ተሐድሶው ይቀጥላል፤ ልማቱም ይፋጠናል

በሀገር ደረጃ ተጀመረው የጥልቀታዊ ተሀድሶው እንቅቃሴ በታቀደለት አቅጣጫ እየተራመደ ይገኛል፡፡ የተሀድሶው ጅምር ከከፍተኛው አካል ወደታችኛው ድረስ የዘለቀ በመሆኑ ከፌደራል ጀምሮ ክልሎች ድረስ በየደረጃው የአመራር ለውጦች በስፋት ተካሂዷል፡፡

 

ኢህአዴግ እስካሁን ባካሄደው ግምገማ ሊታረሙ የሚችሉ አባላቱ እንዲታረሙ፤ ከደረጃቸው መውረድ ያለባቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ፤ ከድርጅቱ መሰናበት ያለባቸው እንዲሰናበቱ የሚያስችሉ አስተዳደራዊና ድርጅታዊ እርምጃዎችን መውሰዱን የድርጅቱ ልሳን በሆነውና መጋቢት 1 ቀን 2009 እትሙ  ለንባብ ባበቃው አዲስ ራእይ መጽሔት ያስታወቀ ሲሆን፤ 50 ሺህ በሚሆኑ አባላቱ ላይም እርምጃ መወሰዱን ይፋ አድርጓል፡፡

 

ከቀድሞው ግዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በተካሄደው ኢሕአዴግ ውስጡን የማጥራት ንቅናቄ (Internal Rectification movement) ይሄን ያህል ግዙፍ ቁጥር ባላቸው አባላቱ ላይ እርምጃ ሲወስድ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ ዋናው ከሕዝቡ ጋር የሚገናኘውና ወርዶ በአካል የሚሰራው የታችኛው አስፈጻሚና አባል እንደመሆኑ መጠን ከሕዝብ ቅሬታ ጋር የሚያያዙት አብዛኛዎቹ ጉዳዮችም መነሻቸው በቀጥታ የታችኛው አስፈጻሚ ከሚፈጽማቸው ሙሰኛነት፤ ኪራይ ሰብሳቢነት፤ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር፤ የመሬት ቅርምትና ደላላነት ወዘተ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በድርጅቱም በሕዝቡም ውስጥ ይታወቃል፡፡

 

ኢሕአዴግን ከሕዝቡ ጋር ያላተሙትና አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ያደረጉት ሕዝቡ በተገኘው የኢኮኖሚ ስኬት እንዳይጠቀም በማድረግ በኢህአዴግ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ያበቁት ማንም ከውጭ የመጣ ኃይል ሳይሆን ራሱ ይሰራሉ ብሎ ያስቀመጣቸው አባላቱ ናቸው፡፡ ከሕዝብ ውስጥ መውጣታቸውን፣ የሕዝብ አገልጋይና ታዛዥ መሆናቸውን ሕዝቡ ድምጹን ሰጥቶ የመረጣቸው መሆኑን ወዘተ እስከመርሳት የደረሱም ነበሩበት፡፡

ከዚህ አኳያ ስንመዝነው የተሀድሶው ጅምር ስርነቀል እርምጃ አበረታችና ተስፋን የሚያጭር፡፡ በእርግጥ ዋናውና ወሳኙ ጥያቄ ምን ያህል ከስህተታቸው ተምረው፣ ተጸጽተው፣ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ዳግም ስህተት ውስጥ ላለመግባት ወስነዋል የሚለው ነው። ይሄ በሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡

 

የድርጅቱ ልሳን የሆነው አዲስ ራእይ እንዳለው እጅግ የሚበዙት አባላት በተሀድሶው እንቅስቃሴ ራሳቸውን አርመውና አስተካክለው በብቃት ለመንቀሳቀስ እንደሚችሉ እምነት የተጣለባቸው መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ የተሐድሶውን ስኬት በተመለከተ ከብሔራዊ ክልል ከመጡ ግብረመልሶች ከሕዝቡም ከተሰበሰቡ የዳሰሳ ጥናቶች በተሐድሶው መሳካት ላይ ጥርጣሬ መታየቱን የሚያስነብበው መጽሔቱ ኢሕአዴግ መታደስና ችግሮቹን ማስተካከል የነበረበት ግዜ አልፎአል፤ በብልሽት ረዥም ርቀት ከሄደ በኋላ የመጣ ተሐድሶ በመሆኑ አይቻልም እና የመሳሰሉ አስተያየቶች የነበሩ መሆኑን በመግለጽ ሀሳቦቹ እውነት የሌላቸው ናቸው ማለት አይቻልም፤ በእርግጥ በጥልቅ የመታደሱ ንቅናቄ ቀደም ብሎ መካሄድ ነበረበት፤ ብልሽቶቹ ሰፊ በመሆናቸው ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት ቀላል አይሆንም ሲል መግለፁም እናምነው ዘንድ የሚጎተጉት ሀሳብ ነው፡፡

