የሕዳሴው ግድብ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ለኢትዮጵያውያን እጥፍ ደርብ ድል እና እርካታ ነው፡፡ ያለምንም የውጭ ኃይሎች ዕርዳታ በራስ አቅም የተገነባ፤ ለዘመናት የነበረውን የውጭ ኃይሎች በተለይም የግብጽን ሴራ እና ደባ የሰበረ፤ በራሳችን ገንዘብ፣ ዕውቀት እና ዓቅም ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችንም መገንባት እንደምንችል መልሶ ለራሳችን ያሳየን እና ትምህርት የሰጠን፤ ሀገራዊ ክብርን እና ሕዝባዊ ሞገስን ያረጋገጠልን ፕሮጀክት ነው፡፡

 

እንደምናውቀው የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እነሆ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በስድስት ዓመታት ውስጥ የሥራው ባለቤት የሆነው ሕዝብ ዓቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ ተግቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬም ይህንኑ አስተዋጽኦውን በተጠናከረ መልኩ ገፍቶበታል፡፡

 

በራስ ዓቅም፣ በራሳችን ወጪ፣ በራሳችን መሀንዲሶች፣ ኢንጂነሮች፣ አናጢዎች፣ ግምበኞች ወዘተ. እየተገነባ ያለው የሕዳሴ ግድባችን ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ለአንዲትም ሰከንድ ጋብ ሳይል ቀን ከሌት ሥራው ቀጥሎአል፤ ግንባታውም ከ56 በመቶ በላይ ተራምዶአል፡፡

 

የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ሥራ ለማሰናከል ሲወጥኑ የነበሩት እና ሙከራም ያደረጉት የውጭ ኃይሎች በተደጋጋሚ ያሰማሯቸው ቅጥረኞቻቸው በመንግሥት እና በሕዝቡ ንቁ ክትትል እና ተሳትፎ ሴራቸው ቢመክንም ከድርጊታቸው ይቆጠባሉ ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም ጥበቃ እና ክትትሉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በሕዝብ ባለቤትነት እና የበላይነት የሚመራውን ይህን ግንባታ ለማሰናከል የሚያደቡ ኃይሎች ዋናው ጠባቸው እና ግጭታቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መሆኑንም ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ የተፈጥሮ ሀብት በሆነው የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ ሳይሆን ቀርቶ በድርቅ እና ረሀብ እየተመታ ብዙ ሺህ ዘመናትን አሳልፎአል፡፡ እነግብጽ በዓባይ ወንዝ ተጠቅመው ሀገራቸውን ሲያለሙ፣ አስዋን የመሰለ ታላቅ ግድብ ሲሰሩ፣ አርቲፊሻል ሐይቆችን ሠርተው ሲጠቀሙ፣ ዓሳ ሲያረቡበት፣ ግዙፍ የአትክልት እርሻዎችን በማልማት እና ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪያቸውን ሲያሳድጉ . . . እና አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ፤ ኢትዮጵያ ግን የውጭ ብድርም ሆነ ዕርዳታ አግኝታ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሠራ ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ሲያደርጉባት ኖረዋል፡፡

 

እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ በራስዋ ዓቅም ዓባይን ትገነባላች ብለው ከቶም አስበው አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያ ፍፁም ድሀ እና ተረጂ፣ ዓቅም የሌላት ሀገር ናት ብለው ስለሚያስቡም በራስዋ ዓቅም በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት ቆርጣ ስትነሳ ለማመን አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ውኃ ተፈጥሮ በጋራ የሰጠችን ስጦታ ስለሆነ ውኃውን ተጋሪ የሆኑ ሀገራት ሁሉ በጋራ ልንጠቀምበት እንችላለን፤ ምንም የሚጋጨን ነገር የለውም በማለት ግልጽ አቋሟን በተደጋጋሚ አሳውቃለች፡፡

 

