ወጣቶች ተጠቅመው እንዲጠቅሙ ምን መሆን አለበት?

በሀገራችን ሰፊ የሆነውን ወጣት በተለያየ ደረጃ ያስራ ባለቤት ለማድረግ በመንግስት በኩል የተጀመረው እንቅስቀሴ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ክልሎች የየራሳቸውን የወጣቶች ፈንድ ድርሻ ወስደው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን በአንዳንዶቹ አካባቢዎችም ፈጣን ስራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ሰፊ የሆነውን የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ በተመለከተ በሕዝብ፣ በመንግሥትና በወጣቱ መጠነ ሰፊ ሥራዎች  በመሰራት ላይ ናቸው።

 

በሁሉም የሀገራችን ክልሎች የተለየ ትኩረት የተሰጠው ወጣቱን የስራ ባለቤት ማድረግ ሲሆን፣ በመንግስት የተመደበውን ፈንድ ወደስራ የማስገባቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በበጀት ምደባውም ሆነ በቅንጅታዊ አሰራሩ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁሉ የላቀ በማድረግ ውጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል፡፡ ወጣቶቻችንም ከዚህ ቀደም በሕብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ ለዘመናት የኖረውን የስራ ባህል በመለወጥ መብቃትና ውጤታማ መሆን መቻል አለባቸው፡፡

 

ስራ ክቡር ነው፡፡ ማንኛውም አይነት ስራ አይናቅም፡፡ ሰውን ከሌሎች ፍጡራን ሁሉ የተለየ ያደረገው ስራን መፍጠርና መስራት መቻሉ ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ሰውን ሰው ያደረገው ስራ ነው፡፡ አለምንም የለወጣት፤ ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ ያስቻላት ስራና ስራ ብቻ ነው፡፡ በላብህ ጥረህ ግረህ ሰርተህ ብላ እንዲል ቅዱስ መጽሀፉ፡፡

 

አለምን የለወጣት፣ የመጠቀ የሳይንስና የቴክኒዮሎጂ ደረጃ ላይ ያደረሳት የወጣቶች ምርምርና የፈጠራ ስራ ነው፡፡ ስራን መፍጠር፣ ስራን መስራት፣ ለስራ ልባዊ ፍቅርና ተነሳሽነት መኖር፣ መዳበርና ማደግ ነው በየደረጃው ሀገራትንና ሕዝቦችን የለወጠው፡፡ የእኛም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ወጣቶቻችን ብሩህ ተስፋ ሰንቃ በማደግ ላይ የምትገኘውን ሀገራቸውን ወደላቀ ደረጃ ሊያደርሱዋት የሚችሉት ማንኛውንም አይነት ስራ አክብረው መስራት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

 

ወጣቱ ትውልድ ስራን አክባሪኝ ስራን ፈጣሪኝ በፈጠረውም ሆነ በሚፈጥረው አዳዲስ ስራ ሀገሩን ወገኑን ትውልዱን ተጠቃሚ ለማድረግ መብቃትና መቻል አለበት፡፡ ሀገራችን በሁሉም መስክ ብዙ ያልተነኩ፣ ጭራሹንም ያልተሞከሩ ሰፊ የስራ መስኮች ያሉዋት ሀገር ነች፡፡ የግድ ስራ ማለት ቢሮ ተቀምጦ መስራት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ከቢሮ ውጭ ሀገርንና ሕብረተሰብን የሚያሳድጉ የሚለውጡ እልፍ የመስክ ስራዎች አሉ፡፡

 

በቴክኒኩ፣ በግብርናው፣ በኮንስትራክሽኑ፣ በትራንስፖርቱ፣ በፓርኮች፣ በእርሻው፣ በግብርና ውጤቶች አሰባሰብና ማከፋፈል፣ የራስን ጋራዥ ሱቆች ማከፋፈያዎች በመክፈት፣ በወተት፣ በማር ምርት ስርጭት፣ በደን ልማት፣ በዱር እንሰሳት ጥበቃና እንክብካቤ ከመንግስት ጋር በመሆን ፓርኮችን በመፍጠር፣ የሆቴልና የቤት አገልግሎት፣ የብረትና የእንጨት ስራዎች በነበሩትና አዳዲስም በሚፈጠሩት ፋብሪካዎች ውስጥ በመስራት የስራ ልምድ ማግኘት ይቻላል። በኋላም አቅም ሲኖር የራስን ለመክፈት ልምዱና እውቀቱ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን ሁሉ ወጣቱ ጠንቅቆ ሊያውቀው ሊረዳውም ይገባል፡፡

