መቋቋም ተችሎአል

ድርቅ ተፈጥሮአዊ ክስተት በመሆኑ ሀገራትን በከፍተኛ ደረጃ እየመታ ይገኛል፡፡ በስፓኒሽ ኤልኒኞ (ትንሹ ሕጻን) እንዲሁም ኤልኒኛ (ትንሿ ሕጻን) በመባል የሚታወቁት የአለምን የተፈጥሮ አየር ንብረት የለወጡ፤ ውሀ ሙላትን፤ የመሬት ናዳን፤ ከፍተኛ ማእበላዊ ሀይል ያለውን አውሎ ንፋስ፤ የመሬትን መድረቅና መሰነጣጠቅ በአለማችን ላይ በማስከተላቸው ለድርቅም በዋነኛነት የሚጠቀሱ ምክንያች ናቸው፡፡

በዚህም የተነሳ በርካታ ሀገራት በከፍተኛ አጥረግራጊ አውሎ ንፋስ፤ በድንገተኛና ደራሽ ማእበላዊ የውቅያኖሶች ውሀ ሙላትና መጥለቅለቅ፣ ከወሰናቸውም አልፈው መንደሮችንና ከተሞችን፣ ድልድዮችና ሕንጻዎችን ማፈራረስ በተለይ የሚታወቁበት ሲሆን፤ ሰብሎችንም በማውደም የሰውን ልጅ ከፍተኛ ፈተና ላይ ጥለውታል፡፡

የተፈጥሮ አየር ንብረት መዛባቱ ከበለጸጉና ካደጉ ሀገራት ከባድ ኢንዱስሪዎች ከሚለቀቀው በካይ ጋዝ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ይሄንን ችግር ለመክላት ምድርን አረንጓዴ ለማልበስ አለምአቀፋዊ የጋራ ስምምነት ላይ ቢደረስም ችግሩን ለመፍታት አልተቻለም፡፡ በእኛም ሀገር  በተደጋጋሚ የሚከሰተው የድርቅ ችግር ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ራሳቸው ያደጉና የበለጸጉ የሚባሉት ሀገራት በተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት መንስኤነት ለበርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች ሰለባ ሆነዋል፡፡ እኛ ጋ የተከሰተው ድርቅ መሬቱን ሙሉ በሙሉ በማድረቅና በመሰነጣጠቅ፣ ውሀ እንዳይኖር በማድረግ፣ ሰብሎችን በማጥፋት፣ ደረቅ አየርና በረሀማትን በመፍጠር በሰውና በእንሰሳት ላይ ከባድ አደጋ የሚያደርሰው አይነት ነው፡፡

ምንም እንኳን ድርቁ ከባድ ቢሆንም በመንግስትና ሕዝብ ርብርብ አደጋውን ለመመከትና ለመቋቋም ተችሎአል፡፡ በሶማሌ፣ በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ሀገራችን ባለፉት ሀምሳ አመታት ከገጠማት ድርቅ ሁሉ የከፋው አይነት መሆኑን የአለም መገናኛ ብዙህን ዘግበዋል፡፡ ቢሆንም ሀገሪቱ ቀድሞ በዘረጋቻቸው የአደጋና ድርቅን የመከላከል መዋቅሮችዋ ተጠቅማ ፈጣን እርዳታና እገዛዎችን ለተጎጂዎቹ አካባቢዎች ለማድረስ በመቻልዋ ድርቁ አስከፊ አደጋ ከማድረሱ በፊት ለመከላከል አስችሎአታል፡፡

ለድርቁ ተጎጂዎች ምግብ፣ ውሀና መድሀኒት በከፍተኛ የመንግስትና የሕዝብ ርብርብ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ሲሆን ስራዉ በዘመቻ ቀጥሎአል፡፡ ከዚህ በላይ ሀገራችን ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ያለቸው ድርቅን በዘላቂነት ለመመከት በሚያስችሉ የተፈጥሮ አየር ንብረት ጥበቃ ስራዎች ላይ ነው። በዚህም መሰረት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶአደሮችና አርብቶአደሮች በአፈርና ውሀ እቀባ የተፈጥሮ ደንን በማልማት የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል በሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች ላይ በዘመቻ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት የጎርፍ አደጋ እንዳያስከትል ጉድጉዋዶች በመቆፈርና ውሀው ወደመሬት ሰርጎ እንዲቀርና ለአካባቢው እርጥበት በመፍጠር ተክሎችን እንዲያበቅል በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራዎች ተሰርተው አበረታች ውጤትም ተገኝቷል፡፡