 

አዲስ ራእይ መጽሔት ያሉን አማራጮች ሁለት ናቸው ይላል፡፡ አንድም ግዜው አልፎአል ማስተካከሉ ከባድ ነው በሚል ችግሮቹ እንዲቀጥሉ መፍቀድና የበለጠ ጥፋትና አርማጌዶን በሀገር ላይ ማወጅ፤ አሊያም ችግሩ ከደረሰበት በላይ እንዳይሄድ መግታትና የተበላሹትን የተቻለውን ያህል አዳዲስ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መቆጣጠር ናቸው፡፡ ኢህአዴግ የመረጠው ሁለተኛውን አማራጭ ነው ሲል የድርጅቱ ልሳን የሆነው መጽሔት ገልፇል፡፡ ተገቢና ትክክለኛ  ውሳኔ ነው፡፡

 

በተጀመረው ተሐድሶ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች ነጥሎና አበጥሮ በማውጣት አቅም የፈቀደውን ያህል ተራምዶ ቁርጠኛ ውሳኔ በመስጠት ማረምም ሆነ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ችግሮቹ ከነበረው በላይ ተለጥጠው እንዳይሄዱ፣ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ችግሮቹ እንዲገቱ ለማድረግና ዳግም እንዳይፈጠሩም ለመከላከል መንግስትና ሕዝብ ተረባርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተሀድሶው በሕዝባዊ ንቅናቄ የሚመራ በመሆኑ ባለቤቱ ሕዝቡ ነው፡፡ የተሀድሶው ዋነኛ አላማ የተጀመረውን ግዙፍ ሀገራዊ ለውጥ በማስቀጠል ሀገሪቱን በልማትና በእድገት ከፍተኛ ማማ ላይ እንድትደርስ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ገጽ ለገጽ ከሕዝቡ ጋር በተደረጉ ፍጹም ነጻና ዲሞክራሲያዊ ውይይቶች በሕዝቡ የተነሱ ሰፊ ቅሬታዎችን፣ ተፈጸሙ የተባሉ በደሎችን፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ እጦትን፣ የመሬት ቅርምትን፣ በስልጣን ያለአግባብ የመጠቀምን፤ የጠባብነትና የትምክሕት አመለካከቶችንና የመሳሰሉትን በመታገልና በመዋጋት ረገድ በተሀድሶው ከፍተኛና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

 

በጥልቅ ተሀድሶው ግምገማ በተለያዩ ደረጃ የቀረቡ የሕዝብ ጥያቄዎች በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ሁሉንም ጥያቄዎች በአንድ ግዜ ለመመለስ አይቻልም፤ ሆኖም በግዜና በሂደት ደረጃ በደረጃም ይመለሳሉ፡፡ መንግስት ትልቁ ያደረገው ነገር የሕዝቡን ጥያቄና የልብ ትርታ በማድመጥ አክብሮም በመቀበል ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ ነው ሊበረታታ የሚገባው፡፡ ከጅምሩም ችግር የለም፤ አልነበረም ብሎ አልካደም፡፡ አዎን ችግሮች ተፈጥረዋል፤ አሉ፤ ትክክል ነው፤ ነገር ግን ሕዝቡን ይዘን፣ ከሕዝቡ ጋር ሆነን እንፈታዋለን ነው ያለው፡፡ ይህ ደግሞ በሕዝብ ላይ ያለን እምነት ያረጋግጣል፡፡

 

በአዲስ አበባ፤ በኦሮሚያ፤ በትግራይ፤ በደቡብ ክልል በአጠቃላይ በመላው ሀገሪቱ በተጀመረውና በመካሄድ ላይ በሚገኘው ሕዝባዊ የተሐድሶ ንቅናቄ ከሕዝቡ ጋር በተደረገ የፊት ለፊት ውይይቶች በተለያየ በአመራር ደረጃ ላይ በነበሩ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ ተወስዶአል፡፡ የመለወጥና የመተካት ስራም ተካሂዷል፤ ሂደቱም እንደቀጠለ ነው፡፡ በጥልቀት የመታደስ ሕዝባዊና ሐገራዊ ንቅናቄው የተጀመረውን ልማት በአስተማማኝ መሰረት ለማስቀጠል የሚያስችል አቅም ይገነባል፡፡  በጥልቀት መታደስ ማለት የአስተሳሰብ ለውጥን በማምጣት መልካም አስተዳደርን ማስፈን መቻል ነው፡፡ በተግባር መታረም በአመለካከት ከመታረም ውጪ ሊመጣም ሆነ ሊፈጠር አይችልም፡፡ በተሐድሶ እንቅስቃሴው የተካሄዱት ሕዝባዊ ውይይቶች ለታሰበው አገራዊ ለውጥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሆናቸውም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ተሀድሶው አንድ ሰሞን በሞቅታና በግርግር ብቻ የሚደምቅ ሳይሆን ሁሌም ሐገራዊ ቀጣይነቱ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ተገነብቶ የሚዘልቅ ራሱን የቻለ ሂደት ነው፡፡ ለዚህ ነው እየታደስን እንሰራለን፤ እየሰራንም እንታደሳለን የሚለው መሪ መርህ በስፋት የሚደመጠው፡፡

