የሰላም ሠራዊት

 

የፌደራላዊ ስርዐቱ ዋልታ የሆነ ህገ መንግስት አለን፡፡ ይህ ህገ መንግስት የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ምሰሶ ነው፡፡ የልማት እና የዕድገት ጉዟችን ጎዳና ነው፡፡ የዴሞክራሲ ስርዐቱ እና የልማት እንቅስቃሴው መሠረት ሰላም ነው፡፡ ይሆን ሰላም ለአፍታም ሳያንቀላፋ፤ ወትሮ ዝግጁ ሆኖ የሚጠብቀውም፤ የህገ መንግስቱ ዘብ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ነው፡፡ ከሐገሩ ድንበር ተሻግሮ የዓለምን ወይም የአፍሪካን ሰላም በማስከበር ድንቅ ታሪኩ የሚታወቀው፤ የአፍሪካ ህዝቦች አለኝታ የመሆን ዝናን ያተረፈው፤ በዓለም ህዝብ ፊት ጅግንነቱን ደጋግሞ ያረጋገጠው፤ በወታደራዊ ሥነ ምግባሩ ምስጉን የሆነው፤ በህዝባዊ ባህርይ የታነጸው፤ ለጠላቱ መደንግጽ – ለወዳጁ መከታ ሆኖ የሚታየው፤ ነጻነቱን ሳያስደፍር ጸንቶ የመኖር አኩሪ ገድል ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ ያፈራው፤ ሰላም ለማስከበር በተሰማራበት አካባቢ ሁሉ ጥልቅ የህዝብ ፍቅር እያተረፈ የሚመለሰው፤ በሰላም እጦት ለተቸገሩ ህዝቦች ፈጥኖ የመድረስ ድንቅ ታሪክ የገነባው፤ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ቀን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በጅግጅጋ በደማቅ ሥነ ስርዓት ተከበረ፡፡

 

በዚሁ ክብረ በዓል፤ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) አካል ለሆነች አንዲት ሻምበል ሽልማት ተሰጥቶ ነበር፡፡ በሐገረ – ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብ የተሰኘው አሸባሪ ቡድን በመደምሰስ፤ የሶማሊያ ህዝብ እና መንግስት የሚያደርጉት ሐገርን መልሶ የመገንባት ጥረት ለመደገፍ ስትንቀሳቀስ ታላቅ የጀግንነት ገድል ለፈጸመች አንዲት ሻምበል ሽልማት የተሰጠበት በዓል ነበር፡፡

 

ሐልጋን ከተባለች ከተማ አቅራቢ ባለ የጦር ሰፈር በምትገኘው 134ኛ ረጅመንት ጥቃት ለመሰንዘር፤ ዓመት ሙሉ ዝግጅት አድርጎ ከሌሊቱ አስር ሰዓት አካባቢ የመጣው የአሸባሪ ቡድን ጀሌ፤ እንደ ቅጠል ረግፎ፤ ይዞት የመጣውን መሣሪያ አስረክቦ፤ ለወሬ ነጋሪ ያህል ጥቂቶች በሽሽት ከማምለጣቸው በስተቀር፤ ኃይሉ ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ የተበታተነበት ውጊያ ተካሂዶ ነበር፡፡ የዚህች ረጅመንት አባላት የጀግንነት መንፈስ፣ የሐገር ፍቅር፣ ጽናት፣ ወንድማዊ የመተጋገዝ እና የመደጋገፍ መንፈስ፣  ወትሮ ዝግጁነት፣ ወታደራዊ ቁመና ሁሉ በቴሌቭዥን መስኮት የመመልከት ዕድል ያገኘውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያኮራ መስተንክራዊ ድል ነበር፡፡ የዚህ ጀግና ሠራዊት ወገን ነኝ ማለት ያኮራል፡፡   

 

ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ የሠራዊቱን ክንድ የቀመሰው አል-ሸባብ፤ የጀግና መከላከያ ሠራዊታችን አንድ ኃይል በመደምሰስ ታሪክ ለመስራት እና የውጊያ ሞራሉን መልሶ ለመገንባት አሰበ፡፡ ያዋጣኛል ብሎ ያሰበውን የማጥቃት ስልት ነድፎ፤ በማዕከላዊ ሶማሊያ ‹‹ሐልጋን›› በተሰኘች ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የሠራዊታችንን የጦር ሠፈርን ለማጥቃት ተንቀሳቀሰ፡፡

