ከኤርትራ መንግስት የማስታወቂያ ሚኒስቴር በሚሰጣቸው የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ የሚሰሩት ኢሳትና ሌሎች መሰል የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ሚዲያዎች ባለፈው ዓመት የሞት ዜና በማውራት ስራ ተጠመደው ነበር። ለሰላማዊ ተቃውሞ የወጡ የዚህ ከተማ ወጣቶች በጥይት እሩምታ ተጨፈጨፉ፣ ይህን ያህሉ አለቁ . . . በሚሉ ዜናዎች ተጨናንቀው ነበር። የማህበራዊ ገጾቻቸው፤ ከተገኘ እውነተኛ ከሁከቱ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን፣ ካልተገኘ ደግሞ በየትኛውም አገር በተለያየ ምክንያት የሞተን የጠይም ሰው/ሰዎች አስከሬን እየለጠፉ ሙሾ ሲያስወርዱ ነበር የከረሙት፤
እርግጥ ነው፤ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት፣ በሁከት ተሳታፊ በነበሩ ወጣቶችና በጸጭታ አስከባሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ከወጣቶችም ከጸጥታ አስከባሪም ወገን፤ የሟቾቹ ቁጥር ግን የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚ ሚዲያዎቹ እንዳወሩት አልነበረም። እነዚህ ሚዲያዎች ዓመቱን ሙሉ ሲሉ የነበረውን የሟቾች ቁጥር ብትደምሩ በትንሹ አስር ሺህ ይደርሳል። ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ግን ከጥቂት መቶዎች አይበልጥም። የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት እንደሌለበት አምናለሁና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ቀላል ነገር ነው እያልኩ አይደለም።
እነዚህ የትርምስ ሚዲያዎች የሞት ዜናዎችን እጅግ እያጋነኑ ሲነገሩን የነበሩት ለሟቾቹ ከመቆርቆር አይደለም። ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን ተገቢ ቅሬታ ለመግለጽ ሲነሳሳ ይህን አጀንዳ ያለወጉ አራግበው፤ በተለይ ወጣቱ አውዳሚ ሁከት ውስጥ እንዲሳተፍ በማድረግ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር መሳሪያ ለመንጠቅ ግብግብ እንዲገጥም በመገፋፋት ለሞት ያጋለጡት እነርሱው ስለሆኑ አያዝኑለትም። የሰው ሞት ለእነርሱ ሲሳይ ነበር። ይፈልጉታል። የሰዎች መሞት ለእነርሱ የመንግስትን ገጽታ በማበላሸት ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ድጋፍ ለማሳጣት የሚያገለግል መሳሪያ ነው። ከህዝብ ጋር እንዲቀያየም በማድረግ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ የሚጠቅም መወጣጫ ነው። በአጠቃላይ የሰዎች ሞት አገሪቱን ማፍረስ የሚያስችል የፖለቲካ ትርፍ የሚያገኙበት ንግድ ነው። እናም ሆይ! ሆይ! ሲሉ የነበረው ለዚህ ነው።
ይህ ተገቢ የህዝብ ቅሬታን በመጥለፍ የተፈጠረ አደገኛ አውዳሚ ሁከት ለዜጎች ህይወት መጥፋት፣ በመቶ ሚሊዮን ለሚለካ የግለሰቦችና የህዝብ ሃብት መውደም፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ምክንያት ቢሆንም አሁን ተረጋግቷል። በተለይ፤ ሁከቱን በተለመደው ሰላም የማስከበር ህግና አካሄድ መቆጣጠጣር ስላልተቻለ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ከታወጀ በኋላ በመላ አገሪቱ ሰላም ሰፍናል። የሰፈነው ሰላም አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መኖሯን እንኳን የማያመለክት አስተማማኝ ነው። ይህ ሁኔታ የአገሪቱ ሰላም በዚህ ደረጃ የተጠበቀው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብቻ ሳይሆን የሰላሙ ባለቤት በሆነው ህዝብ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። በሌላ በኩል፤ የአምናው ሁከት በምልዐተ ህዝቡ ተሳትፎ የተካሄደ እንዳልነበረም ያሳያል። አብዛኛው ህዝብ በመንግስት ላይ ተገቢ ቅሬታ ቢኖረውም ይህን ቅሬታውን የአገሪቱን ህልውና ለአደጋ በሚያጋልጥ አውዳሚ ሁከት እንዲገለጽ አይፈልግም ነበር። የአምናው ሁከት የምልዐተ ህዝቡ ፍላጎት ቢሆንማ ኖሮ፣ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ አያስቆመውም ነበር። የምልዐተ ሀዝቡን ተቃውሞ እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ የጦርነት አዋጅም አይመልሰውም። ይህ የሚያሳየን ሌላው እውነታ አሁን ያለው ፍጹም ሰላም በህዝቡ ጥበቃ የተገኘ መሆኑን ነው።
