ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ከወሰን አከላለል ጋር በተያያዘ የግጭትነት ባህሪ ያለው ችግር ተቀስቅሷል። የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የጋራ ድንበር ቢኖራቸውም የግጭት ባህሪ ያለው አለመግባባት የተፈጠረው በጥቂት አካባቢ ነው። ችግሩ ያለው በኦሮሚያ ቦረና ዞንና በአዋሣኝ የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢ በሚገኙ 26 ቀበሌዎች ላይ ብቻ ነው።
የቦረና (የኦሮሞ) እና የሶማሌ ብሄሮች ከ500 ለማያንሱ ዓመታት በድንበር ተጋሪነት አብረው ኖረዋል። በዚህ የድንበር ተጋሪነት ኑሯቸው ወሰን አስምረው እንደባላንጣ ሩቅ ለሩቅ ከመተያየት ይልቅ በእጅጉ ተቀራርበው ነው የኖሩት። ኦሮሞዎችና ሶማሌዎች ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋል፣ ለጋራ ችግራቸው ሸንጎ ተቀምጠው መክረው መፍትሄ አበጅተዋል፣ የጋራ ጠላታቸውን ለመመከት ጎን ለጎን ተሰልፈው ተዋግተው ደማቸውን አፍስሰዋል። ይህ በሁለቱ ብሄሮች ብዙ ትውልዶች የተካሄደ መቀራረብ በድንበራቸው አካባቢ የሁለቱም ብሄራዊ ማንነቶች ክልስ የሆኑ ማኅበረሰቦች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ይህ ክልስ ማንነት በዋዣቂ ማንነት (flood identity) የሚገለጽበት ሁኔታዎች አጋጥመዋል።
እነዚህ ዋዣቂ ማነነት ያላቸው ማኅበረሰቦች የሁለቱንም ብሄሮች ማነነት በእኩል የሚጋራ መገለጫዎች አላቸው። ለምሣሌ ኦሮሚኛ ቋንቋ የሚናገሩ ሆነው የመኖሪያ ቤት አሠራራቸው፣ የጋብቻ ሥርዓታቸው…የሶማሌ ማኅበረሰብ ባህል የሚሆንበት ሁኔታ አለ። ለምሣሌ የገሪ፣ ጋርባ፣ ጃርሶ…ጎሣዎች ውስጥ ውስጥ የዚህ ዓይነት ነገር ይታያል። ቋንቋቸው ኦሮሚኛ ቢሆንም፣ ከከብት ይልቅ የግመል እርባታ ላይ መመሥረታቸው፣ የቤት አሠራራቸው ከሶማሌ ጋር ያመሳስላቸዋል። አብዛኛው የቦረና ኦሮሞ ጎሣ አባላት ኃይማኖት ዋቄፋታ ሲሆን፣ እነዚህ ሦስት ጎሣዎች ከሶማሌዎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ናቸው።
ይህ ሁለቱንም የሚጋራ ማንነት ያላቸው ማኅበረሰቦች መኖር፣ የሁለቱ ብሄር ማኅበረሰቦች አብሮነቱ ምን ያህል ጥብቅ ትስስር እንዳለው ያሳያል። በጠላትነትና በጥርጣሬ ከመተያየት ይልቅ አንዱ ሌላውን ወገኑ አድርጎ እየተሳሰቡ አብረው መኖራቸውን ያመለክታል። ይህ የጋራ እሴት በአግባቡ ከተያዘ ጠንካራ የጋራ ልማት መሠረት ሊሆን ይችላል።
በሌላ በኩል፤ በኦሮሚያ ቦረና ዞንና በአዋሣኙ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ ናቸው። የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ዋነኛ መለያ ኖሯቸው በአንድ ቦታ የረጋ ሳይሆን በተወሰነ አካባቢ ለከብቶች መኖ የሚሆን ሣርና ውኃ ፍለጋ ተንቀሳቃሽ መሆኑ ነው። አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች አንድ ቦታ ረግተው አይኖሩም። ወቅት ተከትለው ለከብቶቻቸው ሣርና ውኃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። ይህ የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች የኑሮ ዘይቤ ለእርስ በርስ ግጭት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። በሣር መስክና በውኃ መገኛ ሥፍራ ላይ ሽሚያ የሚገቡበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ይህ ሽሚያ ወደግጭት የማምራት እድሉም ሰፊ ነው።
