የቀናውን የማጉበጥ፣ ጅምሩን የማስፎረሽ ፖለቲካ፤ ለምን?

ከ1983 ዓ.ም. በፊት በሃገራችን ፓርቲ ማቋቋም በራሱ ከባድ ወንጀል እንደነበር ይታወቃል። በዚህ የተነሳ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ለነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባዳ ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል ማለት ነው፡፡ የተደራጀና ተቋማዊ ተቃውሞን ማስተናገድ ለቅድመ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ልሂቃን የማይታሰብ ነበር፡፡ ዛሬ ቢያንስ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ከሥርዓቱ መገለጫዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ይህንኑ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ በማስተዋወቅና ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ገዢው ፓርቲ/ኢሕአዴግ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ አያከራክርም። ይህን ስርአት በመዘርጋት ሂደት የመጀመሪያዎቹ  ዓመታት በአገራችን የፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ላይ ከባድ ልዩነትና ተጠራጣሪነት ሰፍኖ የነበረ መሆኑም ሌላኛው የማያከራክር ገጽታ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ በኢትዮጵያ ብዙኅነትን ከቀደምት አስተዳደሮች በተለየ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለመያዝና ለማስተዳደር እንደሚፈልግ ባሳወቀ ጊዜ፣ ሰፋ ያለው የከተማ ማህበረሰብ በተለይም የአገሪቱ ልሂቃን አቅጣጫውን በከፍተኛ ጥርጣሬ ይመለከቱት ነበር። ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንድትቀጥል የነበራቸው ፍላጎት አደጋ የሚጋረጥበት የሚመስላቸውም ጥቂቶች አልነበሩም። ያም ሆኖ ግን ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ብዙህነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተናገድና ለማስተዳደር መቻሏ፤ ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ስጋት ቀስ በቀስ እያረገበው ሊሄድ ችሏል። መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊኖር እንደማይችል በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተን ቁልፍ እንዳልሆነ በተግባር ታይቷል። በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ መንገድ ከፍቷል።

ይህ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት መከበር የጀመረውን መብት ተከትሎ በርከት ላሉ ዓመታት ጥቂት በማይባሉ የህብረተሰብ ልሂቃን ዘንድ ሰፍኖ የቆየውን “መበታተን አይቀሬ ይሆናል” የሚል ጥርጣሬ ትርጉም ባለው ደረጃ ለመፋቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡   ህገ መንግስታችን የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትና በመሆኑ የተሻለ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ የሚገነባው ሥርዓት የነፃ ገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች ሰርተው የመጠቀም ህጋዊ ዋስትና ሊያገኙ እንደሚገባቸው ተመሳሳይ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ላይ ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኞቹ ጠላቶቻችን እንደሆኑ፣ ስለዚህም ደግሞ በፍጥነት መልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳለብን አጠቃላይ የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል፡፡ የህግ የበላይነት መከበር እንዳለበትና ዜጎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል እንደሆኑ ቢያንስ ቢያንስ ለመግባቢያ መነሻ የሚሆን ግንዛቤ ተይዞበታል፡፡ እዚህ ላይ ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል የጋራ ስምምነት የተያዘባቸው ሆነዋል። ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነና ብዙኀኑን ህዝብ እንደሚጎዳ ከሞላ ጎደል በብዙኀኑ ህዝብ ዘንድ ስምምነት እየተፈጠረ ነው። በዚህ ላይ ሰላማዊና የተረጋጋ ህብረተሰብ የመሆናችን አስፈላጊነት በጥልቅ የሚታመንበት ሆኗል። ዜጎች ከአመፅ ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድና በድርድር መብትና ጥቅሞቻቸውን ማስፋት እንዳለባቸው ታምኖበታል።

በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይህ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አሁንም የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች ይታያሉ። ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነ የሚቀበለው ህዝብ ትንሽ በማይባል ደረጃ በዚሁ ዝንባሌ ሲለከፍ ይታያል። የህግ የበላይነትና ሰላማዊ የትግል አግባብን የተቀበለው ህብረተሰብ፣ አልፎ አልፎ ፍላጎቱን በሃይልና በግጭት መንገድ ለማሳካት ሲንቀሳቀስ ይታያል።  

ይህም በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የለም በሚሉና በምርጫ ማሸነፍ ሲሳናቸው ድክመቶቻቸውን ሁሉ ወደ መንግስትና ገዥው ፓርቲ በሚያላክኩ ፓረቲዎች የሰርክ ወሬ የሚረጋገጥ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ባለፉት ሁለት ጠቅላላ ምርጫዎች በፓርላማው የታየው የአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ስለምን ሆነን? ጠይቀው መልስ ከመፈለግ ይልቅ ለመድበለ ፓርቲ ስርአት ማብቃት እንደማሳያነት ይጠቀሙበታል። በዚህ ሳያበቁም    ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ወደኋላ በማለት ወደ አንድ ፓርቲ ሥርዓት ተሸጋግራለች ብለው እስከማሳጣትም መድረሳቸው ይታወቃል።

