የውጭ ምንዛሪን ግኝት ለማሳደግ…!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች፤ በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጋጥሟታል የሚል ወሬ ይሰማል። እርግጥ ነው፤ የውጭ ምንዛሪ እንደልብ የሚዛቅበት ሁኔታ የለም። ይሁን እንጂ፤ አገሪቱ የሚስፈለጓትን ወሳኝ ጉዳዮች መሸፈን የሚያስችል ያህል ምንዛሬ አልታጣም። በከፍተኛ መጠን በውጭ ምንዛሪ ላይ ጥገኛ የሆኑ ሜጋ ፕሮጀከቶችን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን፤ ማዳበሪያ፤ ነዳጅ፤ መድሃኒት፤ የመሳሰሉ የፍጆታ ምርቶችን ለማስገባት የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለመኖሩ የሚያመለክት አንዳችም የጎላ ችግር የለም። ያም ሆነ ይህ፤ ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ የምትገኝ በመሆኗ፤ እንዲሁም ኢኮኖሚውን ወደኢንዱስትሪ ለማሸጋጋር እቅድ እየጣረች ያለች አገር በመሆኗ ያለማቋረጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋታል። በዚህ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውጥረት ሁሌም ይኖራል። በተለይ የሃገሪቱ የወጪ ንግድ በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተያዘለት ልክ መሳካት አለመቻሉ የእጥረቱ ውጥረት ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገት ማሳየቱ ግን በወጪ ንግድ የተፈጠረውን የምንዛሪ እጥረት የሚደግፍበት ሁኔታ ይስተዋለል።

በዚህ ላይ ያለውን እውነታ ለመረዳት የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የወጪ ንግድ ክንውን፤ እንዲሁም የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና እስካሁን ያለውን አፈጻጻም እንመልከት፤-

የመጀመሪያው የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመን ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከወጪ ምርቶች የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ፣ ሀገሪቱ ለገቢ ምርቶች የሚያስፈልጋትን ወጪ በውጭ ምንዛሬ የመሸፈን አቅም ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል። የወጪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ ድጋፎች ተደርገዋል። ታዲያ፤ የወጪ ንግድ ገቢ በዕቅዱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትግበራ ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ እንዲያሳይ ማድረግ ተችሎ ነበር። ሆኖም ከ2005 ዓ/ም በኋላ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ዘርፍ አፈፃፀም ቀደም ሲል እንደነበረው መቀጠል አልቻለም። ከወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገት ሳያሳይ የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ የትግበራ ዘመን እስካበቃበት 2007 በጀት ዓመት ድረስ ቀጥሏል። በመሆኑም  በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተቀመጠውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ግብ ማሳካት ሳይቻል ቀርቷል።

በዚህ ዘርፍ ለታየው ደካማ አፈፃፀም አንዱ ምክንያት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ መቀነስ መሆኑ የእቅዱ የአፈጻጻም ሪፖርት ላይ ተገልጿል። ዋነኛው ምክንያት ግን አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች በዓይነት፣ በብዛት እና በጥራት የሚፈለገውን ደረጃ አለማሟላታቸው መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል። የግብርና ምርታማነት እያደገ ቢመጣም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ነበር። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሠማራት ያለው ፍላጎት እያደገ ቢሂድም፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በማጠናከር የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶችን ወይም አዳዲስ ምርቶችን በዓይነትና በብዛት በማምረት በስፋት ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ሳይቻል ቀርቷል። በመሆኑም በቀጣይ ዓመታት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የኤክስፖርት ሸቀጦችን አቅርቦት በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት ማሻሻልና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ትርጉም ባለው ሁኔታ ማሳደግ በላቀ ትኩረት ርብርብ የሚደረግበት ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ሪፖርቱ አሳስቧል።

በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የወጪ ንግድን ገቢ በየዓመቱ በአማካይ በ29 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ያመለከታል። በ2012 ዓ/ም የዕቅድ ዘመኑ ሲጠናቀቅ የወጪ ንግድ ገቢን 14 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማድረስ ታቅዷል። ከጠቅላላው የወጪ ንግድ የግብርና ምርቶች 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ ማዕድን ደግሞ የ2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድርሻ እንዲኖራቸው ነው የታቀደው፤

