“ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የሃገራችን ህብረ ዜማ! የህዳሴያችን ማማ!”

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ 6ኛ ዓመት ህዝባዊ በዓል አከባበር ገና ከዋዜማው ደምቋል። የድምቀቱ መነሻ ምክንያትም የአገራችን ህብረ ዜማ! የህዳሴያችን ማማ ስለሆነ ነው። መሪ ቃሉም እንዲህ የሆነው በብዙ ምክንያቶች ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ እነዚህን ምክንያቶች መዘርዘር ተገቢ ነው።

በከፍተኛ የህዘብ መነሳሳትና ተሳትፎ የታጀበው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ  በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተከናወነ ነው፡፡ የግድቡን የግንባታ ሂደት ሥፍራው ድረስ ሄደው የጎበኙ ኢትዮጵያውያንም ስለግንባታው ፈታኝነት እና እኛው መሃንዲስ እኛው የገንዘብ ምንጭና እኛው ወዘተ… ስለሆንበት ፕሮጀክት የነበራቸውን ምልከታ በተለያየ መልኩ እና በጋለ ስሜት እየገለጹ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ግድቡን ስለመጎብኘታቸው በግንባታው ሥፍራ የሚገኙ ዶሴዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ለአገራችን ህዝብና ገንቢዎቹ ከፍተኛ መነሳሳትና መነቃቃት ከፈጠሩ ምክንያቶች መሃል በቀዳሚነት የሚጠቀስ እና የአገራችን ህብረ ዜማ፤ የህዳሴያችን ማማ የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን የሚያጠይቅ ነው፡፡

በግንባታው የስድስት ዓመታት ጉዞ እና የበዓሉ ዋዜማ ላይ እያስተዋልናቸው የሚገኙት ህዝባዊ ንቅናቄዎች ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ አብሳሪዎች ናቸው፡፡ በግንባታው ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሽንጣቸውን ገትረው ሌት ተቀን በመትጋት ላይ መሆናቸው ዋነኛው ማሣያ ነው፡፡ በራስ አቅም ለሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያውያንም ምናልባትም ከአቅማቸውም በላይ ለማለት በሚያስደፍር መልክ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑም በተመሳሳይ፡፡

"ጊዜ የለንም እንሮጣለን ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ 85 ሺህ ዜጎችን ያሳተፈ፣ በትግራይ 12፣ በአማራ 40 እና በኦሮሚያ 38 ከተሞች የተከናወነው ታላቅ ሩጫ ከእቅድ በላይ በወጣው ህዝብ መጥለቅለቁ እና ቲሸርት አልቆ በራሱ መለያ ህዝቡ መሳተፉ የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው። ከኅብረተሰቡ ከሚጠበቀው አጠቃላይ የግንባታ ወጪ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ወይም 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ስለዚሁ ማማነቱ ህና ህብረ ዜማነቱ ነው። ዋንጫው እየተዘዋወረ በሚገኝበት ደቡብ ክልል ብቻ በዚህ ሰሞን ከሦስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉም በተመሳሳይ። ህብረ ዜማነቱን እና ማማነቱ በሚዘከርበት በዚህ የዋዜማ ቀናት ገና ለሚከናወኑ በርካታ ዝግጅቶች እና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ህዝቡ ከወዲሁ በችኮላ መቁነጥነጡም የህዳሴያችን ማማነቱን እና የአገራችን ህብረ ዜማነቱን የሚያጠይቅ ነው።     

የአገራችንን የልማት ጉዞ በጥበብና በእውቀት ከማሳለጥ አልፎ ዛሬ መላው የአፍሪካ አገራት የታላቁን ግድብ ዱካ መከተል መጀመራቸውም ሌላኛው የህዳሴያችን ማማ የመሆኑ ማጠየቂያ ነው። ታላቁ ግድባችን ደምና ሥጋችን እንቁ ፕሮጀክታችን እንደሆነ ዓለም እየመሰከረ መሆኑም የአገራችን ህብረ ዜማ ለመሆኑ በቂ ምክንያት ነው። የአገራችንን የልማት ጉዞ ቁልጭ አድርገው ስለሚያሳዩ ግዙፍና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶቻችን ልምድ እየቀሰምንበት፤ ሞክሮም እየቀመርንበት፤ ይቻላልን የተረዳንበት፤ ልናወራቸውም መነሻና መንደርደሪያ የሆነን ይህ ፕሮጀክት የህዳሴያችን ማማ ነው። የአገራችንም ህብረ ዜማ ነው ስንለው፤ መቼም  የዓለማችን መልስ ልክ ብላችኋል እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

ይህ ፕሮጀክት የባለሙያዎቻችንን ላብ እየጨመቅን፣ የምሁራኖቻችንን እውቀት እየተነተንን፤ አገራዊ ደረጃችንን እየመዘንን ወዘተ…ብሄራዊ መነቃቃት እንድንፈጥርበት የተሰጠን የዘመኑ ስጦታችን ነው፡፡ ለሌሎች ፕሮጀክታችን እና ልማታዊ ጉዟችን ማጀቢያ የሚሆነን ሙዚቃ፣ ስኬቶቻችንን የምናደንቅበት ስጦታ፤ ልማታዊ ድርሣኖቻችንን የምንለብጥበት ኢትዮጵያዊነታችንን የምናጀግንበት፤ የነገዋን ኢትዮጵያ እያየን ህዝባዊ ተሳትፎን የምናጠነክርበት ፕሮጀክታችን ስለሆነ ነው የህዳሴያችን ማማ የአገራችን ህብረ ዜማ ማለታችን፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዛሬም ለአንድ ሰኮንድ እንኳን ሳይቆም በመፋጠን ላይ የሚገኘው በእነዚህ ምክንያቶች ነው። የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቻችን ይልቁንም ታላቁ ግድባችን ለህዳሴ ጉዟችን ስኬታማነት  ሚናቸው የጎላ መሆኑን እኛ ቀርቶ ዓለም እየመሰከረ ነው።