በሥራ ሂደት ውስጥ ሁል ግዜም ስህተቶች፣ እንቅፋቶችና ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ አንዳንዴ በቅንነት፤ አንዳንዴም ካለማወቅ፣ የበለጠ፣ የተሻለ . . . ሰራሁ ከሚል፣ ሌላው ደግሞ ከጀርባ ባሉ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች መሰሪ ሴራ አቀናባሪነት መንግስታዊ አስተዳደሩንና ኃላፊዎችን በምርኮኛነት በመያዝ ያሻቸውን ለመዝረፍ ሆን ብለው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች እንደሚኖሩም ይታወቃል፡፡

 

ይህንን ለማጥራት የመታደሱ ሂደት ችግሮችን በየደረጃውና በየተነሱበት አግባብ የመፍታቱና መፍትሔ የማስቀመጡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ የሕብረተሰብ እድገት ራሱን ችሎ የሚያመጣቸውና ትላንት ያልነበሩ፣ ዛሬ የሚታዩ አዳዲስ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ይህ ሲሆን ግዜውን ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አቅምን የመገንባትና የማሳደግ አቅምን ነው ተሀድሶው የሚፈጥረው፡፡ ከዚህ አንፃር በክልሎችስ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። በምሳሌነትም አማራ ክልልን እናንሳ።

 

ሰሞኑን የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ባለፉት 6 ወራት በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄውንና የሌሎችንም ተግባራት አፈጻጸም በመገምገም በኪራይ ሰብሳቢነት በተጠረጠሩ አመራሮቹ ላይ እርምጃ መውሰዱን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡  የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ከጉባኤዉ በኋላ በሰጡት መግለጫ  ከጥልቅ ተሐድሶው በፊት በአንዳንድ አመራሮች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ጐልቶ ይታይ እንደነበረ አውስተው በጉዳዩ የተጠረጠሩ 462 ከፍተኛ እና መካከለኛ፤ 362 የታችኛው አመራሮች ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሚገኝ፤ ከተጣሩት ጉዳዮች ውስጥ 1ኛው ግለሰብ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነቱ እንዲታገድ፤ በሁለተኛው ላይ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ማዕከላዊ ኮሚቴው መወሰኑን፤ ከክልሉ ኃላፊዎች ውስጥ 16ቱ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ፤ 11ዱ ደግሞ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ብአዴን ባሳለፋቸው ሂደቶች ብዙ ውጤቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም ሂደቱ ደረጃ በደረጃ ሕዝቡን ከመምራት ብቃት አኳያ የአስተሳሰብ ድክመትና የአፈፃፀም ጉድለት አጋጥሞታል ያሉት አቶ አለምነው የተሐድሶው ንቅናቄ የአስተሳሰብ ችግሮችን በመፍታት ለሰላም፡ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር የተመቸ፣ የአመራር አንድነትና መዋቅራዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችል፤ የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ለመፍታት ያለመ  ንቅናቄ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የአስተሳሰብ ግልጽነትና የሀሳብ አንድነት በድርጅቱ አመራሮች ዘንድ መምጣቱን የገመገመ  ሲሆን ድርጅቱ  ሕልውናው ተጠናክሮ ሕዝብን መምራት በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኝ የጥልቅ ተሐድሶው ንቅናቄ ትልቅ አቅም የፈጠረለት መሆኑን ሀላፊዎቹ ይናገራሉ። ብአዴን ሕዝብ የመምራት ብቃቱ እንዲረጋገጥ ሕዝብን የሚጠቅሙ አስተሳሰቦችን መያዝ፡ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ መረባረብ፤ የግብርና  ምርት እንዲያድግ ሕዝብን ማነቃነቅ፤ በከተሞች የአምራች ኢንዱስትሪ መስኮችን ማስፋት፤ ሕዝባዊ አገልግሎትና ዲሞክራሲያዊ  ግንኙነትን ለማጠናከር ድርጅቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት መሆኑን  አመልክተዋል፡፡

ለዚህ ሁሉ የጥልቅ ተሀድሶው ፋይዳ የጎላ ነውና ተጠነክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑ የግድ ነው። እየታደሱ መስራት፤ እየሰሩም መታደስ ይሏል ይሄው ነውና።