የጥልቁ ተሀድሶ ትሩፋቶች:- ባለፌክ ዲግሪዎቹ ሲጋለጡ

በመላው ሀገሪቱ ጥልቅ ተሀድሶ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ተሀድሶው በብዙ ክልሎች በስልጣን ላይ የነበሩ ሹሞችን ከላይ እስከ ታች እንዲቀየሩ ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ ዝቅ ብለው እንዲሰሩና በሕግ መጠየቅ ያለባቸውም በሕግ እንዲጠየቁ እያደረገ ነው፡፡ ተሀድሶው በመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰራተኞችና ተቋማት በከፍተኛ፣ መካከለኛውና ዝቅተኛው አመራር፤ በቀበሌም በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር በተደረገ ግልጽ ወይይት እየተካሄደ ሲሆን፤ በእስካሁኑ ሂደትም በርካታ ጉዶችን ለአደባባይ አብቅቷል። ይህ ጥልቅ ተሀድሶ ይፋ ካደረጋቸው ቅሌቶች አንዱ ፌክ ባለዲግሪዎችን ማጋለጣቸውና አንድ፣ ሁለት . . . ተብለው ከየቢሮው እየተለቀሙ ወደ አደባባይ እንዲወጡ ማድረጉ ነው።

የሀሰት የትምህርት ማስረጃ፣ ዲግሪና ማስትሬት ይዘው አይናቸውን በጨው አጥበው ሀገርና ሕዝብን ለአመታት በስልጣን ወንበር ተቀምጠው ሲመሩ የነበሩ ሰዎች በጋምቤላው የተሀድሶ መድረክ ሰሞኑን መጋለጣቸው ሀገርን ጉድ አሰኝቶ ከረመ፡፡ ጋምቤላ እንደመነሻና መንደርደሪያ ማሳያ ይሁን እንጂ ችግሩ በጋምቤላ ብቻ እንደማያበቃ በጋምቤላም ብቻ የሚታይ እንዳልሆነ ልብ ልንለው ይገባል፡፡

ሀገርና ትውልድ ገዳይ የሆኑ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ወረቀቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በሀገራችን እንደጉድ ተቀፍቅፈዋል፡፡ ሀገሪቱ በእውቀት የበለጸገና የታነጸ፣ ችግሮችዋን በየመስኩ ሊፈታ የሚችል ዜጋ ነው የምትፈልገው፡፡ የሀሰት ዲፕሎማ፣ ዲግሪ፣ ማስትሬትና ፒኤች ዲ የተሸከመ አያሻትም፡፡ እውቀት በልፋት፣ በድካም፣ በመስራት፣ ብዙ በመጣር የሚገኝ እንጂ በየመንደሩ የሚቸረቸር የጉልት ሸቀጥ አይደለም። ይህ ያልገባቸው ግን በየስርቻው ሲገበያዩት ይስተዋላሉ።

እውቀትና ሙያ በዘረፋና በማጭበርበር ሊገኝ አይችልም፡፡ በትምህርቱም መስክ ያልደከሙበትን በዘረፋ መልክ የሚሰበስቡ እልፍ ሙሰኞች፣ እልፍ ኪራይ ሰብሳቢዎች በጋምቤላ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ለምሳሌ ከጥቂት አመታት በፊት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንድ ጊዜ በተደረገ ማጣራት ብቻ 19 የሀሰት ባለዲግሪዎች መያዛቸው አይዘነጋም።

መቸም አንዴ ፍርጃ ነው እንበልና ለዚህም አንድ ብሄራዊ ኮሚቴ ማቋቋም ሊኖርብን ነው፡፡ ሁሉንም በሀገሪቱ ያሉ የትምህርት ማስረጃዎችን የሚያጣራ፤ ባለዲግሪዎችን የሚመረምር፡፡

እንደሚታወቀው፣ መንግስት የሚማር ሰው ሁሉ እንዲማር ትልቅ እድልና በር ከፍቶአል፡፡ ታዲያ ሳይማሩ ተምረናል በሚል የሀሰት ማስረጃ መሰብሰቡን ምን አመጣው? ይህ ካልሆነም በረዥም ግዜ የስራ ልምድ ራስን በማብቃትና ከፍተኛ እውቀት በማካበት የጠለቀ እውቀት ባለቤት መሆንም ይቻላል፤ አውቆ ለመገኘት እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ይህን ስንመለከት ተሀድሶውን በስፋት ማስቀጠልና የማጥራቱ ዘመቻ ሳይድበሰበስና ሳይደበዝዝ  በስፋት መቀጠል እንዳለበት እንገነዘባለን፡፡ ዛሬም በሽፍንፍን የታለፉ ሆን ተብሎም ሳይነኩ የተዘለሉ ግን ደግሞ በየመስሪያ ቤቶቹ ሲመዘብሩና ሲዘርፉ የነበሩ ሰዎች እንዳሉ ማስረጃዎቹ በግልጽ የሚታወቁ ሁነው ሳለም በመረብ (ኔትወርክ) ተጠልለው ሳይነኩ ያለፉ መኖራቸው አነጋጋሪ ሆኖአል፡፡ ማስረጃ ከተገኘ የሚለው አባባል ማስረጃው በመንግስት እጅ እያለ ማንን ነው መልሰው የሚጠይቁት የሚለውም የውይይት  ርእስ  ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

በሙሰኛው፣ በኪራይ ሰብሳቢውና በመልካም አስተዳደር በፍትሕ እጦት ሲንገላታ የነበረውን  ሕዝብና ብሶቱን ለመፍታት ገና ሂደቱ ተጀመረ እንጂ እልፍ አላለም፡፡ ዛሬም ሙሰኞቹ ዘራፊዎቹ ዳር ቁመው እያላገጡ ነው፤ አልተነኩም የሚለው የሕዝብ አስተያየት ሚዛን ይደፋል፡፡ ቢሆንም አበረታች ጅምሮች እየታዩ ነው፡፡ በሁሉም ክልሎች ሕዝቡን በበደሉና ባስከፉት ላይ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ይበል የሚያሰኝ ነውና ይህ ህዝቡ እያነሳው ያለው ጉዳይመ በሂደት ይመለሳል የሚል ተስፋ አለ፤ ልክ እንደፌክ ባለዲግሪዎቹ ሁሉ፡፡

ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ያልተሰማራበት፣ ያልገባበት፣ እጁ የሌለበት ማጭበርበር፣ ማታለል፣ ማወናበድ . . .  ምንም አይነት መስክ የለም፡፡ መንጃ ፈቃድና ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ ሀሰተኛ የቤትና የቦታ ካርታ ከማውጣት ጀምሮ የመንግስትን ማሕተም በተመሳሳይ እያሰራ በብዙ መስኮች ታላላቅ የሚባሉ ውንብድናዎች በመንግስትና በሕዝብ ላይ ፈጽሞአል፡፡

በትምህርቱ ረገድ የትምህርት ስርአታችንን እንደገና በጥልቀት መፈተሸና መመርመር ይገባናል። አጠቃላይ ሁኔታው መጠናት ያለበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ በተለይ በአብዛኛው የግል የትምህርት ተቋማት ሀሰተኛ ዲፕሎማና ዲግሪ በሽያጭ ያለእውቀትና ትምህርት ክፍል ሳይገባና ሳይማሩ ጭምር እንደሸቀጥ መቸብቸባቸው አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የከፋ ብቻ ሳይሆን ሀገርና ትውልድ ገዳይ ወንጀል ነው፡፡ በሕብረተሰቡና በሀገሪትዋ ላይ የሚያደርሰውም አደጋ የከፋ ነው፡፡ አሁን አሁን፣ በተለይ ከፌክ ዶክተሩ ዘሚካኤል ወዲህ ፎርጅድ ዲግሪ፣ ፎርጅድ ማስትሬት፣ ፎርጅድ አስተሳሰብ፣ ፎርጅድ ምሁርነት፣ ፎርጅድ ማንነት ተንሰራፍቶ ሞልቶ ፈሷል፡፡ በቅጡ መስራትም ሆነ ማንነታቸውን መግለጽ የማይችሉ፤ በቅጡ አንዲት ገጽ ወይንም ስማቸውን እንኳን አስተካክለው የማይጽፉ ሰዎች ባለዲፕሎማ፣ ባለዲግሪ፣ ባለማስትሬት ለመሆን በቅተዋል፡፡

