ከትክክለኛ ፖሊሲ የተገኘ ወጤት

ኢትዮጵያ የአርሶና አርብቶ አደር አገር ነች። 85 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ በእርሻና በከብት እርባታ የሚተዳደር ነው። ኢትዮጵያን ካለአርሶና አርብቶ አደር ማሰብ አይቻልም። አርሶና አርብቶ አደሩን የዘነጋ የተሳሳተች ኢትዮጵያን ነው የሚመለከተው። አረሶና አርብቶ አደሩነ ዘንግቶ ኢተዮጵያን መገንዘብ አይቻልም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ ታሪክ የአርሶና አርብቶ አደር ታሪክ ነው። ይሁን እንጂ ባለፉት ሥርዓቶች ለዚህ እውነታ ሙሉ እውቅና አልተሰጠውም። የኢትዮጵያን አርሶ አደር የአገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑ፣ የአገሪቱ የመበልጸግ አለመበልጸግ እጣ ፈንታ በአርሶና አርብቶ አደሩ ሀብት ማፍራት አለማፍራት የሚወሰን የመሆኑ ጉዳይ ትኩረት አልተሰጠውም።

በፊውዳላዊው ዘውዳዊው ሥርዓት አርሶ አደሩ ለመሳፍንቱ፣ መኳንንቱና ሌሎች ባለርስትና ባለጉልት የሥርዓቱ ባለሟሎች ያደረ ገባር ነበር፤ ገበሬ የሚሉትም ለዚህ ነበር። አርብቶ አደሩ ደግሞ ለግብርም ለአገዛዝም የማይመች ተዘዋዋሪ በመሆኑ ዘላን ይሉታል። ምንም ዓይነት የመንግሥት አገልግሎት አግኝቶ አያውቅም ነበር፤ እንደ ዜጋም ታስቦ አያውቅም።

በወታደራዊው ደርግ የሥልጣን ዘመን አርሶ አደሩ የራሱ አነሰተኛ መሬት እንዲኖረው ተደርጎ ከርስት አልባ ገባርነት እንዲላቀቅ ተደረጓል፤ በ1967 የካቲት ላይ በታወጀ የመሬት ለአራሹ አዋጅ። ይሁን እንጂ ሌላ አስገባሪ ተጭኖበት ነበር፤ የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት የሚባል። የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት ወታደራዊው መንግሥት ለከተሜው ሸማች  በርካሽ ዋጋ የምግብ ሰብል በማቅረብ በሥርዓቱ ላይ ሊነሳ የሚችለውን ተቃውሞ ለማፈን ከአርሶ አደሩ ላይ በግዳጅ እህል የሚሰበስብበት አሠራር ተዘርግቶ ነበር። በዚህ አሠራር አርሶ አደሩ የማምረት አቅሙን፣ የእርሻ በሬና መሣሪያ ያለው መሆን አለመሆኑን፣ የመሬቱን ለምነትና የአየር ንበረት ለውጥ ባላገናዘበ ሁኔታ በምርት ዓይነትና መጠን ተወስኖ ለእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት እንዲያቀርብ ግዴታ ተጥሎበት ነበር። አርሶ አደሩ ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ ግዴታውን ለማሟላት ምርቱን ለእርሻ ሰብል ገበያ ያቀርባል። ያመረተው ምርት በዓይነትም ይሁን በመጠን የተጣለበትን ግዴታ ማሟላት ካልቻለ ከብቶቹን ሸጦ በውድ ዋጋ ከገበያ ገዝቶ ከስሮ የተጣለበትን ግዴታ ያሟላል። ይህን ማድረግ ካልቻለ ይታሰራል።

በዘውዳዊው ሥርዓት አርሶ አደሩ አርሶ የሚያገኘው ምርት ባለቤት ስላልሆነ ምርታማነቱን የማሳደግ ተነሳሽነት አልነበረውም። በዘውዳዊ ፊውዳላዊ ሥርዓት ባለርስቱ ገባሩን አርሶ አደር ከበሬው ለይቶ እንዲመለከተው የሚያደርግ ሁኔታ አልነበረም። በወታደራዊው ደርግም ቢሆን አርሶ አደሩ ከተሜው በኑሮ ውድነት ሣቢያ ተቃውሞ እንዳያሰማ ቀለቡን ከሚያስችል መሣሪያነት የተለየ አልነበረም። ከዚህ በተጨማሪ ሥርዓቱ በየአቅጣጫው ለገባበትን ጦርነት ተዋጊ ኃይል በገፍ የሚዝቀው ከአርሶ አደሩ ነበር። በመሆኑም የአርሶ አደሩን ህይወት ማሻሻል የሁለቱም ሥርዓቶች ቀዳሚ ጉዳይ አልነበረም። የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችል አንድም ድጋፍ አይደረግም፤ በዘውዳዊው ሥርዓት አርሶ አደሩን መደገፍም አይቻልም ነበር፤ የምርቱ ባለቤት ባለመሆኑ።