በማዕከላዊ ሶማሊያ፣ በሂራን አውራጃ፤ ከዋና ከተማዋ ሞቅዲሾ 300 ኪሜ ርቀት ርቃ የምትገኘውን ረጅመንት ለማጥቃት የተንቀሳቀሰው አሸባሪ ቡድን የተመኘውን ክብር ሳይሆን የለመደውን ውርደት ተከናንቦ ተመለሰ፡፡ አልሸባብ ሰኔ 10/2008 ዓ.ም ባካሄደው ጥቃት 350 ሙት፤ 59 ቁስለኛ ሆኖ ሽንፈት ተከናንቦ ተለመሰ፡፡

ይህን ገድል በመስራት ‹‹ሁለተኛ ደረጃ የአድዋ ሜዳይ›› ተሸላሚ የተደረገውችው 134ኛው ረጅመንት፤ በጅግጅጋ ከተማ በተከበረው አምስተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን (ማክሰኞ፣ 2009) ተሸልማለች፡፡ በዕለቱ በጅግጅጋ ተገኝተው ለጀግኖቹ ሽልማት የሰጡት የኢፌደሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ አልሸባብ በተሰኘው ኢስላማዊ አሸባሪ ቡድን ላይ ታላቅ ኪሳራ በማድረስ የድል ብስራት ባበሰሩት ጅግኖች መካከል መገኘቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ነበር፡፡ የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ሳሞራ የኑስም፤ በውጊያው 15 አውቶማቲክ መሣሪያ፣ 13 ላውንቸር፣ 4 ሞርታር፣ 5 ካሜራ፣ 21 ፈንጅዎች፣ እና የመገናኛ መሣሪያ ገልጸዋል፡፡

        

ታዲያ ‹‹ስለኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ሲታሰብ ድንቅ ነገር ሆነው የሚታዩኝ አንዳንድ ነገሮች አሉ›› ሲል የጻፈ ሮበርት ቤክሁሰን (ROBERT BECKHUSEN) የተባለ አንድ ጸሐፊ፤ ‹‹የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በንጽጽር በጣም ዝቅተኛ በጀት የሚጠቀም ሆኖ ሳለ በጣም ከፍተኛ ብቃት ያለው ሠራዊት ነው›› ይላል፡፡ ይህ ሠራዊት በአደገኛ አህጉራዊ ቀጠና የምትገኘውን ኢትዮጵያ ሐገሩን በአስተማማኝ ከጠላት ጥቃት መጠበቅ የቻለ ሠራዊት ነው፡፡

 

ኢትዮጵያ አካባቢውን የማተራመስ ፍላጎት ያለው የኤርትራ መንግስት ጎረቤት ሆና፤ እንደ አልሸባብ ላሉ አሻባሪዎች መናኸሪያ ከሆነችው ሶማሊያ እና የእርስ በእርስ ጦርነት አውድማ የሆነችው የደቡብ ሱዳን ጎረቤት ሆና፤ ሰላም የሰፈነባት ሐገር ለመሆን የቻለችው በጀግናው የመከላከያ ሠራዊቷ ነው፡፡

 

ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ መዓት ተከብባ፤ አንጻራዊ ሰላም በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ልማት ማዕከል ለመሆንና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የቻለችው ጠንካራ የሰላም ሠራዊት በመገንባቷ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአሸባሪ ቡድኖች ዘግናኝ ጥቃት ሳይደርስባት መቀጠል የቻለችው፤ አሸባሪው ቡድኖች ጥቃት ሳይሰነዝሩ ቀርተው አይደለም፡፡ ይልቅስ ከሁኔታዎች ተጨባጭ ትምህርት በመውሰድ፤ ሐገሪቱን ከጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችል ብቁ ሠራዊት መገንባት በመቻሏ ነው፡፡

ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት፤ (በሜይ 14፣ 2014 ዓ.ም)፤ ‹‹ኢትዮጵያ በክፉ የሚያያትን ሁሉ የሚያርድ እና የሚያንቀጠቅጥ መደንግጽ ያለው ሠራዊት ባለቤት ነች›› ሲሉ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮጳ ህብረት ተወካይ፣ አሌክሳንደር ሮንዶስ (Alexander Rondos) በአንድ ጉባዔ ተናግረው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከያ በጀት ከሐገሪቱ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት (GDP) ያለው ድርሻ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

የኢትየጵያ ወታደራዊ በጀት በአማካይ 0.8 አካባቢ እንደሚሆን የሚናገሩተቋማት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሚያገኘው ወታደራዊ በጀት ከግርጌ ሲሆን፤ በብቃቱ ከራስጌ ነው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በጀቱ በአፍሪካ ደረጃ ሲታይ በቂ የሚባል መሆኑን የጠቀሰው አንድ የስውዲን የምርምር ተቋም (Stockholm International Peace Research Institute)፤ ኢትዮጵያ  ‹‹ባለፉት አስር ዓመታት የመከላከያ በጀታቸውን ከቀነሱ ጥቂት የአፍሪካ ሐገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች›› ይላል፡፡

