አንድ ቆየት ያለ አባባል አለ—“ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም” የሚል። አባባሉ ‘ለሁሉም ጊዜ አለው’ በሚለውን ሌላ አባባል ሊወከል ይችላል። እርግጥም ማንኛውም ነገር በጊዜ ዑደት ውስጥ የሚፈፀም እንጂ፤ ሲሮጡ እንደታጠቁት ቀበቶ ሲሮጡ የሚፈታ ሊሆን አይገባውም። የሰከነና ሁሉንም በጊዜው የመከወን መንገድን የሚከተል ማንኛውም ወገን፤ ከርጋታውና ከስክነቱ ያተርፋል እንጂ አይጎዳም። የመፅሐፍ ቅዱሱ ጠቢቡ ሰለሞን “ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል” ያለውም ይህንኑ ሃቅ ለማመላከት ይመስለኛል።
ከዚህ አኳያ የሀገራችን ዴሞክራሲ ገና በቅጡ 26 ዓመታትን እንኳን ያልደፈነ፣ ህዝቡም ቢሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስለ ዴሞክራሲ እምብዛም እውቀትን ያልገበየ፣ ከፍ ሲልም ባለፉት ስርዓቶች ጥለውበት ከሄዱት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ የተላቀቀ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም። እናም የዴሞክራሲ መብቶቹን በየገቢው ሁኔታ ለመጠቀም አሁንም ቢሆን ጊዜን የሚጠብቅ ይመስለኛል። እንደ እውነቱ ከሆነ እንኳንስ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተለማማጅ የሆንነው እኛ ቀርቶ፤ በመስኩ የትየለሌ ዘልቀዋል የሚባሉት ምዕራባዊያንም ቢሆኑ ዴሞክራሲን በበቂና በትክክለኛ ገፅታው እየተገበሩነት ነው ማለት የሚቻል አይመስለኝም።
ዴሞክራሲ የሂደት ጉዳይ ስለሆነ ግን የአንድ ሀገርና ህዝብ ባህሉን ላለመገንባት እጃቸውን አጣምረው ይቀመጣሉ ማለት አይደለም። እናም የሚከተሉት ስርዓት ዴሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በራሳቸው ልኬታ ሊተገብሩት ይገባል። ዴሞክራሲ አንድ መድብለ ፓርቲን የሚያካሂድ ሀገር ሁነኛ መገለጫ በመሆኑም፤ እሳቤውን ከራስ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እየቃኙ የህዝብን መብት መጠበቅ ይገባል። ምክንያቱም ዴሞክራሲን እንደ ቁሳቁስ ከውጭ እናስገባ ብንል፤ የውጭው ዴሞክራሲያዊ አምድ ሊጠበን አሊያም ሊሰፋን ስለሚችል ነው። እናም ሁሌም ከዴሞክራሲ አኳያ “Think Globally, Act Locally” የሚለው ዓለማቀፋዊ አባባል ሊዘነጋ አይገባም—“ወፍ እንዳገሩ ይጮሃልና።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የምዕራባዊያንን “ወፍ” ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳናደርግበት እንዳለ ልናስጮኸው አንችልም። አዎ! ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ከኢትዮጵያዊ “ወፍ” ውጭ በአግባቡ ሊጮህ የሚችል “ወፍ” ፈልጎ ማግኘት ለአሳር ይመስለኛል። ርግጥም ለሀገራችን ፖለቲካዊ እመርታም ይሁን ተግዳሮት መፍትሔው ያለው በሀገር ልጅ እጅ ውስጥ እንጂ፤ የራሱን የርዕዩተ-ዓለም ስንክሳር ይዞ በሚመጣ የውጭ ሃይል አይደለም። ሊሆንም አይገባም። አበው “የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ” እንዲሉ፤ የዚህ ሀገር የፖለቲካ ዑደት ማደግም ይሁን መታረም ካለበት ሂደቱም ይሁን መፍትሔው መሆን ያለበት በሀገርና በወንዝ ሰው ብቻ ነው። ይህን ትክክለኛ ፖለቲካ መፍትሔ በመተው የሀገራችንን ሰርዶ በሰው ሀገር በሬ ለማስበላት መሞከር “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉት ዓይነት የዋህ አስተሳሰብ ይመስለኛል።
በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ በቅርቡ አዲስ የፈነጠቀ ፀሐይ አለ። ይህ የፖለቲካ ፀሐይ በቅርቡ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል በሚካሄደው ውይይትና ክርክር ይወክላል። ውክልናው የሀገራችንን ዴሞክራሲ ጥልቀቱንና ስፋቱን ከማጎበት አኳያ የሚታይ ነው። ሆኖም ከመሰንበቻው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ሳይስማሙ ተለያይተዋል። ሆኖም ይህን ልዩነት አንዳንድ ፅንፈኞች የነገሮች ሁሉ የመጨረሻ በማድረግ ለተቃዋሚዎቹም ይሁን ለገዥው ፓርቲ የተለያዩ ስሞችን ሲሰጡ ይስተዋላል።
