የማይወጡ መሆናቸውንም ያረጋገጠ መሆኑ በሰፊው ተወስቶአል፡፡
ሕዝብ ግንኙነት ተቋሙንና ሕዝብን በድልድይነት የሚያገናኝ፣ መረጃዎቹንም ለሕዝብ እንዲደርሱ የሚያደርግ፣ በሕዝብና በተቋሙ መካከል አማኳይ ቦታን ይዞ የሚሰራ፣ በተቋሙ ውስጥም ያለው ስራ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲሰራ በሙያው አማካኝነት ሰፊ ድርሻና ኃላፊነትን የሚወጣ መሆኑ እየታወቀ በየተቋማቱ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በሕትመቶቹና በልሳኖቹ የመታገል፣ ለመንግስትና ለሕዝብም የማሳወቅ ሀላፊነት ያለበት ቢሆንም በየመጽሄቶቹ የሹሞችን ፎቶ እየለጠፈ ከማወደስና ከመቀደስ የዘለለ ስራ ለመስራት አልበቃም፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንንም ዋጋ አስከፍሏል።
ከፍተኛ ዋጋ ባላቸው ወረቀቶች የሚታተመው መጽሄት የሚጠበቀውን የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊነትና ግዴታ ለመወጣት እንዳልቻለ፤ በዚህም የመንግስትም ሆነ የሕዝብ ጥቅም እንደተጎዳ በውይይቱ ወቅት በስፋት ተነስቶአል፡፡ የኤሌክትሮኒክስም ሆነ የሕትመት ሚዲያው በበኩሉ ለሕዝብ ተደራሽ ከመሆን የሕዝብን ችግሮች፣ በደሎችና ብሶቶች በተጨባጭ በማሳየት ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትሕ ችግሮችን በመታገልና በማጋለጥ ረገድ የሚጠበቅበትን እንዳልሰራ በአድርባይነት ተውጦ እንደቆመም በስፋት ውይይት ተደርጎበታል፤ አይደገም ዘንድም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
መንግስት የቱንም ያህል በሚዲያውም ሆነ በሕዝብ ግንኙነቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ቢሰራም፣ ማንኛውንም የዘመኑ የቴክኒዮሎጂ መሳሪያዎች እንዲገቡ ቢያደርግም ለሕዝቡ ቅርብ የሆኑ፣ ስሜትና ሀሳቡን የሚገዙ ስራዎች ባለመሰራታቸው የሚዲያዎቹ ተሰሚነት፣ ተደማጭነት ተነባቢነት በሚፈለገው ደረጃ ሊሄድ አልቻለም፡፡
ሚዲያውንም ሆነ የሕዝብ ግንኙነቱን ዘርፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሪፎርም በማድረግ አሰራሩን መለወጥ የሚያስፈልግበት አስገዳጅ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ከተጨባጩ እውነታ በመነሳት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሚዲያውም ሆነ ሕዝብ ግንኙነቱ ሙያዊ በሆነ ብቃት ከተሰራባቸው ለሀገርና ለሕዝብ ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በሌላም በኩል ሚዲያውም ሆነ ሕዝብ ግንኙነቱ በተፈለገው መንገድ እንዳይሰሩ፣ ለሕዝብ ተደራሽ እንዳይሆኑ በየግዜው ማነቆ ሁነው የያዙዋቸው የተለያዩ በቢሮክራሲው ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሹሞች ሕዝቡ የሚፈልገውን ሳይሆን እነሱ የሚፈልጉትን ዜና ብቻ እንዲወጣ በማድረግ ሙያውንና የሕዝቡንም ስሜትና ፍላጎት ሲጫኑ እንደነበረ፤ ይህ ድብቅ ፍላጎትና አካሄድ ለመንግስትም ሆነ ለህዝብ ምንም የጠቀመው ነገር እንደሌለ እንዲያውም ችግሩን እያባባሰው እንደመጣ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም፣ ከዚህ ኋላ ቀር፣ ጎታች አካሄድ በመውጣት ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑ ስራዎችን ለመስራት ሚዲያውም ሆነ የሕዝብ ግንኙነቱ ከየሙያቸው አንጻር ትክክለኛና ተገቢ የሆነ ደርሻቸውን መወጣት ግዴታቸውም ሀላፊነታቸውም ነው፡፡
ለዚህ ነው የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ የሰላም የልማትና የዲሞክራሲ ስኬቶች ቢኖሩትም ጎልቶ የሚነገረው ስህተቶቹ መሆናቸውን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለመገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ፣ ግንኙነት ባለሙያዎችና አመራሮች ለአምስት ቀናት ሲሰጥ በቆየው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የገለጹት፡፡ ይህም በዋነኛነት የሕዝብ ግንኙነቱንና የሚዲያውን በተፈለገው መጠን ለሕዝብ ተደራሽ አለመሆን በግልጽ ያመላከተ ነው፡፡
በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ መንግስት ባለፉት ዓመታት በሰላም፣ በልማትና በዲሞክራሲ በርካታ ስኬቶች እንዳስመዘገበ ሁሉ በርካታ ስህተቶች መፈጸሙንም አምኖ በመቀበል ለማረም በስፋት ጥልቅ ተሀድሶ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ በተለይም በአመራሩ ያለው ችግር በመልካም አስተዳደር የታዩ ጉድለቶችን ዝርዝር በይፋ ለሕዝብ ማሳወቁን ጠቅሰዋል፡፡ መንግስት በተለይም በሙስናና በመልካም አስተዳደር ረገድ የታዩትን ስሕተቶች መፍትሄ መስጠት እንጂ ችግሩ እንዲቀጥል መፍቀድ የለበትም ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር ነገሪ መንግስት አመራር መለወጡ ሳይሆን ዓላማውን ለማሳካት ምን መስራት እንደሚፈልግና የት መድረስ እንዳለበት ለሕዝብ መግለጹን ነው ያመለከቱት፡፡ ይሁንና በመገናኛ ብዙኃን የሚለቀቀው አሉታዊ ዘገባ ሲበዛ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን መተማመን እንደሚቀንስና እንደሚሸረሽርም ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ያሉት እንዳለ ሆኖ የመንግስትን ጠንካራ ስራዎች በአግባቡ ለሕዝቡ የሚያቀርብ፣ ደካማ ጎኖቹን በትክክል በማስረጃ ለይቶ በተጨባጭ የሚያመለክት፣ የሕዝቡንም ስሜት በትክክል የሚያሳይ፣ የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄውም አካል የሆነ ጠንካራ ሚዲያ፤ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ስራና ሰራተኞች መኖር ግድ ይላል፡፡
ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ከአስር ዓመት በኋላ የሚመጣው አገር ተረካቢ ወጣት ምን ዓይነት አስተሳሰብ ሊይዝ እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን፤ በዘረኝነት፣ በሀይማኖት አክራሪነትና በሌሎችም ሴራዎች የተለወሰ፣ የተዛባና አሉታዊ መረጃ ለወጣቱ መስጠት ወደ ተሳሳተ አስተሳሰብና ተግባር ሊያመራ ስለሚችል ዛሬ የሚታዩ አሉታዊ መረጃዎች መናቅ የለባቸውም ሲሉ ጠንካራ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሚመሩት ፅ/ቤት በኩል የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን የአሰራር ለውጥ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በእውቀት የተመሰረተ መረጃ መስጠትና መቀበል እንደሚገባቸው፤ ትክክለኛ መረጃ በትክክል ለሕብረተሰቡ መድረስ ስለሚገባው መንግስት ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ጠንካራ አስራር መዘርጋቱ የግዴታ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መስሪያ ቤታቸው ከሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ሚዲያዎች ጋር አብሮ ወርዶ አሰራሩን በቀጣይነት በመፈተሽ ለማስተካከል ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ባይፈጠር በቅድሚያ የሚጎዳው ሕዝቡ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኢታ አቶ ዛዲግ አብርሃ በዚሁ ስልጠና ላይ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዛዲግ በጥናታዊ ጽሁፋቸው እንደገለጹት በሰላም፣ በልማትና በዲሞክራሲ ዙሪያ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መግባባት ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ሕገመንግስቱን በማጽደቅና በመተግበር አበረታች ለውጦችን ማስመዘገቡንም አስረድተዋል፡፡ እስካሁን በተካሄዱት ምርጫዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በነቂስ እየወጣ ያስተዳድረኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጡ በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባት መስፈኑን እንደሚያሳይ፤ ከሁሉም በላይ ሕዝቡ ሰላሙን በመጠበቅ ረገድ እያደረገ ያለው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት ግን ሁከትና ብጥብጥ አይፈጠርም ማለት አይደለም ያሉት አቶ ዛዲግ ባለፈው አመት በአገራችን አንዳንድ አከባቢዎች የተፈጠረው ሁከት የዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕዝብ መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ብልሹ አሰራርንና ሙስናን ያስወግድልን፤ መልካም አስተዳደር ያረጋግጥልን በሚል ያነሳው ጥያቄ በወቅቱና በአግባቡ ካልተመለሰ አደጋው እንደሚከፋ ጠቁመው በአገር ውስጥ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር ማሳያ ሞዴል ሊሆኑ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
በመልካም አስተዳደር ላይ ባተኮረው ጥናታቸው ላይ እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሀን በአገሪቱ መልካም አስተዳደር እንዲረጋጋጥ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙሐን ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሰው ለማውጣት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በራሳቸው መልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚጠበቅባቸው መሆኑን፤ በተለይም መገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማጋለጥ ሕብረተሰቡን በተገቢው መልክ ማወያያት እንደሚገባቸው፤ ስለመልካም አስተዳደር አስፈላጊውን ዘገባ በማቅረብ ተገቢውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ሚኒስትር ዲኤታ ዛዲግ አብርሀም ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሀን በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች በወጡት ፖሊሲዎች አሠራሮችና ደንቦች በተግባር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማሳየት ረገድ ተገቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸው፤ መንግሥት በመገናኛ ብዙሐን ውስጥ የሚስተዋሉ የደሞዝ ማነስ፤ የግብዓት እጥረቶች፣ የአቅምና ክሂሎት ክፍተቶችን ለመሙሏት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ፤ ባለሙያው በስነ-ምግባር የታነፀ በመሆን በመረጃ የተደገፈ የምርምራ ጋዜጠኝነትን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው ሚኒስትር ዲኤታው በአጽንኦት አስምረውበታል፡፡ ሰልጣኝ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሀላፊዎችና ባለሙያዎችም በዚሁ ተስማመተዋል። ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል ስንልም ይህንኑ ነው። ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል!!!