የማምረቻ ኢንዱስትሪ ምርቶች በወጪ ንግዱ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖራቸው የማስቻል እቅድ ተይዟል። በተለይም፤ ከቆዳ ጫማና ከሌሎች የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውጤቶች እንዲሁም የስኳር ምርቶችን በማስፋፋት ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች እንዲሆኑ ማድረግ በእቅድ ተይዟል። አዳዲስ የኢንዱስትሪ፣ የማዕድንና የግብርና ምርቶችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የተለመዱትን የወጪ ምርቶች በመጠንና በጥራት በማስፋፋት የሚያስገኙትን ገቢ ለማሳደግም ታቅዷል።

የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የመጀመሪያ ዓመት አፈጻጸም ስንመለከት ግን፤ አርኪ ውጤት አለመገኘቱን እንረዳለን። ኢትዮጵያ በ2008 በጀት ዓመት ወደውጭ ከላከቻቸው ምርቶች ያገኘችው ገቢ 2 ነጥብ 86 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነበር። ይህም ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የመጨረሻ ዓመት ማለትም 2007 ዓ/ም ጋር ሲነፃፀር የ4 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። እርግጥ በ2008 በጀት ዓመት የተላኩት ምርቶች በመጠን ከ2007 የጨመረ ነበር። ከገቢ አኳያ ግን  አነስተኛ ነበር። የገቢው መቀነስ ምክንያት ደግሞ፣ የአለም ገበያ ዋጋ መቀነስ ነው። ለምሳሌ፤- ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች አንዱ የሆነው የቅባት እህል ንግድ፣ በ2008 ዓ/ም በዘርፉ የዓለምን ገበያ የተቀላቀሉ ታንዛንያና ማሊን የመሳሰሉት አገራት ምርቱን በስፋት ማቅረባቸው የገበያው ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉን የንግድ ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ። በወርቅ፣ በቁም እንስሳትና በመሳሰሉት ዘርፎች ደግሞ የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት የተገኘው ገቢ ለመቀነሱ ምክንያት መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የያዝነው ዓመት ማለትም 2009 ዓ/ም የመጀመሪያ መንፈቅ የወጪ ንግድ አፈጻጸምም የታቀደውን ያህል መሆን አልቻለም። ባለፉት 6 ወራት ከቅባት እህሎች፣ ከጥራጥሬ፣ ከተፈጥሮ ሙጫና እጣን እንዲሁም ከጫት፣ ከብርእና ከአገዳ እህሎች የተገኘው ገቢ 417 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው። ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ6 በመቶ ጭማሪ ያለው ቢሆንም፣ አጠቃላይ ከወጪ ምርቶች ጋር ተያይዞ የታቀደው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ግን በ15 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽንም በ2009 በጀት ዓመት አጋማሽ የኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ የወጪ ንግድ እድገቱ ተጨባጭ ለውጥ አለማሳየቱን አስታውቋል። የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በታሰበው መልኩ እንዳይራመድ ስጋት ከሆኑት መካከል የወጪ ንግድ እድገት በታቀደው መልኩ አለመፈፀሙ ዋነኛው መሆኑንም ኮሚሽኑ አመልክቷል። ይህም ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ፍጥነት ገትቶታል ተብሏል።

አገሪቱ ከወጪ ንግድ የታቀደውን ያህል ገቢ እንዳታገኝ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል፤ የውጭ ገበያ ምርት አቅራቢ አምራቾች ላይ የሚታየው ደካማ የማምረት አቅም፣ የምርቶች ዓይነት ውስንነትና በዓለም አቀፍ ገበያ የታየው የፍላጎት መቀዛቀዝ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽን ገልጿል። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ለሰፈሩ አብይ የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብለው የተጠበቁ አገራት እድገት መቀዛቀዝም ሌላው ተፅዕኖ የፈጠረ ጉዳይ መሆኑንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።  እንደኮሚሽኑ ገለጻ፤ በንግድ ስርዓቱ እና በአንዳንድ ዘርፎች ላይ የሚታየው ብልሹ አሰራርም ለእድገቱ ስጋት ነው።

እንግዲህ፣ የወጪ ንግድ እድገትን ለማፋጠን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና የአምራች ተቋማትን አቅም ማጎልበት፣ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ካሉ ርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቀመጠውን የወጪ ንግድ ግብ ለማሳካት እቅዱ ተግባራዊ በተደረገበት ያለፈ አንድ ተኩል ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በ2009 ዓ/ም የተሰበሰበው የመኸር ምርት ከባለፈው ዓመት በ12 በመቶ እድገት አሳይቷል። እርግጥ በ2007 ዓ/ም በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በ2008 ዓ/ም ምርት የእድገት መጠን ቀንሷል። ቀደም ሲል በነበሩት ከ10  ተከታታይ ዓመታት በላይ በአማካይ የ8 በመቶ እድገት ሲያስመዘግብ የቆየው የግብርና ዘርፍ በ2008 በጀት ዓመት በ2 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ነበር ያደገው። የግብርና ምርት እድገት በዘንድሮው ልክ መቀጠል የሚችል ከሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የዋጋ መቀነስ ቢታይ እንኳን ይህን በማካካስ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ የሚያስችል በቂ ምርት መላክ የሚያስችል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

