የተፈጥሮ ጥበቃና ግብር ልማት

ሀገሪቱን ካለውና ለወደፊቱም ሊከሰት ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው ድርቅ ለመከላከል የሚያስችሉ ጠንካራ ስራዎች በመላው ሀገሪቱ በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶአደሮችን በማንቀሳቀስ የሚሰራው የአፈርና የውሀ ጥበቃ ስራ ከቀድሞዎቹ ግዜ የሚለየው በዘርፉ በሚገኙ ባለሙያዎች በእቅድና ጥናት የሚመራ መሆኑ ነው፡፡

አምና ድርቁ ተከስቶባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች በወቅቱ የዘነበውን ዝናብ በመጠቀም፣ ውሀ በማቆርና መሬቱ እርጥበት እንዲሰማው በማድረግ የተለያዩ አታክልትና እፅዋቶችን በመትከል ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆን ችሎአል፡፡ ሰፋፊ ጉድጓዶችን ቆፍሮ ውሀ በማቆርና ለመስኖ ልማት በመጠቀም ረገድም በበርካታ አካባቢዎች ቀላል የማይባሉ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡

የአፈር ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ/በማከም የተራቆቱ መሬቶችን በደን ለመሸፈን በተደረገው ጥረት በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሰሜን፣ በምእራብና በደቡብ እጅግ ከፍተኛ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ጠፍተው የነበሩ ተክሎች እንደገና ማቆጥቆጥና መለምለም ይዘዋል፡፡ ያገጠጡና ተራቁተው የነበሩ ተራሮች በደን በመሸፈናቸው ምክንያት ደርቀው የነበሩ የውሀ ምንጮች በየተራሮች ስር መፍለቅ የጀመሩ ሲሆን ጠፍተው የነበሩ ብርቅዮ የዱር አራዊቶች መመለስ ይዘዋል፡፡ እነዚህ ውጤቶች የሚነግሩንና እየሰጡን ያሉት ታላቅ ተስፋ ሀገሪትዋን እንደ ጥንቱ ሙሉ በሙሉ አረንጉዋዴ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ነው፡፡

ስራው የአመታት ድካምን ቢጠይቅም ከፍተኛ ውጤት እየታየበት ነው። በተለይ የአማራና የትግራይ አካባቢዎች ቀድሞ የተራቆቱ መሬቶቻቸው ዛሬ ላይ ወደአረንጓዴነት በመለወጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ስራ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ከመንግስት ጎን በመሆን የሚንቀሳቀሱት መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች የተጫወቱት ቁልፍ ሚና ሁነኛ ድርሻ አለው፡፡

በገጠር መንገዶችንና ትምህርት ቤቶችን የመስራት፣ የተሻሻሉና ድርቅን ለመመከት የሚችሉ የእጽዋት ዝርያዎች፣ ለምግብ የሚውሉ አትክልቶች ተተክለው እንዲለሙና ሕብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው በማድረግ፤ በየአመቱ ችግኞችን ለሕዝቡ በማሰራጨት በዘመቻ እንዲተከሉ በማድረግ ወዘተ በኩል ተጠቃሽ የሆኑ፤ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጁ ሰፊ የልማት ስራዎች ሰርተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚሳተፍበት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መጀመሩን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታውቆአል። የቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ትግበራ አስተባባሪ አቶ አረፈ ኪሮስ ለዋልታ እንደገለጹት በክልሉ በተፋሰሶች ላይ ለ20 ቀናት በሚካሄደው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በየቀኑ 1ሚሊዮን 434ሺህ 587 ሕዝብ እንደሚሳተፍ ይታመናል፡፡

በክልሉ በ100ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ የሚካሄድ መሆኑን፤ በክልሉ ከሚገኙትና በካርታ ተደግፈው የተለዩ 2ሺ 594 ተፋሰሶችን በጥራት ለማካሄድ ልዩ ክትትል እንደሚደረግ፤ ለዘመቻው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በማዘጋጀት ከ84ሺ 258 በላይ የልማት ቡድኖች መደራጀታቸውን ሀላፊው ገልጸዋል፡፡ የአፈርና ጥበቃ ስራው ሰብል ጨርሶ ባልተሰበሰበባቸው ከሰሜን ምዕራብና ምዕራብ ዞኖች በስተቀር በሁሉም የክልሉ ገጠር ወረዳዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አቶ አረፈ ኪሮስ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ በደቡባዊ ዞን ስራውን በይፋ ማስጀመራቸውም ታውቆአል፡፡  በሌላም በኩል በኦሮሚያ ክልል በ2008/9 የመኸር ወቅት በአጠቃላይ 164.6 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ አስታውቆአል፡፡

ባለፈው ዓመት የመኸር ወቅት በአጠቃላይ በክልሉ ከ5.9ሚሊዮን ሄክታር በሰብል ዘር ተሸፍኖ 133ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን፤ በዘንድሮ ዓመት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች በተግባር በመዋላቸውም የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡ በክልሉ አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኒዮሎጂዎችን እንዲጠቀሙ፤ የተሻሉ አሠራሮችን እንዲከተሉና ስራ ላይ እንዲውሉ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ መደረጉን የባለሙያ ድጋፍና ክትትል መኖሩ ለዘንድሮ ምርት ማደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ሀላፊው  ጠቁመዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የግብርና ምርቱን ይበልጥ ለማሳደግ  በክልሉ በሚገኙ 287 ወረዳዎች ከያዝነው ወር ጀምሮ ለሁለት ወራት የሚቆይ፣ 11 ሚሊዮን  ሕዝብን የሚያሳትፍ የተፋሰስ ልማት የዘመቻ  ንቅናቄ  እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሎአል፡፡

ግብርናውን ለማሳደግና ዘመናዊ ለማድረግ ሰፊ ጥረቶች በመንግስት በኩል እየተደረጉ ሲሆን  የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዘንድሮ የበጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 82 የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ምክረ ሀሳቦችን በማውጣት ለተጠቃሚዎች  ማሠራጨቱን  አስታውቆአል፡፡ በኢንስቲትዩቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ ዘገየ ለመገናኛ ብዙሀን እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ  70 የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ምክረ ሀሳቦችን ለተጠቃሚዎች  ለማቅረብ ታቅዶ  82 የሚደርሱትን ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ  አዳዲስ የሚወጡ  የግብርና ቴክኒዮሎጂና ምክረ ሀሳቦችን በተሻለ መልኩ  ተግባራዊ  ለማድረግ  በግማሽ ዓመቱ  21ሺ 709 አርሶና አርብቶ አደሮችን ለማሠልጠን  አቅዶ  23ሺ 920 የሚሆኑት በቴክኒዮሎጂ ማላመድ ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቆአል፡፡ በአገሪቱ  የጥጥ  ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን  ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ኢንስቲትዩቱ  ተባዮችን የሚቋቋም  ምርጥ  የጥጥ ዝርያን  ለማሠራጨት  በወረር፣ ተንዳሆ፣ አሳይታ፣ አሞቴ፣ ወይጦ፣ አሶሳና ፓዌ የሙከራ ሥራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