እነሆ የኤርትራ ህዝብ በራሱ መላ ከሻዕቢያ የግፍ መንጋጋዎች አርነት እየወጣ ነው። ራሱን ከተጫነበት የአፈና ቀንበር በራሱ መንገድ እያላቀቀ ነው። በተለይም በወጣቱ ዘንድ “ዘፀአት” (exodus) እየሆነ ነው—ዘፀአተ-ኤርትራ። በገዛ ሀገሩ የተሰቃየው፣ “ታግዬልሃለሁ” በሚለውና በቀደሙት የትግል ዓመታት ምናልባትም እንደ ሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ሰላምን ያመጣልኛል ይሆናል ብሎ ተስፋ አድርጎበት የነበረውን የሻዕቢያን የስቃይ አገዛዝ እንደ መፅሐፍ ቅዱሱ የግብፁ ፈርኦን በመሸሽ እግሬ አውጭኝ በማለት እትብቱ ከተቀበረባት ሀገር እየሸሸ ነው።
ራሱን “ህግደፍ” (ህዝባዊ ግንባር ለፍትህና ዴሞክራሲ) በሚል ውስጠ ወይራ ስያሜ በሚጠራው ሻዕቢያ ፍዳውን ማየት በቃኝ ያለ ይመስላል—የኤርትራ ህዝብ። ከህዝባዊነትም፣ ከፍትሁም ይሁን ከዴሞክራሲው ጋር ሆድና ጀርባ የሆነውን የሻዕቢያ የግፍ አስተዳደር በመሸሽ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ማቅናት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ተስፋ ወደሚያገኝባቸው ሀገራት ተሰዷል—ለጠረፍ ጠባቂዎች እስከ 100 ሺህ ናቕፋ በመክፈል ጭምር።
ሆኖም ይህ ወንድምና እህት ህዝብ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለፀው እስራኤላውያንን ነፃ እንዳወጣው ሙሴ፤ ሀገሩን ለቆ ለመውጣት የሚያግዘው የለም። በራሱ ጊዜ ሻዕቢያዊው የአፈና ምሬት ሲያንገሸግው በየፊናውና በትናንሽ ቡድኖች ማቄን ጨርቄን ሳይል እብስ የሚል አሳዛኝ ህዝብ ነው።
አዎ! ኤትራዊያኑ በዚህ ጉዟቸው ላይ እንደ መፅሐፍ ቅዱሱ ሙሴ የኤርትራን ባህር በበትር ከፍሎ አርነት የሚያወጣቸው መሪ የላቸውም። እናም በቤተሰብ አሊያም በቡድን በመሆን ነፍሳቸውን ጭምር “በመሸጥ” በሀገራቸው ካለው እጅግ የገዘፈ የስቃይ ቀንበር ተስፋ ወደሰነቁባቸው የጎረቤት ሀገራት ምድር ይሸሻሉ።
ርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ከዚያ ሀገር ህዝብ ጋር በደም፣ በታሪክ፣ በባህልና አብሮ በመኖር ሊፋቁ የማይችሉ ትስስር ያለው ህዝብና መንግስት የዚህን ህዝብ ሰቆቃና ስቃይ በዝምታ ሊያዩ አይችሉም። እናም የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝብ ሻዕቢያንና አገዛዙን በመሸሽ፣ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ሻዕቢያ በራሱ ህዝብ ላይ ያረቀቀውን “ተኩስና ግደል” (Shoot and Kill) ፖሊሲን አምልጠው ወደ ሀገራችን የሚመጡትን ኤርትራዊያን መጠለያ በመስጠት፣ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ተንቀሳቅሰው እንዲኖሩ በመፍቀድና እንደ ሀገራችን ዜጎች እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ በነፃ እንዲማሩ እያደረጉ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ወንድምና እህት የሆነው የኤርትራ ህዝብ ስቃይ የራሳቸው ጭምር መሆኑን እያሳዩ ነው። እርግጥም ወንድምና እህት ኤርትራዊያን ወደ ተስፋዊቷ ሀገር ተስፋቸውን ሰንቀው መምጣታቸው ትክክል መሆኑን በአሁኑ ወቅት ከሀገራችን ዜጎች ባልተናነሰ ሁኔታ ለእነርሱ እየተደረገ ያለውን ነገር የሚገነዘቡት ይመስለኛል።
