ማርች 8፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዘንድሮ በሀገራቸን ለ42ኛ ጊዜ ተከብሮአል፡፡ የሴቶች መብት በእኩልነት መከበር እና መረጋገጥ ለሀገርም ሆነ ለኅብረተብ እጅግ የጎላ ጠቀሜታ አለው፡፡ ያለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሀገር፣ ሕዝብ፣ ኅብረተሰብ የሚባል ነገር የለም፡፡ ከእናትነታቸው ባሻገር ሀገር ራስዋ የምትመሰለው በሴቶች ነው፡፡ እናት ሀገር፣ እናቴ አገሬ . . . እንዲሉ፡፡
የሴቶችን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መልሶ የሚጠቅመው ሀገርን እና ኅብረተሰብን ነው፡፡ የሴቶችን እኩልነት ማክበር/ማስከበር እና ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማብቃት ከፍተኛ ሀገራዊ እና ኅብረተሰባዊ ለውጥን ያቀዳጃል፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ ኃላፊዎችም አፅንኦት ሰጥተው የሚገልፁትም ይህንኑ ነው።
የኢፌድሪ ፕሬዚደንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በአገሪቱ የተደራጀ የሴቶች ተሳትፎን ማረጋገጥ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የተጀመሩ የዴሞክራሲ ግንባታ እና የልማት ሥራዎችን ይበልጥ ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ሴቶችን ያላሳተፈ ልማት ዘላቂነት የለውም” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚደንቱ የሴቶች ሁለንተናዊ፣ የተደራጀ እና ንቁ ተሳትፎን ማጎልበት በሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት እገዛው የላቀ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ መንግሥት የሴቶች ፌደሬሽንን ራዕይ እና ዓላማ ለማሳካት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ሴቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የሚያካሄዱትን የተደራጀ ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የሴቶችን ተሳትፎ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋጋጥ ሴቶች ሊታገሉ እንደሚገባቸው፤ የኢትዮጵያ ሴቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እኩል ተሳታፊ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ በማያቋርጥ ሁኔታ ትግል ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “ማርች 8”ን ምክንያት በማድረግ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡
የሴቶች ተሳትፎ እና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መንግሥት የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ፤ የሴቶች እኩል ተሳትፎ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለኅብረተሰብ ለውጥ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የሴቶችን ትግል ወንዶችም ሊደግፉት እንደሚገባ፤ ሴቶች ያልተሳተፉበት ልማት በየትኛውም መስክ ውጤታማ ሊሆን የማይችል በመሆኑ በአገሪቱ የማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሴቶች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ማጎልበት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሴቶች በንግድ ሥራ፡ በሀብት ፈጠራ፡ በኢንዱስትሪ እና በግብርና ዘርፎች በመግባት በማስመዝገብ ላይ የሚገኙት ውጤት አበረታች መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶች በሙሉ አቅማቸው በአገሪቱ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይገቡ የሚገቷቸውን እንቅፋቶች ደረጃ በደረጃ በመለየት መፍትሔ መሥጠት እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶች በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ባለፉት 25 ዓመታት የነበራቸው ተሳትፎ ቀላል እንዳልሆነ፤ በአገሪቱ በተካሄዱት ተከታታይ አገራዊ ምርጫዎች ተወካዮቻቸውን በመምረጥ እና በተለያዩ አደረጃጃቶች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲ በአገራችንን እንዲያብብ ጉልህ ሚና መጫወታቸውንም አስረድተዋል፡፡
አሁንም ድረስ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በሴቶች ላይ የሚደርሱት ኋላ ቀር እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሆኑት የሴቶች ግርዛት፣ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የሴቶች ትንኮሳ እና የመሳሰሉት አለመቅረታቸውን፤ ድርጊቶቹን ለመከላከል ይበልጥ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ በውሳኔ ሰጪ መድረኮች ላይ የሴቶች ተሳትፎ ዕያደገ መምጣቱ፤ በታችኞቹ ምክር ቤቶች የሴቶች ተሳትፎ ከ50 በላይ መድረሱ፤ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ተሳትፎ 38 በመቶ መሆኑ አበረታች ውጤት መሆኑንም አስምረውበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከወንዶች እኩል፡ በሁለተኛ ደረጃ ከ50 በመቶ በላይ መሆኑን፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴቶች ተሳትፎ ከ40 በመቶ በላይ መድረሱ ትልቅ እመርታ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለ41ኛ፤ በዓለም ለ106ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በተለያዩ መርሐ ግብሮች ነው የተከበረው፡፡ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የሴቶች ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በሴቶች ችግሮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሴቶችን ቀን በተመለከተ ከሴት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት መንግሥት እማዎራ ሴቶችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚደግፍ፤ የሴቶችን ሁለገብ ጥረት ለማገዝ የፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ ማምረት የሚችሉበትን የኢኮኖሚ ዓቅም መገንባት እንደሚገባም፤ መንግሥትም ሆነ ሴቶች ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ የሀገሪቱ የመልማት ዕድል ሰፊ መሆኑን፤ ሴቶች ጤናማ ሆነው እንዲያመርቱ ከተፈለገ ጎታች የሆኑ ጉዳዮችን በማጥራት በበጀትም ጭምር ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን እና ወደፊትም እንደሚደረግ፤ የሴቶችን ዓቅም ሊጨምሩ በሚችሉ የልማት ሥራዎች ላይ ቅድሚያ በመስጠት እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ሴቶች ጤናማ ሆነው እንዲያመርቱ ከተፈለገ በመጀመሪያ በጤንነታቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ማስፈለጉን፤ ለዚህም የሴቶች የጤና ልማት ሠራዊት ተገንብቶ ትልቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፤ የመጠጥ ውኃ ጉዳይ ለሴቶች የቤት ሥራ ጫናን ከመቀነስ አኳያ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ይህንን ለመፍታት መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ 2,500 ተወካይ ሴቶችን በፅ/ቤታቸው ያወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ማርች 8 ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ መራራ ትግል በማድረግ በሚደርሱባቸው የተለያዩ ፖለቲካዊ፡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጭቆናዎች ላይ ድል መቀዳጀታቸውን የሚያስታውስ ቀን መሆኑን በመጥቀስ ሴቶች ለእኩልነት እና ለዴሞክራሲ መከበር ከባድ መስዋትነት በመክፈል ጭቆናን ለማስወገድ ታሪካዊ ትግል ማካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ሴቶች ከመንግሥት ድጋፍ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ነጻነታቸውን ይበልጥ በማስከበር እና በራሳቸው ብርቱ እንቅስቃሴ በማድረግ ለአገሪቱ ጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሴቶች እና ሕጻናት ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ ሐምቢሳ በበኩላቸው የሴቶችን ተሳትፎ ያላረጋገጠ ልማት ውጤታማ እንደማይሆን በመጠቆም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች በመመለስ፤ ፖለቲካ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ መንግሥት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የሴቶች ፌደሬሽን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ በአዲስ አበባ/ጆሞ አካባቢ ዘመናዊ የጉሊት የገበያ ማዕከል ያስመረቀ ሲሆን፤ 140 የሚሆኑ ሴት የጉሊት ነጋዴዎች ቦታ በዕጣ ተሠጥቷቸዋል፡፡ (የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ከስምንት ዓመት በፊት የተቋቋመ እና ከ90 በላይ አደረጃጀቶችን በሥሩ ያቀፈ፤ እንዲሁም በመላ አገሪቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ግዙፍ ፌደሬሽን ነው፡፡)
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚያስችል የሴቶች የልማት እና የለውጥ ስትራቴጂ እና ፓኬጅን ማዳበር የሚያስችል ውይይትም ተካሂዶአል፡፡ ስትራቴጂው እንደ አዲስ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ፓኬጁ ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረው ላይ ማሻሻያ በማድረግ የተሠራ መሆኑ ታውቆአል፡፡ የሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ ሐምቢሳ እንደገለፁት ስትራቴጅ እና ፓኬጁ ቀደም ሲል ትኩረት ያልተሰጠባቸው አቅጣጫዎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማካተት የተዘጋጀ ነው። ስትራቴጂ እና ፓኬጁ የሴቶች ቁልፍ ችግሮች በተለይም ከአመለካከት፤ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲሁም ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች የአካል ጉደተኛ፤ የጎዳና ተዳዳሪዎቸ፣ ሴት አዛውንቶች እና ከስደት ተመላሽ ሴቶችን ያካተተ ሥራ መሠራት አለበት በሚል አዳዲስ አሠራሮችን በማካተት የተዘጋጀ መሆኑንም ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ፓኬጁ ከዚህ ቀደም ያልተካተቱ ጉዳዮችን እና ከዚህ ቀደም ያልተካተቱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማካተቱ በጎ ጎን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በኢትዮጵያ በሕዝባዊ ሩጫ፣ በቦንድ ሽያጭ ሣምንት እና በተለያዩ የልማት ሥራዎች ተከብሮአል፡፡