የሀገራችን ሰላም መሰረቱ ህዝቡ ነው

    ባለፈው አመት በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ትርምስ እንዲገታ ያደረገው ሕዘቡ ነው፡፡ የሀገር ሰላም ዋነኛው ምሰሶ፣ ሰላሙን፣ መረጋጋቱን፣ ልማቱንና እድገቱን ጠብቆ የሚያስቀጥለው የሀገሩ ባለቤት፣ መሪና አሳዳሪ የሆነው ሕዝብና ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ከሕዝብ ውጪ የሚታሰብ ሰላምም ሆነ ልማት የለም፡፡ ይህንንም ራሱ ህዝቡ በተደጋጋሚ አረጋግጦአል፡፡

 

መንግስት አምኖ በተቀበለውና የሕዝቡ መብቴ ይከበርልኝ ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን በገለጸው የውስጥ ችግር መነሻነት በመጠቀም አጀንዳውን ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅምና ፍላጎት ለማዋል ሁከትና ግርግር መፍጠርንና ጥፋት ማድረስን በዋነኛነት ሲያራምዱ የነበሩ ሀይሎችን በየደረጃው ከጸጥታ አስከባሪዎች ጎን ተሰልፎ ያስቆመው ሕዝቡ ነው፡፡

 

በተፈጠረው ግርግር ተጠቅመን፣ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አደፍርሰን የአረቡን አለም አብዮት በኢትዮጵያ እውን እናደርጋለን በሚል በሶሻል ሚዲያዎቻቸው ሰፊ ዘመቻ ከፍተው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የጥላቻ ንግግር በመዝራት የዘመቱትን ኃይሎች እኩይ ሴራ ያመከነው ሕዝብ ነው፡፡ እንደነሱ ስሌትና አጀማመር በሂደት እንደነበረው አካሄዳቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ያለው የተረጋጋና የሰከነ ሰላም በቦታው አይኖርም ነበር፡፡

 

በሐሰት በሚነዛ ወሬ የሚሸበር የኖረውንና የቆየውን አንድነቱን የተሳሳተ መርዘኛ አላማ ባላቸው ሰዎች ቅስቀሳ ተነሳስቶ የራሱን ሀገር የሚያወድም ሕዝብ አይደለም፡፡ ለዚህ የጥፋት ተግባር ጽንፈኛው ተቃዋሚ በብዛት የተጠቀመበት በእድሜ አፍላና በስሜታዊነት በቀላሉ የሚማረከውን ወጣቱን የነበረ ቢሆንም የታላላቆች አባቶችና እናቶች ምክርና ተግሳጽ ሽመግልናና ዳኝነት ወጣቱ በተፈጠረው ሁኔታ ተጸጽቶ ያወደመውን ለመገንባት ቃል ገብቶ በዚህም መሰረት ሕዝቡ የደፈረሰውን ሰላም በአግባቡ ለማስከበር ወሳኝ ሚና ተጫውቶአል፡፡

 

እንደ ሶርያ፣ ሊቢያና የመን ሕዝቦች በጽንፈኛ ተቃዋሚው ተገፋፍተው የራሳቸውን ሀገር አፈራርሰው ዛሬ ባዶ አውድማ መሬት አድርገዋል፤  በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ተገድለው የተቀሩትም ተሰደው በስቃይ ሕይወት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይህን የመሰለ በጥላቻና በስሜታዊነት የተሞላ ጥፋትና ወድመት በኢትዮጵያ  እንዲደርስ የሚፈልግ ዜጋ አይኖርም፡፡

 

በውጭ ኃይሎች ከፍተኛ ገንዘብ የተገዙና በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግዱ፣ ሀገራቸውንና ወገናቸውን የእልቂትና የጥፋት ውድመት ውስጥ ለመክተት የሚክለፈለፉ ሀይሎች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ ስውር አጀንዳና ተልእኮ ተሸክመው በሀገሪቱ ቀውስና ትርምስ እንዲቀጣጠል ለሊት ከቀን እየሰሩ ያሉ መኖራቸውም እብንደዛው፡፡ የግብጽና የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎችና ቅጥረኞችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

 

የሕዝብና የመንግስት የሆነ ንብረት ማውደም ማቃጠል፤በድሀ ሀገር አቅምና ኢኮኖሚ የተገነቡ የልማት አውታሮችን ማጋየት፤ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ አምቡላንሶችን የትራንስፖርት መኪናዎችን ፋብሪካዎችን ማቃጠል ማንደድ ቀዳሚ ስራቸው ነበር፡፡ ይህንንም ያስቆመው ሕዝቡ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሰለፉ ነው፡፡ የሚጎዳው ሕዝቡ መሆኑን ቆም ብለው ለማሰብ እንኳን ያልታደሉ በገሀዱ ጸረ ሕዝብ የሆነ አቋም የነበራቸውና ያላቸው ናቸው፡፡

 

በዘንድሮው አመት የግብጽ ደህንነት ኃይሎች ከጀርባ በመሩትና ባቀናበሩት በቢሾፍቱው የእሬቻ በአል ላይ በሰላማዊው ሕዝብ ላይ በወኪሎቻቸው አማካኝነት ሀይማኖታዊውንና  ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበትን መድረክ ወደፖለቲካዊ ተቃውሞ እንዲለወጥ ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር አድርገው ምን ያህል ንጹሀን ዜጎቻችን እህትና ወንድሞች እንደተጎዱና ሕይወታቸው እንዳለፈ በጸጸት እናስታውሳለን፡፡

 