ለዚህም ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የመንግስታቸውን የስድስት ወራት ሪፖርት ኤርትራን በሚመለከት ሀገራችን የምትከተለውን የፖሊሲ አቅጣጫን ሲገልፁ፤ የኢፌዴሪ መንግስት ፖሊሲ የሁለቱን ሀገራት ወንድምና እህት ህዝቦች ጥቅም ሊያስከብር በሚችል ቅኝት እንደሚመራ ማስታወቃቸውን በእማኝነት መጥቀስ የምችል ይመስለኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ላይ ‘በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ በየቀኑ ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ የዚያች ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ናቸው። ከዚህ ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የሀገሪቱ ወታደሮች መሆናቸው ሁኔታው ምን ያህል የከፋ መሆኑን የሚያሳይ ነው’ ማለታቸው ምናልባትም አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ በዘያች ሀገር ውስጥ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ከ20 የማይበልጡት የኤርትራ መንግስት ቱባ ሹማምንቶች ብቻ ሊቀሩ የማይችሉበት ምክንያት ያለ አይመስልም።
ታዲያ ሃቁ ይህ ቢሆንም ቅሉ፤ የኤርትራ መንግስት ማስታወቂያ ሚኒስቴር የህዝቡን ዘፀአት አስመልክቶ “ለፍልሰቱ ሰበብ ኢትዮጵያ ነች። ስደቱ በሀገራችን ውስጥ ባለው ችግር ሳቢያ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ሊሰነዘር የሚችለውን ጦርነት በመፍራት ነው” ሲል ይደመጣል።
ይህን አባባልም ልክ እንደ አሸባሪው ግንቦት ሰባት አመራሮችና ኢሳት እንደተሰኘው ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት እንደተሰለፈው ጣቢያ ሰራተኞች ሁሉ በሻዕቢያ የደመወዝ መክፈያ ቅፅ ላይ ስሙ የሰፈረው “የመረጃ ዳት ኮሙ” ኤሊያስ ክፍሌ አማካኝነት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ምላሽ በሰጡ ማግስት ይህንኑ የአፀፋ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል። ነገሩ አበው “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉት ዓይነት ራስን የማሞኘት ምላሽ ቢሆንም፤ ሃቁ ግን ያው የተለመደው የኤርትራ መንግስት “የአብዬን ወደ እምዬ” የተሰኘ አስቂኝ ምላሽ ከመሆን የሚዘል አይመስለኝም።
ሻዕቢያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኤርትራን የሰብዓዊ መብት አያያዝ አስመልክቶ በተለያዩ ወቅቶች ‘የህዝብህን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚዘገንን ሁኔታ ትጥሳለህ፣ ተቃዋሚ ዜጎችህን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በየጎጡ በሰራሃቸው ኮንይነሮች ውስጥ አፍነህ ትገድላለህ፣ በግርፋት ታሰቃያለህ፣ አካል ታጎድላለህ፣ ዓይን ታጠፋለህ…ወዘተ.” እያለው፤ እርሱ ግን ዓይኑን በጨው ታጥቦ ያለ አንዳች ሃፍረት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ አማካኝነትና ለእርሱ እንዲሰሩ በቀጠራቸው ኢትዮጵያዊ ባንዳዎች አማካኝነት ‘ኤርትራ ውስጥ ማርና ወተት ይዘንባል’ የማለት ያህል ምላሽ እየሰጠ በራሱ ቀልድ መልሶ ራሱ ለመሳቅ የሚሞክር የሞኝ ተሟጋች ሆኗል። ሆኖም “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንዲሉ፤
ያም ሆነ ይህ ግን፤ ሃቁ ለውድ አንባቢያን ፍንትው ብሎ ይታይ ዘንድ ኤርትራ ውስጥ ስላለው እውነታ፣ ሻዕቢያ በህዝቡ ላይ ምን ዓይነት ስቃይ እንደሚከውንና ኤርትራዊያን በምን ምክንያት ከሀገራቸው እንደሚሰደዱ አንድ ምሳሌ ብቻ ለማንሳት እሞክራለሁ—ከሻዕቢያ የስቃይ ሰለባ የሆነን ዜጋ በመጥቀስ። የዚህን ኤርትራዊ ምልልስ ያገኘሁት በኤርትራ ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት ጥናት ሲያካሂድ ከነበረው ዳን ኮኔል ከተባለ አሜሪካዊ ተመራማሪ ነው።
