የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርና ድርድር ዓላማዎች

                                              

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና 21 የሚሆኑ ተቃዋሚዎች ለሁለት ዙሮች ተገናኝተው ተወያይተዋል— በጥር ወርና በያዝነው የካቲት ወር ውስጥ። በተለይም በየካቲቱ ሁለተኛው ውይይታቸው ወቅት 18 ፓርቲዎች የክርክርና ድርድር አካሄድ የስነ ስርዓት ማዕቀፍ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስገብተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ስድስት ፓርቲዎች አንድ ላይ በመሆን እንዲሁም ሌላ ስድስት ፓርቲዎች ተመሳሳይ ሃሳብ ያለው አንድ ሰነድ አቅርበዋል። ቀሪዎቹ ፓርቲዎችም በተናጥል የክርክርና ድርድር አካሄድ ስነ ስርዓት ማዕቀፋቸውን ማቅረባቸው አይዘነጋም።

ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች የክርክርና የድርድር ዓላማውን አስመልክቶ የተብራራ ነገር ማቅረብ ባይችሉም፤ ኢህአዴግ፣ መድረክና የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ የተደራጀ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። በውይይቱ ወቅት በገዥው ፓርቲ በኩል በክርክርና በድርድሩ የሚነሱ ጉዳዩችን በግብዓትነት በመውሰድ የሚሻሻሉ ህጎች ካሉ ማሻሻልና የአፈፃፀም ጉድለቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ዓላማ ተይዟል። በመድረክ በኩልም “የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ችግር ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ እንዲሰጥ ማስቻል” የሚል አቋም በዓላማነት ተይዟል። የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ደግሞ ግልፅ የሆነ የድርርድር ዓላማ ባያስቀምጥም በጥቅሉ “የሀገሪቱን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ይገኛል” የሚል ሃሳብን አራምዷል።

በድርድሩና በክርክሩ እነማን ይሳተፉ የሚለውን ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ኢህአዴግን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች “በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ፣ በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡና በክልል ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው ሰላማዊና ህጋዊ የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሳተፉ ይችላሉ” የሚል አቋም የያዙ ሲሆን፤ በመድረክ በኩል ስድስት ፓርቲዎች ብቻ በመሪ ተደራዳሪነት ሊቀርቡ ይገባል የሚል አቋም ቀርቧል።

የፓርቲ ተወካዮች ብዛትን አስመልክቶም ኢህአዴግ እያንዳንዱ ፓርቲ አራት ተወካዮችን ያቅርብ ሲል፣ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ እያንዳንዱ ተፎካካሪ ፓርቲ ሶስት ተወካዮችን ቢያቀርብ የሚል ሃሳብን አንሸራሽረዋል። በሌሎች ጉዳዩች ላይም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸውን አቋም አንፀባርቀዋል። እርግጥ በውይይቱ መቼ፣ ማንና የት ይካሄድ በሚለው ጉዳይ የተሟላ መግባባት ላይ ሲደረስ ለህዝቡ መግለጫ እንደሚሰጡ በወቅቱ ተገልጿል።

ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ የሀገራችንን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያጎለብትና የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚያሰፋ ነው። ውይይቱ ገና በቅድመ ሁኔታ ደረጃ ያለ ቢሆንም ቅሉ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ በመገንባት ላይ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሁም የሁሉንም ህዝቦች ውክልና የሚያጠናክር ነው። ስለሆነም ከጅምሩ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን የማጥበብና በሚያግባቡ ጉዳዩች ላይ ለሀገር ጥቅም ሲባል አንድ ላይ መስራት የግድ ይላል። ምክንያቱም ማናቸውም ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች በመቻቻል መርህ መከናወን ስላለበት ነው።

የዚህ ሀገር ፖለቲካዊ አጀንዳ ህዝቡን የሚወክሉትና በሀገራችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ነው። ሌላ የማንም አይደለም። ስለሆነም በአንዳንድ ፅንፈኛ ወገኖችና የውጭ ተላላኪ ሃይሎች አማካኝነት ‘ህገ መንግስቱ ይቀየር፣ የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይፈቱ፣ ድርድሩ ውጤት አያመጣም፣ እኩል ሜዳ አይኖርም…ወዘተ.’ የሚሉ የራሳቸው አጀንዳዎች በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ከክርክሩና ከድርድሩ ዓላማዎች ጋር ፈፅሞ የማይሄዱት አስተሳሰቦች ጤናማ ያልሆኑና የዴሞክራሲያ ስርዓታችንን አንድም ስንዝር ወደፊት ፈቅ የሚያደርጉት ስላልሆኑ ነው። በመሆኑም ለፅንፈኞችና ለተላላኪዎች ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ምንም ዓይነት ጆሮ መስጠት አይገባም። በእነርሱ ተገቢ ያልሆኑ አጀንዳዎች ላለመጠለፍ የክርክሩንና የድርድሩን ዓላማዎች ማወቅ ይገባል።