እነዚህ ኃይሎች፣ በተለይም ግብፅ፣ በዲፕሎማሲው መስክ ሠላማዊ መንገድ የሚከተሉ መስለው ዛሬም ከጀርባ የግድቡን ግንባታ ለማሰናከል ታላቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ግብጾች በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ዓቅም አግኝታ ግድብ ከገነባች የው ድርሻችን ይቀንሳል ከሚለው እና ከጥንት ጀምሮ አብሯቸው ከኖረው ፍርሐት እና ሥጋት የተነሳ በኢትዮጵያ ውስጥ ሠላም እና መረጋጋት እንዳይኖር፤ የሁከት እና ትርምስ ሀገር እንድትሆን፤ ሕዝቡ በጎሳ ፖለቲካ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ፤ ጠንካራ ሀገራዊ ስሜት እንዳይኖረው ወዘተ የተለያዩ የጎሳ እና ሃይማኖት ተኮር ድርጅቶችን በመፍጠር ከቀድሞ የግብፅ መንግሥታት ጀምሮ እስከዛሬም ድረስ በዚሁ ሴራቸው ገፍተውበታል ይገኛሉ፡፡ በሶማሊያ በኩልም ሆነ በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚነሱ ሀገራችንን የመተናኮል ሙከራዎች ጀርባ ግብጽ ነበረችበት፡፡ ዛሬም ያው ነው፤ በደቡብ ሱዳን በኩል በመግባት እና የተለያዩ ኃይሎችን በማደራጀት በእጅ አዙር አማካኝነት ከጀርባ ለመውጋት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

 

በቅርቡ ከኦነግ ጋር የተቀናጀ ሴራ በማሴር እጅግ ሠላማዊ እና መንፈሳዊ በሆነው የእሬቻ በዓል ላይ በሠላም በዓሉን ለማክበር ከቤታቸው ወጥተው ወደስፍራው በሄዱት ዜጎቻችን ላይ ወኪሎቻቸውን በማሰማራት የፈጠሩትን ትርምስ እና የሰው ሕይወት ጥፋት በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን በውል የሚረዳ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በዘር፣ በጎሳ እና በሃይማኖት ሊከፋፍሉት እና ሊያባሉት የሚሞክሩትን ሁሉ ነቅቶ መከላከል እና ሀገሩን ከጥፋት መጠበቅ ግዴታው መሆኑን መረዳት አለበት፡፡

 

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማሰናከል የወጠኑት ሴራ ቢኖር፤ በሀገር ውስጥ ትርምስ እና ሁከትን በመፍጠር ግንባታው እንዲቋረጥ ማድረግ ስለሆነ ይሄንን ጥንስሳቸውን፣ እንደእስካሁኑ ሁሉ፣ ማምከን ይገባል፡፡ ግብጾች አምና የግድቡ ግንባታ ቆመ ብለው በውጭ መገናኛ ብዙኅን በማስተላለፍ ሲጨፍሩ እንደነበር እዚህ ላይ ማስታወሱ አይከፋም፡፡

 

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዛሬም ለአፍታም ሳይቆም ሥራው በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቻችን ለሕዳሴ ጉዞአችን ስኬታማነት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠንቅቀን የምናውቅ በመሆኑ ከምንም በላይ እንጠብቃቸዋለን፡፡ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር ሀገራችንን እና ሕዝቧን ከድህነት አረንቋ የሚያላቅቅ፤ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የተጀመረውን ታላቅ ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ግዙፍ የልማት እና የዕድገት አውታር ነው፡፡

 

የዛሬው ትውልድ ትላንት በጸረ ቅኝ ገዢዎች ትግል እና ትንቅንቅ፣ በታላቅ ሀገራዊ ፍቅር እና የጀግንነት መንፈስ፣ በልበሙሉነት እና በተጋድሎ አያት ቅድመ አያቶቻችን በወራሪው የኢጣሊያን ሠራዊት ላይ በዓድዋ ተራሮች መሀል የፈጸሙትን ወደር የሌለው አንጸባራቂ ድል የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚገነባበት በጉባ የተራሮች ሰንሰለት ውስጥ እና አናት ላይ እየደገመው መሆኑን ስናይ እውነትም የአባቶቹ ልጅ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ያረጋግጥልናል፡፡

 