አርሶ አደሩ በብሄራዊ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች በቅንጅት ባደረገው ከፍተኛ የዘመቻ ስራና ንቁ ተሳትፎ በዘንድሮው መኸር ምርት እጅግ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችሎአል፡፡ የተገኘው ውጤትም በምግብ ራሳችንን የመቻል ሀገራዊ አቅም እየገነባን ለመሆናችን ማረጋገጫና ማሳያ ነው፡፡ አሁን በተደረሰበት ሀገራዊ የእድገት ደረጃ  ድርቅ ለረሀብ ምክንያት የማይሆንበት እድገት ለማስመዝገብ ተችሎአል፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው መንግስትና ሕዘብ በጋራ ርብርብ ባደረጉት ከፍተኛ ትግል ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ድርቅን ከመሰረቱ ለመመከት የሚያስችል ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተቀናጀ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎቻችን ለዘላቂ የሕዝብ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ ልማት ከፍተኛ እገዛና አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን የክልል መንግሥታት ድርቁን ለመመከት በሚደረገው ያላሰለሰ ዘመቻ ውስጥ የበኩላቸውን ከፍተኛ ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርቅን አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በናይጄሪያና በየመን ከ20 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በከፋ የረሃብ አደጋ ውስጥ መሆናቸውን ሲገልጽ በዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያ አልተካተተችም፡፡ ይህ ድርቁን ለመመከት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ታላቅ ርብርብ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተጨባጭ የተገነዘበው ለመሆኑ ማረጋጋጫ ነው፡፡ ለመንግስትና ሕዝብም ታላቅ ውጤት ነው፡፡

ቀድሞ በነበሩት ረዥም ዘመናት ድርቅና ረሀብ በተነሳ ቁጥር የሀገራችን ስም በግንባር ቀደምትነት ነበር የሚጠቀሰው፡፡ ዘንድሮ ይሄ አልሆነም፡፡ በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚህ ዝርዝር ውስጥ አልገባንም፡፡ በአገራችን ድርቅ ቢከሰትም ወደ ረሃብ እንዳይቀየር ለማድረግ ችለናል፡፡ የዚህ ምስክርነት ለበርካታ አመታት በተሰራው ጠንካራ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራና በተገኘውም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ድርቁን ለመመከት በመቻላችን ነው፡፡ ድርቁን ለመመከት ኢትዮጵያ ታላቅ  ርብርብ እያደረገች ባለችበት ሰአት ሰሞኑን የመንግስታቱ ድርጅት አራት ሀገራት በረሀብና ቸነፈር አደጋ መመታታቸውን  አስታውቆአል፡፡

የድርጅቱ የሰብአዊ ድጋፍ ኃላፊ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በሶማሊያ፤ በደቡብ ሱዳን ፤በናይጀሪያና የመን ከፍተኛ ረሀብ መከሰቱን ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ዓለም አቀፍ ተቋማት የበጀትና ሌሎች አስቸኳይ እርዳታዎች እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ድርቅ ሳቢያ ለአደጋ ለተጋለጡት የአገራቱ ዜጎች እስከ መጪው ሐምሌ ወር ድረስ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ መሆኑን፤ አስቸኳይ ድጋፍ ካልተደረገ የከፋ ሰብአዊ ቀውስና እልቂት ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቦአል፡፡   

ከደቡብ ሱዳን ሕዝብ ከፊሉ የምግብ እጥረት ሥጋት እንደተጋረጠበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ገልል፡፡ በደቡብ ሱዳን የቢሮው ቃል-አቀባይ ፍራንክ ንያካይሩ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሄው ቁጥር 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያንን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ የተጠለሉ 260 ሺህ የሱዳን፤ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ ስደተኞችን እንደሚያካትት የደረቅ ወቅቶች መራዘም፡ ጎርፍና የከባቢ አየር ለውጥ የአገሪቱን የእርሻ ሥራ ያስተጓጎለው መሆኑን የዶቼቬሌ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኢዩጊን ኦውሱ ግጭት፤ የኤኮኖሚ ቀውስ እና የከባቢ አየር ለውጥ የደቡብ ሱዳንን ሰብዓዊ ይዞታ በፍጥነት እንዲያሽቆለቁል ማድረጋቸውን፤ የእርዳታ ድርጅቶች በ2017 እኤአ ለደቡብ ሱዳናውያን ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ እርዳታዎችን ለማቅረብ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በናይጀሪያ 11 ሚሊዮን ሕዝብ እጅግ የከፋ የምግብ እጥረት የሚያጋጥመው መሆኑን  የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት አስታወቋል፡፡ ድርጅቱ የምርት ወቅት በሆነዉ ከሰኔ እስከ ነሐሴ ድረስ በሰሜናዊ ናይጀሪያ የሚገኙ አካባቢዎች ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንደሚሆኑ፤ ቦኮ ሃራም በፈጠረዉ ያለመረጋጋት ምክንያት 120 ሺ የሀገሪቱ ዜጎች አደገኛ ለሆነ የረሃብ አደጋ እንዲጋለጡ ማድረጉን ገልጾአል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቦታው ሕጻናት እየሞቱ ስለሆነ አፋጣኝ እርዳታ ካላገኙ ሚሊዮኖች እንደሚያሰጋቸው፤ ሙስናና በመንግሥት እና በእርዳታ ድርጅቶች መካከል ያለዉ ውዝግብም ችግሩን እያወሳሰበዉ እንደሚገኝ እስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣናት የአካባቢዉ መንግሥታት የእርዳታ እህሉን ይሰርቃሉ የሚለዉን ክስ በማጣራት ላይ መሆናቸውን የአሶሼይትድ ፕሬስ ዘገባ ያስረዳል፡፡