መንግስት በየደረጃው እያካሄዳቸው ያሉት ጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች ጥልቀታቸው እየሰፋ ነው። በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ህዘቡን ባማከለ ሁኔታ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው። ህዝቡም ሃሳቡን በነፃነት ከመግለፅ ባለፈ፣ በመልካም አስተዳደር በኩል ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ተሿሚዎችን እስከ ማንሳት ድረስ የዘለቀ መብቱን እየተጠቀመበት ይገኛል። ይሁንና ከዚህ ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታ ባፈነገጠ መልኩ አንዳንድ ወገኖች የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን እያራመዱ ነው። ከእነዚህ አስተሳሰቦች ውስጥ “ተጠያቂነትና ለውጥ የለም” የሚለው ተጠቃሽ ነው። ይህ ፅሑፍም ህዝቡ ከተሃድሶው ያገኘውን ውጤቶች በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዞ የሚያሳይ ነው። ከዚህ አኳያ በቅድሚያ ‘ህዝቡ ከጥልቅ ተሃድሶው ምን አገኘ?’ የሚል ጥያቄን በማንሳት፣ ለጥቆ ደግሞ የተወሰኑ ክልሎችን በማሳያነት በማቅረብ የተገኙ ውጤቶችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
ህዝቡ ከተሃድሶው ያገኘው ጥቅም በዋነኛነት ሊገለፅ የሚችለው ጉዳይ፤ ህገ መንግስታዊ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ዕውን ማድረጉ ነው። እንደሚታወቀው የጥልቅ ተሃድሶው ዋነኛ ምክንያት መልካም አስተዳደርና ከእርሱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዩች ናቸው። ህዝቡ በየደረጃው ባለው የመንግስት አስፈፃሚ ምክንያት እየደረሰበት ያለው ችግርና እንግልት እንዲሰማለት ይፈልጋል።
ይህን ለመፈፀም ደግሞ ቁርጠኝነት ያለውና ከእርሱ ውክልና የወሰደ መንግስት እንዳለው ያውቃል። ርግጥ መንግስትም ቢሆን ይህን የህዝቡን ፍላጎት በመገንዘብ በጥልቅ ለመታደስ መወሰኑ፤ በአንድ በኩል የመንግስትን የግልፅነትና የተጠያቂነትን አሰራር ፍላጎት የሚያሳይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ የመደመጥ መብቱን መጠየቁ አግባብ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
ታዲያ ይህ የመንግስት አቋም ህዝቡ በዴሞክራሲ ውስጥ ሆኖ ላቀረበው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት ብቻ የተገታ አይደለም። ይልቁንም በጥልቅ ተሃድሶው በአቅምም ይሁን በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የተፈጠረውን የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ለመፍታት ህዝ ራሱ የመፍትሔው አካል ሆኖ በየደረጃው የሾማቸውን የመንግስት ስራ አስፈፃሚዎችን እስከማንሳት የደረሰ ዴሞክራሲያዊ አግባብን የተከተለ ነው። ይህ ደግሞ ከህዝቡ ትክክለኛ ጥያቄ አንፃር ተገቢ ምላሽ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውጤት ያገኘበት ነው ማለት ይቻላል። ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር እያገኘ በመሆኑ በውጤትነት መመዝገብ ያለበት ዕውነታ ይመስለኛል።
ከህዝቡ ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ከተካሄዱት የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች ውስጥ አንዱ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የተከናወነው ነው። በክልሉ ህዝቡን በማሳተፍ ባለፉት ስድስት ወራት በተካሄዱት የጥልቅ ተሃድሶ የመጀመሪያ ዙር መድረኮች፤ አራት ሺህ 460 ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ላይ ርምጃ ተወስዷል። በ13 ሺህ 578 ዝቅተኛ አመራሮች ላይም እንዲሁ። በተለይም ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮቹ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ሲመሩ የነበሩ እንደነበር ክልሉ አስታውቋል። አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ርምጃዎች ከተወሰደባቸው አመራሮች በተጨማሪ፤ 694 አመራሮች በብልሹ አሰራር ተገምግመው በ260ዎቹ ላይ ህጋዊ ክስ ተመስርቶባቸዋል። በሌሎቹ ላይም የማጣራት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት ርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ በአቅም ማነስ ሁለት ሺህ 587፣ በኪራይ ሰብሳቢነት 964፣ በስነ ምግባር ችግር 397 እንዲሁም በግል ችግር ምክንያት 512 አመራሮች ናቸው። በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ ሁለት ሺህ 470 አመራሮችን ለህግ ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጅትና የማጣራት ስራ መጠናቀቁም ተመልክቷል። በእነዚህ አመራሮች ላይ ጉዳያቸው ተጣርቶ አስፈላጊው የክስ ሂደት እስኪመሰረት ድረስ የክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በንብረቶቻቸውና በገንዘባቸው ላይ ዕገዳ እንዲጣል አድርጓል። በዚህም በጥሬ ብር ከሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ፣ አራት ተሽከርካሪዎች፣ ሁለት ህንፃዎችና 40 መኖሪያ ቤቶች እንዲታገዱ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም 244 ሺህ 326 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት እና በደን የተሸፈነ 548 ሺህ 662 ካሬ ሜትር መሬትም ታግዷል።