እርግጥ የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች በግጦሽ ሣርና ውኃ ሽሚያ ሁሌም ግጭት ውስጥ ይገባሉ ማለት አይደለም። በተለይ በአየር ንብረት መዛባት ለግጦሽ የሚሆን ሣርና ውኃ ያለው ሥፍራ በሚያንስበት አጋጣሚ ነው በአመዛኙ ወደግጭት የሚገቡት። እናም በተመሳሳይ የአርብቶ አደርነት የኑሮ ዘይቤ የሚተዳደሩ ማኅበረሰቦች ባሉባቸው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ድንበር አካባቢዎች፣ በሁለቱ ብሄሮች ጎሣዎች ወይም ማኅበረሰቦች መካከል ግጭቶች ሲቀሰቀሱ የኖሩበት ሁኔታ አለ። የግጭቶቹ መንስዔ ግን የአንዱ ኦሮሞ መሆን፣ የሌላው ሶማሌ መሆን አይደለም፤ ግጭቱ የብሄር ግጭት አይደለም። ይህ ግጭት በኦሮሞ አርብቶ አደሮች ወይም በሶማሌ አርብቶ አደሮች ማኅበረሰቦች መካከልም ያጋጥማል። ለምሣሌ የተለያዩ የቦረና ጎሣዎች እንዲሁም የቦረናና የጉጂ ጎሣዎች የሚጋጩበት ሁኔታ ነበር። ይህ በኦሮሞና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሣኝ አካባቢ በአርብቶ አደሮች መካከል የሚቀሰቀሱ ግጭቶች መነሻ ብሄር ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን በግልጽ ያሳያል። በሁለቱ ተዋሣኝ ብሄሮች ማኅበረሰቦች መካከል ብሄርን መሠረት ያደረገ ግጭት ተቀስቅሶ አያውቅም። አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታቸው ሲታይ ከግጭት ይልቅ እጅግ ተቀራርበው በሠላም የኖሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ሆኖ እናገኘዋለን።
ከዚህ በተጨማሪ እንደማንኛውም የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ የሚገጥሟቸውን ግጭቶች እንደተገቢ የኑሮ ዘይቤ ቆጥረው አይቀበሉትም። ወይም በእኔ እበልጥ እኔ የጀብደኝነት መገለጫ አያደርጉትም። ግጭቶቹ እንደ ዘመነ መሣፍንት፣ በተስፋፊነት ግንኙነታቸውን ወደአስገባሪና ገባሪ የመቀየር ዓላማም የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ግጭቶችን እንደ ችግር በመመልከት መፍትሄ የሚያገኙበትና ዳግም በቀላሉ ግጭት እንዳይቀሰቀስ እርቅ የሚወርደበት ሥርዓት ነው የሚከተሉት። በተለይ ሦስቱ ጎሣዎች ቦረና፣ ገሪና ጋርባ ግጭት ሲያጋጥማቸው የሚፈቱበት ናጋ ቦረና (የቦረና ሠላም) የሚባል ተቋም አላቸው። ይህ ናጋ ቦረና የተባለ ተቋም ሠላማዊና የተረጋጋ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖር ይሰራል። ተቋሙ በከብቶች ግጦሽ ሣርና በውኃ ሽሚያ ግጭት በሚቀሰቀስበት ጊዜ፣ ለሽሚያው ፍትሃዊ እልባት በማበጀት እርቅ እንዲወርድ ያደርጋል። እነዚህ ሁኔታዎች በኦሮሞና ኢትዮጵያ ሶማሌ አርብቶ አደር ጎሣዎች መካከል ክፍለ ዘመናትን የተሻገረ በመከባበር፣ በመቻቻልና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደነበር ያረጋግጣሉ። ይህ ራስን በራስ እየመሩ በመቻቻል፣ በመከባበርና በእኩልነት የመኖር፣ ችግሮች ሲፈጠሩም በሠላማዊ መንገድ የመፍታት ባህል ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ለሚኖሩበት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ፋይዳ ያለው ትልቅ እሴት ነው።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከ1983 ዓ.