የቆሸሸ ታሪክ ባለቤት ላለመሆን ∙ ∙ ∙

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኤጄንሲ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ከ1900 እስከ 2009 ዓም ድረስ ባሉት ዓመታት 26 ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ኤልኒኖ ድርቅ አስከትሏል። ከኤልኒኖ በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 30 ዓመታት ተጨማሪ የድርቅ አደጋዎች በአገሪቱ ላይ ተከስተዋል። በዚያው ልክ ደግሞ በአለም መድረክ ላይ ቀና ብለን እንድንሄድ ያስቻሉን የበርካታ ድሎች ባለቤትም ነን። እኤአ በ2003 ቶጎ/ሎሜ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ መሪዎች ስበሰባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ ቀርቶ የሊቢያዋ ትሪፖሊ እንድትሆን የአህጉሩን መሪዎች ማግባባት የጀመሩት የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ “አዲስ አበባ የምንሄደው ቆሻሻ ለማሽተት ነው? ስለዚህ ከቆሻሻዋ ከተማ ይልቅ ትሪፖሊ የህብረቱ መናገሻ ልትሆን ይገባል” ሲሉ ተናግረው ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በነዳጅ ዘይት ሀብት አቅላቸውን የሳቱትን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን ሲከራከሩ “እውነት ነው ከተማችን ቆሻሻ በዝቶባት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አገራችን ቆሻሻ ታሪክ የላትም” ሲሉ መመለሳቸውን ስለጸረ-ድህነት ዘመቻችን እና የቀሸሸ ታሪክ ባለቤት ላለመሆን ማስታወስ ያስፈልጋል።

አሁን ይህን እና ቀና ያደረገንን  የቀደመ ስማችንን ለማስመለስና ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ለመሸጋገር በሚያስችለን የህዳሴ ጉዞ ላይ መሆናችን ይታወቃል። ስለሆነም ይህን የህዳሴ ጉዞ የሚያደነቃቅፉ በርካታ ስንክሳሮች ቢኖሩም በጽናት መታገል ቁልፍ ተግባራችን ሊሆን ያስፈልጋል።

የአሁኑ ትግል ከድህነት ጋር ነው። ድህነትን ለመታገል ደግሞ አስፈላጊው ስራና የስራ ተነሳሽነት ብቻ ነው። ጠላታችን ያለው እዚሁ እጉያችን ስር ነው። የቀደሙ አባቶቻችን ግን ከውጭ ጠላት ጋር በጽናት ተፋልመውና የህይወት መስዋእትነትን ከፍለው ለዚህ ዘመን አብቅተውናል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የአገሪቱ ጫፎች ድረስና በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚገለጹበት ስያሜ፣ የአንድነትና የጀግንነት መገለጫ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ የጋራ በሆነው ጠላታቸው ላይ ድርድር የማያውቁ መሆኑንም ስለ ጸረ ድህነት ዘመቻው ማስታወስ ተገቢ ነው። ድህነት ከሁሉም የከፋ ጠላት ነው። ይህች አገር የኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤታቸው በመሆኗም በሚገጥማቸው የጋራ ጠላት ላይ ልዩነቶቻቸው ትዝ አይላቸውም፡፡ አሁን እንደቀድሞው መድፍና ጦር መስበቅ፤ ጋሻና ጦር ለሚያስፈልገው ዘመቻ የተጠራ የለም። እጅ እግርን ከዶማና አካፋ ጋር ማስተሳሰርና በጎደለበት ካለበት ላይ የመሙላት የመቻቻል እና የመደጋገፍ  ዘመቻ ነው የሚያስፈልገን። ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ ድል በመላው ዓለም አንፀባራቂ ሊሆን የቻለው፣ በጠንካራ አንድነት ለአገር ራሱን አሳልፎ በሰጠ ጥቁር ሕዝብ የተገኘ የመጀመሪያው ድል በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ታላቅ መስዕዋትነት የተከፈለበት የጋራ እሴት ነው የሚባለው፡፡