ለመሆኑ ዳን ኮኔል ማነው?…ዳን ኮኔል በትጥቅ ትግሉ ወቅት የኤርትራ ጉዳይ ይመስጠው የነበረ ተመራማሪ ብቻ አይደለም፤ ዛሬ ከምግባራቸው በመነሳት በሙሉ ዓይኑ ሊያያቸው የማይፈቅደው የኢሳይያስ አፈወርቂ አድናቂ የነበረ ጭምር እንጂ። የኤርትራን የትጥቅ ትግል አስመልክቶም መፅሐፍ እስከ መፃፍ የዘለቀም አጥኚ ነበር።
መቼም የሰው ልጅ ሚዛናዊ ህሊና ያለው ፍጡር ነውና በአንድ ወቅት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይዞት የነበረውን አቋም፤ ወደ ትክክለኛው እርሱነቱ ሲመለስ መቀየሩ የሚቀር አይመስለኝም። እናም ዛሬ ሚስተር ኮኔል ወገንተኝነቱ ለሻዕቢያና ለአምባገነናዊ መሪዎቹ ሳይሆን ለኤርትራ ህዝብ ሆኗል። ይህ ደግሞ ትክክለኛ አቋም ይመስለኛል። ይህ አቋሙም ምናልባት ወደፊት ያኔ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያለወቀውን የሻዕቢያን ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ጦረኛ ብሎም ጥገኛ ባህሪያዊ ማንነቱን፣ በአሁኑ ወቅት ሻዕቢያ በህዝቡ ላይ እየፈፀመ ካለው ዘግናኝ ድርጊት ጋር አያይዞ ዳጎስ ያለ መፅሐፍ ያስነብበናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ያም ሆኖ ከዳን ኮኔል ማንነት ልውጣና እርሱ በመጦመሪያ ገፁ ላይ ስላሰፈረው የሻዕቢያ አገዛዝ ሰለባ ስለሆነ አንድ ሰው ላንሳ። ዳን ኮኔል በመጦመሪያ ገፁ ላይ ያሰፈረው የ“ፍስሃዬ” (ለቤተሰቦቹ ደህንነት ሲባል ስሙ ተቀይሯል) ታሪክ እንደወረደ እንዲህ የሚነበብ ነው።…
“…አሜሪካ ከመጣ የአንድ ወር ዕድሜን ብቻ ነው ያስቆጠረው— ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ያገኘሁት የ36 ዓመቱ ፍስሃዬ (ስሙ ተቀይሯል)። ሰውዬው ብዙም የማይናገር፣ ነገር ግን ብርታት ፊቱ የሚታይበት ጎልማሳ ነው። ይህ ሰው የዕድሜውን እኩሌታ መግቢያ እንጂ መውጫ ቀዳዳ በሌለው የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ውስጥ አገልግሏል—ለ18 ዓመታት። እ.ኤ.አ በ1996 ዓ.ም በአስራ ስምንት ዓመቱ በግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ውስጥ እንዲገባ መደረጉንና ቀሪዎቹን አስራ ስምንት ዓመታት እዚያው ሰምጦ መቅረቱን ይናገራል።
እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም የመጀመሪያ የውትድርና አገልግሎቱ ወቅት የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። በቆይታውም የእንስሳት ጤና ሳይንስ ትምህርቱን ተከታትሏል። የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ሲቀሰቀስም እዚያው ነበር። ይሁንና ጦርነቱ እ.ኤ.አ በሰኔ 2000 ዓ.ም እንደገና ሲጀመር ዳግም ተጠርቶ ወደ አሰብ ተጓዘ። እዚያም ለአንድ ዓመት በነበረው ቆይታም በጂቡቲ ድንበር አቅራቢያ ወታደራዊ ተግባራትንና የእንስሳት ጤና ስራን አዳብሎ እንዲያከናውን መደረጉን ፍዝዝ ብሎ ያስረዳል።
