የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መግለጫው በየመን፣ በሰሜናዊ ምሥራቅ ናይጄሪያ፣ በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ችጋር መከሰቱን አስታውቋል። ለእነዚህ በችጋር ምክንያት የሞት አፋፍ ለደረሱ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለማቅረብ 4 ነጥብ 4 ቢሊዬን ዶላር እንደሚያስፈልግም አስታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ዋና ኃላፊ ስቴፈን ኦብሬይን እንዳስታወቁት ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ባሉ 50 ዓመታት የዚህ ዓይነት አስከፊ የችጋር አደጋ አጋጥሞት አያውቅም። እንደ ኦብሬይን ገለጻ 20 ሚሊዬን ሰዎች ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠው በችጋር ላይ ይገኛሉ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ካልተደረሰላቸው በርካቶች በችጋር ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
በኢትዮጵያም ድርቅ ተከስቷል። ይህ ድርቅ 5 ነጥብ 6 ሚሊዬን ዜጎችን ለምግብ እጥረት ያጋለጠ ቢሆንም የምግብ እጥረቱ ግን ወደችጋርነት ተለውጦ የሰዎችን ህይወት ለአደጋ አላጋለጠም። እናም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያን በምግብ እጥረት ሣቢያ ዜጎቻቸውን ለሞት አደጋ ያጋለጠ ችጋር የገጠማቸው አገራት ውስጥ አላካተታትም። ድሮ ቢሆን በኢትዮጵያ ድርቅና ችጋር የማይነጣጠሉ ነበሩ። ድርቅ ሲከሰት ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ ችጋር መኖሩ አይቀሬ ነበር።
በኢትዮጵያ አምናም በተመሳሳይ በአስከፊነቱ ባለፉት 50 ዓመታት ከተከሰቱት ሁሉ ወደር ያልተገኘለት 10 ነጥብ 2 ሚሊዬን ዜጎችን ለምግብ እጥረት የዳረገ ድርቅ አጋጥሞ እንደነበር ይታወሳል። ይህም ድርቅ ቢሆን ወደችጋርነት ተለውጦ ለዜጎች ህይወት መጥፋትና ከመኖሪያ ቀዬ ለመሰደድ ምክንያት አልሆነም።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ስቴፈን ኦብይን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት፣ አገሪቱ የአጋሮችን ድጋፍ ሳትጠብቅ አራት መቶ ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ድርቅን በራሷ አቅም በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም መሥራቷንና የከፋውን ድርቅ ለመከላከል ያደረገችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። በ50 ዓመታት ካጋጠሙት ሁሉ የከፋ የተባለውንና ከ10 ሚሊዬን በላይ ዜጎችን ለምግብ እጥረት ያጋለጠውን ድርቅ ለመከላከል በተወሰደው እርምጃ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የአንበሣውን ድርሻ ወስዷል።
ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ችጋር የማይከሰትባት አገር ለመሆን የበቃችው በራሷ አቅም የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የማቅረብ አቅም በመፍጠሯ ነው። በአሁኑ ጊዜ በድርቅም ይሁን በሌላ ማንኛውም አደጋ ተጽዕኖ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ማቅረብ ሲያስፈልግ፣ ይህን ለማድረግ በቂ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት መያዝ የተቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በ2007 ዓ.ም አገሪቱን በመታው ድርቅ የምግብ እጥረት ማጋጠም ሲጀምር 450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባበቂያ የእህል ክምችት ነበር። በድርቁ ተጽዕኖ ሥር የወደቁት ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ መንግሥት 16 ቢሊዬን ብር በጀት በመመደብ ከውጭ አገር እህል በመግዛት ጭምር የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ አቅርቧል። ዘንድሮ የአገሪቱ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት 600 ሺህ ሜትሪክ ቶን ደርሷል። ይህ የመጠባበቂያ ክምችት መጠን በቅርቡ ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን ያድጋል።