አዎ! ሁሉም ተወያይ ፓርቲዎች የክርክሩንና የድርድሩን ዓላማዎች በተገቢው መንገድ ሊገነዘቡ ይገባል። እንደሚታወቀው ኢህአዴግን ጨምሮ በቀጣይ ለመከራከርና ለመደራደር ውይይት እያካሄዱ ያሉት 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ዓላማዎቻቸው ዴሞክራሲን ማስፋት፣ ሰላምን አስተማማኝ ማድረግና ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ናቸው።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስትም እንዲሆን የሚፈልገው በእነዚህ ዓላማዎች መንፈስ ነው።  ከዚህ ውጭ ፅንፈኞችና የውጭ ሃይሎች ተላላኪዎች የሚያነሷቸው አደናቃፊ ሃሳቦች አንድም ስንዝር ዕውን እንዲሆኑ የሚፈለጉ ሃሳቦችን የሚያመጡ አይደሉም። እናም በክርክሩና በድርድሩ ወቅት ሁሉምወገኖች ማሰብ ያለባቸው የሀገራችን ዴሞክራሲ እንደምን እንደሚሰፋ፣ ሀገራችን ውስጥ የተገኘውን ፈጣንና ተከታታይ ልማት እንደምን በአስተማማኝ ሰላም ማጠናከር እንደሚቻል ብሎም በአብዛኛዎቹ ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ እንደምን ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚቻል ነው።

እንደሚታወቀው ዴሞክራሲን ለማስፋት ጊዜን ይጠይቃል። እንኳንስ እኛ ቀርቶ ተግባሩን ዕውን ካደረጉ ከ200 ዓመት በላይ ያስቆጠሩት ያደጉት ምዕራባዊያን ሀገራትም ቢሆኑ በተሟላ የዴሞክራሲ ቁመና ላይ ነው ያሉት ማለት አይቻልም። ዴሞክራሲ ከህብረተሰብ የአስተሳሰብ ልህቀት ብሎም ጥልቅ ግንዛቤ ጋር በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚጎለብት ነው።

ከዚህ አኳያ በሀገራችን የዴሞክራሲ ምንነት መሰማት ከጀመረ ገና 25 ዓመታት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተወሰነ ርቀት መጓዝ ቢቻልም፤ ያን ያክል የሚያስመካ አይመስለኝም። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች በተግዳሮትነት መጠቀስ ያለባቸው ይመስለኛል—ለዴሞክራሲ ጀማሪ መሆናችንና ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች በተገቢው ሁኔታ አለመቀረፋቸው።

ሀገራችን ለዴሞክራሲ አዲስ ናት። በዚህም ሳቢያ ስለ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች የሚነሱ ጉዳዩች በሁሉም ወኖች በኩል ህፀፆችን መፍጠራቸው አይቀርም። በዚህም ግልፅነትና ተጠያቂነት ብሎም መቻቻልን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ እሴቶችን በተገቢውና በፈጠነ ሁኔታ ገቢራዊ ማድረግ ያስቸግራል። ፅንሰ ሃሳቦች አዲስ በመሆናቸውም በአስተማማኝ ሁኔታ ይተገበሩ ዘንድ ጊዜን ምርኩዝ ያደርጋሉ። ብዥታምን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሆኖም ለተግባራዊነታቸው ከሂደት መማር ይቻላል።

በሌላ በኩልም ያለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ህዝቦች መካከል ፈጥረውት ያለፉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በቀላሉ የሚሽሩ አይደሉም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በዴሞክራሲያዊነት ለመቀየርም አስተሳሰብንና ስለ ዴሞክራሲ ያለንን አመለካከት መለወጥ ይገባል። በህዝቦች ውስጥ ለዘመናት ሲፈጠሩ የነበሩትን የተዛቡ ግንኙነቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ መቀየርም አይቻልም። ቀደም ሲል እንዳልኩት ጊዜንና የአስተሳሰብ ልህቀትን ይጠይቃል። ይህ ሁኔታም ምናምባትም ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያሰናክል ይችላል። እናም ዴሞክራሲው እንዲሰፋ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች መፍታት ይገባል። ይህን ዕውን ለማድረግም የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል። በመሆኑም ፓርቲዎቹ በክርክሩና በድርድሩ ሂደት ውስጥ ‘እነዚህን የዴሞክራሲ ተግዳሮቶች ለመፍታት ከእኔ ምን ይጠበቃል?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል። ይህን ሲያደርጉም ለሀገራቸው ዴሞክራሲ መስፋት የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ።

