የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለውጦችና አንድምታዎቹ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አምስተኛ ወሩን እየተሻገረ ነው። ታዲያ በእነዚህ አምስት ወራቶች ውስጥ በሀገራችን ላይ ተጋርጦ የነበረውን የሁከት አደጋ ህዝቡ የአንበሳውን ድርሻ በመጫወቱ ምክንያት ጉልህ ለውጦች መታየት ጀምረዋል። የአዋጁን መንፈስ በአግባቡ የተረዳው የሀገራችን ህዝብ ለአዋጁ እውን መሆን በግሉ ካደረገው አስተዋፅኦ ባሻገር፤ አጥፊዎችን በመገሰፅና የከፋ ችግር የፈጠሩ ዜጎች የተሃድሶ ትምህርት ወስደው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ህይወታቸውን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንዲመሩ አድርጓል። ይህ ህዝቡ የአዋጁን መንፈስ ተረድቶ ሀገራችን ሰላም እንድትሆንና የጥልቅ ተሃድሶው አካል ሆኖ መንግስት የራሱን የቤት ስራ በአግባቡ እንዲወጣ አስችሎታል። ይህ ህዝባዊ ተግባር ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠሉ የሚቀር አይመስለኝም—ህዝቡ ራሱ የሰላሙ ጠባቂ መሆን እንደሚገባውና ሰላሙን ለማወክ የሚጥሩ ጥቂት ሃይሎችን በተገቢው መንገድ ያወቃቸው ስለሆነ ነው።

ርግጥ ህዝቡ በኮማንድ ፖስቱ ገቢራዊ አድራጊነት በህገ መንግስቱ መሰረት የታወጀውን አዋጅ ሲያስፈፅም ነበር። ለፀጥታ ሃይሎች መረጃ በመስጠት፣ ህብረተሰቡ ውስጥ በሚካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ እንዲሁም የተጀመረው የልማትና የዴሞክራሲ መስመር እንዳይስተጓጎል ያለውን ፍላጎት በመግለፅ ባለፉት አምስት ወራቶች አዋጁ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ጥሯል፤ ውጤትም አምጥቷል። እናም የዚህ ሰላም ባለቤት የሆነውና ሁከቱ በተከሰተባቸውም ይሁን ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኘው የሀገራችን ህዝብ በአያሌው ሊመሰገን የሚገባ ይመስለኛል።

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ከመሰንበቻው የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬትሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ክልከላዎች መነሳታቸውን ሲገልፁ፤ ውጤቱ ሀገራቸው ሰላም እንድትሆን ሌት ተቀን የሰሩት የሀገራችን ህዝቦችና የፀጥታ ኃይሎች ጥምር ውጤት አንድምታ ያለው መሆኑን የሚዘነጋ አይመስለኝም። ይህም የአንድ ሀገር ሰላም አዋጅ ስለወጣ ብቻ ሳይሆን፤ በዋነኛነት ህዝቦች የነቃ ተሳትፎ ዕውን እንደሚሆን ያሳየ ይመስለኛል። ይህ የህዝቡ ተሳትፎ የተገለፀው ደግሞ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በመመመሪያ ቁጥር አንድና ሁለት ላይ የወጡት ክልከላዎች የተወሰኑት እንዲነሱ መደረጉን ሲገልፁ ነው። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በቁጥር አንድና ሁለት ላይ የነበሩት አንዳንድ ክልከላዎች ተነስተው ሶስተኛ መመሪያ ወጥቷል። አራት ክፍሎች እንዳሉት የተገለፀው ይህ መመሪያ፤ በቀዳሚዎቹ ሁለት መመሪያዎች ላይ ያሉት ክልከላዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ የሚከተሉት ክልከላዎች እንዲቀሩ ተደርጓል።

እንዲቀሩ ከተወሰኑት ውስጥ በመመሪያ ቁጥር አንድ አንቀፅ 22 ላይ የነበረውና በልማት አውታሮችና መሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን አስመልክቶ የተደነገገው ይገኝበታል። በዚህ ድንጋጌ የኢኮኖሚ አውታሮች፣ መሰረት ልማትና የኢንቨስትመንት ተቋማት፣ የእርሻ ልማቶች፣ በፋብሪካዎች እና በመሰል ተቋማት አካባቢ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ከተፈቀደለት ሰራተኛ በስተቀር ማንኛውም ሰው እንዳይቀሳቀስ ክልከላ ተጥሎ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፤ በእነዚህ ቦታዎች የሰዓት እላፊውን ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም ሰው፤ የጥበቃ ወይም የህግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ የተቀመጠው ድንጋጌም ሙሉ በሙሉ ቀርቷል።