ም በፊት የነበሩበትን ብሄራዊ ማንነታቸው በህግ እውቅና ተነፍጎት ለጭቆና የተዳረጉበትን ሥርዓት ሽረው፣ በእነዚህ ሥርዓቶች የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በማስተካከል ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበር፣ በመቻቻልና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የህዝቦች አንድነት ያለው የመንግሥት ሥርዓት – የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የመንግሥት ሥርዓት ሲመሰርቱ፣ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄሮች በዚህ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ነበሩ። ይህን የመንግሥት ሥርዓት ለመመሥረት አብረው የመኖር የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነውን ህገ መንግሥት አዘጋጅተው አጽድቀዋል።
በዚህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበርና በእኩልነት የህዝቦች አንድነት መሥርተው በሚኖሩበት ፌዴራላዊ ሥርዓት የሶማሌ ብሄር በራሱ ፈቃድ የኢትዮጵያ ሶማሌ የተሰኘ ክልላዊ መንግሥት መሠረተ። ይህ ክልላዊ መንግሥት ማንነታችን ሶማሌ ነው ብለው የሚያምኑ ማኅበረሰቦችን በሙሉ የያዘ ነው። የኦሮሞ ብሄርም በተመሳሳይ ሁሉንም የኦሮሞ ማንነት ያላቸው ማኅበረሰቦች የያዘ ክልላዊ መንግሥት መሠረተ።
ይሁን እንጂ በሁለቱም ክልሎች አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ወሰን የማካለሉ ሥራ መጠነኛ ፈተና ገጥሞታል። ፈተናው የመነጨው በሁለቱም ክልሎች ያሉት ማኅበረሰቦች አርብቶ አደር በመሆናቸው አንድ ቦታ ረግተው የማይኖሩ ተንቀሳቃሽ በመሆናቸው እንዲሁም በዘመናት ጥብቅ ሠላማዊ የአብሮነት ግንኙነት የሁለቱንም ብሄሮች መገለጫ ያላቸው – ዋዣቂ ማንነት (flood identity) ያላቸው ማኅበረሰቦች መኖራቸው ነው። ይህም ቢሆን ግን ማኅበረሰቦቹ በማንነታቸው ላይ ወስነው ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር በህገ መንግሥት የተረጋገጠ መብት ስላላቸው፣ አወዛጋቢ የሆኑት የሁለቱ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ህዝበ ውሣኔ እንዲያካሂዱ ተደረገ። በዚህ መሠረት 80 ገደማ ቀበሌዎች ላይ የማኅበረሰቦቹ ህዝቦች በህዝበ ውሣኔ ድምጻቸውን ሰጥተው በየትኛው ክልል ውስጥ መተዳደር እንዳለባቸው ወስነዋል።
ይሁን እንጂ፣ ይህ ህዝበ ውሣኔ በተወሰነ ደረጃ ለወሰን ማስከበር ጥያቄው ቁርጥ ያለ መፍትሄ አላበጀም። አጋጣሚዎችን እየጠበቀ የግጭት ባህሪ ያለው አለመግባባት መንስዔ ሲሆን ቆይቷል። ይህ በግጭት መልክ የተገለፀ አለመግባባት በቅርቡ በኦሮሚያ ቦረና ዞንና በአዋሣኝ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አካባቢዎች በተለይ በ26 ቀበሌዎች ጎልቶ ወጥቷል። ይህን ችግር ለመፍታት ሁለቱ ክልላዊ መንግሥታት ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም፤ የፌዴራል መንግሥትም የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ቢጥርም ችግሩ አሁንም ይስተዋላል። ይህ የግጭት ባህሪ ያለው ችግር ግን ከነዋዣቂ ማንነታቸውም ቢሆን ይኼኛውን ነኝ ብለው በወሰኑ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ማኅበረሰቦች መካከል የተፈጠረ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የማኅበረሰቦቹ መሪዎች ነን በሚሉ ክልሎቹን በሚያስተዳድሩ አመራሮች በተለይ የበታች አመራሮች የጥቅምና የሥልጣን ፍላጎት የተፈጠረ ችግር ነው።
