ኢትዮጵያና የአጎራባቾቿ ሠላም

 

 የአካባቢያችን ሰላምና ልማት መረጋገጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሀገራችን ፈጣን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ሁሉ፤ በአካባቢያችን የተረጋጋ ሰላምና ልማት ያለመኖርም በሀገራችን ልማታዊ ጉዞ መሰናክል መሆኑ አይቀሬ መሆኑን በመገንዘብ ለውጫዊ ሁኔታዎችም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው።

መንግስት ለአደጋ ተጋላጭነታችን በምክንያትነት የሚጠቀሰውን ድህነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆነበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን እውን በማድረግ ላይ ያተኮረ የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረጽ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ህዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ተግባራዊ ማድረግ የቻለውና ዛሬ ለምንገኝበት ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለው፡፡ እንደሚታወቀው የቀደሙት መንግስታት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት ውጭውን የመመልከት አካሄድን የተከተለ ነበር፡፡

ይህ አካሄድም የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተስኖት ለከፍተኛ ድህነት ሊዳርገን እንደቻለም በአይናችን ያየነውና በጆሯችን የሰማነው ዕውነታ ነው፡፡ በተለይም ያለፋት መንግስታት የውጭ ፖሊሲ በውጭ ጠላቶች የመከበብ ስሜት ጐልቶ የሚታይበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በውጭ ተመልካችነት ላይ ተጠምዶ መቆየቱ፤ የሀገራችን ውስጣዊ ችግሮችና የአደጋ ተጋላጭነታችን እንዲጐለብት ከማድረግ ባሻገር በሀገራዊ ደህንነታችንና ህልውናችን ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ታዲያ ይህን ጠንቅቆ የሚያውቀው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስት ቀደምት መንግስታት ይከተሏቸው ከነበሩት ፖሊሲዎች የተለየና ለሀገራዊ ህልውናችን ወሳኝ በሆነው ውስጣዊ ችግሮች ላይ የሚያተኩር የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ መኖር አስፈላጊነቱ ከምንም በላይ መሆኑን በመገንዘብ ነው— ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ የቻለው፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ምክንያቱም የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው። ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በአካባቢያችንና በአህጉራችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት ስኬቶች መካከልም ረጅም ኪሎሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን ቀውስ ለማርገብ የተካሄደው ጥረትና የተመዘገበው አበረታች ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡

ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ለጥ ያለና ውሃ ገብ የሆነው መልከዓ ምድሯ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል እንደሆነች ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ሀገሪቱ ግን ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለመቆየት ተገዳለች። በዚህም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግ በመቻሏ ለተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በጐረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሃገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት፡፡

በእርግጥ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ሀገሪቱ ነፃነቷን ከተጐናፀፈችበት እ.ኤ.አ. በ1956 ነበር። ይህ ሁኔታም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያደረሰው አሉታዊ ተፅእኖ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም በሀገሪቱ የሰፈነው ቀውስ ላለፋት አምስት አሰርት ዓመታት የዓለም አቀፋን ትኩረት ሲስብ ቆይቷል፡፡ በተለይም እ.ኤ.አ. ከ1972 እስከ 1983 ድረስ በዘመነ ሃይለ ስላሴ በመዲናችን አዲስ አበባ የተካሄደው ጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡ በግብጽ፣ በናይጀሪያ፣ በጀርመን፣ በአሜሪካ፣ በሊቢያና በሌሎች ሀገራት አማካኝነት የተካሄደው ጥረትም እንዲሁ፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን በሀገሪቱ ለደረሰው ቀውስ እልባት የመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎች የተካሄዱ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ለፍሬ መብቃት አልቻሉም፡፡ ይልቁንም የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ በየጊዜው “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉት ዓይነት ሆኖ እየተባባሰ ሊሄድ ችሏል፡፡

እንግዲህ ሁኔታዎች በዚህ ደረጃ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው— የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም የሚሰፍንበት ሁኔታን ለመፍጠር መንቀሳቀስ የጀመሩት፡፡ እናም እ.ኤ.አ. በ1992 ኢጋድ ለቀውሱ እልባት ለመስጠት በናይሮቢ ባካሄደው የሰላም ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ውጤታማ የሆነበትን ድል ማስመዝገብ ቻለ፡፡ ይኸውም ለዘመናት በእርስ በርስ ግጭት በዘለቁት የሱዳን መንግስትና የደቡብ ሱዳን አማፂያን የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ መቻላቸውና ለዚህ ውጤት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ሚና የጐላ መሆኑ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ወገኖች የሁሉም ነገር መሠረት የሆነው የሰላም ስምምነት ላይ መድረሳችው ቀጣዩን ሁኔታ አመላካች አድርጎት ስለነበር ነው፡፡