 

ዛሬ የአለማችን ግዙፍ ፋብሪካዎች፣ ስመጥር የሆኑ አለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች፣ ትላልቅ የሚባሉ ኮርፖሬሽኖች ስራዎች ሁሉ የተጀመሩት ከትንሽ፣ ምናልባትም በጣም ከትንሽ ደረጃ ነው፡፡  በሂደት ነው እያደጉ እየጎለበቱ በመሄድ ትልቅ የስራ መስክ ለመሆን የበቁት፡፡ ይሄ ለእኛ ወጣቶች ትልቅ የስራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ብቻ ሳየሆን ሰፊ ልምድ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ ስራን ሳይንቁ መስራት ያስከብራል፤ ያሳድጋል፤ ለበለጠ ትልቅ ደረጃም ያደርሳል። ወጣቶቻችንም ይሄንን እውነት ተረድተው የበለጠ ለስራ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

በተለያጉ ጊዜያት ተደጋግሞ እንደተገለፀው፣ መንግስት ለወጣቱ የመደበው 10 ቢሊዮን ብር ፈንድ የሀገር ሐብትና ገንዘብ፤ ተመልሶም ለሌላ ስራ የሚውል ነው፡፡ ወጣቱ ሰርቶ አግኝቶ ራሱን ቤተሰቡን የሚለውጥበት መልሶም የስራ ፈጣሪ በመሆን ሌሎች ዜጎች ሰርተው የሚኖሩበትን የስራእድል የሚፈጥርበት የተበደረውንም የመንግስት ገንዘብ በስርአቱ የሚመልስበት ሁኔታ ነው ከፊት ያለው፡፡

 

ቀደም ሲል በነበሩት አመታት ወጣቶች ራሳቸውን እንዲረዱ በብድር ከቁጠባ ማሕበራት (ከመንግስት) የወሰዱትን ገንዘብ አንዳንድ ወጣቶች አልባሌ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ያጠፉበት፣ ከተያዘለት አላማ ውጪ እንዲውል በማድረግ ራሳቸውን ሳይጠቅሙ ለሕብረተሰቡም የሚጠቅም ስራ ሳይሰሩበት ባክኖ የቀረ መሆኑ ይታወቃል፡፡

እንዲህ አይነቱ ብልሹ አካሄድ እንዳይደገም ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን እድል በአግባቡ አለመጠቀም፣ በስራላይ አለማዋል፣ ሰርቶ የመለወጥና የማደግን እድል ያጨናግፋል፤ ቀጣይ ተስፋዎችንም ያጨልማል፡፡ የዛኑም ያህል በአገኙት ብድር ተጠቅመው ስራን በመስራት ያደጉ፣ የተለወጡ፣ ስራ የፈጠሩ፣ በአቅማቸው ሰዎችን ቀጥረው ለማሰራት የበቁ፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ውጤታማ በመሆን ከፍ ወዳለ አደረጃጀት የተሸጋገሩ፣ ተምሳሌት መሆን የቻሉ ወጣቶች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ይሄንን ተሞክሮና ልምድ ሌላው ወጣት ሁሉ ሊጋራው ይገባል፡፡ በሀገራችን ከአዲስ አበባ ጀምሮ በሌሎች ክልሎችም ሰፊና ያልተነኩ የስራ መስኮች አሉ፡፡ የወጣቱ የስራ ፈጣሪነት ከታከለበት አዳዲስ የስራ መስኮችን መፍጠር ከቻለ በከፍተኛ ደረጃ መለወጥ ይችላል፡፡ መነሻው ግን ስራን ፈጣሪና አክባሪ መሆን መቻል ነው፡፡

 

በአንዳንዶች የሀገራችን ዞኖች ከፌዴራል የተመደበውን በጀት ሳይጠብቁ በራሳቸው ተነሳሽነት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ  አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ወጣቱን የስራ ባለቤት ለማድረግ እየተጉ የሚገኙ አሉ፡፡ እነዚህ ሊደነቁ ሊበረታቱም የሚገባቸው ናቸው፡፡ ስራቸውና ትጋታቸውም ለጉዳዩ ያላቸውን ከፍተኛ የባለቤትነት መንፈስም ያሳያል፡፡

በጠባቂነት መንፈስ ተቀምጠው የራሳቸውን እንቅስቀሴ ሳያደርጉ ፈጥነው ወደስራ መግባትና መነሳሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