ገና አዳዲስ ሀገርን የሚያለሙ ከድህነት የሚያወጡ የቀደመ ክብር እና ዝናዋን የሚመልሱ ታላላቅ ገድሎችን እንደሚሠራ ለአፍታ ልንጠራጠር አይገባም፡፡ የቀድሞው ትውልድ የተጋድሎ እና የድል መንፈስ በአሁኑ ትውልድ ተሸጋግሮ በዓለም 7፤ በአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ የሆነውን ግዙፍ ግድብ በመሥራት ታሪካዊ ሚናውን በመወጣት ላይ መገኘቱ ትውልዱን ብቻ ሳይሆን ሀገሩን እና ሕዝቡን በእጅጉ የሚያኮራ ተግባር ነው፡፡

 

ሕዝቡ ከድህነት ለማውጣት እና ድሕነትን የትላንት ታሪክ አድርጎ ለመቀየር ያለው የልማት ተነሳሽነት በላቀ ደረጃ ላይ መገኘቱ የሀገራችንን የነገ ታላቅ ተስፋ አመላካች ነው፡፡ የሕዳሴው ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በየጊዜው ዕያደገ በመሄድ ሲሆን፤ በቅርቡ በተደረገለት ማስፋፊያ በመቶዎች የሚቆጠር ተጨማሪ ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ተደርጎአል፡፡ እያንዳንዱ ማስፋፊያ ራሱን ችሎ እንደነተከዜ ወይም ግልገል ጊቤ የኃይል ማመንጫዎች ሊቆጠር የሚችል ግዙፍ ኃይል የማመንጨት ዓቅም አለው፡፡ ይህ በየግዜው ሀገራዊ የቴክኒዮሎጂ አቅማችን እየጎለበተ ዕያደገ መምጣቱን በተጨባጭ ያሳያል፡፡

 

አሁን ወደ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና ድጋፍ እንለፍ።

 

በቅርቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ባለፉት ስድስት ዓመታት ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ39 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ከገንዘብ ባሻገር የዓይነት ሥጦታዎችን ማበርከታቸውን፣ ለዚህም ከዱባይ የተላከውን ዘመናዊ ቶዮታ አውቶሞቢል ለማሳያነት በመጥቀስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከኅብረሰተሰቡ ከሚጠበቀው የግንባታ ወጪ ከ70 በመቶ በላይ ወይም 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በአካል በመገኘት ግድቡን እንዲጎበኘው በተደረገው ጥረት መሠረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስቻለ ሲሆን፤ በተበታተነ መልኩም ቢሆን በርካታ ዲያስፖራዎች ግድቡ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ እና ደረጃ በየጊዜው እየጎበኙ እንደሚገኙ ከምክር ቤቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም በርካታ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሚዲያ  (የግብጽን ጨምሮ) አካላት ግድቡን እንዲጎበኙ እና ግድቡ በታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደሌለው በመግለጽ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ዘገባዎችን ሠርተዋል፡፡ በቅርቡም ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ የሚዲያ አካላት ግድቡን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ለመገናኛ ብዙኅን ገልፀዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 6 ዓመት ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚኖሩ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ጋር የተለያዩ የገቢ ማስገኛ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል፡፡ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራው 56 በመቶ ተከናውኗል፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡

ባጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኛው፣ አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ፣ የከተማው ነዋሪ፣ ነጋዴው፣ ባለሀብቱ፣ ተማሪው፣ መምህሩ፣ በውጭ ሀገር ነዋሪ የሆነው ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራ)፣ በጉሊት ንግድ የተሰማሩ እና አነስተኛ ኑሮ እና ገቢ ያላቸው ወገኖች፤ የሃይማኖት ተቋማት፤ በተለያዩ ዘርፎች የተሠማሩ ዜጎች፣ እንዲሁም ሕጻናት ሳይቀሩ በየትምህርት ቤታቸው ለዚህ ለታላቅ ሀገራዊ ግድብ ግንባታ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፤ ዛሬም በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየን ዓቢይ ቁም ነገር ቢኖር “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” የሚለው የጋለ የሕዝብ ወኔ ዛሬም ትንታግ ሁኖ እየተንቀለቀለ መገኘቱን ብቻ ሳይሆን፤ የግድቡ ሥራ በሕዝቡ ባለቤትነት እንደተጀመረው ሁሉ በሕዝቡ ታላቅ ርብርብ የሚጠናቀቅ መሆኑን ነው፡፡