‹‹ይሁንና በአፍሪካ ጠንካራ ከሚባሉ የመከለካያ ሠራዊት አንዱ የኢትዮጵያ ነው፡፡ ምናልባት ግብጽ፣ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ወደረኛ ሊሆኑት ይችሉ ካልሆነ ሌላ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ሆኖም እነዚህ ሦስት ሐገሮች የሚመድቡት ወታደራዊ በጀት ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርት ምጣኔ ሆነ፤ በእቅጩ የዶላር መጠን ከኢትዮጵያ በእጅጉ የላቀ ነው›› ይላል፡፡

በ2014 ዓ.ም በአውሮፓ በተካሄደ አንድ የደህንነት ጉዳዮች መድረክ (European Security Round Table) ተሳታፊ የሆነበሩ አንድ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የገዛ ድንበሩን ተሻግሮ ሰላም የማስከበር ብቃት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹አሸባሪዎችን ለመቅጣት የሚያስችል ብርቱ ክንድ ያለውን ይህን ሠራዊት ማንም ሊተነኩሰው አይሞክርም›› ማለታቸውን አንዳንድ ጋዜጠኞች ጽፈው ነበር፡፡

ወታደራዊ ጉዳዮችን የሚከታተሉ አንዳንድ ተቋማት ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርቷ ከሁለት በመቶ ያነሰ በጀት የምትመድብ ሐገር፤ ከፍተኛ በጀት ከሚመድቡ ሐገራት ጋር የላቀ ወታደራዊ ብቃት እና ጥንካሬ ለመያዝ መብቃቷ አስገራሚ ነው ይላሉ፡፡ ኤርትራ ከዓመታዊ ምርቷ 6.3 በመቶውን ለመከላከያ ትመድባለች፡፡ ጅቡቲ 3.8 በመቶ፣ ግብጽ 3.4 በመቶ ሱዳን 3.0 ኬንያ ከዓመታዊ ሐገራዊ ምርቷ 2.8 በመቶው ለመከላከያ ትመድባለች፡፡

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ከጥይት ጀምሮ ሙሉ ትጥቁን፤ ከባድ መሣሪያ የሚጭኑ መኪናዎችን፣ ታንኮችን እና ሔሊኮፕተሮችን ራሱ ያመርታል፡፡ የሐገር መከላከያ የሚያስተዳድራቸው እንደ ሜቴክ ያሉ (Metals and Engineering Corporation (MeTEC) የወታደራዊ ኢንዱስትሪ ተቋማትን የገነባ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ራዕዩ፤ መከላከያ የራሱን በጀት ራሱ የሚችል ከመሆን ተሻግሮ፤ ለሐገሪቱ ገቢ የሚያስገኝ ተቋም መሆን ነው፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባቋቋመው ዩኒቨርሲቲ፤ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን እና የሠራዊቱ አባላትን እየተቀበለ በዲግሪ መርሃ ግብር ተማሪዎችን ያሰለጥናል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ስኬት የተመሠረተው፤ የሠራዊቱን አባላት ክህሎት ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ እና ዘመናዊ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በሐገር ውስጥ ተቋማት ለማምረት ሥራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ ነው፡፡ በመሆኑም፤ ኢትዮጵያ በሐገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና የማሳያሳድር ብቃት ያለው ሠራዊት ለመገንባት ጥሩ አብነት የሚሆን ሥራ ሰርታለች፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ስኬት ምስጢር ለስልጠና ትኩረት መስጠቱ፤ የሚታጠቀውን የጦር መሣሪያ ራሱ የሚያመርት መሆኑ፤ እየወደቀ እና እየተነሳ ከልምድ ለመማር ዝግጁ ሆኖ ትልልቅ ሥራ መስራቱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሠራዊቱ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚታጠቃቸውን መሣሪያዎች የሚያመርት ሆኗል፡፡

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ የሶማሊያን መንግስት ለመደገፍ በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) አባል ሆኖ ሲሰራ የተከበረ ዝና ያለው ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት፤ ከአልቃይዳ ጋር ትስስር ያለውን አል-ሸባብን ለመደምሰስ በሶማሊያ 22 ሺህ የመከላከያ እና የፖሊስ ኃይል አባላትን ያሉት የሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማርቷል፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የሰላም ሠራዊት ነው፡፡