ዳሩ ግን ዴሞክራሲ ሂደት ነው። ዴሞክራሲ አንደኛው አካል ከሌላኛው ጋር ያለውን ልዩነት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ልዩነቱን ለማጥበብ የሚሰራበት አውድ ነው። በዴሞክራሲ ውስጥ ላለመስማማት መስማመትም ይኖራል። ሁለትና ከዚያ በላይ ሃይሎች ዛሬ ላይ ስላልተስማሙ ነገ ሁሉም ነገር ይጨልማል ማለት አይደለም። ነገ አዲስ ተስፋ፣ አስተሳሰብና የተሻለ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ይዞ ሊመጣ ይችላል። ስለ ዛሬ እንጂ ስለ ነገ ማንም እርግጠኛ ሆኖ ሊናገር አይችልም። ነገ በራሱ አዲስ ቅኝትና አስተሳሰብ ብቅ የማለቱ ዕውነታ ለራሱ ለቀኑና የቀኑ ተዋናይ ለሆኑት አካላት የሚተው ዕውነታ ነው።
ርግጥ 22ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነገን በእንጥልጥል አልተውትም። ነገ በአዲስ ተስፋና አመለካከት እንደ አዲስ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል። በፖለቲካ ሂደት ውስጥ የፓርቲዎች ልዩነት፣ አለመግባባትና ከፍ ሰልም ቡጢ እስከ መለዋወጥ ድረስ የሚደርስ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ፓርቲዎች አንድ ቢሆኑና ተመሳሳይ ምልከታ ያላቸው ከሆኑ በተለያየ ስያሜ ሊጠሩም አይገባም ነበር። የልዩነቱ ምንጭ የፓርቲዎቹ የተለያዩ መሆናቸውና ይህም ትክክለኛ የዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ ፅንፈኞ በባዶ አየር ላይ “እልል በቅምጤ” ለማለት እንደሞከሩበት የተሳሳተ ምልከታ አይደለም። በየትኛው ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ እንደሚሆነው ሁሉ፤ እኛም ሀገር ውስጥ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ በራሳቸው አጀንዳዎች ዙሪያ ሊለያዩ ይችላሉ። ነገ ደግሞ በዴሞክራሲው አውድ ውስጥ በዚያው አጀንዳ ዙሪያ ሊሰማሙ ይችላሉ። ይህ የዴሞክራሲ ውጣ ውረድ ነው። እናም እዚህ ሀገር ውስጥ የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም።
ከዚህ ይልቅ እኔን ሁለት ነገሮች ያሳስቡኛል። አንደኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርና ውይይት በራስ አውድ ውስጥ እስከተካሄደ ድረስ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የሌሉትን አጋር ፓርቲዎች ያለማሰተፉ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የሀገራችንን ፖለቲካ የማጎልበት ሚና ያላቸው የሀገራችን ህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሀገራችንን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መፍትሔው ያለው በእነርሱ እጅ መሆኑን የተገነዘቡ ያለመምሰል ሁኔታ ነው።
ክርክሩና ውይይቱ “የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ”ን የፖለቲካ ምህዳር ይበልጥ ለማስፋት እስከሆነ ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ሁሉም ፓርቲዎች መሳተፍ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም አጋር ድርጅቶች የሚባሉት የሶማሌ፣ የሐረሪ፣ የጋምቤላ፣ የቢኒሻንጉል ጉሙዝና የአፋር የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይቱ አካል መሆን ይኖርባቸዋል። እነዚህ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህጋዊነት ተመዝግበው በያሉበት ቦታ የሚንቀሳቀሱ እንደመሆናቸው መጠን፤ ከ22ቱ ፓርቲዎች ተነጥለው ሊታዩ አይገባም ነበር።