በዚህ ዘመን ከመጠን በላይ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ የትናንቱን የሕዝባችንን የአገር ፍቅርና ታላቅ የአርበኝነት ስሜት የሚያደበዝዙና ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ማንነት ላይ ብቻ በመንጠልጠል ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ሞልተዋል፡፡ ዘመን ያለፈባቸውና ከጊዜው ጋር የማይሄዱ አስተሳሰቦችን የበላይ ለማድረግ መከራ የሚያዩም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ታጋሽነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ርህራሔ፣ ጀግንነት፣ መከባበር፣ ወዘተ ያሉበት ትልቅ የጋራ እሴት መሆኑ ከቶም ሊዘነጋ አይገባም፡፡  

ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ ሃገሩን ማስቀደም እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ልዩነቶች ቢኖሩት እንኳ ከልዩነቶቹ ይልቅ ልክ እንደቀደመው ለአንድነቱ ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑም መዘንጋት አይገባም፡፡  

ይህች  ሃገር ከዚህ በኋላ በዓለም ፊት ልትዋረድ ከሆነ ድህነትን ማሸነፍ ካቃታት ብቻ ነው። ድህነቷን በጋራ ታግለው ከላይዋ ላይ ከማራገፍ ይልቅ ከአለም የአየር ንብረት መለወጥ ጋር ተያይዞ የገጠማትን ድርቅ ለውርደቷ ከሚሰብቁ ጠላቶቿ ጋር ማበር የክህደት የመጨረሻው ጣሪያ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ መወገዝ አለባቸው፡፡ በአገርና በኢትዮጵያዊነት ቀልድ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት መከበር አለበት ሲባል ለአገራቸው ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የሚያደርጉ፣ በክፉ ጊዜ ደራሽ የሆኑና እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ለአገራቸው ቀናዒ የሆኑ ዜጎች ያስፈልጉናል ማለት ነው፡፡ ለዘመናት በላይዋ ላይ ሲጋልቡ ከኖሩት ድህነት፣ በሽታ፣ መሐይምነት፣ ኋላቀርነትና ተስፋ መቁረጥ ጋር ተፋላሚ የሚሆኑ ዜጎች ያስፈልጉናል ማለት ነው።  

አሁን የተያያዝነውን የጸረ ድህነት ዘመቻ እየተፈታተኑብን ከሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መካከል ድርቅ የመጀመሪያውን ረድፍ እየያዘ ነው። ስለሆነም ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ ሲባል ከሚደረጉ ኋላቀር አስተሳሰቦችና አንድም ዕርምጃ ከማያራምዱ ድርጊቶች በመላቀቅ በመፍትሄው ላይ መስራትና ለጊዜውም ቢሆን መደጋገፍ ዋነኛው ስራችን እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

የአገሪቱን የፖለተካ ስልጣን ይዞ መንግስት የመሰረተው ኢህአዴግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ለመሆኑ አለም እየመሰከረ ቢሆንም በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና የአለማችን ዳፋ በተደጋጋሚ ለሚከሰት ድርቅ እና በዚህም ዜጎቿን ለቸነፈር የአገሪቱን ኢኮኖሚም ለከባድ ፈተና እየዳረገብን ነው። በእርግጥም ጨርሰን ማስወገድ ባይቻለን እንኳ ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣን ክስተት እና ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ለውጥ የሚይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡

የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋውን ያሳረፈው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድህነት ጎጆውን በሰራባቸው አገሮች ላይ ሲሆን በተለይ ኢኮኖሚያቸውን በግብርና ላይ በመሰረቱ አገሮች ላይ መሆኑን አለም በተገነዘበበት ሰዓት ላይ ወደመፍትሄው መሮጥ እንጂ ለፖለቲካ ትርፍ አቃቂር ማውጣት ኋላቀር ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ሌላኛው ጠላትነት ነው።

የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኤጄንሲ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን አስታውቋል። ነገርግን ይህ አኃዝ ከፍ ሊል እንደሚችል ደግሞ አስተያየታቸውን የሰጡን ምሁራን ተናግረዋል። ይህ አኃዝ በራሱ ከፍተኛ ሲሆን በቀጣይ በሶማሌ ክልል ድርቁ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰሞኑን ካደረጉት ቃለምልልስ መገንዘብ ተችሏል። ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በአፋር ክልልም ድርቁ ሊከፋ እንደሚችል ግምቶች እንዳሉ በኮሚሽነር ምትኩ የተገለጸ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል (በአሁኑ ወቅት ብቻ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለርሃብ ስጋት የተጋለጠበት ክልል ነው) እና በአማራ ክልልም ተጨማሪ የድርቅ ስጋት ያንዣበበባቸው ናቸው።

