በልዩነቶቻችን መካከል ወፍራም ገመድ አለ – ኢትዮጵያዊነት!

ፌዴራሊዝም በበርካታ የዓለም አገራት በተለይም ብዝሃነት በሚስተዋልባቸው አገሮች ተመራጭ የአስተዳዳር ዘይቤ እነደሆነ በርካታ ምሁራን ይስማማሉ። ብዝሃነትን ለማስተናገድ የፌዴራል ስርዓት ከነድክመቱም ቢሆን በበርካታ ጎኑ ከአህዳዊ ስርዓት የተሻለና ተመራጭ ነው። በየትኛውም አገር እንደተደረገው ሁሉ  ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያም የተመሰረቱ  አህዳዊ ስርዓቶችን ሁሉ በህዝቦች ፍቃደኝነት ያገኙ አልነበሩም።  በመሆነኑም ስርዓቶቹ በሙሉ የህዝቦችን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም ነበር።

በአህዳዊ ስርዓት አንድ አውራ ብሔር የአገሪቱን ተቋማት በመቆጣጠር የራሱን ማንነት እያሳደገ የህዳጣንን ወይም የአናሳ ቡድኖችን ባህልና ወግ መደፍጠጡ የግድ ነው። ይህም በአገራችን በተግባር ታይቷል። አህዳዊ የአስተዳደር ስርዓት አግላይና አብዝሃነትን የማያስተናግድ ስርዓት በመሆኑ ጸረ-ዴሞክራሲያዊ ነው። የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች አገር የሆነችው  አገራችን  በረጅም የፖለቲካ ታሪኳ የአንድ ሃይማኖትና ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች  እንድትተዳደር በመገደዷ በአሪቱ ሰላም አገኝታ አታውቅም። ሁሉም በያለበት ማንነቱን ለማስከበር በሚያደርገው ትግል ሳቢያ የአገራችን ሰላም አደጋ ላይ ነበር።  

ጠንካራ የባህል ተመራማሪ  የሆኑት ቻርለስ ቴይለር ዓይነት ምሁራን በፌዴራሊዝም የአስተዳደር ሥርዓት በርካታ ማንነቶችን ያለችግር ማስተዳደር እንደሚቻል ይገልጻሉ። በፌዴራለ ሰረዓተ የተገለሉ ቡድኖች፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያኙ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ። በርካታ ልዩነቶች በሚስተዋልባቸው አገራት የፌዴራል የአስተዳደር ስርዓት ሁሉም አትራፊ የሚሆንበትን አካሄድ  የሚያሰፍን እንደሆነ ተመራማሪው ይገልጻሉ።

በአገራችንም በሳልና እውቅ የፌዴራል ስርዓት ላይ ብዙጥናቶችን ያካሄዱ ምሁራን እንዳሉ ይታወቃል።   አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የፌዴራሊዝም ተመራማሪ ዶ/ር አሰፋ ፍስሃ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ምሁር ናቸው። መንግስት እንደነዚህ ያሉ ምሁራኖችን በአግገባብ ሊጠቀምባቸው ይገባል።  የአገራችንን የፌዴራል ስርዓት በተመለከተ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ለአገራችን የፌዴራል ስርዓት መጎልበት በርካት ግብዓት አለው። እንደሳቸው እምነት የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት የቡድኖችንም ሆነ የግለሰቦችን መብቶች ማራመድ የቻለ ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ በሊበራል አስተሳሰብ አራማጅ በሆኑ የፌዴራል ስርዓት ተከታይ አገሮች ራሱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድጋፍ እያገኘ ነው።

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት የተለያዩ ቡድኖች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩና ማንነታቸውን እንዲጠብቁ በፌዴራል መንግስትም ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራቸው ተደርጓል። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሰሳቸው  በማስተዳደር ፖለቲካዊና መኤኮኖሚያዊ ችግገሮቻቸውን በመፍታት ላይ ናቸው። ይሁንና አሁንም ያልተፈቱ ችግገሮችን እግር በግር እየተከታተሉ መፍታት አስፈላጊ ነው። የፌዴራል ስርዓታችን ገና ለጋ ነው። በመሆኑም እንክብካቤ ይፈልጋል።  

በፌዴራል መንግስት ውስጥ ተመጣጣኝ ውክልና ሊኖር የግድ ነው። በፌዴራል መንግስት ውስጥ ተገቢው ውክልና ለእያንዳንዱ ቡድን መስጠት ተገቢ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ  የፌዴራል ስርዓት ውስጥ እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ተገቢው ውክልና እንዲኖረው ተደርጓል።  ይህ በመደረጉም ሁሉም  ቡድኖች በብሔራዊ ደረጃ የፖሊሲ አወጣጥ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድል እንዲያገኙም ተደርጓል። በዚህም አሁን ላይ ህዝቦች በፌዴራል ደረጃ አልተወከልንም የሚል ቅሬታ ሲነሳ አይደመጥም።

በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ከሚታዩ ማንነቶች መካከል የክልል ወይም የቡድን ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች  ሳይዛነፉ እኩል ሊዳብሩና ሊተገበሩ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ችግር ይፈጠራል። በኢትዮጵያ ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔር ማንነት መካከል እኩል እንዲዳብሩ ተገቢው ስራ አልተሰራም። ይህ በመሆኑም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች መደነቃቀፍ ተከስተዋል። ዜጎች ከኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል ወዘተ አይነት መልካም ያልሆኑ ነገሮች ተከስተዋል።

በቀጣይ የብሄር ማንነቶችንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስታርቀን መሄድ ካልቻልን ችግሮቻችን ሊወሳሰቡ ይችላሉ። አንዱ በአንዱ መስዋዕትነት የሚገኝ ሳይሆን ሁለቱንም ማታረቅ የሚቻልበት ሁኔታ አለ። ከላይ እንዳነሳሁት መንግስት በዘርፉ  በቂ ልምድና እውቀት ካላቸው ምሁራን ጋር በቅርበት በመስራት ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም ከተለያዩ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ብንሆንም ሁላችንንም በአንድነት የሚያስተሳስር ወፍራም ገመድ አለ- ኢትዮጵያዊነት። የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ራሱን በራሱ ማስተካከል የሚችልበት አሰራር ያለው በመሆኑ ይህን መጠቀም አስፈላጊ  ነው።

የብሔር ማንነችንን በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ልንጠቀምባቸው፣ ቡድናዊ ትስስሮቻችንን ልናጎለብትባቸው እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር የምንተሳሰርበት ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያዊ ማንነት ሌሎች ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲገኝ አለማድረግ በተመሳሳይ የቡድን ወይም የብሔር ማንነትን ከሌሎች ማንነቶች በተለይ ከኢትዮጵያዊ ማንነት  በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም ስርዓት  እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሁሉንም በልክ በልክ የማናስኬደው ከሆነ ዋጋ ያስከፍለናል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህን በአግባብ ተገንዝቦ ፍላጎቶቹን  ማስታረቅ ይኖርበታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የፌዴራል ስርዓት ላይ ራስን በራስ በማስተዳደር ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተሳሳተ ዕይታዎች ይስተዋላሉ። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት የራስን ቋንቋና ባህልን መጠቀምና ማዳበር እንጂ  አናሳዎችን ማጥቃት መሆን የለበትም። እንዲህ ያሉ አካሄዶች በክልል መንግስታትም ይሁን በፌዴራል መንግስቱ በወቅቱ ተገቢው እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። ተገቢው እርምጃ በወቅቱ የማይወሰዱ ከሆነ ውጤቱ አያምርም።  

በቅርቡ በአገራችን በተከሰቱ ግጭቶች ቡድናዊ ማንነቶች ከኢትዮጵያ ማንነት እኩል ሊጎለብት ሲገባቸው  በአንዳንድ  አካባቢዎች አንድነትን የሚሸረሽሩ አካሄዶችና የቡድንተኝነት ስሜት በስፋት ሲራገቡ ተስተውለዋል።  እነዚህን ሁለት ማንነቶች ማመጋገብ የማይቻል ከሆነ   አደገኛ ነገር ሊፈጠር ይችላል።

በፌዴራል ስርዓት አካሄድ የፌዴራል መንግስትን ፖሊሲና ስትራቴጂ እኩል መተግበር አስፈፈላጊ ነው። አንዳንድ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን በሂደት ልዩነትን የሚያሰፉ የፌዴራል ስርዓቱን አንድነት  ሊያስትሳስሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች  በአግባብ አልተተገበሩም። ለአብነት የትምህርት ፖሊሲው ላይ የሰፈረውን የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ  የሆነው የአማርኛ ቋንቋ  የትምህርት አሰጣጥ  ላይ በአንዳንድ ክልሎች የሚታይ ክፍተት አንዱ  ማሳያ ነው።

ሌላው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት ተደጋጋፊ መሆን መቻል ይኖርባቸዋል። በፌዴራል አስተዳደር ክልሎች ያለ መዓከላዊ መንግስት እንዲሁም መዓከላዊ መንግስት ያለ ክልሎች አይኖሩም። አንዱ ክልል ቀውስ ሲገጥመው ችግሩ የዚያ ክልል ብቻ የሚቆም ሳይሆን አገር አቀፍ ችግር ይዞ ነው የሚመጣው። በቅርቡ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጠሩ ችግሮች አገር አቀፍ ቀውስ አስከትለው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት የታሰበለትን ግብ መምታት ችሏል። ይህ ስርዓት የአገሪቱን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ቀርፏል። አንዱ ለዘመናት የአገራችን ችግር ሆኖ የኖረውን የፖለቲካ ችግር ማለትም የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነት ጥያቄዎች መመለስ አስችሏል። ሌላው ደግሞ የአገሪቱ የልማት ፍላጎት መመለስ የሚያስችል አሰራርን ዘርግቷል።  የፌዴራል ስርዓቱ ፍተሃዊ ልማትን በማስፈንና ድኅነትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። በእነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች ረገድ የአገራችን የፌዴራል ስርዓት ስኬታማ ነው።