የፀረ-ድህነት ትግሉ ውጤቶች

 

ሀገራችን ድህነትን ለመቅረፍና የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፖለሲዎችና ስትራቴጂዎችን አውጥታለች። በተለይም ከመጀመሪያው የተሃድሶ ወቅት ወዲህ ባሉት ዓመታት መንግስት የመሪነት ሚናውን ወስዶ ባከናወናቸው ድህነትን የመቀነስ ተግባራት፤ ሀገራችን ውስጥ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ ፖለሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመከተል ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

በእነዚህ ዓመታት በዋነኛነት የመንግስት አስተዳደርንና ሀገሪቱ የምትመራባቸውን ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያልተማከሉ የማድረግ፣ ኢኮኖሚውን ከዕዝ ወደ ገበያ መር ስርዓት የማምጣት፣ በፖሊሲ መዛባት በጦርነትና በተፈጥሮዊ ክስተቶች ሳቢያ የተሽመደመደው ኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዲቀየር የማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል።

መንግስት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የተሟላ ዝግጅት በመደረጉና ህዝቡም መንግስት የቀረጻቸውን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ወደ ተሻለ እመርታ ለመሸጋገር በቅቷል፡፡ ላለፉት 15 ዓመታትም መንግስት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥናት ለማስወገድ በመሞከርና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ክንዋኔዎችን በመስራት፣ ያሉትን ውስን ሀብቶች መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱበት የልማት ስራዎች ላይ በማዋል፣ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንት በማበረታታት ፈጣን ቀጣይነትና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት ለማምጣት ተችሏል፡፡

መንግስት የተለማቸው የልማት ፕሮግራሞች ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ እንደሚረዱ ታምኖባቸው በዚህም ከቀበሌ እስከ ሀገር አቀፍ ድረስ ህብረተሰቡን እንዲሁም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያሉትን የልማት አጋሮች ለማሳተፍ በሚያስችል መልኩ የተቀረፁ ነበሩ፡፡ እያንዳንዱ የልማት ዕቅድም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ብሎም የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ የተቀየሱ በመሆናቸው የየራሳቸው መሰረታዊ የትኩረት አቅጣጫ ያላቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም ህዝቡን በበልማቱ ላይ በማንቀሳቀስ ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል።

ይህ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መጠን ትልቅ የገበያ ምንጭ ስለሆነና በተፈጠረውም አመቺ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ተበረታትተው በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች እንዲንቀሳቀሱ አስችሏቸዋል፡፡ የተጀመረው ዕድገት በዚሁ ከቀጠለ ሀገራችን በቅርብ ዓመታት ከአፍሪካ በኢኮኖሚ ታላቅነቷን ልታስመሰክር እንደምትችል መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገሮችና ከዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር ሀገራችን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ በማምጣት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ከዓለም አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ሲሆን፤ በተለይም የዓለም ኢኮኖሚ በ2002 ከዜሮ በታች ዕድገት ሲያስመዘግብ፤ ሀገራችን ግን የላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት አፈጻጸም ነበራት፡፡ ታዲያ ይህ ድል የተገኘው ሀገራችን የነደፈቻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ በመሆናቸው እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

ከ1994 ዓ.ም በፊት የተከናወኑ የኢኮኖሚ መዋቅር ማስተካከያና ማሻሻያ ፕሮግራሞች የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴውን ከማነቃቃታቸው ባሻገር፤ የኋሊት ሲጓዝ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ትክክለኛ አቅጣጫውን ይዞ እንዲጓዝ ያደረጉ መሆናቸውን እየተመዘገቡ ካሉት ዘርፈ ብዙ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡

ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መኖር ወሳኝ መሆኑ ስለታመነበት፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የፊስካልና የሞኒተሪንግ ፖሊሲዎችን በማጣጣም እንዲሁም ዝቅተኛ የመንግስት በጀት ጉድለትንና የውጪ አሸፋፈን እንዲኖር በማድረግ ብሎም የገንዘብ እንቅስቃሴው ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዋጋ ዓመታዊ ዕድገት ጋር የተዛመደ እንዲሆንና የውጭ ምንዛሬ ምጣኔዎችን ለማስተካከል ያለሰለሰ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ውጤት ተገኝቷል።