በአገሪቱ ያለውን የሰላም ሁኔታ ለመረዳት ከጥቅምት ወር በኋላ የተካሄዱትን ከ40 ሺህ ሰው በላይ የተሳተፈበትን ታላቁ ሩጫ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በመስጊዶች የታደሙበትን በተለይ በአገር አቀፍ ደረጃ በጂማ ከተማ የተከበረውን የመውሊድ በአል፤ እንዲሁም በመላው አገሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው የታደሙበትን የጥምቀት በአል ሰላማዊ አከባባር ማንሳት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ፤ የ2009 ዓ/ም የቱሪስት ፍሰትና ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ሁኔታም በአገሪቱ ያለውን ሰላምና መረጋገት ያሳያል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በዘንድሮው ግማሽ በጀት ዓመት፤ ማለትም ከሃምሌ 1/ 2008 እስከ ታህሳስ 30/ 2009 ዓ/ም 439 ሺህ 359 የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። የጎብኚዎቹ የቆይታ ጊዜም በአማካይ 16 ቀን ነው። ከቱሪዝም የተገኘውም ገቢ 1 ቢሊዮን 644 ሚሊዮን ዶላር ነው። እርግጥ ዘንድሮ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ጎብኚዎች ቁጥርና ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ከ2008 ዓ/ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በተለይ በሃምሌ፣ በነሃሴና በመስከረም ወራት ላይ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ምክንያት ቅናሽ አሳይቷል። ከመስከረም ወዲህ በሰፈነው ሰላምና መረጋጋት ምክንያት የቱሪስቱ ፍሰት በመስተካከሉ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ያለው ልዩነት ግን እጅግ ጠባብ ነው። ባለፈው ዓመት ከ478 ሺህ 890 ጎብኚዎች ከ1 ቢሊዮን 789 ሚሊዮን 964 ሺህ 160 ዶላር ገቢ ተገኝቶ ነበር። የዘንድሮው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የጎብኚዎች ቁጥር በ39 ሺህ 531፣ ገቢውም በ145 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ዝቅ ብሏል።
አገሪቱ ያለውን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ የሚያሳየውን የውጭ ቀጥታ ኢቨስትመንት ስንመለከት፣ በ2007 ዓ/ም 2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር። በ2008 በጀት ዓመት የፀጥታ ችግር፣ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ እና የድርቅ አደጋ ባለበት ሁኔታ የአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከ2007 በጀት ዓመት በ50 በመቶ በመጨመር 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደነበር የኢትዮጵያ ኢነቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል። በ2009 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመዝግቧል። ይህም ካለፈው ዓመት አቻ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ተመሳሳይ ነው።
