መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በውስጣቸው የበቀለውንና የተንሰራፋውን ለመልካም አስተዳደር መጓደል፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት መደንደን ምክንያት የሆነ ደዌ ከውስጣቸው ለመንቀል የተሃድሶ እንቅስቃሴ ማካሄድ ከጀመሩ መንፈቅ ሆኗል። ይህ ህዝብን ያማረረ የመልካም አስተዳደር መጓደልና ኪራይ ሰብሳቢነት አብዛኛውን የአገሪቱን አካባቢ ያመሰ የህዝብ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑም ይታወቃል። እርግጥ ይህ የመልካም አስተዳደር መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት ደዌ አዲስ አይደለም። ከአስራ አምስት ዓመት በፊትም እንዲሁ ተከስቶ ነበር። ይህ በ1993 ዓ/ም በተካሄደ ተሃድሶ ተፈውሶ ነበር።
ይህ የ1993 ዓ/ም ተሃድሶ ያመጣው ፈውስ ብዙ ለውጥ አምጥቷል። አገሪቱ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት፣ በውጭ ግንኙነት . . . እመርታዊ ለውጥ እንድታሳይ ያደረጉት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ልማት፣ የውጭ ግንኙነትና ደህንነት ስትራቴጂዎች የወጡት በተሃድሶው ማግስት ነበር። ስትራቴጂዎቹ ይፋ እንደሆኑ በመላ አገሪቱ ስትራቴጂውን የማስረጽ ሰፊ የስልጠናና የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተዋል። በስትራቴጂዎቹ ላይ የተመሰረቱ የአምስት ዓመታት እቅዶችም ተነድፈው ተግባራዊ ተደርገዋል። ከ1998 እስከ 2002 ተግባራዊ የተደረገው ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት እቅድ፤ ከ2003 እስከ 2007 ተግባራዊ የተደረገው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ፤ እንዲሁም አሁን ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው 2ኛው የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና በእነዚህ እቅዶች የተመዘገበው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ እድገት የ1993ቱ ተሃድሶ ወጤቶች ናቸው።
ኢህአዴግ በ1993ቱ ተሃድሶ ውስጡ የተፈጠረውን ብልሽት ባያርም ኖሮ፤ ለራሱ ጠፍቶ አገሪቱም ለከፋ አደጋ ትጋለጥ እንደነበር እርግጥ ነው። ይህ የመጀመሪያው ተሃድሶ መለያ በተሃደሶው ማግስት በስትራቴጂና በእቅድ መልክ የፈለቁ ንድፈ ሃሳቦች ናቸው። ይህ ተሃድሶ ሁለንተናዊ እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ቢያስችልም በገዢው ፓርቲና በመንግስት ውስጥ ዳግም ክፉ ደዌ ተፈጥሯል። ፈጣኑን የኢኮኖሚ እድገት የሚገታ፣ የህዝብን እርካታ የሚቀንስ፣ ለእርስ በርስ ግጭት የሚዳርግ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የጠባብነት፣ የትምክህትና የሃይማኖት አክራሪነት በሽታ፤ እነዚህ የስርአቱ ደዌ መገለጫዎች የተለያዩ ቢመስሉም አንዱ ከአንዱ ተደጋጋፊዎች ናቸው።
ይህ በኢህአዴግና በመንግስት ውስጥ የተፈጠረ በሽታ ህዝቡን ክፉኛ ስላስመረረው አጋጣሚ ሲያገኝ ምሬቱ በቁጣነት ገንፍሎ ወጥቷል። ይህ ድንገት የገነፈለ ምሬት ደግሞ አገሪቱን ዳግም አገር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ ማፈራረስ ለሚፈልጉ ጠላቶች የትርምስ ስትራቴጂያቸውን የሚያስገቡበት ሰፊ ቀዳዳ ከፍቶላቸዋል። ባለፈው ዓመት አገሪቱ በሁከት ስትናጥ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠላቶችና በውጭ ለሚኖሩ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎቻቸው የድል ዋዜማ ነበር። አገር ቤት የሁኔታውን አደገኝነት የተረዱ ዜጎች በጭንቀት ሲዋጡ፣ ለአገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች ደግሞ የፈንጠዝያ ወቅት ሆኖ ነበር።
መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ዳግም ተሃድሶ ወይም በጥልቀት መታደስ ያስፈለጋቸው እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ነው። ዘንድሮ የተጀመረውን የዳግም ወይም ጥልቅ ተሃድሶ ከመጀመሪያው ተሃድሶ የሚለየው፤ የመጀመሪያው ገና ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲቆጣ በሚያደርግ መጠን ምሬት መፍጠር ደረጃ ያልደረሰ መሆኑ ነው። በመሆኑም ህዝብ ለተቃውሞ አደባባይ አልወጣም። ተሃድሶው እንዲያውም አገሪቱ የኤርትራ መንግስት የፈጸመውን ወረራ ቀልብሶ ዳግም የወረራ ስጋት እንደማይኖር ባረጋገጠበት ማግስት ስለነበረ እንዲያውም በወታደራዊው ደርግና ርዝራዦቹ ፕሮፓጋንዳ ህዝብ በስርአቱና በገዢው ፓርቲ ላይ የነበረውን ጥርጣሬ የሻረበትና የመቀራረብ መንገድ የተከፈተበት ነበር። የያኔው ብልሽት በአመዛኙ ህመሙ የተሰማው በድርጅቱ ውስጥ ነበር። የአሁኑ ግን ሞልቶ ፈሶ ህዝብን አሳምሞ እንዲቆጣ አድርጓል።
እናም፤ የዳግም ወይም የጥልቀት ተሃድሶው ጉዳይ ፋታ የሚሰጥ አይደለም። አንድ ዓመት እንኳን ፋታ አይሰጥም። ተሃድሶውን አካሂዶ መፈወስ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የስርአቱ መቀጠል ወይም አለመቀጠል ጥያቄ ነው።
እንግዲህ ዳግም ተሃድሶው መንፈቅ አስቆጥሯል። ህዝብ አሁን ተሃድሶ ላካሂድ ነው ወይም እያካሄድኩ ነው የሚል ተስፋ ሳይሆን ተጨባጭ ለውጥ ማየት የሚፈልግበት ሁኔታ ላይ ይገኛል። በኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ ባለስልጣኖችና ሰራተኞች እርምጃ የተወሰደባቸው ስለመሆኑ፣ በኪራይ ሰብሳቢነትና በአቅም ማነስ የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች ስለሚጠናቀቁበት ሁኔታ፣ ምንም ሳይንገላታ የመንግስት አገልግሎት ማግኘት ስለመቻሉ፣ ፍርድ ቤት ለባለወገንና ባለገንዘብ የማይፈርድ ስለመሆኑ ወዘተ. እየጠየቀ ይገኛል።
በቅርቡ በኦሮሚያ ሃያ ዞኖችና አስር የከተማ አስተዳደሮች የተካሄደው የተሃድሶው ማጠቃለያ ህዝባዊ ውይይት ይህን በተጨባጭ አሳይቷል። በእነዚህ የኦሮሚያ የህዝባዊ ውይይት መድረኮች ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። ውይይቶቹ በክልሉና በፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች የተመራ ነበር። የህዝባዊ ውይይቱ ዓላማ የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን ጥያቄ በመመለስ ረገድ ምን ያህል ስራዎችን በቁርጠኝነት እንዳከናወነና ህዝቡም የስርዓቱ ባለቤት በመሆን ያደረገው አስተዋፅኦ ምን ያህል እንደሆነ መፈተሽ ነበር።
ክልሉ ባካሄደው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ፈጣን አገልግሎት አለመስጠት፣ የፕሮጀክት መጓተት፣ በተሟላ ሁኔታ የልማት ስራዎችን አለማከናወን ወዘተ በችግርነት ለይቶ ነበር። የተሃድሶ ማጠቃለያ ህዝባዊ ውይይቱም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። በኦረሚያ ቴሌቪዠን የቀረቡትን በተለያየ ዞንና ከተሞች የተካሄዱትን ውይይቶች እንደተከታተልኩት፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በሁሉም ዞኖች የተነሳው የልማት ጥያቄና የፕሮጀክቶችን መጓተት የተመለከተ ነበር። እርግጥ በተለይ በምስራቅ ሐረርጌ፣ በባሌና በቦረና ዞኖች የተካሄዱት ውይይቶች ላይ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በወሰን ይገባኛል ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ተነስቶባቸዋል።