ታዲያ እዚህ ላይ ‘ይህ የክልሉ የጥልቅ ተሃድሶ የመጀመሪያ ዙር ርምጃ ምን ያሳያል?’ ብሎ መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል። ርግጥም በየመድረኮቹ የተገኙት እነዚህ በጥልቀት የመታደስ ሂደት ውጤቶች የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ የታከለባቸው ናቸው። በእኔ እምነት የክልሉ መንግስትና ህዝብ በመጀመሪያ ዙር ብቻ ባካሄዷቸው የተሃድሶ መድረኮች የተጎናፀፏቸው ውጤቶች ሁለት መሰረታዊ ጉዳዩችን የያዙ ይመስለኛል።
አንደኛው ቀደም ሲል በክልሉ ተከስቶ የነበረው ሁከት አነሳሽ ምክንያቶችን ለማጥራትና ወደ ተጨባጭ መፍትሔዎች ለመግባት የሚያግዙት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ክልሉ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መልሶ ህዝቡን በግልፅና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ማሳተፉ ተጠያቂነትን በክልሉ ማስፈን መቻላቸው ነው። ያም ሆነ ይህ ግን ከመድረኮቹ የተገኙት ውጤቶች ለውጥንና ተጠያቂነትን የሚያጎናፅፉ በመሆናቸው በቀጣይ ዙሮችም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል እላለሁ።
በጥልቅ ተሃድሶው ውጤት የተመዘገበበት ሌላው ማሳያ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ነው። ክልሉ በየደረጃው ባካሄዳቸው የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች በክልሉ የተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ፤ የህዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች በተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት አቅም መፍጠር መቻሉን ክልሉ ገልጿል። ልክ እንደ ኦሮሚያ ክልል ሁሉ፤ በደቡብ ክልልም የተሃድሶው ዋነኛ ተሳታፊ ህዝቡ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በክልሉ አምስት ነጥብ ሶስት ሚሊየን ህዝብ በጥልቅ ተሃድሶው ተሳታፊ ሆኗል። ህዝቡ በእያብዳንዱ የመንግስት ተሿሚ ላይ ሂስ እየሰጠ በመገምገም ከስልጣን እንዲወርዱ አድርጓል።
በዚህ መሰረትም ከከፍተኛው አመራር ጀምሮ በየደረጃው በተካሄዱት ግምገማዎች መሰረትም አመራሩን እንደገና የማዋቀር ስራ ተሰርቷል ብለዋል። አንድ ሺህ 920 ከፍተኛ፣ መካከለኛና ጀማሪ አመራሮች እንዲሁም 18 ሺህ 250 የታችው አመራሮች ከሃላፊነት እንዲነሱ ተደርጓል። በአንፃሩም በህዝብ የታመነባቸው ሁለት ሺህ 359 አዳዲስ ምሁራንና ወጣት አመራሮች ወደ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል።
ማንኛውም የመንግስት ተሿሚ በአጠፋው ወይም ለህዝቡ ባላበረከተው አስተዋፅኦ ልክ አስተዳደራዊና ህጋዊ ርምጃዎች ይወሰዱበታል። በመሆኑም በክልሉ በተለያዩ መንገዶች የተመዘበረ 15 ሚሊዮን ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆን የተደረገ ከመሆኑም በላይ፤ በየደረጃው የተጠያቂነት መንፈስ እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ የክልሉ የጥልቅ ተሃድሶው መድረኮች የህዝቡን ተሳታፊነትና ግልፅ ተቺነት ብሎም የስልጣን ባለቤትንትን ያረጋገጡ በመሆናቸው በቀጣይም የተሃድሶ መድረኮቹ ሊጎለብቱና ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
ከጥልቅ ተሃድሶው ጋር በተያያዘ ሌላው ማሳያ የአዲስ አበባ አስተዳደር ነው። አስተዳደሩ ባለፉት 15 ዓመታት የተጓዘበት መንገድና ያመጣቸው ለውጦች የጥልቅ ተሃድሶው መነሻ መሆናቸውን በማስታወቅ፣ በእነዚህ ዓመታት በከተማዋ በተከናወኑት ስራዎች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች በመጡት ለውጦች በየደረጃው መብቱን የሚጠይቅና ጥቅሙን የሚያስከብር ህብረተሰብ መፍጠር እንደተቻለ ተገልጿል። በጥልቅ ተሃድሶውም ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ከህዝቡ ጋር በመሆን ርምጃዎች ተወስደዋል።
እነዚህ ርምጃዎች በከተማዋ የተፈጠሩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዙ ናቸው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠሙ ችግሮች ለህዝቡ ሁሉን አቀፍ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ ባለመሰጠቱ የተከሰቱ በመሆናቸው፤ እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ርብርብ እያደረገ ነው። ያም ሆኖ ህብረተሰቡ አሁንም በበቂ ሁኔታ በመሳተፍ በከተናዋ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት የመፍትሔው አካል መሆን ይጠበቅበታል። የጥልቅ ተሃድሶው ርምጃ ተጠቃሚ እርሱው ነውና።
ከላይ ለማሳያነት ያቀረብኳቸው የጥልቅ ተሃድሶ ርምጃዎችና ውጤቶቻቸው ገና ከጅምራቸው ለውጥን የሚያመጡና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው የዴሞክራሲ መገለጫዎች መሆናቸው ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። ይህ ዕውነታም በአንዳንድ ወገኖች ‘ተጠያቂነትና ለውጥ የለም’ የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። እናም ጥልቅ ተሃድሶው ለውጥን በማምጣት ላይ ያለና እያንዳንዱን የሂደቱን ተዋናይ ተጠያቂ የሚያደርግ ግልፅ የዴሞክራሲ አካሄድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል እላለሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝቡ ያቀረበው ጥያቄ በራሱ ተዋናይነት አግባብ ባለው መንገድ ምላሽ እያገኘ መሆኑን መረዳት ይገባል። ስለሆነም የጥልቅ ተሃድሶውን ርምጃዎች በተጨባጭ ማስረጃዎች ማጤን ያስፈልጋል።