ይህ ባለመሆኑም “አሳታፊነት” የሚሰኘው የዴሞክራሲ አንዱ መርህ የተጣሰ ይመስለኛል። በዴሞክራሲ ዓይን ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው። ገዥው ፓርቲም ይሁን አጋሮቹ አሊያም ተቃዋሚዎች በአንድ ሚዛን ላይ ነው የሚቀመጡት። እናም በእኔ እምነት አጋር ፓርቲዎችን ወደ ጎን በማለት ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ለብቻቸው የሚያደርጉት ውይይትና ክርክር ተገቢ አይመስለኝም። እናም “እንከራከር፣ እንወያይ” ብሎ መድረኩን ያዘጋጀው ገዥው ፓርቲ ይህን ሁኔታ በጥልቀት በማጤን አጋር ፓርቲዎች የውይይቱ አካል የሚሆኑበትን መንገድ መፈለግ ያለበት ይመስለኛል።
ርግጥ አጋር ፓርቲዎችን ወደ ውይይቱ ጠረጴዛ ለማምጣት ጊዜው ገና አልረፈደም። 22ቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ገና በቅድመ-ውይይት ላይ ነው ያሉት። ዋነኛው ውይይትና ክርክር ገና አልተጀመረም። በመሆኑም ኢህአዴግ እጅግ በርካታ ደጋፊዎችና አባላት ያሏቸውን እነዚህን ፓርቲዎች ወደ ጎን ብሎ ከተወሰኑ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገው ውይይት የህዝብን ውክልና ከማዳመጥ አኳያ የራሱ ችግር ያለበት ስለሚሆን ፈጥኖ ማስተካከል ይኖርበታል እላለሁ። ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንዳይገለፅበት ስለሚያደርግም ይህን ሁኔታ በማስተካከል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
ከአጋር ፓርቲዎች በክርክሩና በውይይቱ ላይ ያለመሳተፋቸውን ያህል የሚያንገበግበኝ ሌላው ጉዳይ በፓርቲዎች መካከል ኢትዮጵያዊ ፖለቲካን በውጭ ታዛቢዎች ለመቃኘት ያለው ፍላጎት ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ የአፍሪካ ፖለቲካ የምዕራቡ ዓለም ርዕዩተ-ዓለም የተጫነው ነው። ርግጥ ምዕራባዊያን ከዴሞክራሲ አኳያ ባስቆጠሩት ዘለግ ያለ ዕድሜ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ሆኖም የእነርሱ ፖለቲካዊ አውድና የእኛው ጀማሪ የዴሞክራሲ መንገድ ለየቅል ናቸው። “ስልቻም ቀልቀሎ፤ ቀልቀሎም ስልቻ” ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። ሁለቱም የፖለቲካ ምህዳሮች የየራሳቸው የማስፈፀሚያ መንገድ፣ ተከታይ ህዝብና ሀገራቱ ያለፉበት የኋላ ታሪክ ለየቅል ነው። አይገናኙም።
እናም የሀገራችንን ፖለቲካ በእነርሱ ለመዘወር ብንሞክር አሊያም የእነርሱን ስልጡን መንገድ በእኛ መንገድ ለመቃኘት ብናስብ ውጤቱ ሊሆን የሚችለው እንደ ባቢሎን ዘመን ህዝቦች አለመግባባት ብቻ ነው። በዚያ ዘመን አንዱ አሸዋ ሲል ሌላኛው ድንጋይ፣ አንዱ ውሃ ሲል ሌላኛው እሳት ያቀብል እንደነበረው ሁሉ፤ ምናልባትም እኛ ስለ ሀገራዊ ዴሞክራሲ ስናስብ እነርሱ ስለ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ከፍ ሲልም ስለ ኒዮ-ሊበራሊዝም አስፈላጊነት ሽንጣቸውን ይዘው ሊመክሩን ይከጅሉ ይሆናል። በዚህም ሳቢያ አንግባባም፤ አንደማመጥም። የሁለት ዓለም ሰዎች የሆንን ያህል ምልከታችን “አራምባና ቆቦ” የሚሉት ዓይነት ይሆናል።
ስለሆነም 22ቱ ፓርቲዎችም ይሁኑ ምናልባትም በዚህ ፅሑፍ ላይ ከአሳታፊነትም ይሁን የህዝብን ውክልና ከማካተት አኳያ የውይይቱ አካል እንዲሆኑ የምሻው አጋር ፓርቲዎች፤ የሀገራችን ፖለቲካ ምንጩ የሀገራችን ህዝብ መሆኑን ሊያጤኑት ይገባል። የኢትዮጰያ ህዝብ ደግሞ የራሱ ባህል፣ ወግና ፖለተካዊ ምልከታ ያሉት ነው። እናም ፓርተዎቹ ስለዚህ ህዝብ እየተወያዩና እየተከራከሩ አሸማጋይ ሌላ ወገን ይሁን ብሎ ማሰብ ይህን ህዝብ መናቅ ይመስለኛል። ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱ በውጭ ሃይሎች እንዲዘወር መመኘትም ጭምር። ለኢትዮጵያዊ ፖለቲካ መፍትሔው ኢትዮጵያዊ እንጂ የውጭ ሃይሎች ወይም የራሳቸው ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው “አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓቾች” ሊሆኑ አይገባም—የሀገራችን ፖለቲካዊ አውድም ይሁን ህዝቡ አይፈልጋቸውምና። አዎ! ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚያስፈልገው ሀገር በቀል መፍትሔ ብቻ ነው።