ፓርቲዎቹ ሌላው ሊያነሱት የሚገባው ጉዳይ ክርክሩና ድርድሩ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ሊኖረው የሚገባውን ፋይዳ ነው። እንደሚታወቀው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት ተፈጥሮ ነበር። የሁከቱ አነሳሽ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፤ ፓርቲዎች እንዲያ ያለው ሁከት ዳግም እንዳይፈጠር መስራት ይኖርባቸዋል።

ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ክርክርና ድርድር መቋጫው ጥርጣሬንና ግጭትን በማስወገድ ሰላምን ማምጣት ነው። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ። ያለ ሰላም ልማትን ማሰብ አይቻልም። ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱንም ስር እንዲሰድ ማድረግ አይቻልም። ዴሞክራሲ ስር ባልሰደደበት ሀገር ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልባቸው ሃሳባቸውን ለህዝባቸው ሊያስተዋውቁና በህዝቡ ይሁንታ በሚካሄድ ምርጫ ሀገር ሊመሩ አይችሉም።

እናም ከክርክርጨሩና ከድርድሩ ዴሞክራሲንና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የራሳቸውን ህልውና ጭምር የሚያረጋግጡ መሆናቸውም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊገነዘቡት የሚገባ ይመስለኛል። አሊያ ግን ክርክርንና ድርድርን ላለመግባባትና ለህገ ወጥነት የሚያልም የፖለቲካ ፓርቲ ካለ፤ ርግጥም ያኔ ህዝቡ የራሱን መፍትሔ መውሰዱ ስለማይቀር “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ አሊያ ግን…” የሚለውን ሀገራዊ ብሂል ማስታወስ ይገባዋል ባይ ነኝ።

ተከራካሪና ተደራዳሪ ፓርቲዎች በውይይት ሂደታቸው ሊገነዘቡት የሚገባ ሌላኛው ዓላማ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ ያለውን ዕውነታ ነው። ርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ ህዝቦች በሁሉም ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባትን ሊፈጥሩ አይችሉም። ብሔራዊ መግባባት በማንኛውም ሀገር ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው በዋና ዋና ጉዳዩች ላይ ነው። ይህን ዕውነታ ወደ ሀገራችን ስንመልሰው፤ ሁለት ምሳሌዎችን በአስረጂነት ለማንሳት እፈልጋለሁ።

አንደኛው፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወራሪውን የኤርትራ ሰራዊት ከግዛታችን ለማስወጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወኑት አንፀባራቂ ድል ነው። በወቅቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ሰው በመሆን ወረራውን ለመቀልበስ ያደረጉት ሁለንተናዊ ትብብር በሀገራቸው ጉዳይ አንድ መሆናቸውን የሚያሳይ ሆኖ አልፏል። ሁለተኛው ደግሞ፤ የሀገራችን ህዝቦች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሀገራችን ህዝቦች ያሳዩት የጋራ ክንድ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በዕውቀቱ በመረባረብ ግድቡን 58 ከመቶ ለማድረስ ችሏል። ግንባታውን ለመፈፀምም ቃል ገብቷል። ይህም የብሔራዊ መግባባታችን መገለጫ ነው ማለት ይቻላል።

ከዚሁ ከህዳሴው ግድብ ጉዳይ ሳንወጣ፤ በቅርቡ የሀገራችን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኙበት የፖለቲካ ፓርተዎች ምክር ቤት የያዘውን አቋም ማድነቅ ተገቢ ይመስለኛል። ምክር ቤቱ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የማልማትና የመጠቀም አቅም እየፈጠረች መምጣቷን ማረጋገጡን በመስክ ጉብኝቱ መገንዘቡን ገልጿል። ገዥውና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚገኙበት ምክር ቤቱ፤ የግድቡ ግንባታ በሀገር ውስጥ አቅም በጥራትና በፍጥነት እየተከወነ መሆኑን መግለፁ የፖለቲካ ፓርዎች ለብሔራዊ መግባባት ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋፅኦ የሚያሳይ ነው። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በሀገራዊ ጉዳዩች ላይ ለመከራከርና ለመደራደር በቅድመ ውይይት ላይ የሚገኙት ሁሉም ፓርቲዎች ብሔራዊ መግባባትን በዓላማነት ሊይዙት ይገባል እላለሁ።

በአጠቃላይ ሁሉም ተወያዩች የክርክራቸውና የድርድራቸው ዓላማዎች ማጠንጠን የሚገባቸው፤ የሀገራቸውን ዴሞክራሲ ከማጎልበት ከፍ ሲልም የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ከማስፋት፣ የሀገራቸውን ሰላም ከማረጋገጥና ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ መሆኑን ደግመው ደጋግመው ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።