ወጣቶች ኋላቀር ከሆነው ስራን ያለማክበርና የመናቅ እጅግ ጎጂና ደካማ አመለካከት በመውጣት አዲስ አስተሳሰብና የስራ መንፈስ ይዘው መነሳት አለባቸው፡፡  ማግኘትና ሕይወትን መለወጥ የሚቻለው ስራን አክብሮ በመስራት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ሳይሰሩ የመክበር የመበልጸግ ተቀምጦ ከሰማይ መና የመጠበቅ የጠባቂነትና የተረጂነት አስተሳሰብ እጅግ ጸያፍ መሆኑን በቤተሰብም ሆነ በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚያስከብረው የወጣቱንም ሕይወት የሚለውጠው ስራና ስራ ብቻ መሆኑን አውቆ በአዲስ መንፈስ ለስራ ተግቶ መነሳት ይጠበቃል፡፡

 

መንግሥት ቀደም ባሉት አመታትም እንደአሁኑ ግዙፍ ባይሆንም ወጣቱ የስራ እድል እንዲያገኝ በብድርና ቁጠባ ማሕበራት አማካኝነት ተጠቃሚ እንዲሆን ተደራጅቶ የራሴ የሚለውን ስራ እንዲሰራ በብዙ መስኮች ሰፊ ጥረት ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ወጣቱ ከጠባቂነት መንፈስ ተላቅቆ በሥራ ፈጣሪነት ላይ ማተኮር እንዳለበት በተደገጋጋሚ ሲገለጽም ነበር፡፡

 

ይህን ካልን ዘንዳ ለመሆኑ ከወጣቶች ተጠቃሚነት አንፃር በክልሎች ምን እየተሰራ ነው? የሚለውን እናንሳና አንዳንድ ሀሳቦችን እንለዋወጥ፤ ለዚህም የአዲስ አበባን ተሞክሮ እንቃኝ።

 

በአዲስ  አበባ  ከተማ  ስራ አጥ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን ከሰሞኑ አስታውቆአል፡፡ በአዲስ አበባ  ከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች መንግሥት በመደበው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቅመው በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሠማራት  ተጠቃሚነታቸውን  እንዲያሳድጉ ፌደሬሽኑ እየሠራ መሆኑን የፌደሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት አበባው ተስፋ ለዋልታ አስታውቆአል፡፡

 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ የተለያዩ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ መስኮች እንዲገቡ ለማድረግ እስካሁን ድረስ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ 400 ሚሊዮን ብር በጀት  መያዙን፤ ለአስተዳዳራዊ ጉዳዮች ለሚውል ወጪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  8 ሚሊዮን ብር መመደቡን ሀላፊው የገለፀ ሲሆን፤ ለወጣቶች የተመደበው ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንዴትና  በምን መልኩ ስራና ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ግንዛቤ ለመሥጠት ፌደሬሽኑ ሁለት  መድረኮችን  ማዘጋጀቱን፤  ወጣቶች ሥራን ሳይንቁ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ የቅስቀሳ ሥራም በመሰራት ላይ መሆኑንም ወጣት አበባው ተስፋ ተናግሮአል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ  በመጀመሪያ ዙር 19ሺ የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችን ቤት ለቤት  በመቀስቀስ፣ በመመልመል፣ በመለየትና በመመዝገብ  ወደ ሥልጠና እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በመጀመሪያ ዙር የተመዘገቡት 19ሺ ወጣቶች ለሁለት ወር የሚቆይ ሥልጠና  በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲከታተሉ ተደርጎ በአሁኑ ወቅት በ16 ተቋማት የተግባር ተኮር ሥልጠና በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ታውቆአል፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ  በዘንድሮ የበጀት ዓመት 156ሺ የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች  በተለያዩ  መርኃ ግብሮች ታቅፈው የሥራ  ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ  ከአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮማንድ ፖስት እና ከከተማዋ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምክር ቤት ጋር በመቀናጀት በተለያዩ  ዘርፎች ለሚሠማሩ ወጣቶች ምን ያህል የብድር ገንዘብ እንደሚቀርብ የሚወስን የአሠራር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ወጣት አበባው ገልፇል፡፡ በአዲስ ከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታና አጋጣሚ ተጠቅመው  በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ራሳቸውን ከመጥቀም አልፈው  ለአገር እድገት እንዲተጉ ወጣቱ ጥሪውን አስተላልፎአል፡፡