በቅርቡ ይፋ በሆነ የዓለም ሚዲያዎች መረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ አጎራባች በሆኑት በሶማሊያ፣ በኬኒያ እና በደቡብ ሱዳን ድርቅ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን በሶማሊያ ወደ 200 የሚጠጉ ዜጎች ሞተዋል። ኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን ደግሞ ድርቁ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አውጀዋል። እነዚህ አጎራባች አገራት በተለይም ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ከድርቁ በተጨማሪ ባለባቸው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በርካታ ዜጎቻቸው እግራቸው ወደመራቸው የሚሰደዱ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ኬኒያን ደግሞ የመጀመሪያ መጠጊያቸው አድርገዋል። ጦርነቱ ላይ ድርቁ ተጨምሮ በሁለቱ አገራት ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ የበረታ ሊሆን ስለሚችል ኢትዮጵያ ደግሞ ከራሷ ችግር በዘለለ ድንበር ተሻጋሪ ችግር ተጨምሮባት የበለጠ ስጋት ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ይጠበቃል። ስለሆነም የቤት ስራችንን በሚገባ መስራትና በተለይም የሞላለት ላልሞላለት ሶስቴ የሚበላ አንዱን ባዶ ቤት ለሆነው በማገዝ ይህንን ክፉ አጋጣሚ ማለፍ ወሳኙና ቁልፉ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል። ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀንም በእንዲህ አይነት ፈተናዎች የሚገለጽ እንጂ ባዶ ትምክህት ሊሆን አይገባም።

አሁን በድርቅ ምክንያት የተከሰተውን የውኃ እጥረትም ሆነ የእንስሳት መኖ እንዲሁ ተጋግዞ እና ተደጋግፎ መሻገር ይገባል። ለድርቅ ምክንያት የሆነን ኤሊኖ የድንገቴ ዝናብ ምክንያት መሆኑም ይጠበቃልና የውኃ ማጠራቀሚያ ኩሬዎችን ተረባርቦ መቆፈር ይገባል። ከሁሉ በላይ ግን ለዘላቂ መፍትሄው መረባረብ ይገባል። ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆን ይገባዋል።  ድንገቴውን ዝናብ ተከትሎ በጎፍር የሚጠቁ አከባቢዎችን ሥጋት ለመቀነስ እና ለድርቅ አካባቢ የሚሆንን ማካካሻ ለማትረፍ የእርጥበት ዕቀባ ሥራም ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት ። 

ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ ዛሬም ዋናው ችግር የግብርና ሥራው ኋላ-ቀር ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ደግሞ   በየጊዜው ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙንን ችግሮች በአስተማማኝ መልኩ ለመቋቋም አያስችልም፡፡ ህዝቡን ከድህነት የሚያላቅቅ በሂደትም የበለፀገ ሀገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርና ልማትን የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ሲሆን መንግስትም ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች እና ለገጠሩ ህብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መገኘቱ የማይተባበል  ቢሆንም በመንግስት እቅድና ፍላጎት ልክ ዛሬም እየተሰራ አይመስልም።  የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂው  ያለንን የልማት አቅም ማለትም ሰፊ ጉልበት፣ መሬትና ውሃ እና ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን መዘንጋት ለእንዲህ ያለ አደጋ ከሚያጋልጡን ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑን ተገንዝቦ በአቅጣጫው አግባብ መስራት ያስፈልጋል።   

በግብርናው ሴክተር የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ በግብርናው ሴክተር ያለውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክህሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራ በመስራት የሰው ኃይሉን ምርታማነት የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ማከናወን ዘላቂነት ያለው የድርቅ መፍትሄ ነው፡፡ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እየተሻሻለ እና ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ መምጣቱን ታሳቢ ያደረገ  የአኗኗር፣ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤንም ጭምር መቀየር ያስፈልጋል፡፡