ሴራና ደባው የተቀነባበረው በጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ሲሆን ሀገሪቱ የጀመረችውን ልማትና እድገት ከድህነት የመውጣት ትግል ለማደናቀፍ በተለይም የግብጾቹ አላማና እቅድ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ስራ ለማስቆም ነበር፡፡ ይሄንን እነሱም ተናግረውታል፡፡ ዛሬም በስውር ከዚሁ ሴራቸው አልታቀቡም፡፡

 

በየትኛውም አቅጣጫ፣ ወቅትና ሰአት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ፣ ሀገሪቱ የትርምስና የሁከት ማእከል እንድትሆን፣ ሕዝብ ከሕዝብ እንዲጋጭ በዚህም አንድነታችን እንዲፈርስ ለማድረግ ከጥንት ጀምሮ ግብጾች ዛሬም ድረስ እየሰሩበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄንን ተተኪው ኢትዮጵያዊ ትውልድ በሚገባ ካላወቀው በእነሱ ሽፍንና ምስጢራዊ አቀራረብ ከተረታ ሀገሩን፣ ሰላሙንና መረጋጋቱን፤ ልማትና እድገቱን ሁሉ አሳልፎ ሰጠ ማለት ነው፡፡

 

በተለይ ግብጾች እጅግ መግለጽ ከሚቻለው በላይ ራስ ወዳዶች ስለሆኑ የአባይ ውሀ ባለቤትና 85 በመቶ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆንዋን እያወቁ ከእኛ ውጭ መጠቀም ማንም አይችልም በሚል እብሪት የታወሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በአባይ ወንዝ  ግድብ እንዳትሰራ ከጥንት ጀምሮ ሲያሴሩ ኖረዋል፤ ሠራዊታቸውን አዝምተውም ተሸንፈዋል፡፡ በብዙ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ሲያደሙና ሲያቆስሉ ኖረዋል፡፡ ተቃዋሚዎችን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ ወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት፣ በማስታጠቅና በማዝመት ሲሰሩት የነበረውን ስራ ዛሬም ችላ ሲሉት አይታይም፡፡

 

በየትኛውም አቅጣጫ የሀገርን ሰላምና ጸጥታ ለማናጋት የሚቃጣውን በውጭ ኃይሎች የጀርባ ገፊነት የሚደረግ የጥፋት እንቅስቃሴ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ወደፊትም መክቶ የሚያከሽፈው ሕዝቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ በሰላሙና መረጋጋቱ፤ በሐገሩ ሕልውናና ደህንነት ላይ አይደራደርም፡፡ በመሆኑም የሕዝብን ሰላምና ጥቅም በማወክ ከከፋ ኪሳራ ያቀለፈ የፖለቲካ ትርፍ እንደማይገኝ ጽንፈኛው ኃይል አጥብቆ ሊረዳው ይገባል፡፡

 

ለኢትዮጵያ ጠላቶች በተላላኪነት የተሰለፉ፣ ከህዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የቆሙ፣ በጭፍን የፖለቲካ ጥላቻ የታወሩ፣ ኃይሎች የትኛውንም አይነት የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ አይችሉም፡፡

 የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አርቀው የሚያስቡ፣ የሚያስተውሉ፣ በስሜት የማይነዱ፣ ሀገራዊ ጥቅምና ጉዳታቸውን በአግባቡ የሚያመዛዝኑ መሆኑን ደግመው ደጋግመው አረጋግጠዋል፡፡ ሕዝቡ የሰላሙ ጠባቂ ዘብ በመሆኑ ሰላምን ለማምጣት በአዋጅ የምትኖር አገር እንዳልሆነች ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡

 

ሕብረተሰቡ ሰላሙን ያረጋገጠው እራሱ ለሰላሙ መከበር ጸንቶ በመቆሙ ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ አዋጁ ያስፈለገው ያንዣበበውን አደጋ መቀልበስ በማስፈለጉና የተረጋጋ ሰላም እንዲፈጠር ለማመቻቸት ብቻ ነበር፡፡ እየሆነ ያለውም ሄው ነው።

 

በአገሪቱ የተለያዩ ማእዘናት ተደጋጋሚ ችግሮች ተፈጥረው በሰላም የተፈቱበትን ሁኔታ ስናስተውል ችግሮች ሲፈጠሩ የመፍታት አቅም ያለው ጠንካራ መንግሥት መኖሩ ለሕዝቡም ለሀገሪቱም አስተማማኝ መሰረት ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀሰቀሱ ችግሮች በግለሰቦችና ኃላፊነት በጎደላቸው ሰዎች ቆስቋሽነት የሚነሱ እንጂ በሕዝብና ሕዝብ መካከል የሚፈጠር ግጭት አለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡  መንግስት እነዚህን በተለያዩ አካባቢዎች ብልጭ ድርግም እያሉ የሚነሱ ችግሮችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን እንደ ቀድሞው ሁሉ ዘለቄታዊ መፍትሄ እያበጀላቸው ይገኛል፡፡ ይህም አሁን ላይ ላለው ሰላም የጎላ አስተዋፅኦ ማድረጉ ግልፅ ነው። ዛሬ የተረጋጋ ሀገራዊ ሰላም በመፈጠሩ የተነሳ ቀደም ሲል፣ ከአምስት ወራት በፊት ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ከተደነገጉት  ክልከላዎችና እርምጃዎች   የተወሰኑት  እንዲነሱ  መደረጉን  የኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ማስታወቁም ከዚሁ ህዝቡ ለሰላም ካለው ፅኑ አመለካከተና፣ ለሰላም ካለው የልተገደበ አስተዋፅኦ የመነጨ ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም። በመሆኑም ይህ የህዝቡ ሰላም ወዳድነትና ስለሰላም ሲል የሚከፍለው መስዋእትነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፤ አፍራሽ ሀይሎችም ያዋጣኛል በማለት ከያዙት አፍራሽ አቋም መለስ ሊሉ ይገባል።