ለእነዚህ አስተያየቶች ሩቅ ያልሆነው ገዢው ፓርቲ ከላይ የተመለከቱት መከራከሪያዎች ምክንያታዊ እንዳልሆኑ እያወቀም ዝምታን አልመረጠም። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የአንድ ፓርቲ ሥርዓትን እንደማይፈቅድ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ እና ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ብቻ ሳይሆን ያለነሱ ተሳትፎ የትም መድረስ የማይቻል መሆኑን አምኖ በመቀበል እየተጋ ለመሆኑ በርካታ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህም መካከል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ሲደረግላቸው በነበሩ ድጋፎች ታግዘው መንቀሳቀስና መነቃነቅ ያቃታቸው መሆኑን የተገነዘበው መንግስትና ገዥው ፓርቲ ስለመድበለ ፓርቲ ስርአት ግንባታው ሲል ቀድሞ የነበሩ የምርጫ አሰራርና ስርአቶች በፓርቲዎች አቅምና ቁመና ልክ ሆነው ቢሻሻሉ የተሻለ እድል ይፈጥርላቸዋል በሚል እምነት በርካታ ህግጋትን ለመሻር ለሚያስችል የድርድር መድረክ ያመቻቸ መሆኑ ዋነኛው ማሳያና ሊጠቀስ የሚገባው አስረጅ ነው።  

ገዥው ፓርቲ ይህን መድረክ ሲያመቻች በመሠረቱ በ1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የኢፌዴሪ ሕገ መነግሥት ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በፍትሐዊነት በምርጫዎች እንዲሳተፉና እንዲንቀሳቀሱ መሠረታዊ ማዕቀፉን የዘረጋ መሆኑን እያወቀ መሆኑ ለመድበለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ መሄድ የሚገባው  ድረስ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው፡፡

አሁን ዋናው ጥያቄ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የተረጋገጡላቸውን መብቶች ሊጠቀሙባቸው አለመቻላቸው የቀደመ ድክመታቸው ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያሉ እና እድል የሚፈጥሩላቸው አማራጮችም ላይ ማጉረምረማቸው እና ጥላሸት ለመቀባት ማሰፍሰፋቸው ነው።  

ገዢው ፓርቲ  በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ መድረኮች የአገሪቱን ብዝኃነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበትን እድል አመቻችቶ የነበረ መሆኑና ይህን እድል በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉት እነርሱው መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሳለ ዛሬም በቅድመ ሁኔታ የታጀቡ መፈክሮች ከነዚሁ ስብስቦች አካባቢ መሰማቱ ግራ አጋቢና አስደንጋጭ ነው ።

ከዚህ አንፃር በተቃውሞው ጎራ ያሉትን ፓርቲዎች ባሳተፈ ሁኔታ በገዢው ፓርቱና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ድርድር ለማድረግ መወሰን በራሱ ዴሞክራሲያዊነት ነው። ኢሕአዴግ ቃሉን በማክበር ለሁሉም አገር አቀፍ ፓርቲዎች የውይይትና የድርድር ጥያቄን ያቀረበው ከሁለት ወራት በፊት ነው። በዚሁ መሰረትም እስካሁን ከ21 (ከራሱ ጋር 22) አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር ስድስት ዙር ውይይቶችን አድርጓል።

ውይይቶቹና ድርድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶች ለመወሰን በተደረገው ጥረትም 22ቱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች በስምምነት ለመወሰን 12 ጉዳዮችን ለይተዋል፡፡ እነዚህም ጉዳዮች የድርድሩ ዓላማዎች፣ የድርድርና ክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር አባል ፓርቲዎችና የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ ስለማቅረብና የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ አስተዳደርና የሎጂስቲክስ ድጋፍና የስብሰባ ቦታ ሲሆኑ የደንቡ ዝርዝር ይዘቶች ላይ ውይይት ከመጀመራቸው በፊት የደንቡ ርዕስ ላይ አድርገውት የነበረው ክርክር የጽንፈኝነታቸውን ልክ የሚያሳይ ነበር። ለድርድር ውይይቶችና ክርክሮች ዝግጁ ከሀነ የትኛውም ፓርቲ የኋላን አንስቶ ማብጠልጠል የማይገባ ቢሆንም ጉዳዩን  በዚህ አዙሪት ውስጥ ለመክተት መዳከር የሚሆነው ጉዳዩ ገና ሳይጀመር ማስፎረሽ ነው ።

የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ባይፈጠር ኖሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳን ለድርድር ለውይይትና ለክርክርም ቢሆን ዕድል አያገኙም ነበር ሲሉ በዚህ ክርክር ላይ ማንሳታቸው የማስፎረሽ ተልእኮን ፍንጭ የሚሰጥ ነጥብ ነው፡፡  ከላይ በተመለከቱት አግባቦች ግን ኢህአዴግን የሚገልጸው በክርክሩ ላይ ኢህአዴግን ወክለው የነበሩት አቶ አስመላሽ ‹‹ኢሕአዴግ የሚፈራ ድርጅት አይደለም፡፡ በተፅዕኖ አይደለም ወደ ድርድር እየገባ ያለው፡፡ የምንወያየውና የምንደራደረው የዚህን አገር ሕዝብ ይጠቅማል ብለን ስለምናምን ነው›› በማለት የተናገሩት ነው።  