የአገራችን ህብረ ዜማ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አገራችንን ከድህነት የሚያወጣ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ አገራትንም የሚጠቅም ግዙፍ የልማት ሥራችን ነው። ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት  የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት የጀመረችው ጤናማ አካሄድ አንዱ አካል መሆኑንም ጭምር ለዓለም ያረጋገጥንበት ይህ ፕሮጀክት አገራዊ ዜማችን ብቻም ሳይሆን ብሄራዊ መዝሙራችን ነው ቢባል አያንስበትም፡፡ የዓለማችን  ትልቅ ሥጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ብክለትን ለመዋጋት አገራችን እየሄደችበት ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስኬት ያረጋገጠው ይህ ፕሮጀክት የህዳሴያችን ማማ ነው ስንለውም ስለማያንስበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት የዜጎቿን ፍላጎት ለማሟላትና ኢኮኖሚውን የሚሸከም ኃይል ለማቅረብ እየተጋች የመሆኗ ትልቁ ማሣያም ነው – ታላቁ  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፡፡

አያት ቅድመ አያቶቻችን በአድዋ ተራሮች መሃል የፈፀሙትን አንፀባራቂ ድል አዲሱ ትውልድ በጉባ ተራሮች መሃል እየደገመው ነው። ሁሉም አሻራውን ለማሳረፍ የሚረባረብበት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን በክፍለ አህጉሩ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ሊያደርጋት ከአፋፉ ደርሷል፡፡ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የነደፈችውን ዕቅድም ለማሳካት ድርሻው የጎላ መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡ አገራዊ የቁጠባ ባህላችንን ለማሳደግም ትምህርት አግኝተንበታል፡፡ በቴክኖሎጂና በእውቀት ሽግግር ረገድም ወደር የማይገኝለት ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ የኤሌክትሮ ማካኒካል ሥራውን በሚያከናውነው አገር በቀሉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አቅማችንን እየገነባንበት ነው።  በዚህም ተመሳሳይ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት የሚያስችል ደረጃ ላይ ስለመድረሳችን አመላክቷልና የህዳሴያችን ማማ ነው ብንለው ሲያንስበት ነው፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መንደር ያለው ሁኔታ የትም ቦታ ያልታየና ያልሆነ በየትኛውም ወቅት ያልተከሰተ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር ነው። ሁላችንም በተሰማራንበት የሥራ መስክ በጥድፊያ፣ ባለመታከትና ወደር በማይገኝለት ወኔ የበለፀገችውን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የትጋት መሠረታችን መሆኑን ያረጋገጠልን ፕሮጀክት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ነው። ብዙ ውጣ ውረዶችን ያለፍንበት እንደሆነም  ፕሮጀክቱ ይናገራልና ይህንን አክብሮና ሙጥኝ ብሎ መያዝ የመላው የአገራችን ህዝቦች ቃል ኪዳን  ነው።

ህብረ ዜማነቱ እና ማማነቱ የተሰላው በቁመቱና በስፋቱ አሊያም በሚይዘው የውኃ መጠን አይደለም፡፡ ተዓምራዊ መስታወታችን ስለሆነ ነው፡፡ ህብረ ዜማነቱ የቆምንበትን፣ የምንሄድበትን፣ ያለፍንበትን፣ የምናስበውን፣ የምናልመውን የምናይበት አጉሊ መነጽራችንም ስለሆነ ነው። ማማነቱ መልካችን፣ ልካችን በደማቁ የሰፈረበት ውድ ገጻችንም  በመሆኑ የሚገለጥ ነው። 

የህዝቡ ንቅናቄ በሠራተኛው ዘንድ የሚጠበቀውን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ስንቅ ሆኗል። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ትልቅ አስተሳሰብ አሰንቆ ወደ ታላቅነት እያስገሰገሰን ያለ፤ የአብሮነት ስሜት የፈጠረ፤ የድህነት ቁጭትን በልማት መበቀል እንደሚቻል በአብሮነት እንጂ ለብቻችን የምንጓዝበት ዘመን ያከተመ መሆኑንም ስላረጋገጠልን ነው – የህዳሴያችን ማማ ነው ማለታችን።

በጥቅሉ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አገራዊ መግባባት ፈጥሮ የሁሉንም ህዝብ አሻራ በማኖር እየተገነባ ያለ የባንዲራ ፕሮጀክታችን ነው። የህዳሴው ግደብ በዚህ ዘመን የተገኘ የአገራችንና የህዝቦቿ ታላቅ ስጦታም ነው። የህዳሴው ግድብ እንደ አድዋ ድል እስከ ወዲያኛው በትውልድ የሚዘከር እና የኢትዮጵያውያን ቋሚ ሐውልት እንደሆነም በማያጠራጥር አግባብ ከልባችን የገባና በደማችን የሰረፀ ፕሮጀክታችን ስለሆነ ነው – የአገራችን ህብረ ዜማ እና የህዳሴያችን ማማ ነው እንድንለው ያበቃን።