በመስኖ ከሚያለሙት ማሳ ከፍተኛ ምርት እያገኙ ቢሆንም የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው የልፋታቸውን ዋጋ ሊያገኙ እንዳልቻሉ በጉራጌ ዞን የሚገኙ የመስቃን ወረዳ አርሶ አደሮች መናገራቸውን ከሰሞኑ ሰምተናል፡፡ ባለፉት አራት አመታት አብዛኛው አርሶአደር በነፍስ ወከፍ በዓመት እስከ 150ሺህ ብር ትርፍ ማግኘት የቻለ ቢሆንም የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ምክንያት አብዛኛውን ምርት በአነስተኛ ዋጋ ለመሸጥ መገደዱን በምሬት ሲገልጽ ጭምር ነው የሰማነው፡፡ በተለይ ዘንድሮ ያለሙት የቲማቲም ምርት ፈጥኖ የደረሰ ቢሆንም በውርጩ ምክንያት ዋጋ ከሚያጡ በርካሽ ለመሸጥ መገደዳቸው ተጠቃሽ ነው፡፡
እነዚህ አርሶ አደሮች ደግሞ ዋና ችግራቸው ብቻቸውን መፍጨርጨራቸው ነው። በዚያው በመስቃን ወረዳ በጋራ ሆነው ቢያለሙ የተሻለ አቅም መፍጠር እንደሚያስችላቸው በማመን 20 ሆነው የተደራጁ አርሶ አደሮች 8 ሄክታር ማሳ ላይ ቲማቲም፣ ቃሪያና ፎሶሊያ በማልማት ላይ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ያለውን አቅም በአንድ ላይ አሰባስቦ ማልማት የተሻለ ጥቅም እንደሚያስገኝ በማመናቸው በጋራ የመስኖ ልማቱን ጀመሩት፤ ተሳካላቸውም፡፡ ቲማቲም በሄክታር እስከ አራት መቶ ኩንታል፤ ቃሪያ ከግማሽ ሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት ማግኘት ቻሉ። ይሁን እንጂ፣ ላመረቱት ምርት አመቺ የገበያ ስርዓት ባለመዘርጋቱ ምርቱን በተሻለ ዋጋ ሸጠው መጠቀም አልቻሉም፡፡ ይህ እንግዲህ ከራሳቸው የሰማነው መሪር ዜና ነው።
አሁን የሁለቱም ችግር ግልጽ ይመስላል። በህብረት ስራ ማህበራት የመታቀፍ ችግር። የገበያ ትስስርን ለመፍጠርም ሆነ ከዋጋ መዋዠቅ ለመዳን ብቸኛ መፍትሄዎች ጠንካራ የህብረት ስራ ማህበራት ናቸው።
አራተኛው አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ዓውደ ርዕይ "የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግብይት ለዘላቂ ልማታችን ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ ከየካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለ8 ተከታታይ ቀናት በኤግዚቢሽን ማዕከል ለእይታ ክፍት በሆነበት አጋጣሚ የተመለከትነው ለመስቃን ወረዳ አርሶ አደሮች ችግር ሆኖ የኖረውን የገበያ ትስስር ነው።
በአገሪቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠናከርና ለማደራጀት በተደረገው እንቅስቃሴ ከ79ሺህ በላይ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከመፈጠራቸው አንፃር ስንመለከተው የገበያ ትስስር ለመስቃን ወረዳ አርሶአደሮች ችግር ሊሆን ባልተገባ ነበር። ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ የሚያሳየው ከ15 ሚሊዮን በላይ አባላትን ማፍራት የቻሉ የህብረት ስራ ማህበራት በአመት ሁለትና ሶስቴ የገበያ ምርቶችን ለሚያመርቱ አርሶአደሮች ፍቱን መድሃኒት ሆነዋል፤ ገበያ ከማፈላለግድረስ ያለውን ክፍተት በመሙላት።
እነዚህ ማኅበራት በአጠቃላይ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን 370 የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዮኒየኖችም በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራጅተዋል። እናም የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን በዓውደ ርዕዮች እንዲያስተዋውቁ በማድረግ የገበያ ትስስር እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ከሰሞኑ በሚገባ ለመገንዘብ ችለናል። ዓውደ ርዕዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ያላቸውን ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ለማስተዋወቅ የሚረዳ ነው። ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የኅብረት ሥራ ማህበራት በዓውደ ርዕዩ መሳተፋቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና ተሞክሮን እንዲቀስሙም ትልቅ ዕድልን ይፈጥርላቸዋል። ምርትና አገልግሎታቸውን ለሸማቹ ኅብረተሰብ ከማቅረብ ባለፈ ከሌሎች አምራቾች ጋርም የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላቸዋል። ሸማቹም የሚቀርቡለትን ምርትና አገልግሎቶች ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ ይሆናል።
የማህበራቱ ፋይዳ ይህ ብቻ አይደለም። የኅብረት ሥራ ማኅበራት አርሶና አርብቶ አደሩን በገበያ በማስተሳሰርና ተጠቃሚ በማድረግም ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው። መንግስት ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ለቀረጻቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተግባራዊነትና ለተመዘገበውም ፈጣን ዕድገት በተመሳሳይ ።