ሰዓት እላፊን የሚመለከተው የመመሪያው አንቀፅ 23 ላይም ማናቸውም ሰው በኮማንድ ፖስቱ ውሳኔ የሰዓት እላፊ በይፋ በሚገለጽበት ቦታና ጊዜ የሰዓት እላፊ ክልከላን በመተላለፍ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይፈቀድለትም በማለት የተቀመጠው ድንጋጌም በአዲሱ መመሪያ እንዲቀርተደርጓል። እንዲሁም ክልከላዎቹ ተጥሰው ሲገኙ የህግ አስከባሪዎች የሚወስዷቸውን ርምጃዎች በተመለከተም በመመሪያ ቁጥር አንድ አንቀፅ 28 ላይ የሚገኙት ክልከላዎችም እንዲነሱ ተደርጓል።

እነርሱም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ አዋጁ ተፈፃሚነቱ እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ቦታ እንዲቆይ ማድረግ፣ ተገቢውን የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት የሚለቀቀውን እንዲለቀቅ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርበውን ደግሞ እንዲቀርብ ማድረግ እንዲሁም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማናቸውም ሰዓት ብርበራ ለማድረግ የአካባቢውን ህዝብና ፖሊስ በማሳተፍ ማንኛውም ወንጀል የተፈፀመበትን ወይም ሊፈፀምበት የሚችል ንብረትን መያዝ ወይም ንብረቱ ባለበት እንዲጠበቅ ማድረግ፣ በማንኛውም ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ፅሑፍ፣ ምስል፣ ፎቶግራፍ፣ ቲያትርና ፊልም የሚተላለፉ መልዕክቶችን መቆጣጠርና መገደብ ብሎም የተዘረፉ ንብረቶችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመፈተሽ ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ ማድረግ የተሰኙት ክልከላዎች ናቸው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ክልከላዎች ቢነሱም ሌሎቹ ክልከላዎች ባሉበት ሁኔታ አዋጁ እስካለ ድረስ የሚቀጥሉ ይሆናል።

ያም ሆነ ይህ ግን በእኔ እምነት ወሳኝ ብዬ የምገልፃቸው የእነዚህ ክልከላዎች መነሳት ትልቅ ትርጉም ያለው ይመስለኛል። በአዋጁ ላይ የተደረገው ለውጥ ሀገራችን ከሁከቱ በኋላ በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሰላሟን እያረጋገጠች መሆኗን ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህልም በትላልቅ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች አካባቢ በምሽት ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተጥሎ የነበረው ገደብ መነሳቱ፤ በልማት አውታሮቹ ላይ ጨለማን ተገን በማድረግ ሊፈፀሙ የሚችሉ ጥቃቶች በአመዛኙ እንደ ስጋት የሚቆጠሩ አለመሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

ከሰዓት እላፊ ጋር ተያይዞ የነበረው ገደብ መነሳቱም እንዲሁ። የክልከላዎቹ መነሳት በህግ ተገድቦ የነበረውና በአንዳንድ አካባቢዎች ተጥሎ የነበረው የዜጎች የመንቀሳቀስ መብትን በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል። የፀጥታ ኃይሉ ርምጃ እንዲወስድ ተሰጥቶት የነበረው መብት እንዲቀር መደረጉም ህዝቡ የፀጥታውን ስራ ተረክቦ ሰላሙን በባለቤትነት መንፈስ እያከናወነ መሆኑን አመላካች ይመስለኛል።

ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችንና ንብረቶቻቸውን መፈተሽና አዋጁ እስካለ ድረስ ይዞ ማቆየትን የሚፈቅደው ክፍል መቅረቱም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ ሊፈፀሚ የሚችሉ የህግ መተላለፎች ካሉ፤ በመደበኛው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያሳያል። በአንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ዜጎች በሂደት ወደ ሰላማዊውና ወደ ነበረው ሁኔታ መመለሳቸውንም ያመላክታል። በጥቅሉ የእነዚህ ክልከላዎች መነሳት ሀገራችን ወደ ቀድሞ ሰላሟና ልማቷ በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለሷን የሚያረጋግጥ ነው።

