አገር ግኡዝ መሬት ወይም ወንዝ፣ ተራራ፣ ሸለቆ . . . ብቻ አይደለም። አገር በአንድ በተወሰነ መልከዓምድራዊ ወሰን ውስጥ የሚኖሩ ጥቅምና ፍላጎት፣ መብትና ነጻነት ያላቸው ሰዎች የሚመሰርቱት ግዙፍ ማህበረሰብም ነው። አገርን ከሰው ነጥሎ ማየት አይቻልም። አገር የመሰረቱ ማህበረሰብ አባላት በግል፣ በእርስ በርስ ግንኙነት፣ ከሌላ ማህበረሰብ (አገር) ጋር የሚመሰርቱት ግንኙነት ፍትሃዊ እንዲሆን ይሻሉ። በማንኛውም ግንኙነት መብትና ነጻነታቸው እንዲረጋገጥ ይሻሉ። መንግስት ያስፈለገው ለዚህ ነው፤ የሰዎችን መብትና ነጻነት፣ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ፤ በመርህ ደረጃ የመንግስት ስልጣን ምንጭና ባለቤት ህዝብ ብቻ ነው። መንግስት ስልጣን መያዝ ያለበት በህዝብ ውክልና ብቻ ነው። ይሁን እንጂ፤ የህዝብ የመንግስት የስልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት የማይረጋገጥባቸው ሁኔታዎች የተለመዱ ናቸው። በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የግለሰብ – ንጉሳዊ (monarchy) አሊያም የቡድን (oligarchy) ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ ስርአቶች ይኖራሉ። እነዚህ ግለሰባዊና ቡድናዊ አምባገነኖች ስልጣን የሚገባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ መለኮታዊ ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ አስረጂ ያቀርባሉ።
በኢትዮጵያ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ከአርባ ዓመት በፊት ንጉሳዊ ፈላጭ ቆራጭ (monarchy) ስርአት ነበር። ይህ ንጉሳዊ ፈላጭ ቆራጭ ስርአት ሲወገድ የነበረውን የስልጣን ሽግግር ክፍተት በመጠቀም በምትኩ ምንም የህዝብ ውክልና ያልነበረው ወታደራዊ ቡድን ፈላጭ ቆራጭ (oligarchy) በመንግስት ስልጣን ላይ ወጣ።
እነዚሀ ሁለት የመንግስት ስርአቶች የባለአገሩ ህዝብ ውክልና አልነበራቸውም። ተጠሪነታቸውም ለህዝብ አልነበረም። የህዝብ ተጠያቂነት የለባቸውም። እናም ዓላማቸው የህዝቡን መብትና ነጻነት፣ ጥቅምና ፍላጎት ከማስጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ቤተሰባዊና ቡድናዊ የርእዮተ ዓለም የበላይነት ማስጠበቅ ነበር። ሁለቱም ስርአቶች የተወገዱት በህዝባዊ አመጽ ነው። ዘወዳዊው ስርአት የተወገደው ባልተደራጀና በከተሞች አካባቢ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በተወሰነ የህዝብ ተቃውሞ ስለነበረ የህዝብ ውክልና ያለው አካል ወይም የህዝብን የስልጣን ምንጭነት የሚያረጋግጥ አካል ወደስልጣን መምጣት አልቻለም። ከዚህ ይልቅ፤ ያንኑ ዘውዳዊውን ስርአት ሲያገለግል የነበረውን ወታደራዊ ክፍል የሚወክሉ ጥቂት መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ተመራርጠው ስልጣኑን በእጃቸው አስገቡ።
የወታደራዊው ቡድን አባላት ወደስልጣን እንደመጡ ህዝባዊ መንግስት ለመመስረት ቃል ገብተው ራሳቸውን “ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” ብለው ነበር የሰየሙት፤ ይሁን እንጂ፤ ስልጣን ለህዝብ የማስረከቡ ነገር አልሆነላቸውም። አላደረጉትምም። ዴሞክራሲያዊ ወይም ህዝባዊ ባህሪ ስላልነበራቸው ነው ስልጣን ያላስረከቡት። ወታደራዊው ደርግ በአገሪቱ የነበሩ ሁሉንም የተለዩ አመለካከቶች በህግ እውቅና ነፍጎ በሃይል ደፈጠጠ። የደርጉ አባላት ወታደራዊ መለዮዋቸውን አውልቀው አይነኬ የገዢነት ባለመብት የሆነ መሪ (vanguard) ፓርቲ መሰረቱ። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ( ኢሠፓ)ን፤ ጊዚያዊ ወታደራዊው ደርግ ስልጣን በያዘ በአስረኛው ዓመት ነበር ኢሠፓን የመሰረተው፤ የደርግ ኢሠፓ መንግስት ወደመመሰረት ተሸጋግሮ በአገሪቱ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች ውክልና ያላገኙበት የህገመንግስት አርቃቂና አጽዳቂ ሸንጎ መስርቶ ህገመንግስት አጸደቀ። የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ (ኢህዴሪ) ህገመንግስት፤ በዚህ ህገመንግስት ላይ ተመስርቶም መንግስት መሰረትኩ አለ።
በ1980 ዓ/ም በኢህዴሪ ህገመንግስት መሰረት ተቋቋመ የተባለው መንግስት በአገሪቱ ያሉትን የተለያዩ ጥቅምና ፍላጎቶች፣ አመለካከቶች የሚወክል አልነበረም። የህዝብ ውክልና ያለው ለማስመሰል “ብሄራዊ ሸንጎ” የተባለ ምክር ቤት መስርቶ የአባላት ምርጫ ቢያካሂድም በምርጫው ላይ የተሳተፉት ግን የኢሠፓ አባላት ብቻ ነበሩ። ከኢሰፓ የተለዩ አመለካከቶች በሙሉ እውቅና አልነበራቸውም። በዚህ ውድድር የተወዳደረውም፣ አሸነፈ የተባለውም፤ የተሸነፈውም ኢሠፓ ነበር።
የአገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ ለነበረው የብሄር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የሚወክሉ አካላት በህገመንግስቱ ዝግጅትም ሆነ በብሄራዊ ሸንጎ ውስጥም አልተካተቱም። ያኔ በአገሪቱ ሃያ ገደማ በብሄራዊ ማንነት ላይ ተመስርተው የተደራጁ ቡድኖች የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የነበሩ ቢሆንም፣ ወታደራዊው ደርግ ሊያዳምጣቸው ፍቃደኛ አልሆነም። በአገሪቱ የነበሩ የወታደራዊ ቡድኑ አባላት ወታደራዊ ዩኒፎርማቸውን አውልቀው የመሰረቱት ኢሠፓ ከሚከተለው ኮሚኒስታዊ ርዕዮተ ዓለም የተለየ አመለካካት የነበራቸው ዜጎችም ሰሚ አላገኙም። ወታደራዊው ደርግና በኋላ መሰረትኩት ያለው መንግስት ለዜጎች የብሄር፤ የአመለካከት፣ የመደራጀት፣ ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር፣ በህዝብ ድምጽ በሚገኝ ውክልና ስልጣን የመረከብ መብትና ነጻነት እውቅና ነፍጓል።
በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶችና ነጻነቶች፤ እንዲሁም በአገሪቱ ያሉ ሌሎች አመለካከቶች በመንግስት ውስጥ ውክልና አግኝተው የሚረጋገጡበት እድል ሙሉ በሙሉ ዝግ ነበር። በዚህ ሁኔታ የመብትና የነጻነት፣ የጥቅምና የፍላጎት ጥያቄዎች ውክልና እንዲኖራቸውና እንዲረጋገጡ ማድረጊያ ብቸኛው አማራጭ የሃይል ትግል፤ ማለትም የትጥቅ ትግል ብቻ ነበር። ወታደራዊውን ደርግ ኢሠፓን በይፋ የትጥቅ ትግል፣ በህቡዕና ውጭ አገር በመሆን በተለያየ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ ቡድኖች የተፈጠሩት ለዚህ ነው። በመጨረሻም ወታደራዊው ደርግ የወደቀው በእነዚህ ሃይሎች ትግል ነው።
ወታደራዊው ደርግ ኢሠፓ ሲወገድ በየአቅጣጫው ሲካሄድ የነበረው የብሄራዊ ነጻነት ትግል አገሪቱን በመበታተን ጠርዝ ላይ አስቀመጣት። ይህ ወቅት በተለይ የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን መብትና ነጻነት አለማክበርና ለመከበሩ ዋስትና አለመስጠት አገሪቱን ወደየት ሊወስዳት እንደሚችል በተግባር የታየበት ነበር። ያም ሆነ ይህ፤ ደርግ ኢሠፓ ከተወገደ በኋላ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም በትጥቅ ትግልና በውጭ አገራት በተለያየ መንገድ ስርአቱን ሲታገሉ የነበሩና አዲስ የተደራጁ ፓርቲዎች በአገሪቱ መጪ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አዲስ አበባ ላይ ተሰበሰቡ። ይህ የሰኔ ኮንፈረንስ በመባል የሚታወቀው ወሳኝ ጉባኤ ነው።