እንግዲህ ይህ ከግለሰቦች የጥቅም ፍላጎት በመነጨ ማኅበረሰቦቹን በማደናገር ወደአለመግባባት እንዲገቡ የማድረግ አካሄድ አዲስ አይደለም። ክልሎቹ ከተዋቀሩና በህዝበ ውሣኔ ድንበር ከተካለሉ ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው። ይህ በግለሰቦች የጥቅምና የሥልጣን ፍላጎት አነሳሽነት የሚፈጠረውን አለመግባባት ገጽታ በግልጽ ለመረዳት አንድ እውነተኛ ተጨባጭ አስረጂ እንመልከት።
በ1987 ዓ.ም በተካሄደው አንደኛው ዙር አገራዊ ምርጫ አቶ ሸኑ ጎዳና የተባሉ የጋርባ ጎሣ አባል በኦሮሞ ማንነት የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አባል በመሆን በድርጅቱ አቅራቢነት የኦሮሚያ ሞያሌ ወረዳን በመወከል የፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ይመረጣሉ። አቶ ሸኑ ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም ለሁለት ዙር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካገለገሉ በኋላ ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደመጡበት አካባቢ ይመለሳሉ። ከዚህ በኋላ የክልሉ መንግሥት አቶ ሸኑን የቦረና ዞን የህዝብ አደረጃጀትና ማስፈር መምሪያ ኃላፊ አድርጎ ይሾማቸዋል። በዚህ የኃላፊነት ቦታ ለተወሰነ ዓመት ካገለገሉ በኋላ ክልሉ ከኃላፊነታቸው ያነሳቸዋል። ይኼኔ ማንነታቸውን ወደሶማሌነት በመቀየር የኢትዮ ሶማሌ ክልልን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አባል ሆነው ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳ አስተዳደር ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ ይሾማሉ። ይኼኔ፣ ጋርባ የተባለው የእርሳቸው ጎሣ ሁሉም አባላት ሶማሌዎች መሆን አለባቸው የሚል አቋም ማራመድ ይጀምራሉ። እዚህ ላይ አቶ ሸኑ ጎዳና በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ቀስቅሰዋል ብዬ እየወነጀልኳቸው አለመሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ግለሰቡን የጠቀስኳቸው በአጠቃላይ በአካባቢው በግለሰቦች ፍላጎት ወደግጭት ሊያመራ የሚችል ሁኔታ እንዴት እንደሚፈጠር ለማሳየት ስለሚያስችል ነው ያስታወስኩት። እርግጥ ነው አቶ ሸኑ ጎዳና ማንነታቸውን ከኦሮሞነት ወደሶማሌነት የመለወጥ መብት አላቸው። በራሱ ምርጫ ኦሮሞ ነኝ ብሎ በሠላም የሚኖረው የጋርባ ማኅበረሰብ አባላት በሙሉ ሶማሌ መሆን አለባቸው ብለው ህዝቡን መቀስቀሳቸውን ግን ጤናማ ውጤት ይኖረዋል ብሎ መገመት ስህተትነቱ ያይላል። አቶ ሸኑ ጎዳናን በምሣሌነት አነሳሁ እንጂ በሁለቱም ክልሎች የዚህ ዓይነት ሥልጣንና ጥቅም እያሸተቱ የሚዋልሉ በርካታ ፖለቲከኞች አሉ።
በእንዲህ ዓይነት ጥቅምና ሥልጣን አሳዳጅ የበታች አመራሮችና ፖለቲከኞች አካሄድ የአካባቢው ማኅበረሰቦች፣ በህዝበ ወሣኔ ባፀደቁት ወሰን ውስጥ ረግተው እንዳይኖሩ የሚያደርጉ ግጭቶች ሲቀሰቀሱ ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው የወሰን ይገባኛል አጀንዳ ይዞ የተነሳው በሁለቱም ወገን ለንጹኃን ዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ችግር የተቀሰቀሰው በዚህ አኳኋን ነው። ግጭቱ በሁለቱ ብሄሮች ማኅበረሰቦች መካከል የተፈጠረ ሳይሆን፣ በተለይ ጥቅም አሳዳጅ የአካባቢዎቹ የበታች አመራሮችና ያስታጠቋቸው ሚሊሻዎች የፈጠሩት ነው። ይህ ለንጹኃን ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ችግር የተፈጠረው ከዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ወሰን አከላለል ሳይሆን፣ እንደዘመነ መሣፍንት ግዛት የማስፋፋትና የግል ፍላጎታቸውን የማስጠበቅ ዝንባሌ ባላቸው አመራሮች ነው። ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ህዝቡ ላይ ተለጥፈው በዘመነ መሣፍንት እሳቤ የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ዓላማ ግጭት የሚቀሰቅሱ ፖለቲከኞችንና ተከታዮቻቸውን የህግ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል። የአካባቢውን ሠላም ለማስከበር የሚያስችለው ርምጃ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻፀም ሪፖርት ሲያቀርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ አዋሣኝ አአካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ከላይ ከተወሳው የችግሩ መንስዔና መፍትሄ ጋር ይጣጣማል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየ አብሮነት እንጂ ጠላትነት የለም፣ ለግል ፍላጎታቸው መጠቀሚያ በአዋሣኝ ቀበሌዎች ዙሪያ ችግር ሲፈጥሩ የቆዩት የአካባቢው የበታች አመራሮችና ሚሊሻዎች ናቸው። ግጭት የተፈጠረው በሁለቱ ክልሎች የሚሊሻ ኃይሎችና ልዩ ኃይሎች መካከል ነው። በእነዚህ አካላት በሚፈጠሩ ግጭቶች አርብቶ አደሮች እና አርሶ አደሮች ተገድለዋል ብለዋል። መንግሥት እነዚህን ወገኖች ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
አወዛጋቢ የሆኑ 26 ቀበሌዎች ጉዳይ በህዝብ ውሣኔው ውጤት መሠረት መፍታት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ችግሩን ለመፍታት በቅድሚያ ደም ያፋሰሱ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ለማድረግ ህጋዊ ርምጃ መወሰድ አለበት። ይህን ተፈጻሚ ለማድረግም ሙሉ ማስረጃዎች ተሰብስቧል። የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በደረሱት ስምምነት መሠረትም የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳዩን የሚያስፈፅም ይሆናል ብለዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበርና በእኩልነት ላይ በተመሠረተ የህዝብ አንድነት የሚኖሩበት ፌዴራላዊ ሥርዓት መዳረሻ በክልሎች መካከል የጋራ እሴቶችን በመፍጠር በጋራ መልማትና አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መመሥረት ነው። ይህ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ በመነሻውም በመድረሻውም የመሪዎችና የጦር አበጋዞችን ጥቅም ማስጠበቅ ላይ በመመሥረት በተለያዩ ገዢዎች ከተከፋፈለ የዘመነ መሣፍንት ሥርዓት ይለያል። አሁን ወሰንን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች የህዝቡን ፍላጎት የሚወክሉ ሳይሆኑ፣ ልክ እንደዘመነ መሣፍንት ወሰን ማስፋትና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ በሚፈልጉ የአካባቢ አመራሮችና ጀሌዎቻቸው የሚፈጠሩ መሆናቸው መታወቅ አለበት።