መንግስት ሀገሪትዋ የተማረና የበቃ የሰው ኃይል እንዲኖራት እጅግ ብዙ ሰርቶአል፡፡ እየሰራም ነው፡፡ ግን ግን በውስጡ ያለው ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል ደግሞ በዚህ መልኩ ሀገሪትዋንና ትውልዱን እየገደላት ይገኛል፡፡ መንግስት ለትምህርት ባለው ቁርጠኝነት ላይ ምንም ክርክር የለም፡፡ የትምህርት ስርአቱ እንዲበላሽ እያደረገ ያለው ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ ውስጥ ተዘፍቆ የሚልከሰከሰው ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ክፍል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንዲህ አይነት የአካዳሚክ እውቀትን አውርዶና አፍገምግሞ በትምህርት ማእረግ ላይ የተቀለደበት የተሳለቁበት የተረገጠበት ግዜ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ለዚሁ ብለው በየሽርንቁላው በስውር የተመሰረቱ፤ በድብቅ ዲፕሎማ፣ ዲግሪ ማስትሬት ለፈለገው ሰው በገንዝብ የሚሸጡ አላማቸው ገንዘብ መሰብሰብ እንጂ ስለሀገርና ስለሕዝብ ምንም ደንታ የሌላቸው የሰው አሳማዎች ለቁጥር በሚያታክት መልኩ ተቀፍቅፈዋል፡፡ ዲግሪ፣ ማስትሬትና ሌሎችንም እየሰሩ  መሸጥን የጉሊት ንግድ ያደረጉ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል ባለመሆኑ መንግስት በጋምቤላዎቹ ብቻ ሳይወሰን የተጠናከረ አርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

በኔትወርክ ስራ የሚያስቀጥሩ ስውር ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች በአዲስ አበባም በክልሎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሕክምና ሳያጠኑ ዶክተሮች፣ ነርሶች፤ አስተዳደር ሳያጠኑ የማኔጅመንት ተመራቂዎች፤ መደመርና መቀነስ ሳይችሉ የአካውንቲንግ  ተመራቂዎች፤ የኮንስትራክሽን እውቀት ሳይኖራቸው መሐንዲሶች፤ በስፋት የታዩበት የወርደት ዘመን ቢኖር ይህ ዘመን ማለት ይቻላል፡፡

አልፈው ተርፈው እንደጋምቤላዎቹ ሀላፊዎች የሀሰት የትምህርት ማስረጃ ይዘው ለአመታት ሕዝብን ሲመሩ የኖሩትን ስንትና ስንት አመት የበሉትን የመንግስት ደሞዝና በሀሰት የተሰሩትን ስራዎች ማስታወስ እንደሀገርና እንደሕዝብ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ ጋምቤላን እንደማሳያ እንውሰድ እንጂ ችግሩ ሁሉም ጋር ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም።

ከአዲስ አበባ ጀምሮ በክልሎች ሁሉ ፎርጀሪ የትምህርት ማስረጃ ሀገሪትዋን እንደ አረም እንደወረራት መንግስት ካላወቀ በመንግስትነት ቦታው በወንበሩ የለም የማለት ያህል ነው፡፡ ድሮ አባቶች ከመጠምጠም መማር ይቅደም የሚሉት ሳይማሩ ወንጌሉንና ስርአቱን ሳያጠኑ መቀደሱን ሳያውቁ ቄስ መሆን አይቻልም ማለታቸው ነበር፤ ይህ የአባቶቻችን አባባል ለዚህ፣ ለአሁኑ ዘመን አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡

በጋምቤላ ክልል ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተገኘባቸው ዘጠኝ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ ከስራ መባረራቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ማስታወቁ ለሌሎችም በማስጠንቀቂያነት የሚያገለግልና ትምህርት ሰጪ፤ ክልሎች ራሳቸውን ምን ያህል የፌክ ባለዲግሪዎች ዋሻ አለመሆናቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኡማን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የጋምቤላ ሕዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ጋህአዴን ከጥር ወር አጋማሽ አንስቶ ባካሄደው ጥልቅ ተሀድሶ ማጣራት ከተካሄደባቸው ከ201 የክልሉ  ከፍተኛ ስራ አመራሮች ውስጥ ዘጠኙ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው ተገኝተዋል። ከነዚህም ውስጥ ቀደም ሲል የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ አሁን ደግሞ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ቱት ጆክ፣  የክልሉ  የኮንስትራክስን ቢሮ  ኃላፊ   ጋትዊች ዋር   እና – የክልሉ መገናኛ ብዙኃን መረጃ ነፃነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ፖል ጆክ  እንዲሁም  የክልሉ ዋና ኦዲት  መስሪያ ቤት ምክትል ኦዲተር ኚሙሉ ኦጋኒ፣ የክልሉ መስተዳደር  ምክር ቤት  የመሰረተ ልማት አማካሪ ቾል ኮር  እና  የክልሉ መስተዳደር የአስተዳደርና ማሕበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሳይመን ጋትልዋክ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንደተገኘባቸው ተረጋግጦአል፡፡ ይህ ድርጊት ምን ያህል አሳፋሪ ምን ያህል በሀገር ደረጃ አንገት አስደፊ ወንጀል እንደሆነ ለማንኛችንም ግልጽ ነው፡፡  

በተጨማሪም በጤናና ጤና ነክ  ሴቶች ኤጄንሲ የሴቶች ዩኒት አስተባባሪ ሜሪ ኛንዌር ዶክ፣ የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር  ጽሕፈት ቤት የሴቶች ዩኒት ኃላፊ  ኙዌች ጋችሉል እና  በክልሉ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ  የመንገድ ዩኒት አስተባባሪ ኛዬር ሉልዴንግ  ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው በመገኘታቸው በጥልቅ ተሀድሶው መድረክ ተጋልጠዋል፡፡ የተሀድሶው መድረክ በሁሉም ክልሎች በሁሉም መስሪያ ቤቶች ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል የምንለው ለዚህ አይነቱ ሽፍንፍን ቅሌት አደባባይ መውጣት ስንል ነው፡፡ ሀገርንና ህዝብን ለማዳን ሲባል ደሞ ከዚህም በላይ ርቀት መሄድ ይገባል፡፡

ከፍተኛ የመንግስት አመራሮቹ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ/ማስትሬት ዲግሪ ድረስ ይዘው በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ለዓመታት ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸው ታውቆአል፡፡ እስከዛሬ ላደረሱት በደል፣ ለፈጸሙት ወንጀል መንግስት በሕግ እንደሚጠይቃቸው ግልጽ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም፣ ከክልል እስከ ቀበሌ የስራ አስፈጻሚዎች እና ባለሙያዎች ድረስ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የሰሞኑ የሕዝብ አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡ 

በጋምቤላ ክልል አሁንም የሌሎች 328 አመራሮችና ባለሙያዎች የትምህርት ማስረጃ እየተጣራ መሆኑን አቶ ኦኬሎ አስታውቀዋል፡፡ መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት በሚያደርገው ጥረት ሕዝቡና ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉበት ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡

የጋምቤላው አስደንጋጭ ዜና ከወዲሁ ካልተገታ ሀገርና ትውልድ ገዳይ ታላቅ በሽታ በመሆኑ ወዴት እየሄድን ነው ብሎ ቆም ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ወዴት እየሄድን ነው??