እ.ኤ.አ. በ2001 ዓ.ም ፍስሃዬ ወደ ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አስመራ ዪኒቨርሲቲ ተመለሰ። ከተመረቀ በኋላም በግብርና ሚኒስቴር ስር ተመድቦ ደቡባዊ ዞን (ዞባ ደቡብ) ይመደባል። ከዓመታት ቆይታ በኋላ እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ወደ አስመራ ዋናው መስሪያ ቤት እንዲዛወር ተደርጓል። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ለረጅም ጊዜ የወር ደመወዙ 145 ናቕፋ (10 ዶላር) እንደነበር የሚናገረው ፍስሃዬ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በማይታወቅ ሁኔታ የወር ደመወዙ ባንዴ 500 ናቕፋ እንዲሆን መደረጉን ያስረዳል። ይሁንና በአንዴ የተጨመረው የወር ደመወዝ ምክንያትን ብዙም ሳይቆይ ግልፅ እንደሆነለት ይናገራል።
አዎ! መቼም ስም አይከለከልምና ራሱን “ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ” (ህግደፍ) እያለ የሚጠራው ፀረ-ህዝብ ድርጅት ካድሬ እንዲሆን እንደመለመለው ሲነገረው፣ የጭማሪው ምስጢርም ፍንትው ብሎ ተገልፆለታል። ዳሩ ግን ፍስሃዬ የሻዕቢያን በካድሬነት ተመልማይነቱን አልተቀበለውም። ግና አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ “አልፈልግም” ማለት ወይም የተለየ ሃሳብ ማራመድ ለራስ መሰቀያ የሚሆን ገመድ ገዝቶ ለመሰቀል የመሰናዳት ያህል ነውና ይህ የፍስሃዬ እምቢተኝነት መዘዝ አስከተለበት። ወደማይወጣው ጥልቅ ሻዕቢያዊ የፖለቲካ መቀመቅ ውስጥም ከተተው።
አስገራሚው ነገር ፍስሃዬ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ፤ የሻዕቢያን የፖለቲካ ሹመኞች የጠየቃቸው ጥያቄ ነው—“የተጠየቅኩት የህግደፍ ካድሬ እንድሆን ነው። ለምን ሌሎች ፓርቲዎች ወይም ግንባሮች አልኖሩም?” የሚል። በእውነቱ አስገራሚ ጥያቄ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ “ለኤርትራ የፖለቲካ ፓርቲና ምርጫ ምን ያደርግላታል?” ለሚለው ህግደፍ ስለ ሌሎች ፓርቲዎች አለመኖር መናገር የቅንጦት ያህል የሚታይ አባባል ነው። ከፍ ሲልም ራስን ለሻዕቢያ የማሰቃያ እስር ቤቶች የሚዳርግ ቅብጥብጥነት።… እናም ፍስሃዬ ባሬንቱ አቅራቢያ ወደሚገኘው እስር ቤት ተጋዘ። ለ28 ቀናትም የካድሬ ምልመላውን እስኪቀበል ድረስ ተከርቸም ገባ። በእነዚህ ቀናትም ውስጥ አሁንም “ለምን?” የሚል ጥያቄውን ከማቅረብ ግን ወደ ኋላ አላለም።
በህግደፍ በኩል ግን የፍስሃዬ ጥያቄ የታየው የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርናን ይቃወም ከነበረውና የተማሪዎች ቀስቃሽ ሆኖ ይሰራ ከነበረው ከሠመረ ከሰተ ጋር ካለው ቁርኝት አኳያ ነበር። ሰመረ እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም ክረምት ላይ በምረቃው ዕለት የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርናን አውግዞ ባደረገው ንግግር ሳቢያ በሻዕቢያ ሰፋፊ የግፍ እጆች ታፍሶ ወደ ዘብጥያ የወረደ ኤርትራዊ ነው። ተማሪዎች እንዲቃወሙ ሲገፋፋ የነበረ ትንታግ ቀስቃሽም ነበር።
የዚህ ሰው መታሰር በተለይም “ዋርሳይ ይኽኣሎ” በሚባለው ፕሮግራም በሀገሪቱ ቆላማ ከባቢዎች በነፃ ስራ ላይ ተሰማርተው ጉልበታቸውን ይበዘበዙ የነበሩ ተማሪዎችን ቁጣ መቀስቀሱ ይታወቃል። እናም የፍስሃዬ ጥያቄ በሻዕቢያ ዓይን የታየው ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ነው። ያም ሆነ ይህ ግን ፍስሃዬ ሁለት በሁለት ነጥብ አምስት ሜትር (2×2.5 ሜትር) ስፋት ባለው፣ ከበረዶ የሚቀዘቅዝ ባዶ የሲሚንቶ ወለል፣ መስኮት አልባና ብርድ ልብስ በሌለው በዚህ እጅግ ጠባብ የስቃይ እስር ቤት ውስጥ ከመከርቸም አላመለጠም።
