በሂደት ላይ የሚገኘውና ከሞላ ጎደል እንደተጠናቀቀ የሚነገርለት ጥልቅ ተሃድሶ እንደ ድርጅትና እና መንግስት ያጋጠሙትን ድክመቶች በማስወገድ አገራዊ/ክልላዊ ለውጥ ማምጣትን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ፣ ግለሰቦችን ከመቀያየር ጋር አያይዘው ተሃድሶውን የሚያሄሱ ወገኖች ተሃድሶው አቅጣጫውን እንደሳተ ይከራከራሉ። ለመከራከሪያቸው የሚጠቅሱት የመጀመሪያው አስረጅ ባለፉት ዓመታት በፌዴራልም ሆነ ክልሎች በከፍተኛ አመራር ኃላፊነት ደረጃ የነበሩ ሰዎች በመልሶ መደራጀቱ በስልጣናቸው ላይ መቀጠል አልነበረባቸውም የሚል ነው። ይህ አመለካከት በኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች እስካልተቀየሩ ድረስ ምንም አይነት ለውጥ አይመጣም የሚልና ተሃድሶው ለውጡን ከግለሰቦች ጋር አስተሳስሮ የሚመለከት በመሆኑ የተሳሳተ ነው።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሌላም አመክንዮ/መሟገቻ መጥቀስ ይቻላል። ድርጅቱ ከስህተቱ እንደሚታረመው፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና አባላትም ሂስ/ግለሂስ አድርገው፤ ታርመው እንደሚቀጥሉት ሁሉ በከፍተኛ አመራርና ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች በሰሩት ስህተት ላይ ሂስ/ግለሂስ አካሂደውና ታርመው በአመራር ኃላፊነታቸው የማይቀጥሉበት ምክንያት አይኖርም። ይህንን የሚከለክል የፖለቲካ ድርጅት መርህም የለም። በመሆኑም በከፍተኛ የአመራር ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች የሚቀየሩት የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ሲፈቅድና በደንብ መሰረት ከኃላፊነት እንዲነሱ የሚያደርግ ሁኔታ ሲኖር ነው። ይህ ደግሞ ተቀባይነት ባገኘ የግል የመልቀቂያ ጥያቄና ለቦታው የተሻለ እጩ ሲገኝ፤ እንዲሁም በኃላፊነት የማያስቀጥል ጥፋት መፈፀሙ በውል ሲረጋገጥ የሚሉትን ያካትታል። ከዚህ ውጭ ግን፣ እንደ ድርጅት የነበረውን ስህተትና ጉድለት ስለሚጋራ ወይም የተሟላ ግለሂስ ስላልወሰደ ወይም ደግሞ ብዙ ሂስ ስለቀረበበትና በአግባቡ ስላልተቀበለ . . . በመሳሰሉ መመዘኛዎች በየትኛውም አካል ላይ ያለን አመራር ከኃላፊነት ማውረድ ገንቢ አይደለም።
መሰረታዊ የሆኑትን የአመራር ብቃት መለኪያዎች የሚያሟላና በድርጅቱ መተዳደሪያና በመንግስት መመሪያ ከኃላፊነት የሚያስነሱ ተብለው የተቀመጡት ነጥቦች የማይመለከቱት እስከሆነ ድረስ ድክመቶቹን በሂደት እንዲያሻሽል ጊዜ መስጠትና በኃላፊነቱ እንዲቀጥል ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል። ስለሆነም በፌዴራልና በክልል በተካሄደው መልሶ ማደራጀት የተከናወነው ሹመት በዚህ አግባብ ተገምግሞ ነው ተሃደሶው መስመሩንና አቅጣጫውን ስለመሳቱ እርግጠኛ ሆኖ መከራከር የሚቻለው።
ከሰሞኑ ለንባብ የበቃችውና ዋነኛ ትኩረቷን በዚሁ ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ላይ ያደረገችው የገዥው ፓርቲ መጽሄት (አዲስ ራእይ) ይህንኑ ሃሳብ በተለያዩ አመክንዮዎች ታጠናክራለች።