ባለፉት 15 ዓመታት ለሁለት ዓበይት የኢኮኖሚ ዘርፎች (ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ) ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍም በግብርና እና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ መቻሉን ነው።

መንግስት ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለስራው የሰው ሃይል ልማት በመንግስት የተሰጠው ትኩረት የላቀ በመሆኑ የተገኙ ውጤቶችም አበረታች ሆነዋል፡፡ እርግጥም በመንገድ ግንባታ፣ በኤሌትሪክ ሃይልና በቴሌኮሙኒኬሽን እንዲሁም በንጹህ ውኃ አቅርቦት ረገድ የተገኘው መሻሻል አገልግሎቶቹን ለማስፋፋት የጠየቁት ከፍተኛ የፋይናንስና የሙያ ክህሎቶች፤ የተፈራውን ያህል ስራዎቹን ሊያስተጓጉሏቸው አለመቻላቸውን የተገኙት ውጤቶችን በማየት መመስከር የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የኢኮኖሚ ዕመርታችን የሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዘገቡ ሀገራችን በኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና በአፍሪካ ከሚገኙ ሶስት ሀገራት ግንባር ቀደም በመሆን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡ የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር እንዲቀንስና በየደረጃውም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ ነው፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የቻለ ቢሆንም፤ በያዝነው ሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትና የዕድገቱ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ መተግበር ከጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ተቆጥሯል፡፡

እርግጥ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታትም በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሚሊዮነር ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል፡፡

የሀገሪቱ የግብርና መር ፖሊሲ ወደ ኢንዱስትሪ መር በሂደት እንዲሸጋገር እየተደረገ ያለው ጥረትም የሚደነቅ ነው፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት መንግስትና ህዝብ በጋራ በመሆን ባከናወኑት ሰፊ ጥረት እያስመዘገቡ ያሉት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት አሁንም ግለቱን ጠብቆ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በዚህም ሀገራችን ቀይሳ ወደ ተግባር ገብታ የፈፀመችው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም አበረታታች በሚባል ደረጃ ገቢራዊ ሆኗል፡፡ በልማት ዕቅዱ ዓመታት በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተከናውነዋል። በከተሞች በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የተደረጉት ጥረቶች በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ልማታዊ የኢኮኖሚ አውታሩ ፈጣን ልማትን የማረጋገጥና ህዝብን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡ በዚህም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ትግበራ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአነስተኛና ጥቃቅን የተሰማሩ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏል፡፡ ይህ ቁጥርም በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ይበልጥ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሀገሪቱ ገጠራማ ክፍልም አርሶ አደሩ እያካሄደ ያለውን ምርትና ምርታማነት የማሳደግ እንቅስቃሴ በእጅጉ ውጤታማ በመሆኑ፤ ሞዴል ሚሊዮነር አርሶ አደሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እየተደረገ ያለውን ሽግግር የሚያፋጥን መሆኑም አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ተፈጥረው በልማቱ ላይ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።

ሀገራችን በአሁኑ ወቅት መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ በገጠርም ሆነ በከተማ የምታከናውነው የልማት ርብርብ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እንዲቀየር ማድረጉ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ እናም አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚተትኑት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቱ በዚሁ ከቀጠለ በቀሚቀጥሉት አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ ባስቀመጠችው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ጎራ ለመሰለፍ ያስችላታል፡፡ በመሆኑም የልማት ዕቅዱ በሀገራችን ውስጥ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ በቀሪዎቹ ዓመታት ሁሉም አዜጎች በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ሀገራችን የጀመረችውን የፀረ-ድህነት ትግል በአሸናፊነት እንድትወጣ ያደርጋታል፡፡