ለድርቅ ተጎጂዎች ፈጣን ምላሽ

 

                                                                                     

በአንድ ወገን ድርቅን በሌላው ጎን የልማት ስራዎችን በማቀናጀት እየተሰራ ያለው ስራ ለወጦችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ድርቁ በበረታባቸው አካባቢዎች የፌደራሉ መንግስት ከክልል መንግስታት ጋር በመቀናጀት ውሀ፣ ምግብና መድሀኒት በማድረስ ስራዎች ላይ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ የድርቅ ተጎጂዎች አስፈላጊው ሁሉ በመከፋፈል ላይ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገልፇል፡፡ ኮሚሽነር መኮንን ለሊሳ  በክልሉ የአርብቶ አደር ቆላማ አካባቢዎች የሚጠበቀው ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት በቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ሐረርጌና  ምዕራብ አርሲ ዞኖች በአጠቃላይ  2ሚሊዮን 49ሺ የሚደርሱ ሰዎች ለድርቅ መጋለጣቸውን ለመገናኛ ብዙሀን  ገልጸዋል፡፡  በደጋማና ወይና አደጋ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ በመዝነቡ አምና በክልሉ  ከነበረው 3.7ሚሊዮን የድርቅ ተረጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ ማስቻሉን፤ ለድርቅ በተጋለጡ ዘጠኝ ዞኖች ለተረጂዎች  የመጠጥ ውሀ፣ ምግብና የእንስሳት መኖ የማከፋፈል ሥራዎች መከናወናቸውን፤ ለእርዳታ ሥራ የሚውለውን 186ሚሊዮን ብር የክልሉ መንግሥት መመደቡን እና 97ሚሊዮን ብር የፌደራል መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን  ሀላፊው ተናግረዋል፡፡

በአርብቶ አደሩ አከባቢ ድርቁ ያስከተለውን የእንስሳት መኖ እጥረት  ለመፍታት  የክልሉ መንግሥት 57 ሚሊዮን ብር በማውጣት በሁለት ዙር የእንስሳት መኖን ከመሀል አገር በመግዛት የእንስሳት ሕይወትን ለመታደግ ጥረት መደረጉ ታውቆአል፡፡ በክልሉ በድርቅ የተጎዱ ዞኖች ያጋጠመውን የመጠጥ ውሀ ችግር ለመቅረፍ 166 የውሀ ቦቴዎች  በዘጠኝ ዞኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡   

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ድርቅ ለመቋቋም 948ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የገለጸ ሲሆን ኮሚሽኑ ከሕዳር 7/2009 ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ (በ246 ወረዳዎች) 23 ቡድኖችን በማሰማራት ባከናወነው የዳሰሳ ጥናት 5.6ሚሊየን ሕዝቦች ለድርቅ መጋለጣቸውንና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መለየቱን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ  መግለጻቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተገልፇል፡፡

ከጠቅላላው የድርቅ ተጋላጭ ቁጥር አንጻር በኦሮሚያ ክልል 36 በመቶ፣ በሶማሌ 29 በመቶ እንዲሁም በአማራ 11 በመቶ ያህል በዋናነት በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንደሚገኙና ለዚህም አስፈላጊው በጀት የተያዘ መሆኑ፤ ከተያዘው በጀትም 198ሚሊዮን ብር ለትምህርት ቤት ምገባ፣ እንዲሁም 118ሚሊዮን ብር ለእንስሳትና አሳ መድሐኒትና መኖ አቅርቦት እንደሚውል ታውቆአል፡፡ ቀደም ሲል በተደረገው የመኸር ጥናት ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑት ዜጎች ቁጥር ከ10.2ሚሊዮን ወደ 5.6 ሚሊዮን መቀነስ መቻሉንም አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡  መንግስት 16.5 ቢሊዮን ብር በመመደብ ለኤልኒኞ ድርቅ ለተጋለጡ ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ፣ ጤና፣ ትምህርትና ውሀ አቅርቦትን ተግባራትን በማከናወን በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ማቃለል ተችሎአል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬስና የድርጅቱ  የእርዳታ ዋና ኃላፊ ስቲፈን ኦብራይን የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ  የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ለሚወስደው እርምጃ ድጋፍ እንዲሠጥ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ለድርቅ  አፋጣኝ ምላሽ መሥጠት  አስፈላጊ  መሆኑን  የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኃላፊ ስቴፈን  አብራይን ገልጸው የኢትዮጵያ  መንግሥት  እ.ኤ.አ በ2017  ለሰብዓዊ እርዳታ  ያስፈልገኛል ብሎ ላቀረበው ድጋፍ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ  ምላሽ  እንዲሠጥ ጥሪ አቅርበዋል፤ በየትኛውም የአለም አካባቢ ለሚከሰት ድርቅ ምላሽ መስጠት በጎ ምግባር ብቻ ሳይሆን የአለምን ጥቅም የማስከበር ጉዳይ  መሆኑንም  ሰሞኑን በተካሄደው 28ኛው  የአፍሪካ  የመሪዎች  ጉባኤ ላይ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት  በኢትዮጵያ  የተከሰተው ድርቅ  በቆላማ የአርብቶ አደሩ አካባቢ በመሆኑ   ለተጎጂዎች እርዳታ በማድረስ  የድርቁን አደጋ መቀነስ  የሚቻል መሆኑን ኦብራይን ማስገንዘባቸውን ፋይናንሺያል ትሪቡን  ዘግቦታል፡፡

በአየር መዛባት ምክንያት እየተከሰተ ያለው ድርቅ ተደጋጋሚነቱና አስከፊነቱ ቀላል እንደማይባል አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ ጠቁመዋል። ሰላምና መረጋጋትን ለማስከበር በየአገራቱ የሚደረገው ጥረት ድርቅን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት  ተግባር መሆኑንም አስምረውበታል፡፡ ድርቅ የግጭትና ስደት መስፋፋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ያረጋገጠችውን ሰላምና መረጋጋት አስጠብቃ መቀጠል እንዳለባት፤ አገራት ድርቅን ለመከከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ ብቻ ሳይሆን ሰላም መረጋጋትና ዘላቂ ልማትን በማፋጠን ላይ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የግብርና ምርምር ማዕከላት የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን በምርምር በማውጣት ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል የገጠር ዘርፍ አሰተባባሪ አቶ ተፈራ ደርበው በግብርናና ገጠር ልማት ፖሊስና ስትራቴጂ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማመንጨት፣ በማላመድ፣ በማቅርብና በማሰራጭት በኩል ከሀገሪቱ ስነ-ምሕዳር ስፋትና ከአርሶ አደሩ ፍላጎት አንፃር ቀሪው ስራ የሚበልጥ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

ከምርምር ማዕከላት የወጡትን ምርጥ ዘሮች በመጠቀም ረገድ አርሶ አደሩ ሊተጋባቸው የሚገቡ ስራዎች መኖራቸውን እስከ 70 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎች በአማካኝ ከ30 ኩንታል አለመዝለላቸውንም በገለጻቸው ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሩ ልምድን መነሻ በማድረግ ተግባራዊ ያደረገው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የተራቆቱ አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ወደቀድሞው ስፍራ ከመመለሳቸውም ባሻገር ምርታማነቱን በማሳደግ ውጤት እያገኘበት መምጣቱን በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ ይህና ከላይ የጠቋቆምናቸው አበረታች ለውጦች እንዳሉ ሆነው፣ በአሁኑ ሰአት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍና እርዳታ ከመቸውም በላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።