 

ይህ አይነቱ የነፕሮፌሰር ምልከታ ሊመነጭ የሚችለው ኢሕአዴግ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር በየትኛውም ጉዳይ ድርድር፣ ክርክር ወይም ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነው ማለት የፖሊሲ ወይም የሕግ ለውጥ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ይኖራል ማለት እንዳልሆነ ካለመገንዘብ ነው፡፡ ሊደራደር ዝግጁ የሆነ የትኛውም ፓርቲ ሊከተል የሚገባው መርህ ያለ ሲሆን ሲደራደር አጀንዳዎችን መመዘን የመጀመሪያው መርሁ ነው፡፡ ሁሉም የየራሱ ርዕዮተ ዓለም አለው፡፡ ከራሱ ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ በመነሳት የሚቀበለውን ይቀበላል፣ የማይቀበለውን ደግሞ አልቀበልም ማለትም ተያያዥ የሆነው መርሁ ነው፡፡

በእርግጥ በርዕሱ ላይ ከተደረገው ሞቅ ያለና ጽንፈኝነት ጎልቶ ከታየበት ክርክር በበለጠ የድርድሩ ዓላማዎች ላይ ሰፋ ያለና ጤናማ ውይይትና ክርክር ተደርጎበት ነበር፡፡   በውይይታቸው መጨረሻ በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት፣ በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብ፣ ያላቸውን አማራጭ ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት፣ ድርድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ተስማምተዋል፡፡

ያም ሆኖ ግነ እንደገና መድረክ  ድርድሩ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ እንዲሆን ለማረጋገጥና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን ለማድረግ መዋል አለበት በማለት፤ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቱ ላይ እንደሌለ እና ወይም ተቀባይነት ያለው ምርጫ ተካሂዶ እንደማያውቅ የማስመሰል የማስፎረሽ ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸው ሌላኛው ፍንጭ ነው። በእርግጥም ለሁለት የሥራ ዘመናት የፓርላማው አባል የነበሩት ፕሮፌሰር በየነ፣  ተወዳድረው ፓርላማ የገቡት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ዕውን ስለሆነ መሆኑን እያወቅን ጆሯቸውን ደፍነው እንዲህ ያለ አስተያየት መስጠታቸው ሊሆን የሚችለው የማስፎረሽ ተልእኮ ነው።

በኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ተንታኞችም በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላሉበት የማይፈለግ ደረጃ ኢሕአዴግ ብቸኛው ተጠያቂ አካል አይደለም፡፡ በከፊል ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ብዙም ትርጉም ያለው ሚና እንዳይኖራቸው ለማድረግ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚከሰሱባቸው ጉዳዮች መካከል እጅግ ደካማ መሆናቸው፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉና የተከፋፈሉ መሆናቸው፣ ከሁሉም በላይ ለራሳቸው ክብር ይበልጥ ትኩረት በሚሰጡ ግለሰቦች የሚመሩ መሆናቸው፣ ጠንካራ የድጋፍ መሠረትና አማራጭ ፖሊሲ የሌላቸው መሆናቸው፣ እንዲሁም እርስ በርስ በጥርጣሬ የሚተያዩና የሚገዳደሩ መሆናቸው በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአምስት ዙር ውይይት ወቅት እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ባህሪያት ከተወሰኑ ፓርቲዎች በግልጽ ተንፀባርቀዋል፡፡

ይልቁንም የተሳታፊ ፓርቲዎች ማንነት ላይ ውይይት ሲካሄድ የፕሮፌሰሩ ፓርቲ ባለፈው ጠቅላላ ምርጫ ባቀረበው የዕጩ ተወዳዳሪዎች ቁጥር የተነሳ ዋነኛ ተቃዋሚ በመሆኑ ከኢሕአዴግ ጋር ብቻ ለብቻ ለመደራደር ጥያቄ ማቅረቡ፤ በሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያስወገዘው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የማስፎረሽ አላማውን በግልጽ የሚያመላክት ነው። ሌሎቹም ቢሆኑ ለፕሮፌሰሩ ሃሳብ ተቃውሞዋቸውን የገለጹበት መንገድና ቋንቋም ደካማውን የመቻቻል ባህላቸውን ገሃድ ያሳየና ስለሁሉም ነገር በተጠያቂነት ደረጃ የራሳቸው ድርሻ የሚጎላ መሆኑን ያመላከተ ነው፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ ፓርቲዎች አገር አቀፍ ናቸው። ኢሕአዴግ በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ክልላዊ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ቢጋብዝም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐሳቡን ባለመቀበላቸው ውድቅ መሆኑም ማናቸው ጸረ ዴሞክራሲያዊ እና አምባገነን እንደሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