ይህ ያለማንም የውጭ ሃይል አደራዳሪነት በአገሪቱ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል የተካሄደው ጉባኤ፣ በተለይ የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ብሄራዊ ንቅናቄዎች ከመበታተን ይልቅ መብትና ነጻነታቸው ተረጋግጦላቸው አብረው መኖር ይችሉ እንደሆን ለመሞከር ተስማሙ። እናም ሌሎች ቡድኖችንም አካትተው ስልጣን የተጋሩበትን የሽግግር መንግስት መሰረቱ። የዚህ የሽግግር መንግስት ዓላማ ብሄራዊ ጭቆና የሌለበትን፣ ሁሉም አመለካካቶች የሚስተናገዱበትን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመመስረት የሚያስችል ህገመንግስት ማዘጋጀት ነበር። በነገራችን ላይ፤ እስከ 1987 ዓ/ም ማገባደጃ አገሪቱን ያስተዳደረው የሽግግር መንግስት እንደህገመንግስት ሲተዳደርበት የነበረውና በሰኔው ኮንፈረንስ የጸደቀው ቻርተር ለአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናጸፈ ነበር። አሁን የፌዴራሉ መንግስት አካል የሆኑት ክልላዊ መንግስታት የተጸነሱት በሽግግር መንግስቱ ወቅተ ነበር።
ህገመንግስት የማዘጋጀት ተልዕኮ የተሰጠው የሽግግር መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች ያካተተ የህገመንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ሰየመ። ይህ የህገመንግስት አርቃቂ ኮሚሽን በባለሞያዎች እየታገዘ የህገመንግስት ረቂቅ አዘጋጀ። ረቂቁን ግን በራሱ አላጸደቀውም፤ ወይም ለሽግግር መንግስቱ የተቃዋሚ ሃይሎች ምክር ቤት አላቀረበውም። ከዚህ ይልቅ ህዝብ እንዲወያይበት ወደህዝብ መራው። ህዝብ በረቂቅ ህገመንግቱ ላይ አንቀጽ በአንቀጽ ተወያይቶ፤ ማሻሻያ ሃሳቦችን አቅርቦ ረቂቁን ወደኮሚሽኑ መለሰው። ይህ ተሻሽሎ የተላከ ረቂቅ ተመልሶ ወደህዝብ ተመራ። ህዝብ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ ተወያይቶና አስተያየቶችን አክሎ መለሰው።
አሁን፤ ህገመንግስቱን የማዘጋጀቱ ሂደት ወደ መጽደቅ ተሸጋጋረ። በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና በጉዳዩ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት የነበራቸው ግለሰቦች የተሳተፉበት የህገመንግስት አጽዳቂ ጉባኤ አባላት ምርጫ ተካሄደ። ምርጫው በምስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ ስርአት የተካሄደ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ነበር። ይህ ጉባኤ በህዝብ የዳበረውን ህገመንግስት አንቀጽ በአንቀጽ እየተወያየ፤ በአብላጫ ድምጽ እያሳለፈ፤ በመጨረሻም ህገመንግስቱን አጸደቀ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት የጸደቀው ይህን ሂደት ተከተሎ ነበር።
የኢፌዴሪ ህገመንግስት ባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የኢፌዴሪ ህገመንግስት እንደዘውዳዊው ወይም እንደወታደራዊው ስርአት መለኮታዊና ርዕዮተዓለማዊ አስረጂን መነሻ በማድረግ የስልጣን ባለቤት የሚሆነውን አካል አይወስንም። ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ለህዝብ፤ ለአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነው የተሰጠው፤ የስልጣን ምንጭም ህዝብ ነው። ህገመንግሰቱ በአንቀጽ 8 የህዝብ ሉዓላዊነት በሚል ርዕስ ስር ይህን የሚመለከት ድንጋጌ አስፍሯል። ይህም ድንጋጌ፤-
- የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።
- ይህ ህገመንግስት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው።
- ሉዓላዊነታቸው የሚገለጸው በዚህ ህገመንግስት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው። ይላል።
ይህ በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት የተቋቋመው መንግስት በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው የመንግስት ስልጣን ብቸኛ ምንጭና ባለቤት ህዝብ መሆን አለበት የሚለውን መርህ እንደሚያሟላ ያመለክታል።
የኢፌዴሪ ህገመንግስት የአመለካካት ነጻነትን አረጋግጧል። ዜጎች የፈቀዱትን አመለካካት የመያዝ፣ የመግለጽ፣ የማራመድ፣ በአመለካካታቸው የመደራጀት፣ በድርጅትና በግል ለመንግስት ስልጣን የመወዳደር፣ በህዝብ ድምጽ በሚገኝ ውክልና የመንግስት ስልጣን የመረከብ መብቶችን አረጋግጧል። በአመለካካትና አመለካካትን በማራመድ፣ ለፖለቲካ ስልጣን በመፎካከር መብትና ነጻነት ላይ ምንም አይነት ገደብ አለመደረጉ የህዝብን መብትና ነጻነት፣ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስጠብቅና የሚወክል አካል ብቻ ወደስልጣን የሚወጣበትን ሁኔታ ፈጥሯል።
ዴሞክራሲ በአዋጅ የሚመሰረት አይደለም። ዴሞክራሲን ማስፈን ባህል የመገንባት ሂደት ነው። ዴሞክራሲ የአንድ ህዝብ የፖለቲካ ባህል በመሆኑ አመለካካት በህዝብ ውስጥ ሰርጾ የህዝቡን የኑሮ ዘይቤ የሚወስን ባህል እስኪሆን ጊዜ ይወስዳል። እናም፤ በኢትዮጵያ የህዝብ የስልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት የተረጋገጠበት፣ ሁሉም አመለካከቶች የሚወከሉበትተና የሚሰሙበት ምሉዕ ዴሞክራሲ የሰፈነበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም። ይሁን እንጂ፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዴሞክራሲን በመገንባት ሂደት ጉልህ ስራ ተሰርቷል፤ ውጤትም ተገኝቷል። ከአሁን በኋላ የአገሪቱ ዴሞክራሲ ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ወደነበረበት ሊመለስ በማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሰ ይችላል።
የኢትዮጵያ ህዝብም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዴሞክራሲን ቀምሷል። ዴሞራሲን የቀመሰ ህዝብ ደግሞ ያለማቋረጥ የበለጠና የገጎለበተ ዴሞክራሲ እንዲመጣ ይጠይቃል። አሁን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን መገደብና መቀልበሰ አይቻልም። አሁን ባለው ሁኔታ አምባገነኖች ወደስልጣን ሊመጡ የሚችሉበት መንገድ ሙሉ በሙሉ ከመዘጋቱ ባሻገር፤ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የአገሪቱን ዴሞክራሲ ህዝብ በሚጠየቀው ልክ ካላሳደገ ህዝቡ ስለሚታፈን (safocated) አይታገሰውም። የመንግስት የህዝብ አገልጋይነት በታገተና በተሸራረፈበት ልክ ህዝብ በመንግስት ላይ ይቆጣል። ውክልናውንም ይነፍገዋል። ኢህአዴግና መንግስት አሁን በጥልቀት መታደስ ያስፈለጋቸው ለዚህ ነው። መንግስትና ገዢው ፓርቲ ህዝቡ በሚፈልገው ልክ አገልጋይ መሆን ስላቃታቸው ህዝብ ቁጣውን ገልጿል። ይህ የህዝብ ስሜት የአገሪቱ ዴሞክራሲ የማይቀለበሰበት ደረጃ ላይ መድረሱን በግልጽ ያሳያል።