የዘንድሮው ድርቅ ተጽዕኖ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻፀር በሚሸፍነው አካባቢ ስፋትም በተጠቂዎች ቁጥርም ያነሰ ነው። በመሆኑም የድርቁን ተጽዕኖ መቋቋም ለኢትዮጵያ ከባድ ፈተና ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። እስካሁን መንግሥት የአንድ ቢሊዬን ብር በጀት መድቦ የድርቁን ተጽዕኖ ለመከላከል እየሰራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ድርቁ ያጠቃቸው የኦሮሚያ፤ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የኢትዮጵያ ሶማሌና የአፋር ክልላዊ መንግሥታት የራሳቸውን በጀት መድበው እርዳታ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
የዘንድሮው የድርቅ ተጽዕኖ ከአምናው ጋር ሲነጻጻር አነስተኛ ይምሰል እንጂ ድርቁ ያጋጠመው በአገሪቱ ቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች – በኦሮሚያ፣ ቦረናና ጉጂ ዞኖች፤ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን ሰገን ወረዳዎች፤ በኢትዮጵያ ሶማሌና አፋር ክልሎች አብዛኛዎቹ የአርብቶ አደር መኖሪያ አካባቢዎች በመሆኑ ተጽዕኖውን በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የመከላከሉን ሥራ አስቸጋሪና ውስብስብ አድርጎታል። የአርብቶ አደሩ የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታ ከከብቶቹ በሚያገኘው የእንስሳ ተዋጽኦ (ወተት፣ ቅቤ፣ ትኩስ ደም…) ላይ የተመሠረተ በመሆኑና እነዚህ የምግብ ፍጆታዎች ደግሞ በየእለቱ የሚገኙ እንጂ ለመጠባበቂያነት በጎተራ የማይከማቹ በመሆናቸው የድርቁ ተጽዕኖ ፋታ የማይሰጥ እንዲሆን አድርጎታል። በድርቁ ሣቢያ የእንስሳ መኖ ሲጠፋ ከብቶቹ ነጠፉ፤ መሞትም ጀመሩ። እናም ድርቁ በምግብ እጥረት ያሳደረው ተጽዕኖ ፋታ የሚሰጥ አልነበረም።
ሌላው ችግር ለሰዎች ከሚደረገው የእርዳታ አሰጣጥ በተጨማሪ፣ አርብቶ አደሩ ለዘለቄታው ለችግር እንዳይጋለጥ የእንስሳቱን ህይወት ማትረፍ አስፈላጊ መሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት ለሰዎች ከሚቀርብ እርዳታ ጎን ለጎን የእንስሳ መኖ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኗል። የእንስሳ መኖ የማቅረብ ሥራ ደግሞ አዳጋች ነው። አንድ፣ አገሪቱ የእንስሳ መኖ መጠባበቂያ ክምችት የላትም፣ ሁለት የእንስሳ መኖ በአብዛኛው በተፈጥሮ የሚገኝ እንጂ ሰው የማያለማው በመሆኑ በየአካባቢው ያለው የእንስሳ መኖ (ሣር) የዚያኑ አካባቢ ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ለሌላ የሚተርፍ አይደለም። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የመኖ አቅርቦት ችግር አጋጥሟል። የእንስሳ መኖ ሰፊ ቦታ የሚይዝ በመሆኑ የማጓጓዣ ወጪው ከፍተኛ ነው። አንድን እንስሳ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ከሚርቅ ሥፍራ ሣር እያጓጓዙ ለወራት መቀለብ ከእንስሳው ዋጋ በላይ ወጪ ስለሚጠይቅ ከኢኮኖሚ አንጻር አዋጭ የማይሆንበት ሁኔታም አለ። ይህም ሆኖ ግን አርብቶ አደሩ ቢያንስ ለዘር የሚሆኑ እንስሳት እንዲተርፉት የመኖና ውኃ ማቅረብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ያም ሆኖ እስካሁን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ እንስሳት በድርቁ ምክንያት አልቀዋል። በገበያ ትስስር ተጽዕኖውን ለመቋቋም የተደረገው ጥረትም ያን ያህል ውጤት አላስገኘም።
የፌዴራል የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ ብዛት ያላቸው እንስሳት በውኃና መኖ እጥረት እየሞቱ ነው። ድርቅ በተከሰተባቸው የአርብቶ አደር አካባቢዎች የእንስሳትን ህይወት ለመታደግ የሚደረጉ ጥረቶች የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ድርቅ የተከሰተባቸው ክልሎች ከመደቡት በጀት በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት ለእንስሳት መኖ የሚሆን 100 ሚሊዮን ብር መድቦ የመኖ እጥረቱን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፣ አርብቶ አደሩ ቀደም ሲል የነበረውን መኖ በመጨረሱ መኖ ራቅ ካለ አካባቢ ተገዝቶ እየተሰራጨ መሆኑን አስታውቋል።
የእንስሳ መኖ ራቅ ካለ ሥፍራ ገዝቶ የማቅረብ ሥራ ከኢኮኖሚ አንጻር አዋጭ ባለመሆኑ፣ ውኃ ባለባቸው አካባቢዎች በፍጥነት የሚደርስ መኖ የማልማት ሥራ እየተከናወነ ነው። ይሁን እንጂ፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ ወንዝ ባለመኖሩ መኖ የማልማት ሥራው እየተከናወነ አይደለም። በተያዘው ዓመት በተለያዩ ክልሎች በአጠቃለይ 2 ሺህ 496 ሄክታር መሬት መኖ በመስኖ እየለማ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥም በአፋር ክልል 495፣ በሶማሌ ክልል 1 ሺህ 889 እና በደቡብ ክልል 112 ሄክታር መሬት መኖ በመስኖ እያለማ ነው።
ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ድርቁ በሰው ህይወት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ መከላከል ቢቻልም፣ እንስሳቱን ግን ማትረፍ አዳጋች ሆኗል። ይህ ሁኔታ ድርቁ ካለፈ በኋላ አርብቶ አደሩን መልሶ የማቋቋም ሥራ መከናወን እንዳለበት ከወዲሁ ያመለክታል። እናም ለዚህ ዝግጅት መደረግ አለበት።
በአጠቃላይ በአገሪቱ በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚያጋጥም የድርቅን ተጽዕኖ ለዘለቄታው መቋቋም የሚያስችል ብልሃት ሊበጅ ይገባል። በዘመቻ ተጽዕኖውን ለመከላከል የመሯሯጥ አካሄድ ማብቃት ይኖርበታል። ይህ በቀዳሚነት ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን ይሻል። ይህ ደግሞ የመስኖ እርሻ ማስፋፋትን የሚመለከት ነው። ለእንስሳቱ ሣርና መኖ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚኖረውን አርብቶ አደር አንድ ቦታ ረግቶ በግብርና ሥራ ወደሚተዳደር አርሶ አደርነት ማሸጋገርም ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ እስከ አሁን ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የሚያሳዩ አስረጂዎች አሉ።
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሰባት ዓመታት በዘጠኝ ዞኖች 40 ወረዳዎች ውስጥ ከስምንት ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የአነስተኛ መስኖ ልማት ሥራ ተከናውኗል። በየአካባቢው ያሉትን ወራጅ ወንዞችን በመጥለፍና ሌሎች የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በየአባወራዎቹ ይዞታ እንዲደርስ በማድረግ አርሶ አደሮቹ የጓሮ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን እንዲያለሙ የማስቻሉ ሥራ በአማራ ክልልም በስፋት መከናወኑን የክልሉ ተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህም ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማትም ከሦስት ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥራ ተከናውኗል። በትግራይ ክልል 22 ወንዞችን በመጥለፍ ከአራት ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ የመስኖ አውታሮች ተገንብተዋል። በዚህም ከ13 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።
ዘንድሮ በቀጣይ ዓመታት ሥራ ላይ የሚውል 108 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች ተጀምሯል። ፕሮግራሙ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ወረዳዎችን በማሳተፍ የሚከናወን ነው። ለአነስተኛ መስኖ ልማት ሥራው የዲዛይን፣ የገበያ ጥናትና የመሳሰሉት ተግባራት ተጠናቀው ወደሥራ ተገብቷል።
የድርቅን ተጽዕኖ መከላከል የመጨረሻው ዘላቂ መፍትሄ ግን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የመሪነት ሚና ለድርቅ ወደማይንበረከኩት የማምረቻ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች ማሸጋጋር ነው። ይህ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ሲሆን እስካሁን የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው። ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም ኢኮኖሚዋን ወደ ኢንዱስትሪ ትራንስፎርም አድርጋ የመካከለኛ ገቢ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ እስካሁን ያለው የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ሂደት ያመላክታል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ድርቅ የሚያስከትለውን የምግብ እጥረት ተጽዕኖ ተቋቁማ ችጋርን ታሪክ ያደረገችበት ደረጃ ላይ መድረሷ ትልቅ ስኬት ነው። ዓለም አሁን ኢትዮጵያን የችጋር ሥጋት ካለባቸው አገራት ተርታ አውጥቷታል። ይህ ትልቅ የገጽታ መሻሻል አስከትሏል። አገሪቱ በድርቅም ይሁን በሌላ አደጋ የምግብ እጥረት ቢያጋጥም እንኳን በራሷ አቅም መከላከል የምትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። አሁንም ግን ብዙ ይቀራል። ድርቅ የምግብ እጥረት ተጽዕኖ ወደማያስከትልበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መሻገር ይቀራል።