ይሁን እንጂ በሁለቱም ሥርዓቶች የአገሪቱ ኢኮኖሚ በገጠርና በግብርና ላይ የተመሠረተ ነበር። ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የሰው ኃይል በገጠር የሚኖር አርሶ አደር ነበር። ከ80 በመቶ የማያንሰው የአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርትና የወጪ ንግድ ከግብርና የሚገኝ ነበር። እናም የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ማሻሻል፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፉን መፍጠርና ማጎልበት የሚያስችል የካፒታል ክምችት መፍጠር ይቻል የነበረው ከዚሁ የግብርና ዘርፍ ነበር። ይህ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እምቅ አቅም ያለበት የግብርና ዘርፍ ግን ተረስቶ ነበር። እናም ኢኮኖሚውን ማሳደግ፣ የህዝቡን የድህነት ደረጃ ማሻሻል ሳይቻል ቀርቷል።

የአገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት የሆነውን ግብርና ትቶ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፉን ለመፍጠርና ለማሳደግ መሞከር ጉም እንደመዝገን የሚቆጠር ነው። ያለፉት ሁለት ሥርዓቶች አገሪቱን ከማሳደግ ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድታሽቆለቁል ላደረገ ሁኔታ እንዲዳርጓት ያደረጋው አንዱ ምክንያት ለግብርናው ዘርፍ ልማት ትኩረት መንፈጋቸው ነው።

ይህ ሁኔታ ከደርግ ውድቀት በኋላ ተቀየረ። የአገሪቱን ዜጎች ህይወት ማሻሻልና የመኖር ዋስትናን የማረጋጋጥ ጉዳይ አርሶና አርብቶ አደሩን ትቶ እንደማይታሰብ፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግም ገጠርን፣ አርሶ አደሩንና ግብርናን ትቶ እንደማይታሰብ ከግንዛቤ ተወሰደ። እናም የአገሪቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ፖሊሲዎች ገጠርና ግብርና ላይ እንዲያተኩሩ ተደረገ።

የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ርምጃ በቀን አንዴ መመገብ የማይችል የነበረውን ህዝብ በተለይ አርሶ አደር በቀን ሦስቴ እንዲመገብ ከማስቻል ሲጀምር ገጠርና አርሶ አደሩን በማሰብ ነበር። በአነስተኛ ማሣ ላይ የተመሠረተውን ግብርና ምርማነት በማሳደግ አርሶ አደሩ ራሱን በወጉ እንዲመገብ የማድረግ ሥራ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ‘ሀ’ ብሎ ተጀመረ። በመጀመሪያ አርሶ አደሩ የተሻሻለ የግብርና ቴክኖሎጂን እንዲለማመድ፣ በድጎማ በተመጣጣኝ ዋጋ በብድር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲያገኝ ተደረገ። የብድር አቅርቦት ሥርዓትም ተዘረጋ። እነዚህ ርምጃዎች የኢትዮጵያ አርሶ አደር አስሮት የኖረውን የድህነት ቀለበት መፈልቀቅ እንዲጀምር፣ የግብርናን ያህል ካረጀ የእርሻ ሥልት መላቀቅ እንዲጀምር አደረጉ። ይህን ተከትሎ ምርታማነቱ ማደግ ጀመረ። ከምርታማነቱ ዕድገት ጋር ገቢውም ያሻቅብ ጀመር።

አርሶ አደሩ ገቢው ማደግ ሲጀምር በቀን ሦስቴ በወጉ መመገብ ጀመረ። ከዚህም አልፎ ቀደም ሲል ለከተሜዎች ብቻ የተፈቀዱ ይመስሉ የነበሩ የፋብሪካ ውጤት የሆኑ የፍጆታ ምርቶችን – የምግብ ዘይት፣ ሣሙና፣ ላምባ . . . የዘወትር ፍጆታው ማድረግ ጀመረ። በዓመት አንድ ልብስ መቀየር ይቸግረው የነበረ፣ የረባ የሌሊት ልብስ ያልነበረው አርሶ አደር የተሟላ የአዘቦትና የክት ልብስ፣ የሌሊት ልብሰ ኖረው። ለከተሜ ብቻ የተፈቀደ ይመስል የነበረውን ጫማ መጫማትም ጀመረ። ከተማ ሲወጣ ከከተሜዎች ጎን ተቀምጦ መዝናናትን ተለማመደ።

እያደረ ይህንንም አለፈ – ሃብት ማጠራቀም። ልጆቹን ከተማ ልኮ ማስተማር፣ የቆርቆሮ ክዳን የመኖሪያ ቤት መገንባት፣ የከብት በረቱንና የጪስ ቤቱን ከመኖሪያው ቤት  መለየት ጀመረ። እየከረመ ከዚህም ያለፉ ወደባለፀጋነት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮች መፈጠር ጀመሩ። እነዚህ በአካባቢያቸው የእህል ወፍጮ አቆሙ፤ በከተማ የሚከራይ የመኖሪያ ቤት አስገነቡ፤ የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ መኪና ገዙ። አርሶ አደሩን በቀን ሦስት ጊዜ ራሱን እንዲመግብ ከማድረግ የጀመረው ገጠርና ግብርና ላይ ያተኮረው የልማት ፖሊሲ  አንድ ተኩል አሥርት ዓመታት ሳይሞላው በየአካባቢው በመቶ ሺህዎች፣ በሚሊየን የሚለካ ሃብት ያካበቱ አርሶ አደሮችን መፍጠር አስቻለ።

ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት በአርሶ አደሩ መኖሪያ አካባቢ የማህበራዊ አገልግሎት – የጤና፣ የትምህርት፣ . . .  እንዲስፋፋ አደረገ። ይህ ከአርሶ አደሩ ገቢ ማደግ ጋር ተዳምሮ የአርሶ አደሩን ህይወት ማሻሻል አስቻለ።

የአርሶ አደሩ ገቢ ማደግ በአርሶ አደሩ ህይወት መሻሻል የተገደበ አልነበረም። ትልቅ አገራዊ የገበያ አቅም ፈጥሯል። ይህ በአርሶ አደሩ ገቢ ማደግ የተፈጠረው የገበያ አቅም የአምራቹ፣ የንግዱና የአገልግሎት ዘርፉ ገበያ እንዲያድግ በማድረግ ትርፋማነታቸውን ከፍ አደረገ። ይህ ሁኔታ በየዘርፉ የኢንቨስትመንት ካፒታል ክምችት ፈጠረ። ይህ የካፒታል ክምችት እስካሁን አገር በቀል ባለሃብቱ በአምራች ዘርፍ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ ቢሆንም አገር በቀል ባለሃብቶች የተሳተፉበትን ያህል የማምረቻ ዘርፍ እንዲያድግ አድርጓል። በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የጎላ ድርሻ ያላቸው የአገልግሎትና የኮንስትራክሽን ዘርፎች እንዲፈጠሩና እንዲያድጉ ማድረግ ያስቻለ አቅም ፈጥሯል። ይህ የካፒታል ክምችት የተፈጠረው ከግብርናው ዘርፍ ነው።

ግብርና ላይ የተመሠረተው የኢንዱዱስትሪ ልማት ልማት ፖሊሲ በአርሶ አደሩ ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲታይ ከማድረግ ተነስቶ፣ አገራዊ የካፒታል ክምችት መፈጠርና ማሳደግ ሲጀምር መንግሥት በዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት ንቅናቄ ውስጥ የጎላ ድርሻ ያላቸውን የልማት ጀግና አርሶ አደሮች እውቅና መስጠት ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ በ1999 ዓ.ም  በቀን ሦሰቴ ራሳቸውን መመገብ ከመቻል ተነሰተው ወደባለፀግነት የተሸጋገሩና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያነቃቁ የልማት ጀግና ሞዴል አርሶ አደሮች በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጣቸው፤ ተሸለሙ። በ2003 ዓ.ም በ3ኛው ዙር የአርሶ አደሮች ቀን በርካቶች ከአርሶ አደርነት ወደአገር በቀል ኢንቨስተር ባለሃብትነት ተሸጋግረው መመረቅ ጀመሩ።

መጋቢት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ወደ ባለፀግነት የተሸጋጋሩና አገር በቀል ኢንቨስተር ባሃብትነት ደረጃ ላይ የደረሱ የልማት ጀግና ሞዴል አርሶ አደሮች ለ8ኛ ጊዜ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፤ በአዳማ ከተማ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ። እርሻን በማዘመን የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግርን እናፋጥን በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ በተካሄደው  ሥነ ሥርዓት ላይ 550 አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የህብረት ስራ ማህበራት፣ የጽህፈት ቤት ባለሙያዎች በልማት ጀግናነት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከእነዚህ መካከል 60ዎቹ ሴት አርሶ አደሮች ናቸው። የልማት ጀግና ሞዴል አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮቹ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ማፍራት የቻሉ ናቸው። ከዚሀ በተጨማሪ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ሃብት ያፈሩ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ደግሞ ወደ አገር በቀል ባለሃብትነት ተሸጋግረው ተመርቀዋል። ወደኢንቨስተር ባለሃብትነት ከተሸጋገሩት መሃከል በአንደኛ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ የተሸለሙት የ21 ሚሊየን፣ የ20 ሚሊየንና የ18 ሚሊየን ብር ሃብት ያፈሩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፈው ዓመት የተከሰተውን በ50 ዓመታት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መቋቋም የተቻለው በግብርናው ዘርፍ በተሰራው ሰፊ ሥራ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ የአገሪቱ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ውጤት ነው እየተባለ የሚነገርለት የድርቅን ተጽዕኖ በመቋቋም ረገድ የታየ ስኬት በዋናነት በአርሶ አደሩ የተገኘ መሆኑንና ይህም የግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ውጤት መሆኑን ያረጋግጣል። በአጠቃላይ በአርሶ አደሩ ህይወት መሻሻል የጀመረውና አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የዕድገት ሃዲድ ላይ አውጥቶ ወደትራንስፎርሜሽን በማምራት ላይ የሚገኘው ስኬት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን የትክክለኛ ፖሊሲና አፈጻፀም ውጤት ነው።