በወጪ ንግድ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ኢንዲኖረው የታሰበውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሚፈለገው ልክ ለማሳደግ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በተለይ በወጪ ንግድ ምርቶች ላይ ያተኮሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም ለወጪ ንግድ አቅርቦትና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ላይ አተኩረው የሚሰሩ የአግሮ ፕሮሰሲንግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው።

በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን፣ ባለፈው ዓመት ግንባታው ተጠናቆ ከተመረቀው የሃዋሳ የጨርቃጨርቅ ኢንደስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በአራት የሃገሪቱ አካባቢዎች ማለትም፤ አዳማ፣ ድሬ ዳዋ፣ ኮምቦልቻና መቀሌ ተመሳሳይ የወጪ ንግድ ምርቶችን ማምረት ላይ ያተኮሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገነባሉ።

በያዝነው በጀት ዓመት በአራት ክልሎች ማለትም፤ በትግራይ ሁመራ አካባቢ፣ በአማራ ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ፣ በኦሮምያ ዝዋይ እና በደቡብ ክልል ሲዳማ ላይ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ /የአግሮ ፕሮሰሲንግ/ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለማስጀመር እቅድ ተይዟል። ግንባታቸው የሚጀመረውና በአራት ዓመታት ውስጥም የሚጠናቀቁት ፓርኮቹ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ያፋጥኑታል  የሚል እምነት አለ። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከሚያስፈልጋቸው ከፍተኛ ስራና የፋይናንስ አቅርቦት  አንጻር በአራት ይወሰኑ እንጂ፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ በአስራ ሰባት ቦታዎች ላይ  ለማስገንባት ጥናት ተካሂዶ ተጠናቋል።

የግብርናን ዘርፍ እድገት ጨምሮ እነዚህ በወጪ ንግድ ምርት ላይ ያተኮሩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማስፋፊያ ተግባራት ውጤታማ ከሆኑ የአገሪቱን የወጪ ንግድ በማስፋት የውጭ ምንዛሪን ግኝት ማሳደግ ይቻላል።

የውጭ ምንዛሬን ግኝት ለማሳደግ ከወጪ ንግድ በተጨማሪ ቀጥታ የውጭ ኢቨስትመንት ከፍተኛ ሚና አለው። ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን እድገት የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑ ሳይዘነጋ፣ የኢፌዴሪ መንግስት የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ የማበረታቻ ፖሊሲዎች ተግባራዊ አድርጓል። በዚህም የአገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደጊዜ እድገት አሳይቷል።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ክንውን ዘመን ዓመታዊ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ደርሶ ነበር። በ2008 በጀት ዓመት የፀጥታ ችግር፣ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና የድርቅ አደጋ ባለበት ሁኔታ የአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከ2007 በጀት ዓመት በ50 በመቶ በመጨመር 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደነበር የኢትዮጵያ ኢነቨስትመንት ኮሚሽን አሳውቋል። በ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከግማሽ ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መገኘቱን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ተመሳሳይ መሆኑን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

በአጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ሳይቆራረጥ አሁን ባለበት ፍጥነት ለማስቀጠል፣ በተለይ ኢኮኖሚውን ወደማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መር በማሸጋጋር የመወቅር ለውጥ ለማምጣት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከጊዜ ወደጊዜ መጨመር አለበት። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበት ሁኔታ እድገቱን ማስቀጠልና መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ህልም ነው። በመሆኑም፤ በህገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡትን የወጪ ንግድ ምርቶች መቆጣጣር ወሳኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸውን ምርቶች በዓይነት የማስፋት፣ በመጠን የማሳደግ፣ ጥራትና እሴት የመጨመር ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ረገድ እስካሁን የሚታዩት ጅምሮች በተጨባጭ ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም፤ ለተግባራዊነታቸው መትጋት ግን አስፈላጊ ነው። ካለበቂ የውጭ ምንዛሪ አቅም የእድገት ጉዞ አንካሳ እንደሚሆን በማስታወስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ መትጋት ይጠበቅባቸዋል።