ራሱን በህይወት ለማቆየት ሲል ብቻ ተጥላ ባገኛት የዱቄት መያዣ ከረጢት ውስጥ ጥቅልል ብሎ ይተኛል። ግፍ የማይፈራው ሻዕቢያም በየቀኑ አንድ ሲኒ ሻይና አንድ ዳቦ ይወረውርለታል።…የሌት ተቀን ህይወቱም ይኸው ነው።…የአብዛኛዎቹ ኤርትራውያን ስደተኞች ታሪክ ተመሳሳይ ነው። የሻዕቢያ የግፍ አፈፃፀም ከግለሰብ ግለሰብ ይለያይ እንደሆን እንጂ፤ ከፍስሃዬ ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ሃቅም የአቶ ኢሳያስ መንግስት በዜጎቹ ህይወት ላይ ምን ያህል ቀላጅና አረመኔያዊ ተግባር እንዲሚፈፅም የሚያሳይ ነው።…” ይላል ተመራማሪው ዳን ኮኔል።
ርግጥ ይህ የግለሰቡ እማኝነት ሻዕቢያንነናበህዝቡ ላይ የደቀነውን ስቃይ የሚያሳይ ነው። ኤርትራዊያኑም የራሳቸው ሙሴ ሆነው ከሻዕቢያ የግፍ ቀንበር ራሳቸውን ነፃ እያወጡም ጭምር መሆኑን። ይህም ኤርትራዊያኑ ከሀገራቸው የሚሰደዱት ሻዕቢያ እንደሚለው ሀገራችን ጦርነት ትከፍትብናለች ብለው ሳይሆን፤ የሻዕቢያን የስቃይ አስተዳደር በመሸሽ ብቻ መሆኑን ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በኤርትራ ወንደሞቻቸውና እህታቸው ላይ የሚሰብቁት ጦር የለም።
ጦረኝነት የሻዕቢያ እንጂ የኢፌዴሪ መንግስት መለያ ባህሪ አይደለም። ሻዕቢያ ከሳህል በረሃ ወጥቶ ኤርትራን ሲያስተዳድር በጦረኛ ክራንቻ ጥርሱ ያልነከሰው የጎረቤት ሀገር የለም። በቅድሚያ “ሃኒሽ ደሴት የኔ ነው” ብሎ የመንን ወረረ፣ ወረራው በፍርድ ቤት ሲቀለበስበትም ወራሪ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ። ይህም ቢሆን አልቀናውም—በሀገራችን ህዝቦችና በመከላከያ ሰራዊታችን ጥምረት በመጣበት እግሩ ወደ አስመራ ተፈተለከ። ከዚያም በሱዳን መንገስት ላይ “የቤጃ እንቅስቃሴ” የሚል አንጃዎችን በመፍጠር በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ይፈተፍት ገባ። ይህ አልበቃ ብሎትም “ራስ ዱሜራ” የሚባለውን የጂቡትን ግዛት “አሸዋ ልወስድ ነው” በሚል ዘልቆ በመግባት ደፈረ።
በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ በመግባትም ለአሸባሪው አልሸባብ በየወሩ 80 ሺህ ዶላር በደመወዝ ሲከፍልና የሎጀስቲክስ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አረጋግጧል። በአንድ ወቅትም የሻዕቢያ ረጃጅም የሁከት እጆች በአዲሲቷን ደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ግጭት ውስጥ አስገብቶ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ይህም ሻዕቢያ በጦርነት አውድ እንጂ በሰላም ውስጥ መኖር የማይችል የጦር አምላኪዎች ስብስብ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህ ሁኔታም በእኔ እምነት ሻዕቢያ የጦርነት ሱሱን ለመወጣት በሀገራችን ፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እንደ አሮጌ ዕቃ የወዳደቁ ተስፋ ቢስ ተላላኪዎችን ከየጎሬያቸው እየለቃቀመ፣ እያሰለጠነ፣ እያደራጀና እያስታጠቀ ወደ ሀገራችን ለማስገባት በመሞከር የሀገራችንን ሰላም ለማወክ በመሞከር ይገለፃል። ያም ሆኖ ግን የሻዕቢያ ጦረኛ ፍላጎት በየጊዜው በፀጥታ ሃይሎችና በየአካባቢው ሚሊሻዎች ብቻ እየከሰመ በመሆኑ ሻዕቢያ ጦርነት እንዳማረው እንደቀረ ነው።
ምንም እንኳን በህዝባዊ አመለካከትና በልማት አኳያ ሻዕቢያንና የኢፌዴሪ መንግስትን ማወዳደር አግባብ ባይሆንም፤ ጦርነት የሻዕቢያ ማንነት መገለጫ እንጂ መቼም ቢሆን የቀጣናው የሰላም አውራ የሆነው የኢፌደሪ መንግስት ፍላጎት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም የኢፌዴሪ መንግስት ለቀጣናው፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላም መሆን ላለፉት 26 ዓመታት እየተጋ የሚገኝ የሰላም መቅረዝ በመሆኑ ነው።