በነበራቸው ኃላፊነት እንዲቀጥሉ የተደረጉት በሙሉ ባለፉት የአመራር ዘመናቸው እንደ ድርጅት በተገመገሙባቸው ድክመቶች ላይ የየራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። ሁሉም ግን ተመሳሳይና እኩል ስህተት ፈፅመዋል ማለት የሚቻል አይሆንም። እንደየስህተታቸው መጠንም የወሰዱት ሂስ/ግለሂስ የተለያየ እንደሚሆን ይታመናል። በነበራቸው ኃላፊነት እንዲቀጥሉ የተደረጉት ግን ድርጅቱን መንታ መንገድ ላይ እንዲደርስ ያበቃው የአመራር ችግር አካል እንደነበሩት ሁሉ ድርጅቱ በጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄ የመፍትሄው አካል ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ብቃት ስላላቸው እንደሆነ መግባባት ያስፈልጋል።
የሚለው መሰረታዊ ተጠየቅ አንደኛው የመፅሄቷ ማጠናከሪያዋ ነው።
በመልሶ ማደራጀቱ በተደረገው ሹመት ላይ የሚነሳውና ተሃድሶው አቅጣጫውን ስቷል ለሚለው መሟገቻ የሚቀርበው ሁለተኛው የተዛባ አመለካከት ደግሞ ተጠያቂነትን የሚመለከተው ይሆናል። በእርግጥ በጥልቀት ወደመታደስ ንቅናቄ ድርጅቱ እንዲገባ ያስቻለው ግምገማ ላይ በግልጽ እንደቀረበው ላጋጠመው ችግር ተጠያቂው አመራሩ፣ በዋነኛነትም ከፍተኛ አመራሩ ነው። ነገር ግን የአመራሩ ተጠያቂነት ሲባል እንደአካልና በግለሰብ ደረጃ ያለው ተለይቶ መታየት ይኖርበታል። የጋራና የግል ኃላፊነትና ተጠያቂነትን በሚመለከት ድርጅቱ በሰሞንኛዋ ልሳኑ በግልፅ እንዳስቀመጠው፤ ይህ የሚታወቅ ቢሆንም ተጠያቂነትን በሚመለከት ሁለት የተሳሳቱ አመለካከቶች ይነሳሉ። ሲል ያቀረበው የመከራከሪያ ነጥብ ግና ከጅምሩ ስህተት እንዳለበት ያጠይቃል።
የመጀመሪያው ማጠየቂያ “የጋራ ኃላፊነት በሆነ ተግባርና ስልጣን ላይ ግለሰብ ተነጥሎ መጠየቅ አለበት” የሚለው ነው። በድርጅቱ መርህ መሰረት ለአንድ “አካል” የተሰጠ ስልጣንና ተግባር የጋራ ኃላፊነት ሲሆን የአካሉን ኃላፊነት ለአንድ ግለሰብ አሳልፎ መስጠት አይቻልም። አንድን ተግባር እንዲፈፅም ተልዕኮ የተሰጠው የአካሉ አባል ስህተት ፈፅሞ ቢገኝ እንኳ የአካሉ ኃላፊነት ስለሆነ አካሉ ተጠያቂ ነው። ከአካሉ የኃላፊነት ክልል ውጭ በመሄድ በግሉ፤ ወይም ደግሞ በግል በተሰጠው ኃላፊነት ክልል የተፈፀመ ስህተት ሲኖር ግን ግለሰቡ ተጠያቂ ይሆናል። ከዚህ የድርጅቱ መርህ ያፈነገጠና ከአመራሩ የተወሰነ ግለሰብን ለይቶ ተጠያቂ የሚያደርግ አመለካከት ለተሃድሶው መመዘኛ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም።
ተጠያቂነትን የሚመለከተው ሌላው የተሳሳተ አመለካከት ደግሞ ከቅጣት ጋር ተያይዞ የሚቀርበው አስተያየት እንደሆነ የገዥው ፓርቲ/ድርጅቱ ልሳን ታብራራለች። የኢህአዴግና የየብሔራዊ ድርጅቶቹ ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ባካሄዱዋቸው ግምገማዎች በነበሩ ድክመቶችና በተፈፀሙ ስህተቶች ላይ እንደአካል ግለሂስ ወስደዋል። ለተፈጠረው ችግርም እንደአካል ተጠያቂ መሆናቸውን ተቀብለዋል። በግል በነበራቸው ኃላፊነትም ግለሂስ የወሰዱና ሂስም የተደረጉ እንዲሁም ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን ተጠያቂነትን ከኃላፊነት በማውረድና መሰል የቅጣት ክልልን ብቻ የሚመለከት የተሳሳተ አስተሳሰብ ይታያል። በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ለደረሰ ጥፋት ቅጣት የሚያሰጡ የተለያዩ የቅጣት አይነቶች ከቀላል ማስጠንቀቂያ እስከ ማባረር አሉ። ስለሆነም ተጠያቂነትን አምኖ መቀበልና ራስን መውቀስ ለመታረምም ዝግጁነትን ማረጋገጥ እንዲሁም በቀጣይ ኃላፊነቱን በትክክል እንዲወጣ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት በተሰራው ስህተት ተጠያቂ የማድረግ እርምጃዎች እንደሆኑ መረዳት ያስፈልጋል።