የውሃ፣ የኤሌትሪክና የቴሌፎን አገልግሎት አለመኖርና መቆራረጥ ችግር፣ የመንገድ ይግባልን፣ መንገዳችን ከጠጠር ወደአስፓልት ይሻሻልልን፣ ለወጣቶች በተለይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመረቀው በየቤታቸው ለተቀመጡ ወጣቶች የስራ እድል ይፈጠር፣ ወዘተ. በህዝቡ ሲነሱ የነበሩ ዋነኛ ጥያቄዎች ነበሩ። በውይይት መድረኮቹ ላይ ጥያቄያችንን መመለስ ካልቻላችሁ ከወንበራችሁ ተነሱ! የሚሉ ማሳሰቢያዎችም ተሰጥተዋል። ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ የተነሳው ጥያቄ ብዙም ባይሆንም ሲያማረሩን የነበሩ አመራሮች አሁንም አሉ የሚሉና እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቁ ሃሳቦች ቀርበዋል። ሌላው በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ካለው የወሰን አለመግባባት ጋር ተያይዞ በአካባቢያችን ሚዳቆ፣ ከርከሮ መግደል የተከለከለ ቢሆንም አሁን ግን ሰዎች በገፍ እየሞቱ ነው፣ መንግስት ይህን ማስቆም አለበት፣ ይህን ማስቆም ካልቻለ ምንድነው የሚጠቅመን? የሚሉ አስተያየቶችም ተደምጠዋል። መንግስት ያከናወናቸውን በጎ ተግባሮች፣ የተገኙትን ወጤቶች እያነሱ አድናቆታቸውን የገለጹና ያመሰገኑ ድምጾችም ተሰምተዋል።
በአጠቃላይ በኦሮሚያ የተካሄደው የተሃድሶ ህዝባዊ ውይይት መንግስት በህዝቡ ዘንድ እርካታ ለመፍጠር ምን ተግባሮች እንዳከናወነ፣ ምን እንደቀረውና ህዝቡ ተሃድሶውን በምን ያህል ደረጃ በሃላፊነት እየመራው እነደሆነ በትክክል አሳይቷል። ህዝባዊ ውይይቱ በተለይ ከልማት ስራዎች ጋር እንዲሁም ከተጓተቱ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ጋር በተያያዘ ህዝብ አንስቶት የነበረው ጥያቄ በቂ ምላሽ አለማግኘቱንና ህዝቡ አሁንም ቅሬታ ውስጥ መሆኑን ያመላከተ ነበር። ሌሎች ክልሎችም ሊማሩበት የሚችሉበት ውይይት ሆኖ አግኝቼዋሁ። በሁሉም ክልሎች የእስከዛሬውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ ሂደትና የህዝቡን ሰሜት ለመረዳት ተመሳሳይ ውይይቶች መካሄድ አለባቸው።
ያም ሆነ ይህ፤ ኦሮሚያም ሆነ ሌሎች ክልሎች በተሃድሶው እንቅስቃሴ የሚቀሯቸው በርካታ ተግባራት ቢኖሩም፣ በእስከአሁኑ ሂደትም የእርምት እርምዎች ተወስደዋል። ተጨባጭ ውጤቶችም ተገኝተዋል። በዚህ ረገድ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል የኦሮሚያንና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስታትን እንመልከት።
በኦሮሚያ ክልል በመጀመሪያው ዙር በተደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ችግር የተገኘባቸው 4 ሺህ 460 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፤ እንዲሁም ከ13 ሺሀ 5 መቶ በላይ ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት ውስጥ ይመሩ በነበሩ ዝቅተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል። አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ ከተወሰደባቸው አመራሮች በተጨማሪ 694 አመራሮች በብልሹ አሰራር ተገምግመው በ260ዎቹ ላይ ክስ ተመስርቷል። በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ ማጣራት እየተደረገ ይገኛል። አመራሮቹ ጉዳያቸው ተጣርቶ ክስ እስኪመሰረትባቸው ድረስ የክልሉ የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተለያዩ የንብረት እና የገንዘብ እገዳ መጣሉንም የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል። በዚህም ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ፣ አራት ተሸከርካሪዎች፣ ሁለት ህንጻዎችና 40 መኖሪያ ቤቶች ታግደዋል። እንዲሁም 244 ሺህ 326 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት እና በደን የተሸፈነ 548 ሺህ 662 ካሬ ሜትር መሬት ታግዷል።
በመላው ኦሮሚያ በተካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ መድረክ ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። በክልሉ በተካሄደው የመንግስት መዋቅርን መልሶ የማደራጀት ሂደት 5 ሺህ 832 ምሁራን ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ባለው እርከን ወደ ኃላፊነት መምጣታቸውንም የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮው አስታውቋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተካሄደ የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ 20 ሺህ 173 ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ የክልሉ ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል። በሁሉም ደረጃ የሚገኙ 496 ሺህ 311 አመራሮች በተሃድሶ ሂደቱ እንዲያልፉ ተደርጎ 1ሺ 920 ከፍተኛ አመራሮችና 18 ሺህ 253 መካከለኛ አመራሮች ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ያብራሩት፤
የኦሮሚያና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስታትን ለአብነት አነሳሁ እንጂ፤ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በሌሎች ክለሎች ተመሳሳይ እርምጃዎች ተወስዷል።
እንግዲህ ከፍተኛ አመራሮችና መካከለኛ አመራሮችን ከሃላፊነት ማንሳት፣ ምሁራንን ወደሃላፊነት ማምጣት፣ ከሃላፊነት የተነሱና አዲስ የተመደቡ ምሁራን ቁጥር መበራከት የዳግም ወይም የጥልቀት ተሃድሶው ሂደት ዋና ግብ አይደለም። ዋናው ጉዳይ በህዝቡና በአጠቃላይ በገዢው ፓርቲ አባላትና አመራሮች ዘንድ፣ በመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በባለሞያዎች ዘንድ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ነው። የመንግስት ሃላፊነትና ስራ መድረሻ ራስን መጥቀም ሳይሆን ህዝብን ማገልገል መሆኑ ባህል ሊሆን ይገባል። የተጓተቱትን የልማት ስራዎች በፍጥነት በማስቀጠል፣ አዳዲስ የልማት ሰራዎችን በማስጀመር በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ማድረግ የሚያስችል አዲስ የስትራቴጂ ሃሳብ ማመንጨት ይሻል። የህዝቡን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋጋር የተቀረጹ ስትራቴጂዎችንና እቅዶችን የማስፈጸም ቁርጠኝነት ይሻል። የተሃድሶው ግብ እነዚህ ናቸው። ተሃድሶውን ዘላቂ የሚያደርጉትም እነዚህ ናቸው። ተሃድሶው ዘላቂና በህዝብ ዘንድ መተማመንን የሚፈጠረው በመንግስት አገልግሎት ምንነት ላይ የአመለካካት ለውጥ ሲፈጠር፣ የማስፈጸም ቁርጠኝነት ሲጠነክር፣ ህዝብን ያማረሩ ችግሮችን በፍጥነት መፍታት የሚያስችሉ ሃሳቦች ሲመነጩ ነው።