የኢፌደሪ መንግስት የሚከተለው የውጭ ፖሊሲ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት እንዲሁም የቀጣናው ሀገራት በልማት ተሳስረው ምስራቅ አፍሪካን የዕድገት ማሳያ የማድረግ መርሆችን እንጂ ስለ ጦርነት የሚያስብበት የሰከኮንዶች ሽርፍራፊ የሚሆን ጊዜ የለውም። ይህ ማለት ግን ሻዕቢያ እንዳሻው ሲፈነጭ ዝም ብሎ ይታያል ማለት አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንዳሉት “ተመጣጣኝ ምላሽ” ያገኛል። እናም ሻዕቢያ አንድ ትንኮሳ ከመፈፀሙ በፊት ሶስቴ ማሰብ ያለበት ይመስለኛል።
-የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡ እያንዳንዷ የሰላም ቀን በልማታቸውና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እመርታቸው የምታመጣውን ለውጥ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ እየተገነዘቡ የመጡ እንጂ፤ እንደ ሻዕቢያ በየሀገሩ እየዞሩ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” የሚሉ አይደሉም። ለጎረቤቶቻቸው ስለሚጨነቁም ሰላም ለራቃቸው አፍሪካዊ ወንድሞቻቸው የሰላም ጠባቂ ሆነው ተሰማርተዋል።
በብሩንዲ፣ በላይቤሪያ በሱዳን-ዳርፉር፣ በሶማሊያ፣ በአብዬ ግዛትና በደቡብ ሱዳን ሰላምን ለማስፈን ያደረጉትና በማድረግ ላይ ያሉት ጥረት ተጠቃሽ ነው። ይህ ጥረታቸውም ዕውቅና አግኝቶ ሀገራችን በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና እንድትመረጥ አድርጓታል። በዚያው ሰሞን ደግሞ ሻዕቢያና አመራሮቹ በህዝባቸው ላይ በሚፈፅሙት መገለጫ የሌለው አሰቃቂ ተግባር ሲወነጀሉ እንደነበር የኤርትራ ሹማምንቶች ሊዘነጉ የሚገባ አይመስለኝም።
በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግስት ወንድምና እህት የሆኑትን የኤርትራን ህዝቦች ሲያስጠጋ፣ መጠለያ ሲሰጥና እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማሩ ዕድል ሲሰጥ ካለው ህዝባዊ ባህሪ በመነሳት መሆኑን ሻዕቢያውያን ሊዘነጉት የሚገባ አይመስለኝም። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ነገ የሀገራችንን ህዝብና ወንድም የሆነውን የኤርትራን ህዝብ ግንኙነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ፖሊሲዎች ይጠናሉ እንጂ፤ ያ ወንድምና እህት ህዝብ የሻዕቢያ የስቃይ ገፈት ቀማሽ ሆኖ እንዲቀጥል ድንበሩን ሊዘጋ አይችልም። እናም የኤርትራዊያኑ ዘፀአት ትክክል ብቻ ሳይሆን አዲስ ተስፋ ወደሚሰንቁባት ሁለተኛ ሀገራቸው ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ ይመጣሉ። የኤርትራዊያኑ ችግር የሚፈታው በራሳቸው በኤርትራዊያኑ ነው። የሻዕቢያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እየደጋገመ እንደሚለው እኛ የእነርሱ ሙሴ ልንሆን አንችልም። የራሳቸው ሙሴ መሆን ያለባቸው ራሳቸው ናቸው። ወደ እኛ ሲመጡ ግን ኢትዮጵያዊያን እንኳንስ ወንድሞቻችን ቀርቶ፤ የትኛውንም ህዝብ በእንግዳነት የምንቀበል ሰው አክባሪዎች በመሆናችን፤ እነርሱ ወደ ተስፋይቷ ሀገር ተስፋቸውን ሰንቀው ሲመጡ እኛም “ቤት ለእንቦሳ” ማለታችን መቼም ቢሆን የሚቀር አይደለም።