እነዚህ ሁኔታዎች የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ መሆኑን ያመለክታሉ። ይህ በአገሪቱ የሰፈነው ሰላም የጠላት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ሚዲያዎችን የትርምስ መቀስቀሻ አጀንዳ አሳጥቷቸዋል። እነዚህ ሚዲያዎች በፌስ ቡከ ገጾቻቸው ጭምር በዚህ ቦታ ሁከት ተካሄደ፣ ይህን ያህል ሰው ተጨፈጨፈ፤ ወዘተ .ማለት አልቻሉም። አንዳንዶቹ የፌስ ቡከ ገጾች ከወጣቱ ትኩረት ሳይርቁ አመቺ አጋጣሚ እስኪያገኙ ለመቆየት ስፖርት ነክ ወሬዎችን መለጠፍ ጀምረዋል። ወሲብ ጠቀስ ወሬ፣ ፎቶግራፍና ተንቀሳቃሽ ምስል የሚለጥፉም አሉ። ይህ ለጊዜውም ቢሆን ተስፋ መቁረጣቸውን ያሳያል። አመቺ አጋጣሚ ሲያገኙ ግን መነሳታቸው አይቀሬ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ታዲያ፤ ሰሞኑን ሌላ ግብአተመሬታችን እንዲፈጸም ያደርጋል በሚል ያሰጋቸው ሁኔታ ስለተፈጠረ ደንግጠው ባንነዋል። ይህም ህጋዊ ሆነው በአገር አቀፍ ደረጃ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በኢህአዴግ መካከል መካሄድ የጀመረው የድርድርና የክርክር ሂደት ነው። ይህ በህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎቸና በገዢው ፓርቲ መካከል ሊደረግ በሂደት ላይ ያለው ድድርና ክርክር የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት ዴሞክራሲውን ያጎለብተዋል። ይህ ደግሞ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ስርአት በማጽናት ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድና አገሪቱን ለማፍረስ ለሚካሄዱ ሙከራዎች መንገድ ይዘጋል። ይህ ነው አስደንግጦ ያባነናቸው።
እናም ሰሞኑን ውዠንብር መንዛት ጀምረዋል። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር የሚያደርጉት ውይይት ዋጋ የለውም፤ በአዲስ አበባ ዘረፋ ተባብሷል፤ ወዘተ. የሚሉ ወሬዎችን በመንዛት፤ ከዚህ በመነሳት መንግስት በሃይል መወገድ አለበት የሚል አቋምም ይዘው ውዥንብር እየነዙ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዘረፋ ተባብሷል የሚለውን ህዝቡ በሚገባ ስለሚያውቀው ብዙ ማብራሪያ መስጠት አያስፈልገውም። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እንደመሆኔ፣ በፊት ከነበረው የተለየ ልዩ ትኩረት የሚስብ የዘረፋና የሌብነት ድርጊት የሚታይበት ሁኔታ አለመኖሩን አውቃለሁ። ምናልባት ግን፤ እነዚህ የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚ ተላላኪዎች፤ ህዝቡ እንዲማረር ወሮበሎችን መልምለው በማሰማራት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያና ዝርፊያ የመፈጸም እቅድ ሊኖራቸው እንደሚችል ግን እገምታለሁ። ህዝቡም ሁኔታውን ከዚህ አኳያ ቢረዳው መልካም ነው።
በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ክርክርና ድርድር የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት አሳታፊ፤ ፍትሃዊና ተአማኒ ምርጫ በማካሄድ፤ አናሳ ድምጾች ጭምር በምክር ቤት ውክልና የሚያገኙበትንና ሁሉም አመለካከቶች የመደመጥ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ ደግሞ የአገሪቱን የዴሞክራሲ እድገት እመርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ያስችላል። ሁሉም ድምጾች የሚሰሙበት እድል መፈጠር ለሃይል ተቃውሞ የሚገፋፋ ሁኔታን ያስወግዳል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊደርስበት የሚፈልገው የዴሞክራሲ ደረጃ ነው። እናም ድርድሩንና ክርክሩን በጉጉት ነው የሚጠብቀው፤ ወይም መጠበቅ ያለበት፤ ይህ የዴሞክራሲ እድገት ደረጃ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ለሚፈለጉ አገራትና ቡድኖች መንገድ የሚዘጋባቸው በመሆኑ የትርምስ ራዕያቸውን ያመክነዋል። ሰሞኑን ድርድርና ክርክሩን ለመቃወም የተነሱት ለዚህ ነው።
እናም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በእጁ ያለውን ሰላም በትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች ላለማስነጠቅ አጥብቆ መጠበቅ አለበት። የአገሪቱን ዴሞክራሲ እመርታዊ ለውጥ እንዲያሳይ ሊያደርግ የሚችለውን በኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ድርድርና ክርክርም እንዲሰምር ከመሰናክሎች ሊታደገው ይገባል።