እንዲሁምም እ.ኤ.አ. በ1998 በመዲናችን አዲስ አበባ ለተካሄደው ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት ድርሻ የላቀ ነበር፡፡ በመሆኑም ኢጋድ እንዲሁም ሀገራችን ለዓመታት ያካሄዱት ጥረት በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት በማግኘቱ በመጨረሻ እ.ኤ.አ. በ2ዐዐ5 የተደረገው ስምምነት ለውጤት መብቃት ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ሀገሪቱ አንዱን ቀውስ ለመፍታት ያደረገችው ጥረት የተሳካ ቢሆንም ሌላ ቀውስ መከተሉ አልቀረም፡፡ በዘር ግጭት ላይ የተመሰረተውና የተለያዩ ተዋናዬች የተካፈሉበት የዳርፋር ቀውስ ተሰሰተ፡፡ ቀውሱን ለማርገብ እና እልባት ለመስጠት ታዲያ ጥረት መደረጉ አልቀረም፡፡ ከዚህ አኳያ በእነ ቻድ የተደረገው ቀጥሎም በአፍሪካ ህብረት የተካሄደው ጥረት ይጠቀሳል፡፡ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለው የዳርፋር ቀውስ በሱዳን መንግስትና በሁለቱ ታጣቂ ሃይሎች መካከል በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የማስማማት ጥረት በአዲስ አበባ ቢካሄድም ለውጤት ሳይበቃ ተበትኗል፡፡

ኢትዮጵያ መልካም ጉርብትናን የመፍጠር ፍላጐቷ ከውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዋ የሚመነጭ በመሆኑ፤ ቀደም ሲል በሁለቱ ሃገሮች ይስተዋል ለነበረው ግንኙነት መለወጥ አስችሏል፡፡ በተለይ ከሱዳን ጋር የነበረውና የደርግ መንግስት ይከተለው በነበረው የጣልቃ ገብነት ፖሊሲ በጆን ጋራንግ የሚመራው የደቡብ ሱዳን አማጽያንን የማስታጠቅና የመደገፍ ተግባር ለሁለቱ ወገኖች መተማመንን አሳጥቶ ቆይቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኤርትራ መንግስት በሚከተለው የማተራመስ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ በሚያደርገው ጥረት ሱዳንን ተጠልለው የሽብር ተግባር ለመፈፀም የቀድሞ የግብጽ ኘሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ ያካሄዱት የግድያ ሙከራ ለሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ችሏል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነትና መልካም ግንኙነት መስፈን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን መጠናቀቅ ተከትሎ የሀገራቱ ግንኙነት እያደገ ከመምጣቱ ባሻገር የላቀ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፤ የባህል ትስስር፤ የፀጥታና ደህንነትና ሌሎች ተግባራት በመከናወናቸው ጠንካራ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ ለዚህም ነው በሁለቱ ሃገራት መካከል የመተማመን መንፈስ መፍጠር የተቻለውና የሱዳን መንግስትና ህዝብ ከኢትዮጵያ በላይ ችግሩን ሊፈታለት የሚችል ሃይል እንደሌለ በማመን በዳርፋር ለተከሰተው ቀውስ እልባት ለመስጠት የኢትዮጵያ መከላከያ የሰላም አስከባሪ ሃይል መሰማራትን ቀዳሚ ምርጫ ያደረገው፡፡ ኢትዮጵያ ለሶማሊያም ይሁን ለደቡብ ሱዳን ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት እየሰራች ነው፡፡

ይህ ሀገራችን የአጎራባቾቿን ሰላም ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ብዙ ርቀት የተጓዘ ነው፡፡ የራሷን የውስጥ ሰላም ከማረጋገጥ አልፋ ለጎረቤቶቿ የምታደርገው አስተዋፅኦ ሀገራችን የቀጠናውን አገራት ለማገዝ እየተጠቀመችበት ያለው ፍፁም ሰላማዊ መንገድ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ነው፡፡ መንግስት ይህን ጥረቱን ወደፊትም ቢሆን አጠናክሮ በመቀጠል የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦችን ሠላም ይታደጋል፡፡