እዚህ ላይ በጥሞና ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ገና ተሃድሶው እየተጀመረ ባለበት ሁኔታ የታየው የከፍተኛ አመራሩ ከኃላፊነት መነሳት ከተጠያቂነት አኳያ የመጨረሻ ነው ማለት እንዳልሆነ ነው። አሁን በተካሄደው ሂስና/ግለሂስ እንደአካልም ሆነ እንደግለሰብ ብዙ ድክመቶች ተነስተዋል። ይሁንና ያልተወሰዱ ግለሂሶች፤ ከቀረቡ ሂሶችም ተሸፋፍነው ያለፉ፣ ወይም ደግሞ በቀጣይ የሚቀርቡ አይኖሩም ተብሎ አልተደመደመም። ንቅናቄው ወደ አባላት፣ ወደ ፐብሊክ ሰርቪሱ እንዲሁም ወደ ህዝቡ በገባ መጠን አዳዲስ ጉዳዮች ሊነሱና የተለየ ርምጃ ሊወሰድ የሚችልበት ሁኔታ ዝግ አይደለም። በበላይ አካላት የተካሄደው ሂስ/ግለሂስ ወደ ታች በወረደ መጠን ከወዲሁ የታየውም ይህንን ያመለክታል።
አሁን ገና ሁሉም ወደ ንቅናቄው ሰፊ ሜዳ እየወረደ ነው። በንቅናቄው ፈጥኖ የሚሮጠውና የሚያዘግመው፤ ወይም ደግሞ የማይነቃነቀው በግልጽ ተለይቶ የሚታወቀው ወደፊት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ያኔ የሮጠው አዝጋሚውንም፤ የቆመውንም እያለፈ መድረስ የሚገባው ቦታ ላይ ይደርሳል። የሚያዘግመው ደግሞ ማዝገም እስከሚፈቀድበት ደረጃ ድረስ እንዲያዘግም፤ የማይነቃነቀው ደግሞ ቦታውን በትህትና እንዲለቅ ይደረጋል።
ከሹመቱ ጋር በተያያዘ ተሃድሶው አቅጣጫ ስቷል በሚል በሶስተኛ ደረጃ ለሚነሳው የተሳሳተ አስተሳሰብ በአስረጂነት የሚቀርበውን የምሁራንነ ወደ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት መምጣትን በተመለከተም መፅሄቷ (አዲስ ራእይ) ከድርጅቱ መርህ ጋር ተያያዥ የሆኑ መከራከሪያዎችን ታቀርባለች። በዚህ ረገድ የሚቀርቡ መከራከሪያዎች በድርጅቱ የአመራር ደረጃ ምደባ ከፍተኛ አመራር ያልሆኑ አባላት በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ላየ መመደብ የለባቸውም፣ የድርጅት አባላት ያልሆኑ የመንግስት ኃላፊነቱን በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ አይመሩትም፤ ችግራችን የምሁራን በመንግስት ኃላፊነት ላይ ያለመመደብ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው። ምሁራንን ወደ አመራር ማምጣት መፍትሄ አይሆንም . . . የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህ ሃሳቦች በአብዛኛው በድርጅት አባላት የሚነሱ ሲሆን በተወሰነ ደረጃም በፐብሊክ ሰርቪሱና በህዝቡም የሚነሱበት ሁኔታ አለ። የነዚህ አስተሳሰቦች ዋነኛ መነሻም እየተለመደ የመጣው የመንግስት ሹመት አሰጣጥ እንደሆነ ግልፅ ነው። ይሁንና ከተሃድሶው ተልእኮዎች አንዱ ደግሞ በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ያሉ ድክመቶችን ማስተካከል፣ አዳዲስ አስተሳሰቦችንና ተግባራዊነታቸውንም ማስተዋወቅ ስለሆነ ይህ ያልተለመደ የሚመስል አሰራር ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።
በመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ መመደብ/መሾም ያለባቸው የድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው የሚለው አስተሳሰብ በጥልቀት የመታደሱን ንቅናቄ የግድ ካሉት መሰረታዊ ጉድለቶች መካከል ቁልፉ የሆነው በመንግስት ስልጣን ላይ ከተፈጠረው የተዛባ አተያያ የሚመነጭ ነው። ቁልፉ ችግር ድርጅቱ የስልጣን ምንጭ መሆኑ ነው። በድርጅቱ ወደ ከፍተኛ አመራር በተመጣ መጠን ወደ መንግስት ከፍተኛ ስልጣን መሸጋገር እየተለመደ ትክክለኛ መርህም ተደርጎ እየተወሰደ የመጣበት ሁኔታ የጥፋቱ ሁሉ መንስኤ ሆኗል። ይህ አካሄድ ግን በአስከተለው ጉዳት ብቻ ሳይሆን ከትክክለኛ የድርጅትና የመንግስት ኃላፊነት አመዳደብ መርህ አኳያ ሲታይም ቀልጥፎ መታረም ያለበት ስህተት ነው። ድርጅትና መንግስት ሁለት የተለያዩ ፍጡሮች ናቸው። በየራሳቸው መተዳደሪያ ደንብና ህግ የሚመሩ፣ የየራሳቸውም ተልዕኮ ያላቸው ሁለት አካላት መሆናቸው ይታወቃል። በምርጫ አሸንፎ የመንግስት ስልጣን የሚይዝ ድርጅት የሁለቱን ልዩነት በሚገባ ጠብቆ መምራት ካልቻለ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ እስከመፍጠር የሚዘልቅ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ድርጅቱ ለመንግስት ፖለቲካዊ አመራር ይሰጣል፣ መንግስት ደግሞ ከፓርቲው ፖለቲካዊ አመራር የሚመነጩ ፖሊሲዎችን መሰረት በማድረግ ይንቀሳቀሳል።
በልዩ ትኩረትም ሆነ በሙያዊና የአመራር ብቃታቸው የሚሾሙ የፓርቲ አባላት በሚኖሩበት ሁኔታ ግን የግድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑ ብቻ የሚባል ባይሆንም በፓርቲው ከፍተኛ አመራር ኃላፊነት ላይ የደረሱ ሰዎች የተሻለ ብቃት ያላቸው እንደሚሆኑ ስለሚጠበቅ ባብዛኛው ቀዳሚና ተመራጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
ትክክለኛው መርህ ይህ ሆኖ ሳለ የመንግስት የኃላፊነት ቦታ ሁሉ በድርጅት አባላት ያውም ከፍተኛ አመራር በሆኑት ብቻ መያዝ አለበት የሚለው ዝቅ ያለ አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው። የመንግስት ኃላፊነት የድርጅት አባላትና ከፍተኛ አመራር ባልሆኑ ከተሞላ በመንግስት መዋቅሩ ፖለቲካዊ አመራር ለመስጠትና የድርጅቱን ፖሊሲ ለማስፈፀም ያስቸግራል የሚል ምክንያትም አይሰራም። ድርጅት በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት ውስጥ ፖለቲካዊ አመራር የሚያረጋግጠው መዋቅራዊ አቅም ስለያዘ አይደለም። ፖለቲካዊ አመራር የሚረጋገጠው ድርጅቱ ፕሮግራሙንና አቋሞቹን ለማስተዋወቅና ምልአተ ህዝቡ የሚደግፋቸው፤ በሂደትም የኔ ብሎ የሚቀበላቸውና የሚመራባቸው የሚሆኑበትን ሁኔታ ከወዲሁ መፍጠር የሚያስችል ውጤታማ የፖለቲካ ስራ በመስራት ነው። ይህንን የመፈፀም ኃላፊነት ደግሞ የድርጅት መዋቅሩ ይሆናል።
ስለሆነም በተጀመረው የመልሶ ማደራጀት በከፍተኛ ተቋማትና በተለያዩ ቦታዎች ሲያገለግሉ ለነበሩ ምሁራን የተሰጠው ሹመት በዚህ መንፈስ መታየት ይኖርበታል። ምሁራኑ ለሹመት የተመረጡት የተመደቡበትን ተቋም ለመምራት ብቻ ሳይሆን ሙያቸውና የስራ ልምዳቸው ብቁ ስለሚያደርጋቸው ነው። ውጤታማነቱ በተግባር የተረጋገጠ መስመር እያለው በማስፈፀም አቅም ድክመት የተነሳ ህዝቡ የሰጠውን መንግስትን የመምራት ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደተሳነው ለሚረዳው ኢህአዴግ የማስፈፀም አቅም ክፍተቱን የሚሞሉ ባለሙያዎችን መሾም ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ውሳኔው በርግጥም በጥልቀት የመታደስ ርምጃ መጀመሩን የሚያመለክት፣ ፖለቲካዊ አመራርን በፖሊሲ ጥራትና ፖሊሲው ተቀባይነት እንዲያገኝ በሚሰራ ፖለቲካዊ ስራ ብቃት፣ በድርጅት መዋቅሩ አማካይነት በሚሰራ የፖለቲካ ስራ እንጂ በየተቋሙ በሚመደቡ ካድሬዎች ዘበኝነት ማረጋገጥ እንደማይቻል፤ መንግስትና ድርጅት የተለያዩ መሆናቸውን፣ የድርጅት አባልነት የስልጣን ምንጭ መሆን እንደማይገባው የተገነዘበ ርምጃ ነው።