ሆኖም አንዳንድ ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ማየት የማይሹ ፅንፈኛ ሃይሎች በተጠና አኳኋን “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቼ ይነሳል?” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ይደመጣል። የእነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች ፍላጎት ምንም ይሁን ምን፤ የአዋጁ መነሳት የሚጠቅመው ለሰላም በመትጋት ላይ ላሉት የሀገራችንን ህዝቦች እንጂ ለእነርሱ አለመሆን ሊገነዘቡት የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ሃይሎች በአንድም ይሁን በሌላ መልክ ለሀገራችን በጎ አሳቢ ስላለሆኑ ነው። ምናልባትም ፅንፈኞቹ ከአዋጁ መነሳት ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው አስበው ከሆነ፤ አዋጁ የሚነሳው አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑት ጉዳዩች ሙሉ ለሙሉ ሲቀሩ ብቻ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። እንዲሁም አዋጁን ከሰላሙ አኳያ የመነዘረው የሀገራችን ህዝብ ከተጨባጭ የአካባቢው ሁኔታ በመነሳት በውውይትም ይሁን በወከላቸው እንደራሴዎቹ አማካኝነት እንዲቀር ሲወስን መሆኑን መረዳት ተገቢ ይመስለኛል።

እንደ እውነቱ ከሆነ በመመሪያ ቁጥር አንድና ሁለት ላይ ያሉት ክልከላዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ የተደረጉት ዝም ተብሎ አይደለም። ደረጃ በደረጃ በመደበኛ የህግ ማዕቀፎች ውስጥ ሊከናወኑ የሚችሉ በርካታ ጉዳዩች ቢኖሩም፤ አሁንም ቢሆን በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የኮማንድ ፖስቱንና በአካባቢዎቸን የፀጥታ ሃይሎች ጥምረት የሚጠይቁ ስራዎች መኖራቸው አልቀረም። በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች ሆን ተብሎ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስተጓጎል፣የግለሰቦችን ነፃነት የመጋፋትና ተቀጣጣይና ፈንጂ ነገሮችን የመጣል ምልክቶች እየታዩ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች በመደበኛው ህግ ብቻ እነዚህን ችግሮች ማስወገድ አይቻልም። እናም ችግሩን ከህዝብ ጋር ሆኖ በጋራ ለመፍታት ጊዜ ይጠይቃል።

ርግጥ በጊዜ ሂደት ውስጥ አስተማማኝ ሰላም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች እውን መሆኑ አይቀርም። “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” እንደሚባለው ነገሮችን በሰከነ መንገድ መመልከት ያስፈልጋል። አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የህዝቡን ስሜት በማጤንና ተገቢውን ጥናት በማካሄድ አዋጁ እንዲቀጥ አሊያም እንዲቀር ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚህ ውጪ እን እገሌ ስላሉ ተብሎ የሚቀርም ይሁን የሚቀጥል አዋጅ ሊኖር አይችልም። ምናልባት ፅንፈኞችና የፀረ-ኢትዮጵያ ሃየሎች ተላላኪዎች ዛሬም እንደ ትናንቱ ቀዳዳ እናገኛለን በሚል ቀቢፀ-ተስፋ የአዋጁን መነሳት ይፈልጉት ይሆናል።

ሆኖም እነርሱ ያሻቸውን ያህል የአሉባልታ እምቢልታቸውን ቢጎስሙም፤ ገና ከመጀመሪያው አዋጁ ሲወጣ የህዝቡንና የሀገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ በመሆኑ ውሳኔውም ይህን ዕውነታ ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል። አዋጁ ሊጠናቀቅ የቀረው የአንድ ወር ዕድሜ ብቻ ነው። በዚህ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የአዋጁን መቀጠልና መቅረት ለሚወስነው የሀገራችን ህዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ በማወያየትና የመርማሪ ቦርዱን ሪፖርት በማዳመጥ የህዝብንና የሀገርን ሰላም በዘላቂነት ሊያረጋግጥ ከሚችል የውሳኔ አንድምታ አኳያ በመመርመር መሆን አለበት። ፅንፈኞቹና የፀረ- ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪዎችም ቢሆኑ ይህን ሃቅ በማወቅ፤ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ቦይ ውሃ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ የሚነጉድ ህዝብ ሊኖር እንደሌለ ከጥላቻ ቆፈናቸው ወጥተው መገንዘብ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ።