ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን ሐዘን ላይ ሰንብተናል። ሐዘን ላይ የጣለን በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በልማድ "ቆሼ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈጠረ ድንገተኛ የቆሻሻ ክምር መናድ 113 የሚደርሱ ወገኖቻችን ህይወት በመጥፋቱ ነው። የኢፌዴሪ መንግሥት በዜጎቻችን ላይ ለደረሰው አደጋ የሦስት ቀናት ብሄራዊ የሐዘን ቀን አውጇል።
አደጋው የደረሰበት አካባቢ ቆሼ የሚለውን ሥያሜ ያገኘው ቆሻሻ ከሚለው ቃል ነው። ሥፍራው ለግማሽ ክፍለ ዘመን የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ ማከማቻ ሆኖ ሲያገለግል ኖሯል። ይህ ሥፍራ አንድ ጋሻ ያህል ወይም 37 ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ነው። ቦታው በዘውዳዊው የመንግሥት ሥርዓት ዘመን ለአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ መጣያነት ሲመረጥ ከዋናው የከተማ ክፍል ብዙ ርቀት ነበረው። እስከ 80ዎቹ መግቢያ ድረስ በዚያ አቅጣጫ የአዲስ አበባ ከተማ በጅማ መንገድ ከዘነበ ወርቅ ሆስፒታል፣ በመካኒሳ አቅጣጫ ደግሞ ከመካኒሳ አረቄ ፋብሪካ አላላፈም ነበር። ቆሼ በእነዚህ ሁለት መንገዶች መሃል ያለ ሥፍራ ነው። ሁለቱን መንገዶች የሚያገናኝ መንገድ ስላልነበረ ቦታው ከእይታ የተሰወረ በመሆኑ ብዙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አያውቁትም ነበር።
ቆሼ ገሃድ የወጣው የቀለበት መንገዱ ሲሰራ ነው። ከቃሊቲ ተነስቶ ወደአየር ጤና በሚዘልቀው የቀለበት መንገድ ላይ አየር ጤና ለመድረስ አንደ ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀረን ቆሼን እናገኘዋለን። የቆሼ ጀርባ ከመካኒሳ ወደ ዘነበ ወርቅ ወይም አለርት ሆስፒታል በሚዘልቀው መንገድ ላይ ይገኛል። ይኼኛው የቆሼ ጠርዝ በዘውዳዊው ሥርዓት ዘመን ጉድ ሼፐርድ በመባል የሚታወቀው የአሜሪካኖች ትምህርት ቤት፣ በደርግ የሥልጣን ዘመን የቁስለኛ ወታደሮች ማገገሚያ የነበረው ቆሬ ማገገሚያ ካምፕ፣ አሁን ደግሞ የመከላከያ ሚኒስቴር የሎጂስቲክስ ኮሌጅ ሆኖ በማገልገል ላይ ከሚገኘው ግቢ ጀርባ ባለው ሥፍራ ይገኛል።
አሁን ለወገኖቻችን ሞት ምክንያት የሆነው የቆሻሻ ክምር መደርመስ ያጋጠመው በዚህኛው የቆሼ ጠርዝ አንድ ጥግ ላይ ነው። የቆሻሻ ክምሩ የተናደበት ሥፍራ ከአጠቃላይ የቆሼ ርዝመት አኳያ ሲታይ ትንሽ ነው። የክምር መደርመሱ ቢበዛ 100 ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ነው። ይሁን እንጂ በዚህ የቆሻሻ ክምር ሥር በህጋዊም ይሁን በህገ ወጥ መንገድ ቦታ ይዘው መኖሪያ ቤት ገንብተው የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች አሉ። በ1982/83 ዓ.ም በማህበር ተደራጅተው በህጋዊ መንገድ ቦታ ተመርተው ቤት ገንብተው ከሚኖሩት በተጨማሪ በላስቲክ ጊዚያዊ መጠለያ ሰርተው የሚኖሩ ሰዎችም አሉ። ይሁን እንጂ ምናልባት አካባቢው የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ባገለገለባቸው ዓመታት ሁሉ በአካባቢው በጊዚያዊ መጠለያ ሰዎች ይኖሩ ነበር። እነዚህ በአካባቢው በጊዚያዊ መጠለያ የሚኖሩ ሰዎች የአብዛኞቹ ኑሮ ከቆሻሻው ላይ የሚገኙ ዋጋ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን በመልቀም ላይ የተመሠረተ ነው።
ሰሞኑን ሐዘን ላይ የጣለን አደጋ የተከሰተበትን ቦታ ይህን ያህል አስተዋውቄ ወደአደጋው ልመለስ። አደጋው የደረሰው ቅዳሜ ከምሸቱ ሁለት ሰዓት ላይ ነው። ይህ ሰዓት በተለይ ህጻናትና ሴቶች በሙሉ ቤት ውስጥ የሚሰባሰቡበት በመሆኑ አብዛኞቹ ተጎጂዎች ሴቶችና ህጻናት እንዲሆኑ አድርጓል። በግምት 20 ሜትር ገደማ ከፍታ ያለው በመቆየት ብዛት ተብላልቶ ወደጥቁር አፈርነት የተቀየረው የቆሻሻ ክምር በሥሩ በነበሩ የመኖሪያ መንደሮች ላይ ተደርምሶ ነው አደጋውን ያደረሰው።
እንግዲህ ይህ በብዙ ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚለካው ብስባሽ አፈር ነው በየቤታቸው የነበሩትን ሰዎች ቀብሮ ለህልፈተ ህይወት የዳረገው። ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ ነበር። አደጋው ሲደርስ ወዲያውኑ የኤሌክትሪክ መስመር በመቆራረጡ የአካባቢው ነዋሪዎችና የአደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ያደረጉትን ህይወት የማትረፍ ሥራ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር። ይህም ሆኖ ግን በአፈር ተውጠው የነበሩ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ማትረፍ ተችሏል። በተለይ በዚያ ጨለማ አካባቢውን በደንብ የሚያውቁት የሰፈሩ ወጣቶች በነብስ ማዳን ሥራ ላይ የሚደነቅ ተግባር ከውነዋል። የሰፈሩ ወጣቶች ለህይወታቸው ሳይሳሱ ነብስ ለማዳን ባይረባረቡ ኖሮ ከተረፉት መካከል አብዛኞቹ በህይወት አይገኙም ነበር። እናም የቆሼ ወጣቶች የህይወት ማዳን ሥራ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ ተግባር ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢፌዴሪ መንግሥትና የክልል መንግሥታት አደጋው ዜጎች ላይ ያደረሰው ጉዳት የአገር ጉዳትና ሐዘን ለመሆኑ እውቅና ሰጥተው ይፋዊ የሐዘን መግለጫ አውጥተዋል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ የሐዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ አደጋው በደረሰበት ቦታ የተገኙት በማግሥቱ ነበር። አደጋው በደረሰበት ሥፍራ ተገኝተው ለሰዓታት ቆይታ በማድረግ በአደጋው የተሰማቸውን ድንጋጤና ሐዘን ከህዝቡ ጋር ተጋርተዋል። ከአደጋው የተረፉና በአካባቢው የሚኖሩ ለተመሳሳይ አደጋ የተጋለጡ ዜጎች ከሥፍራው ተነስተው በጊዚያዊ መጠለያ እንዲጠጉ አድርገዋል። የአስቸኳይ ጊዜ የመሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለሟማላት ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ከመንግሥት በተጨማሪ ህዝቡ ቤተሰቦቻቸው በአደጋው ህይወታቸውን ያጡትን በማፅናናት፣ በጊዚያዊ መጠለያ ያሉትን በመደገፍ ላይ ይገኛል። ህዝቡ አደጋው በደረሰበት ሥፍራ አቅራቢያ በተተከሉ ድንኳኖች ውስጥ ሐዘን የተቀመጡ የተጎጂ ቤተሰቦችን በባህላችን መሠረት ለቅሶ እየደረሰ፣ የእዝን ድጋፍ እያደረገ፣ እንግዳ እያስተናገደ በማስተዛዘን ላይ ይገኛል። የአዲሰ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለቅሶ ደርሰው ለተጎጂ ቤተሰቦች የቀብር ማስፈፀሚያ አስተዳደሩ የሰጣቸውን ገንዘብ አስረክበዋል። በአዲስ አበባ ቀብር ላከናወኑ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው የአሥር ሺህ ብር፣ አስከሬን ወደሌላ አካባቢ ለሸኙ ደግሞ የ15 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጓል።
ከንቲባ ድሪባ ኩማ በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖችንም መጠለያቸው ድረስ ሄደው ጠይቀዋል። በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አስታውቀዋል። በመጠለያ ለሚገኙት ሰዎች መንግሥት ከሚያደድርግላቸው ድጋፍ በተጨማሪ የአካባቢው ማኅበረሰብ በራስ ተነሳሽነት ገንዘብ እያዋጣ፣ ምግብ እያዘጋጀና እያስተናገደ በመንከባከብ ላይ ይገኛል። በአካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ህጻናት ሳይቀሩ ያላቸውን እያዋጡ ለወገኖቻቸው ድጋፍ እያደረጉ ነው።
ተቋማትም ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህን ጽሁፍ እስካዘጋጀሁበት ጊዜ ድረስ ባለኝ መረጃ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አምስት ሚሊዬን ብር፣ ኢትዮ ቴሌኮም አንድ ሚሊዬን ብር፣ የሜድሮከ ኩባንያና ባለቤቱ ሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ 40 ሚሊዬን ብር ድጋፍ አድርገዋል። በተመሳሳይ የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን ለተጎጂ ቤተሰቦች የ324 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል። የተጎጂ ቤተሰብ አራት ህፃናትንም ለማስተማር ቃል ገብተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሁለት መቶ ሺህ ብር፣ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶች በድምሩ ሁለት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ይህ ወገን ለወገኑ የሚያደርገው የመደጋገፍ ተግባር ተጎጂዎችን ያጽናናል፣ ከደረሰባቸው ቁሳዊ ጉዳት እንዲያገግሙ፣ በዘላቂነትም እንዲቋቋሙ ያግዛል። ይህ የወገን ለወገን ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረዋል። ይህ ድጋፍ ከመንግሥት ድጋፍ ጋር ተዳምሮ የጉዳቱ ተጽዕኖ በዚሁ እንዲቆምና ቀሪዎቹ ቤተሰቦችና ለተመሳሳይ አደጋ የተጋለጡ ዜጎች ለዘለቄታው ከሥጋቱ ተላቀው እንዲቋቋሙ ያደርጋል። ይህ ሊወደስ የሚገባው በኢትዮጵያዊያን የተከናወነ ትልቅ የወገናዊነት ተግባር ነው። የኢትዮጵያዊያንን ማንነት ያሳየም ነው።
ይሁን እንጂ ማንኛውም ለኢትዮጵያ ህዝብ የመጣ በጎ ነገር እንዲሁም በኢትዮጵያዊያን ላይ የመጣ አደጋ ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም ተዘጋጅተው የሚጠባበቁ ቡድኖች በኢትዮጵያዊያን ላይ ከደረሰው አደጋ የርዕዮተ ዓለማዊ የበላይነት ትርፍ ለማግኘት የሞከሩበትን ሁኔታ ታዝበናል። ይህን ለማድረግ ከሞከሩት መካከል አንዱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ካባ የደረበው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘ ተቋም ነው። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የሚከናወን ማንኛውንም የልማት ተግባር፣ መንግሥት የህዝቡን ሠላም ለማረጋገጥ የሚወስደውን ማንኛውንም ህግ የማስከበር ርምጃ በሰብዓዊ መብት ጥሰትነት እየፈረጀ በመግለጫ የማውገዝ ልክፍት የተጠናወተው ተቋም ነው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኦሞ ሸለቆ አካባቢ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ያለምንም ሐፍረት፣ አንዴ የአካባቢው ነዋሪ በሆኑ ነባር ህዝቦች ላይ እንደተፈፀመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማስመሰል፣ ይህ ሰሚ ሲያጣ ደግሞ በኦሞ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ ኬንያውያን ላይ እንደተፈፀመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያቀረበ መንግሥትን ሲያብጠለጥል መቆየቱ ይታወቃል። አሁንም ከዚህ ድርጊቱ አልተቆጠበም። በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚፈፀም የሽብር ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያልሆነ ይመስል የኢፌዴሪ መንግሥት በተጨባጭ ማስረጃ አሸባሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ክስ ሲመሰርት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፀመ ብሎ ለመጮህ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቀዳሚ ነው። አምነስቲ ኢንተርናሽናልና መሰሎቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጡትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የውንጀላ ሪፖርቶች የተከታተለ ሰው፣ የሰብዓዊ መብት ትርጉም ምንነት ሊምታታበት እንደሚችል እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።
እንግዲህ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነኝ ባይ ተቋም፣ ሰሞኑን ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ ያሳዘነውን በቆሼ አካባቢ በቆሻሻ አፈር ክምር ናዳ የወገኖቻችን ህይወት መጥፋት ለርዕዮተ ዓለማዊ ትርፉ ሊጠቀምበት ሞክሯል። የተቋሙ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠሪ ሙቶኒ ዋኜኪ የቆሼውን አደጋ መነሻ በማድረግ መንግሥትን ለመወንጀል የቀደማቸው የለም። ገና የአደጋው መንስዔና መጠን ሳይታወቅ ነበር መግለጫ ለመስጠት የሮጡት። እኚህ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተጠሪ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ “ከ60 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው በአዲሰ አበባ የደረቅ ቆሻሻ ማከማቻ ቦታ የደረሰው አደጋ የመንግሥት ቸልተኝነት ወጤት ነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት መከላከል ይቻል ለነበረው አደጋ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ነው።” ብለዋል።
በቅድሚያ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሚሊዬን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከድህነት አውጥተው የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ የሚያደርጉ በመንግሥት የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ያለሐፍረት በማይጨበጥ ምክንያት ሲቃወም የቆየ በመሆኑ መንግሥት ለዜጎቹ የተሻለ ህይወት ስለሚያከናውነው ሥራና ስላለበት ኃላፊነት የማውራት የሞራል መብት አለው ብዬ አላምንም። ወደ እውነታው እንመለስ። ሰሞኑን በቆሼ የቆሻሻ አፈር መደርመስ አደጋ የደረሰባቸውን አብዛኞቹን ሰዎች በዚያ ሥፍራ ከደረጃ በታች በሆኑ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ድህነት ነው። በቆሼ አካባቢ አደጋ ደርሶ ለጉዳት ስለተጋለጡ ለሰሞነኛ ቀልባችን ቅርብ ሆኑ እንጂ፣ ከቆሼ ነዋሪዎች ባልተናነሰ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በመላው ኢትዮጵያ አሉ።
መንግሥት የእነዚህን በድህነት ውስጥ ወይም ከድህነት በታች የሚኖሩ ዜጎቸ ህይወት ለማሻሻል ጉዳይ የሰጠው ትኩረት የሚለካው በአጋጣሚ ከድህነት ጋር በተያያዘ ጎልቶ የወጣ ጉዳት በአንድ አካባቢ ሲደርስ ይህን ጉዳት ነጥሎ በማየትና በማጉላት አይደለም። የመንግሥት ተግባር መመዘን ያለበት፣ በአጠቃላይ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያለውን ለዘመናት የተከማቸ ሥር የሰደደ ድህነት ለማቃለልና ለማስወገድ በሚከተለው ስትራቴጂ፣ ስትራቴጂውን በሚያስፈፅምባቸው ፖሊሲዎችና በአፈጻፀም በተገኘ ስኬት ነው።
ኢትዮጵያ ለክፍለ ዘመናት ከድህነት ጋር የኖረች አገር ነች። አሁን በአገሪቱ ያለው ድህነት (እንደ ቆሼ ነዋሪዎች ዓይነት ድህነት) ከሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ የተፈጠረ ሳይሆን በክፍለ ዘመናት ጉዞ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ተከማችቶ እዚህ የደረሰ ነው። በመሆኑም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በአገሪቱ ባለው ድህነት ተጠያቂ አይሆንም። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ተጠያቂ የሚሆነው ይህን ለክፍለ ዘመናት የተቆለለ ድህነት በማቃለል ረገድ ባከናወነው ተግባርና ባስገኘው ውጤት ነው።
አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የኢፌዴሪን መንግሥት ከዚህ አኳያ ስንመዝነው “ድህነት የጠላቶቻችን ሁሉ ጠላት በመሆኑ ሊወገድ ይገባል” የሚል አቋም በመያዝ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊያን ሰው ሊኖር ከሚገባው በታች እንዲኖሩ ያደረጋቸው በተለይ ድርቅን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ በችጋር እንደቅጠል እንዲረግፉ ሲያደርጋቸው የኖረው፣ እንደ አገር ተመጽዋች ያደረጋቸው፣ ዜጎች የተሻለ ህይወት እናገኝ ይሆናል በሚል ተስፋ ወደውጨ ተሰደው ለውርደት እንዲጋለጡ የዳረጋቸው…እንደ አገር ደሃ መሆናቸው ነው። የኢፌዴሪ መንግሥት ይህን በይፋ የተናገረና እየተናገረ ያለ መንግሥት ነው።
ድህነታችን ከሰው በታች እንድንሆን ከማድረግ ባሻገር ለውጭ ጠላት ጥቃት የሚያጋልጠን መሆኑን በይፋ የገለፀ መንግሥት ነው። የሽብርተኝነትና የእርስ በርስ ግጭት ምክንያትም ድህነት በዜጎች ላይ የሚፈጥረው ተስፋ መቁረጥ መሆኑን የተገነዘበና በይፋ የገለፀ መንግሥት ነው። እነዚህን ችግሮች በልማት፣ በሠላም፣ በደህንነትና የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂዎቹ ላይ በይፋ አስፈሯቸዋል። እናም ድህነትን መዋጋት የአገራዊ ህልውና አደጋም ጭምር ነው የሚል አቋም አለው። ይህ አቋሙ ደግሞ በህዝቡም ዘንድ ድህነትን የመዋጋት ቁርጠኝነት ፈጥሯል።