ማህበራቱ ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚ እንዲገነባና የአርሶና የአርብቶአደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ግብአቶችን፣ ምርጥ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በተቀላጠፈና በጥራት በማቅረብ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
ባለፉት ዓመታት ለተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት የኅብረት ሥራ ማኅበራት አርሶና አርብቶ አደሩን በገበያ በማስተሳሰርና ተጠቃሚ በማድረግ የላቀ ሚና እንደነበራቸው ከኤጀንሲው የወጡና በኤግዝቢሽኑ ላይ የተሰራጩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተመሳሳይም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና በዘላቂነት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ አቅም ለመገንባት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ፋይዳ ከፍተኛ ነው። የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖርና ተወዳዳሪ የወጪ ንግድ ለመገንባት ማህበራቱ በግብርና ምርቶች እሴት ጭማሪ ላይ መሳተፍ ያስፈልጋቸዋል። ገበያ ተኮር የአመራረት ስርዓት በመከተል የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪውን በመመገብ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው የኢኮኖሚ ሽግግር ማህበራቱ በግብይት ስርዓቱ ላይ የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ አያጠያይቅም ። በመሆኑም ከውጭ የሚገቡ ልዩ ልዩ ምርቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን የማስቀረት ስትራቴጂና ዘመናዊ የግብርና ግብይት ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን በአግሮ ፕሮሰሲንግ የሚሰማሩ የኅብረት ሥራ ማህበራትን ቁጥር ማሳደግ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል። ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬሙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አብረዋቸው ከሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከግብርና ግብዓት፣ ከማምረቻና የፍጆታ ዕቃ አቅራቢዎችና ከፋይናንስ አገልግሎት ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ስለዚህ ነው።
የዘርፉ ተመራማሪዎችም ሆኑ ለሙያው ቅርበት ያላቸው እንደሚሉት፣ ለሕብረት ሥራ ማህበራት ስኬታማነት ውጤታማ የሆነ አመራር ወሳኝ ነው። የሕብረት ሥራ ማህበራት ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በውጤታማ አመራር ማገዝ ሊታገዙ የግድ ነው፡፡ ማህበራቱ በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በውጤታማነት ራሳቸውን በመፈተሽ ሀገሪቱ በምታደርገው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ሂደት ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል የሚችሉት ውጤታማ በሆነ አመራር ሲታገዙ ብቻ ነው፡፡
የሀገሪቱን የግብይት ሥርዓት በማዘመን የሸማቹንና የአምራቹን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድም የሕብረት ሥራ ማህበራት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦዋቸውን ታሳቢ ባደረገ አመራር ሊመሩ ይገባል ፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ብቻ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በሕብረት ሥራ ማህበራት ግብይት መካሄድ መቻሉ ዘርፉ በአበረታች የዕድገት ጎዳና ላይ ለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ ዘርፉ በሀገሪቱ ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሕብረት ሥራ ማህበራትን ቁጥር ከመጨመር ይልቅ ጥራት ላይ ያተኮረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም በኤግዝቢሽኑ ላይ ይፋ የሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትም በርካታ ሴቶችና ወጣቶች በ79ሺህ መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራት፣ በ373 የሕብረት ሥራ ዩኒየንና በ4 የሕብረት ሥራ ፌዴሬሽን ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው። ማህበራቱና ዩኔዮኖቹ በሀገሪቱ 15 ነጥብ 4 ሚሊየን አባላትን የያዙ ሲሆን፤ ከ17 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታልም አፍርተዋል ፡፡
ከዚህ፣ ከላይ ከዘረዘርናቸው ተሞክሮዎች በመነሳት፤ የመስቃን ወረዳ አርሶአደሮችም የዚህ ተቋዳሽ በመሆን የገበያ ትስስር የተባለ ችግር ማንሳት የማይችሉበትን እድል የዞኑ አመራር ሊፈጥርላቸው ይገባል።