እንግዲህ ድህነትን የዜጎች የተንጨራቆሰና አዋራጅ ኑሮ መንስዔ፣ የአገራዊ ህልውና አደጋም ጭምር መሆኑን መነሻ በማድረግ የልማትና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ነድፎ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ለስትራቴጂው ተፈጻሚነት ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። ይህ ርብርብ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የኋሊት ጉዞውን ገትቶ ማደግ ጀምሯል። በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት 14 ዓመታት በተከታታይ በአማካይ ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ የኢኮኖሚ ዕድገት በተጨባጭ በህዝቡ ኑሮ ላይ መሻሻል ያመጣ ልማት አስከትሏል። ኢትዮጵያ አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣለች። ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የነበረውን የድህነት ምጣኔ በግማሽ ቀንሳለች። በዚህ ዙሪያ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባት አልፈልግም። የተባበሩት መንግሥታት የሚሊኒየም የልማት ግቦችን በማስፈፀም ረገድ ያገኘችውን ስኬት ከራሱ ከተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ገለልተኛ ተቋማት የመረጃ ቋት ማግኘት ይቻላል።
ይህ ስኬት የኢትዮጵያን የክፍለ ዘመናት የድህነት ጉዞ ገትቶ፣ አገሪቱ በዘመናት ጉዞ ከወደቀችበት የድህነት አዘቅት ሽቅብ መውጣት እንድትጀምር አድርጓታል። ይህ ሽቅብ ጉዞ የአገሪቱ የባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ገጽታ ነው። እርግጥ አሁንም ድህነት አለ። አሁንም እንደ ቆሼ ነዋሪዎች ዓይነት ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች አሉ። አጠቃላይ የአገሪቱን ድህነት የማቃለል ጉዳይ ትኩረት ስለተሰጠው እነዚህ ድሆችም በትኩረቱ ውስጥ ናቸው። አጠቃላይ የአገሪቱ ሁኔታ፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የሁሉም ዜጎች ድህነት ወደሚቃለልበት ደረጃ የሚደረግ ግስጋሴ መኖሩን የሚያሳይ ነው።
ታዲያ የቆሼ ነዋሪዎችም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዚህ ትኩረት ውስጥ ናቸው። ተለይተው ችላ አልተባሉም። ሰሞኑን የደረሰባቸው አደጋ አጠቃላይ የአገሪቱ የዘመናት ድህነት ሸክም ተቃልሎ ባለማለቁ ያጋጠማቸው እንጂ መንግሥት በተለየ ትኩረት ስለነፈጋቸው ያጋጠመ አይደለም። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን ግዙፍ እውነታ ችላ ብሎ የዘመናት የድህነት ሸክም በዜጎቻችን ላይ ያደረሰውን ጉዳት፣ ያልሆነ ትርጉም በመስጠት መንግሥትን ሊያሳጣ ሞክራል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን ያደረገው እርግጥ ለተጎዱት ወገኖቻቻን በመቆርቆር አይደለም።
ከዚህ ይልቅ ያቋቋሙትንና ገንዘብ እየለገሱ የሚመሩትን የባለፀጎች ርዕዮተ ዓለም የበላይነት ለማሳየት ነው። ኢትዮጵያ ከኒዮ ሊበራሊዝም በተለየ የልማት መንገድ ተጨባጭ ዕድገት ማሳየቷ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጌቶች ጎርባጭ ሆኗል። እናም በድህነታችንና በጉዳታችን ሊያተርፍ ሞከረ። በመሠረቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የቆመላቸው ባለፀጎች ለብዙሃን ደሃ የዓለም ህዝቦች ከድህነት መውጣት ደንታ የላቸውም። ፍላጎታቸው የድሆቹን አገር ነጥቆ መበልፀግ ነው። አገራቸውን አላስነጥቅ ያሉ መንግሥታት ደግሞ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን በመሳሰሉ ተላላኪዎች የፈጠራ ወሬ ክፉ ተደርገው እየተሳሉ ለዓለም አቀፍ ውግዘት እንዲጋለጡ ይደረጋሉ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰሞኑን የቆሼ አደጋ መነሻ በማድረግ የሰጠው መግለጫ ዓላማ እንደተለመደው የአጉራሾቹን ተልዕኮ ማስፈፀም ነው። ለኢትዮጵያዊያን ተጎጂዎች ከመቆርቆር የመነጨ አይደለም። ድህነታችንንና ጉዳታችንን በመሸጥ ሊያተርፍ ነው የሞከረው።